እስትንፋሳችን እንዲቆይ ችግኞቻችንን እንንከባከብ!
‹‹ …አረንጓዴ መሬት – ሰማያዊ ሰማይ፤
ውሃ ሙሉ ባህር – ወንዙ ጎሎ እንዳናይ፤
እንላለን ሁሌም እንድንኖር በዓለም ላይ፤
ዛፍ ይኑር ፤ ዛፍ ይኑር -ዝናብ ይጣል ሰማይ፤
ዛፉ ዛፉ – እስትንፋሴ ፤
ልጠብቅህ – እንደራሴ ፤
ዛፉ ዛፉ – አረንጓዴ ፤
አንተ ባትኖር እኛስ አለን እንዴ ?….››
ሲል ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ማቀንቀኑ ሁሉም ተፈጥሮን መጠበቅ እንዳለበት ኃላፊነቱን እንዲገንዘብ ለማድረግ ነው። እርግጥ ነው አረንጓዴ መሬት፣ ሰማያዊ ሰማይ፣ ውሃ ሙሉ ባህር፣ ዝናብ የሚጥል ሰማይ ፣እስትንፋስ የሚሆን ዛፍ የምናገኘውና የመኖር ዋስትናችን የሚረጋገጠው መሰረታዊ የሆነውን ዛፍ ለማግኘት ዛሬ በምንተክላቸው ለጋ ችግኞች ነው።
የሰው ልጅ በምድር ላይ ከኖረበት ጊዜ ጀምሮ አጥፊም አልሚም ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል። ምድር የለገሰችውን የተፈጥሮ ሀብት-ዛፍ ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ የመቁረጫ መሳሪያዎች በመጠቀም፤በሰደድ እሳትና በምንጣሮ በማውደም ወደር ያልተገኘለት ፍጡር ቢኖር የሰው ልጅ ብቻ ነው። በዚህ የራሱ ጥፋት ምክንያት ተፈጥሮ ፊቷን በማዞሯ የዝናብ እጥረት ፣ የሙቀት መጨመር፣ የወንዞች መድረቅ፣ የምርት መጥፋት፣ በንፋስና በጎርፍ ማዕበል መመታት ተከስቶ ስንት ፍጡር አለቀ።
የዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያቱ ራሱ ሰው መሆኑን እያወቀ እንኳ አሁንም እጁን ሊሰበስብ ያለመቻሉ የሚያስገርምም የሚያሳዝንም ሆኗል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት አረንጓዴ ልማት ማካሄድ ብቸኛው አማራጭ ሆኖ የቀረበውም ይህንን የሰው ልጆችን ወደ ዕልቂት እየመራ ያለውን አሳሳቢ የሙቀት መጠንና የአየር መዛባት ለመቀነስ የሚያስችል በመሆኑ ነው።
የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አጀንዳ መሆኑም ለዚሁ ነው። የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ አሁን የሰው ልጆች ከሚፈልጉት ውጪ በመሆን ወደ ጥፋት ሊወስደን የቻለው የዓለም የደን ሽፋን ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ እየሳሳ መምጣቱ ለሙቀት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጉ ነው። ለዚህ ሁሉ ለውጥ በምክንያትና በዋነኛነት የሚጠቀሱት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ጉዳዮች በመሆናቸው ኢትዮጵያ ይህንን ጥፋት ለመቀነስ የበኩሏን ኃላፊነት ለመወጣት የአገሪቱን ዜጎች በማነቃነቅ ታሪክ መሥራት የቻለችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች።
ለዚህም ነው ባለፉት ወራቶች ታቅዶ በያዝነው ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ሕዝብ በነቂስ በመውጣት በተደረገው ርብርብ በአጠቃላይ ከ353 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የተቻለው።
አዎ! የዛሬ ችግኞች የነገ ዛፎች ሆነው የምናያቸው እንደተከልናቸው ተንከባክበን ስናሳድጋቸው ብቻ ነው፤ በብዙ ሚሊየን ብር የወጣባቸውን የነገ ተስፋ ችግኞችን ተከታትለን ካላሳደግናቸው ቀበርናቸው እንጂ ተከልናቸው ማለት አይቻልም። በአንድነት ያሰባሰቡንና የጥንቱን ህብረታችንን ዳግም ያየንበት ይህ መልካም ሥራ በዓለም ተደናቂነትን በማትረፉ የዓለም መገናኛ ብዙሃን አስተጋብተውታል።
‹‹ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ባካሄደችው ችግኝ ተከላ ሪኮርድ ሰበረች›› በማለት የዘገበው ቢ.ቢ.ሲ. ሲሆን፤ ‹‹ከ353 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በ12 ሰዓታት ውስጥ በመትከል ኢትዮጵያ የዓለምን ሪኮርድ ሰበረች›› ያሉት ደግሞ አፍሪካ ኒውስና ዚ ኢንዲፕንደንት ናቸው። ዚ ቴሌግራፍና አሶሺዬትድ ፕሬስ በበኩላቸው ‹‹ኢትዮጵያ የተራቆተ መሬቷ እንዲያገግም በአንድ ቀን ብቻ ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተከለች›› በማለት ዘግበዋል።
ብዙዎች ያሞካሹት ይህንን መሰሉ ድንቅ ተግባር ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ እንዲሆን ጅምሩን ዳር ማድረስ ኃላፊነት ከሚሰማውና አገሩን ከሚወድ ዜጋ የሚጠበቅ ነው፤ የዛሬዎቹ ችግኞች አረንጓዴ መሬት ፣ ሰማያዊ ሠማይ፤ ውሃ ሙሉ ባህር ሆነው እስትንፋስ እንዲያቆዩ ተንከባክበን ፍሬያቸውን ማየት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011