
ዛሬ ኢትዮጵያውያን በፋሽስት ጣልያን በድጋሚ የተፈጸመባቸውን ወረራ በመቀልበስ ድል የተቀዳጁበት 84ኛው ዓመት የድል ቀን ነው። ይሄ ታላቅ የድል በዓል በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል። በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድላችን ሀውልት ስር ጉንጉን አበባ በማስቀመጥ በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ይውላል።
ፋሽስት ጣሊያን ዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ለ40 ዓመታት ዝግጅት በማድረግ በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በፈፀመበት እና ለአምስት ዓመታት አርበኞች በዱር በገደሉ፤ በወንዝ በሸንተረሩ ወጥተው ወርደው፤ ተጋድለው ሚያዚያ 27 ቀን የሽንፈት ካባ አከናንበውታል። ኢትዮጵያውያን ጣልያንን በገዛ እጁ ለሁለተኛ ጊዜ አዋርደውና የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ አድርገውታል። ዳግም ኢትዮጵያን እንዳይመኝ ለዓለም ጭምር ማስተማሪያ፤ የኢትዮጵያውያንን ማንነትን ደግሞ አደባባይ የገለጠ ታሪክ ሰርተዋል።
ጣልያኖች በዓድዋ ጦርነት ወቅት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቀው፤ የሠለጠነ ሠራዊት አሰልፈው ወደ ጦርነቱ በገቡበት ወቅት ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በባሕላዊ መሳሪያ በጦርና ጋሻ ታግዞ ሊያንበረክካቸው የመጣውን የጣልያንን ጦር ድል አድርገዋል። ይህን የጣልያኖች ወረራ ለመመከት ኢትዮጵያውያን ማይጨው ላይ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል:: ይሁንና ፋሽስቱ ወራሪ በዓለም መንግሥታት የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ጭምር በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን በገዛ ምድራቸው በመጨፍጨፍ ለአምስት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ ፈጽሟል::
ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ለጠላት አንበረከክም በማለታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 12 ቀን ንጹሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፈዋል፤ በዚህም ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል:: ይህ ጭፍጨፋ አሰቃቂ በሆነ መልኩ በዶማና በአካፋ ጭምር የተፈጸመ ሲሆን ታሪክ መቼም የማይረሳው ነው። በወቅቱ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ግፍ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም:: በገዛ ሀገራቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል።
ኢትዮጵያውያን ጣልያን በወረራ ላደረሰባቸው ግፍ አልተንበረከኩም፤ ይልቁንም ትግላቸውን አቃጣጠሉ፤ አንድነታቸውን አጠናከሩ፤ ወንድ ሴት ሳይሉ፤ እምነት ቋንቋ ሳይለዩ የሀገራቸውን ዳር ድንበር የደፈረው ኃይል ላይ ዘመቱ። አምስት ዓመታትን በዱር በገደል ተጋድሎ አደረጉ፤ ሌሎች ደግሞ ጠላትን በመሰለል ለወገን ጦር መረጃ በማቀበል የበኩላቸውን ተወጡ፤ በዚህ ሁሉ ተጋድሏቸው ጠላትን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ተረጋግቶ እንዳይቆይ አደረጉት::
በዚህም ቅኝ ገዥዎች በመላ ዓለም ረጅም ዓመታትን መቆየትና ያሰቡትን ማሳካት ቢችሉም በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ ግን ይህን ማድረግ አልቻሉም። ወራሪውንም መቀጣጫና ለቀኝ ገዢዎች ጭምር ማስተማሪያ ማድረግ ተችሏል:: ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ፋሽስቶች ላይ ባደረሱባቸው አሳፋሪ ሽንፈት ፋሽስቶቹ ተዋርደው ሀገሪቱን ጥለው ወጥተዋል::
በዚህም ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ነጻነት ለመጠበቅ፣ ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የቱንም ያህል ተደራጅቶና ታጥቆ የመጣን ኃይል ድል ከማድረግ እንደማይመለሱ በዓድዋ ላይ የሠሩትን ታሪክ በፋሽስት ላይ በመድገም ማንነታቸውን ለዓለም በድጋሚ ማሳየት ችለዋል::
ኢትዮጵያውያን ይህን ሁሉ ድል የተጎናጸፉት በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ፣ የውስጥ ችግር ቢኖርባቸው እንኳን በሀገር ጉዳይ የሚመጣን ኃይል ለመመከት ልዩነታቸውን በይደር አስቀምጠው ለሀገራቸው ክብር በቁርጠኝነት የሚታገሉ በመሆናቸው ነው። በጣልያን የወረራ ወቅትም የታየው ይሄው እውነታ ነው።
ሀገር ተደፈረች የሚል ጥሪ ሲቀርብ ዛሬ ነገ የሚል አንድም ዜጋ የለም። ጥሪውን አክብሮ ደረቱን ለጥይት፤አንገቱን ለጎራዴ አዘጋጅቶ ክተት በተባለበት ቦታና ሰዓት ሁሉ አለሁ ለሀገሬ ይላል። የሀገሩን ስም በጀግንነት ያስጠራል። ይሄ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ሁልጊዜም አብሮ የሚኖር በታሪክም የሚዘከር ሲሆን በዚህ ዘመን ይህ ትውልድ ደግሞ ይሄንን ጀግንነቱን የሚደግመው በልማት ነው። በማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ሁሉ ዋነኛው ባለቤት በመሆን ሀገር በምትመራው መስመር ሁሉ ቀዳሚ ተሰላፊ ነው።
የሀገርን ብሄራዊ አንድነት በሚያጠናክር፣ልማትን በሚያፋጥን የእናት ሀገር ጥሪ ሁሉ ምላሽ ይሰጣል። የአያቶቹን የጀግንነት ታሪክ በኩራትና በድል አድራጊነት መንፈስ እየዘከረ በልማት ጀግንነቱን ይወጣ ዘንድ የዱላ ቅብብሎሹን አንስቷል። ይሄንንም ለታላቁ የዓባይ ግድብ ግንባታ ወቅት ባደረገው ኅብረት አሳይቷል።
ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ሀገር በገዛ ሀብታቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ታሪካዊ ጠላቶች ልማቱን የማደናቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻዎችን ከዳር እስከ ዳር ከፍተዋል። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና ርዳታ እንደማያደርጉ በአደባባይ አሳውቀዋል። የገንዘብ አቅም ፣ እውቀት እና ኅብረት የላቸውም ብለው በተሳሳተ መልኩ ቢረዱም ኢትዮጵያውያኖች ግን አንድነታቸውን ፤ እውቀትና ሀብታቸውን አስ ተባብረው ዓባ ይ ግድብ ግንባታን ጀ ምረው ለፍጻሜ አብቅተውታል።
አሁን የዓባይ ግድብ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በመስከረም የ2018 የአዲስ ዓመት አዲስና ድንቅ ስጦታ ሊሆን በዋዜማው ላይ ይገኛል። ይሄ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳዩት ርብርብ የዘመኑ ትውልድ የልማት አርበኝነት ዋናው ማሳያ ነው። ይህ በዓለምም በአፍሪካም ደረጃ ግዙፍ የተባለ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የማድረግ አቅም የሚያሳይ ጉልህ ምስክር ነው። ይሄንን የልማት ታሪክ በሌሎችም ልማቶች ልንደግም ዳግም በቁርጠኝነት መነሳታችንን እስካሁን የተሰሩ የልማት ሥራዎች ምስክሮች ናቸው።
ጀግንነታችን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በልማት ጭምር መሆኑን በአደባባይ ምስክርነቱን ይሰጣል። ይሄንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። የተገኘውን ውጤት እያጣጣሙ ለአዳዲስ የልማት ዕቅዶች ትግበራ ወገብን አስሮ ትከሻን አደንድኖ መቆምን ይጠይቃል። ይሄ ሲሆን የጀግንነት ጽናታችን ዳግም ለዓለም ይገለጣል!
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም