አዲስ አበባ፦ በ2007 ዓ.ም. የኮከብ ደረጃ ያገኙ ሆቴሎች በመጪው ዓመት እንደ አዲስ ተመዝነው ደረጃ ሊሰጣቸው መሆኑን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ደረጃ ምደባው ዳግም የሚካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በየሦስት ዓመቱ እንደሚካሄድ ደንብ ቁጥር 172/2002 በተወሰነው መሠረት ነው፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ የተደረገው ከአራት ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም. ሲሆን በወቅቱ በዓለም ቱሪዝም ድርጅት አማካኝነት 365 ሆቴሎች ተመዝነው 270 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ውስጥ ገብተዋል። የኮከብ ደረጃ ላገኙት ሆቴሎች በ2012 ዓ.ም. በድጋሚ ምዘና ሲደረግላቸው የተሻሻሉትና ማስፋፊያ ያደረጉት ደረጃቸው ከፍ የሚል ይሆናል፤በዚህ አጋጣሚ ከነበሩበት ዝቅ ብለው የተገኙም ከነበሩበት ደረጃ እንዲወርዱ ይደረጋል።
ቀደም ሲል ምደባው የተደረገው ከውጭ አገር ድርጅቶች በመጡ ሙያተኞች እገዛ ነበር ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ዳግም ምደባው ሳይደረግ የዘገየውም የራሳችንን ባለሙያዎች ለማብቃትና አቅም ለመፍጠር ሲባል ነው። በሌላ በኩልም ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስር የገቡ አዳዲስ ሆቴሎችን መዝኖ የመመደብ ሥራ ስናከናውን ቆይተናል ብለዋል፡፡
እስካሁን ደረጃ ላልወጣላቸው ሎጆችና ሬስቶራንቶች በመጪው ዓመት ምዘና ተካሂዶ የኮከብ ደረጃ ምደባ የሚሰጣቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ በ2011 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ በተደረገው የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ለ83 ሆቴሎች ከ1 እስከ 4 ኮከብ ደረጃ መሰጠቱን አስታውሰው፣ ከባለ ኮከብ ደረጃ ሆቴሎች አመዳደብ ጋር ተያይዞ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሆቴሎች ካሉ ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ዳንኤል ዘነበ