
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው ስፖርታዊ ውድድሮች አንዱ የሆነውና የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚካሄደው የሜይ ዴይ መታሰቢያ ውድድሮች አጠቃላይ አሸናፊዎች ተለይተዋል።
ሜይ ዴይ ትናንት በኢትዮጵያ ለ50ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ136ኛ ጊዜ ሲከበር፣ ሠራተኛው በአዳማ በተካሄዱ የሜይ ዴይ የፍፃሜ ስፖርታዊ ውድድሮች ቀኑን አክብሮ ውሏል። ለሜይ ዴይ መታሰቢያ ውድድሮች ከወር በፊት በአዲስ አበባ እና በአዳማ አካባቢ የሚገኙ የሠራተኛው የስፖርት ማህበራት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹ አሸናፊዎችም ባለፉት ጥቂት ቀናት የፍፃሜ ጨዋታዎችን አድርገው የሜይ ዴይ ቻምፒዮኖች ታውቀዋል። በትናንትናው እለትም በሠራተኛው ስፖርት ዘንድ ከፍተኛ ፉክክር የሚካሄድበት የእግር ኳስ ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ በማስተናገድ ተደምድሟል።
ባለፈው ሰኞ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የዋንጫ ተፋላሚ ለመሆን በእግር ኳስ በተደረገው ጨዋታ ከመከላከያ ኮንስትራክሽንን 3ለ1 በመርታት የፍፃሜ ተፋላሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፍፃሜውም ድል ቀንቶታል። ንግድ ባንክ ትናንት በፍፃሜው ጨዋታ ከአዳማና አካባቢዋ ለዋንጫ የቀረበውን ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፎ የሜይ ዴይን የእግር ኳስ ዋንጫን አንስቷል። መከላከያ ኮንስትራክሽን ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
በሠራተኛው ስፖርት ሌላው ብርቱ ፉክክር በሚደረግበት የቮሊቦል ውድድር በሁለቱም ፆታ የሜይ ዴይ ቻምፒዮኖች የተለዩበት ጨዋታዎች ከቀናት በፊት ተደርገዋል። በዚህም በወንዶች አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን፣ ፋፋ ምግብ የብር ሜዳሊያ ወስዷል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የነሐስ ሜዳሊያው አሸናፊ ነው። በተመሳሳይ በሴቶች የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዋንጫውን ሲወስድ፣ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የብር፣ መከላከያ ኮንስትራክሽን የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል።
ከጥሎ ማለፍ ውድድሮች ጀምሮ ጥሩ ፉክክር ሲታይበት በነበረው የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በወንድ ብርሐንና ሰላም ማተሚያ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። ኢትዮ ኤሌክትሪክና የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ የብርና የነሐስ ደረጃውን ይዘው አጠናቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አሸናፊ በሆነበት የሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ኢትዮ ቴሌኮምና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታዮቹን የሜዳሊያ ደረጃዎች ይዘው ፈፅመዋል።
በወንዶች የቼስ ውድድር ኢትዮ ቴሌኮም የዋንጫ ባለቤት ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስና አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ሆነው አጠናቀዋል።
በሁለቱም ፆታ በተካሄዱ የዳርት ውድድሮች በሴቶች አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ አሸናፊ ሲሆን፣ ብርሐንና ሰላም ማተሚያ ሁለተኛ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሦስተኛ ሆነው ፈፅመዋል። በወንዶች ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም አሸናፊ ሲሆን መከላከያ ኮንስትራክሽን ሁለተኛ፣ ብርሐንና ሰላም ማተሚያ ሦስተኛ ሆነዋል።
በወንዶች የዳማ ውድድር አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አንደኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛና ብርሐንና ሰላም ማተሚያ ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በከረንቦላ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች አሸናፊ ሲሆን፣ ብርሐንና ሰላም ማተሚያ ሁለተኛ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።
በሠራተኛው መካከል የሚካሄዱት ስፖርታዊ ውድድሮች ከሜይ ዴይ በተጨማሪ የበጋ ወራት ውድድሮችና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ተብለው ባለፉት ከሃምሳ ዓመታት በላይ ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል። ኢሰማኮ እነዚህን ውድድሮች በማስተባበርና በመምራት ሠራተኛው በስፖርት አማካኝነት የአካልና የአዕምሮ ዝግጁነት እንዲኖረው ጥረት እያደረገም ይገኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም