አዲስ አበባ፡- የአገሪቱን ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ለአህጉር አቀፍ ትብብሮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ከተሞች የውሃ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙክታር አሕመድ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የከተሞች የውሃ አገልግሎት መስሪያ ቤቶች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎት በማዘመን ጥራቱን ለማሻሻል በዘርፉ የተሻለ ልምድ ካላቸው አጋር የአፍሪካ ተቋማት ልምድ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሰራ ይገኛል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ በአፍሪካ ደረጃ የውሃ ብክነትን ከመቀነስ፣ ገቢን በአግባቡ ከመሰብሰብና ጥራት ያለው አገልግሎትን ከመስጠት አንጻር ጥሩ ልምድ ያካበቱ ብዙ ከተሞች ስላሉ ትብብሮቹ ለኢትዮጵያ ከተሞች ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡
የአፍሪካ የውሃ ፌዴሬሽን ለወላይታ ሶዶ፣ ለደሴ እና ለዓድዋ ከተሞች የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን ዕድል በማመቻቸት የአገልግሎት ጥራታቸውን የሚያሳድጉበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ ለአብነት ያህልም የወላይታ ሶዶ ከተማ ውሃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ከደቡብ አፍሪካዋ የደርባን ከተማ አቻ ተቋም ድጋፍ የሚያገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት በ82ኛው የአፍሪካ የውሃ ፌዴሬሽን የቴክኒክና ሳይንስ ጉባዔ ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተፈራርሟል፡፡
ከአፍሪካ አገራት በተጨማሪ ከአገር ውስጥም በዘርፉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ከተሞችም ለሌሎቹ ከተሞች ልምዳቸውን የሚያጋሩበት አሠራር ስለመኖሩም ተናግረዋል፡፡ ለአብነት ያህልም የውሃ ብክነትን በመቀነስ ረገድ ጥሩ ተሞክሮ ያለው የአምቦ ከተማ የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ለሌሎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች ልምዱን የሚያካፍልበት አሠራር እንደተዘረጋም ገልጸዋል።
«ብዙ የውሃ ተቋማት ቢገነቡም በብክነት ምክንያት የተመረተው ውሃ በአግባቡ ወደ ደንበኞች አይደርስም» ያሉት አቶ ሙክታር፣ ብክነቱን ለመቀነስ ፌዴሬሽኑ ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
አንተነህ ቸሬ