
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በዓለም ማህበረሰብ ድጋፍና ተቀባይነት እንዲያገኝ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌታሁን አስታወቁ። ሥራው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነም አመልክተዋል።
ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሀገሪቱ ሕዝብ የህልውና ጥያቄ መሆኑን የዓለም ህብረተሰብ በአግባቡ ተገንዝቦ ድጋፍ እንዲሰጠው ለማድረግ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ይጠይቃል።
መንግሥት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት ለማድረግ የጀመረው ንቅናቄ የሚበረታታ መሆኑን የገለፁት ኢንጅነር ጌታሁን፤ በተለይም ታሪካዊ ዳራዎችን ዋቢ በማድረግና ሀገሪቱ አሁን ላይ ካላት የሕዝብ ቁጥር፤ እያደገ ካለው ኢኮኖሚዋ አንፃር የራሷ የባሕር በር መኖር ምን ያህል ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የዲፕሎማሲ ሥራው ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ልክ እንደህዳሴ ግድብ ሁሉ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ፤ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን ማዋቀር፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በያሉበት ሆነው ሊሠሩት የሚገባ ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
‹‹የባሕር በር የሌለው ሀገር በሌሎች ሀገራት ተፅዕኖ ስር ስለሚወድቅ እድገቱ በፈተናዎች የተሞሉ ናቸው። በሌሎች ሀገራት ወደብ ተጠቅሞ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረግ ጥረትም ብዙም ፈቅ የሚያደርግ አይደለም›› ያሉት ኢንጅነር ጌታሁን፤ ይህንን እውነታ ፍፁም ሰላማዊና የጋራ ተጠቃሚነትን ባገናዘበ መልኩ ለዓለም መንግሥታት ማቅረብ እንደሚገባ አመልክተዋል። አክለውም በተጓዳኝም የኢትዮጵያን ፍላጎት በግልፅ በማሳወቅ ጎረቤት ሀገራት እንዲረዱት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
‹‹ኤርትራ ስትገነጠል የኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅና ይሁንታ አልሰጠም ነበር፤ ይልቁንም በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሃይሎች የሀገሪቱን ሕዝብ በማፈን የፈፀሙት በደል ነው›› ያሉት ኢንጅነር ጌታሁን፤ ከዚያ ወዲህም ቢሆን በሂደት የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውህደቶችን በማምጣት በጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር አለመቻሉን አስገንዝበዋል።
‹‹ሥልጣን ወዳዶችና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይ ሃይሎች በባህልም በቋንቋም አንድ የሆነውን ሕዝብ ለመከፋፈል ጥረት ያደርጉ ነበር›› ያሉት ኢንጅነር ጌታሁን፤ ከዚያ ይልቅ ትልቅ ሃሳብ ይዞ ለጋራ ብልፅግና መሥራት ለሁለቱም ሀገራት ሕዝብ የሚጠቅም እንደነበርም አመልክተዋል። እነዚህ ሃይሎች ያራምዱ የነበሩት ፖሊሲ የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ላይ እንቅፋት ሆኖ መሻከር እንዲፈጠር ያለመ እንደነበር ገልጸዋል።
አክለውም ‹‹ያም ቢሆንም አሁንም ድረስ ሕዝብ ለሕዝብ የመቀራረብና አብሮ የመኖሩና የማደጉ ፍላጎት በግልፅ የሚታይ ነው›› ብለዋል። ይህንን ታሳቢ ያደረገ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክር ቀጣይነት ያለው ሕዝባዊ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
‹‹የኤርትራ ሕዝብም ቢሆን በባህል በቋንቋና በሥነ ልቦና አንድ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተቀራርቦ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው እምነት አለኝ›› ያሉት ኢንጅነር ጌታሁን፤ ይህንንም በተለያዩ አጋጣሚዎችም እየገለጸ ነው ፤ የኤርትራ ምሁራንም ይህንኑ እውነታ እንደሚቀበሉት ጠቁመዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም