
በአንድ ጣሪያ ስር እየኖሩ ነገር ግን የተለያዩ አንሶላ እንኳን ተጋፈው ልብ ለልብ ያልገጠሙ ጥንዶች መሆናቸው ሲገርማት እሱነቱን ያሳያት ይመስል የግል ማህደሩን ብትገልጥ ስሟ ተጽፎ ማስታወሻነቱ ለራሷ የሆነ ግጥም ሰፍሮ አገኘችና ከግር እስከራሱ ባይነቁራኛ መነሸችው።
ስንቴ አግብቼ ስንቴ ፈታሁሽ
በጻፍኩልሽ ግጥም፣
ያሰፈርኩት ትርጉም፣
ማርያምን አልወድሽም፣
ገብርዔልን አልጠላሽም።
ይዘቱ ይህን ይመስላል፣
ስሜት ከእምነት ይገዝፋል።
ተቀበይ!
ቆጥ ጫማ ተጫምታ፣
በቫኔል ፋይቭ ሽቶ እልፍ ወንድ ተጣርታ፣
ብትገባ ውቤ በረሃ፣
አሰኘችኝ ውሃ።
በትኩሳት ንዳድ ሌቱም ባይነጋልኝ፣
ኦሮማይ ብያለሁ የልምዣት ታምጣልኝ።
ልምዝምዝ ፍቅራችን በጣምራ ጦር ግሎ፣
ወንጀለኛው ዳኛ ባይፈርድ ኩታ ጥሎ፣
አውቃለሁ
ካድማስ ባሻገር ነው ያንቺ መከተቻ፣
የተገናኘን እለት ያቢዮት መባቻ።
አውቃለሁ
ከአሜን ባሻገር አልወለድም ነው፣
የወዲያ ነሽ ብዬ አላለፍኩሽ ምነው?
ትዝ ይልሻል ያኔ?
ሳለን በዘመቻ በቀይ ኮኮብ ጥሪ፣
ቀይ ባህር ቁጭ ብለን ሳጠልቅልሽ ድሪ፣
ጆሮዬ ሲያንቃጭል የህሊናን ደወል፣
አዲስ አለማየሁ ሊታየኝ ነው መሰል፤
ብዬ በምስጋና ሳልጨርስ የአፌን፣
የመውደድ ሰመመን አሳየኝ ልክፍቴን።
እናም
የብዕር ወገብ አንቄ፣
ጥበበቃል ሰንቄ፣
አንቺን ልስል ብታትር፣
ፈገግታሽን ፍለጋ ብዛክር፣
የለሽም ከመንበርሽ፣
ፍቅር ጎሎት ወንበርሽ።
ፍቅር እስከመቃብር እንዳላልሽኝ፣
ታብርን እንዳልጋትሽኝ፣
ሄድሽ አሉ በቢሆን አለም ተነጥቀሽ፣
አንድ ለናቱን ተሰርቀሽ።
እኔም በተራዬ፣
እየዘፈንኩ ሆዴን አበባዬ፣
አንቺን ለመርሳት ከትርምሱ ስገባ፣
ድንገት ብመለከት የጉንጉን ሽሩባ፣
ተዋስኩና ከቴድሮስ እንባ፣
ስምሽን ገደፍኩት ከብራናው ጀርባ።
ከዚያማ
ከሄድሽ በኋላ፣
ዓመት እንደሞላ፣
በሙት መንፈስ፣
ሀገር ሲታመስ፣
ደብዳቤሽ ደረሰኝ፣
ከነገ መለሰኝ።
እኔ ግን
ልቤ ይህን ይላል፣
እንድትሰሚው ይሻል።
ስንቴ ፈታሁሽ ስንቴ አግብቼ፣
ወግቶ ይማርህን ካንቺ አይቼ።
ጦቢያው ግጥሙን አንብባ ጨርሳ እንደፎካሪ ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች ነገር ስታላምጥ ክር እንደነከሰ ቴፕ የተጎለጎለ ድምጽ ሰምታ ጆሮዋን ወደውጭ ተከለች። የሷው ጉድ ነበር ባለቤቷ አድባሩ።
“ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ፣
ትቆጣኛለች እንጀራ ሚስቴ።”
በማለት እየዘፈነ ጉበኑን አልፎ ከቤት ሲዘልቅ “እሺ አቶ እንጀራ ባል” አለችው እንደገደል ዛፍ የሚወዘውዘውን ስካር እጅጉን ተጸይፋ። “እንወራረድ አህያ እንረድ፤ እኔ መታሪ አንቺ ጎንታሪ፤ የእንጀራ ባል እንዳልሆንኩ ልብሽ ያውቀዋል” አለ መደቡን ከቁሙ እየወደቀበት። “አንዴ ምን ሆነ መሰለህ” አለች ከስሩ ራቅ ብላ ከሽቦው አልጋ ጫፍ እየተቀመጠች። “ምን ሆነ?” አለ ሁኔታዋ ግድ ሳይሰጠው። “እግዜር ፍጥረቶቹን እየጎበኘ ዎክ ሲያደርግ ሰይጣን አግኝቶ ፈተነው፤ እንዴት አምላክህን ትፈታተናለህ? ብሎ ሲጠይቀው ጊዜ ንጉሥ ሰማይ እንጂ ምድር ላይ ምን ይሠራል? ብዬ ነው ሲል መለሰለት” አለች የጎሪጥ እያየችው። “ላይፈቱ አይተርቱ፤ ምን ማለት ነው እሱ?” አላት እሱም በተራው አትኩሮ እየተመለከታት።
“አካል ይመዘናል ልብ አይመዘንም፣
እየሰሙ መቻል ያንንም ያንንም።
እንዲል አዝማሪው ወረቀት የእንጀራ ሚስት ጎተራዋ እንጂ ልቧ አይገኝም” ስትለው “አፈኛና ጥቅመኛ ነህ እያልሽኝ ነው?” አለና ያለ የሌለ አቅሙን አሟጦ በያዘው ሽመል አበራያት።
አያ ሸንቁጤ አምሽተው ከገበያ ሲመለሱ ጩኸት ሰምተው ከመንገድ አገለሉና ከቤታቸው ደርሰው አንኳኩ፣ “ወትሮስ
የሽቦ አልጋ ያረገርጋል፣
የሰው ነሽና ምን ይደረጋል።
አይደል ነገሩ?” አለና አድባሩ ሊከፍትላቸው እየተንገዳገደ ወደበሩ አዘገመ። እግራቸውን እንዲያጥፉ ቢጋብዛቸው ሳይቀመጡ “አንተ ሰውዬ ብትመከር ምን አለበት?” ሲሉት “ወደል ውሻ ቦሃቃ ሊልስ የመንደር አርበኛ ከጋለሞታ ጭን ተወትፈው ሳይ ንቀቴ ያይላል፤ የናንተ ዘመዶች ሁሉ በዚያድባሬ ጦርነት ጊዜ ላለመዝመት ስትሉ ጉልበታችሁን በጓያ የሰበራችሁ፣ ጥርሳችሁን በመሮ ያወለቃችሁ፣ አይናችሁን በወረንጦ ያወጣችሁ ጉዶች ሳላችሁ ልምከርህ ስትሉኝ በጣም ያስቀኛል” አለ አድባሩ ባይኑ እየገፋቸው።
“የኛን ተወውና ምን ብታደርግህ ነው እንዲህ የወረድክባት?” በማለት ሲጠይቁት “የሷ የሴትነት መለኪያው የውበት ማሰሪያው የወንድ ቀበቶ መፍታት ነውና በፍቅሯ ተነድፈው ሽጉጥ ሲጋቱላት፣ ገመድ ላይ ሲሰቀሉላት፣ አሽከረ ብዙ ናትና ቁንጅናዋን አይተው ገላዋን ተመኝተው ከባህር ማዶ ሳይቀር የተንጋጉ ሴሰኞችን ሊከላከሉላት ሲነጠፉላት ልቧ አበጠና እኔን ፈነገለችኝ፤ ይሁን እንጂ ትንቀኛለች ስል አክብራኝ አያታለሁ ክፉ ናት ስል ደግ ሆና አገኛታለሁ፤ መላው ቢጠፋኝ ከትንፋሿ ሳልርቅ ከወዟ ሳልጣበቅ የእንጀራ ሚስቴ ላደርጋት ቆርጬ በሃሳቤ ስንት ጊዜ አግብቼ ፈታኋት መሰለዎ” አለ እንባውን እያንዠቀዠቀ።
አያ ሸንቁጤ “ሸኘኝ” ብለው እጁን ይዘውት ወጡና እንደሙላ ነስሮዲን ከልማዱ ውጪ ለአህያው አንገት ጀርባቸውን ሰጡና ተኮፈሱበት። “እንዴት ያለ አቀማመጥ ነው? ደግሞም አህያው ይበደላል” አለ አድባሩ ቂል ናቸው ሲል እያሰበ።
“ልብ ብለህ ስማኝ” አሉትና የሙላ ነስሮዲንን አስተምሮ አስተጋቡለት። “ሙላ በአህያ ቢቀመጥም ተማሪዎቹ ከፊቱ ሲጓዙ ቢመለከት ማህበረሰቡ ለመምህራቸው ክብር የሌላቸው ይላቸዋል፤ ከኋላም ቢሆኑ ተማሪዎቹን የሚንቅ መምህር ይሉታል፤ ብልሃት ያደረገው ለአህያው አንገት ጀርባውን ሰጥቶ ከተማሪዎቹ ጋር እየተያየ መጓዝ ነው፤ ላንተም ጦቢያው የንጀራ ሚስትህ ብትሆንም አንተም ለሷ የንጀራ ባሏ ነህና ጸባችሁ አይበርድም፤ ይልቁንም ከዚያስ? የሚለው ጥያቄ የፈጠረብህን ፍርሃትና ጥርጣሬ አስወግደህ ሙሉ ልብህን ስጣት መለያየት ታስቦ ፍቅር አይወጠንምና” አሉት።
አድባሩ ተመልሶ ጸጉሩን እያከከ እንደጅብራ ከፊቷ ሲገተር በቆመበት ትታው መኝታ ቤት ዘለቀች።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም