በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጁ ወንጀሎች መበራከታቸው ይነሳል፡፡ ለውጡን ለማደናቀፍ አልሞ ከሚንቀሳቀሰው ጀምሮ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በአቋራጭ ለመክበር የሚዳዳው ወንጀለኛ መጠን በማደጉ ህብረተሰቡ ከቤቱ በሠላም ወጥቶ በሠላም መግባቱ ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ አስገድዷል፡፡ በከተማዋ የወንጀል መስፋፋትና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደራጁ ዝርፊያዎች የተበራ ከቱበት ቁልፍ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምን እርምጃ እየተወሰደ ነው ?
ም/ል ኮሚሽነር ዘላለም፡- ባለፉት አራትና አምስት ወራት የተደራጁ ዝርፊያዎች በከተማዋ ተበራክተዋል፡፡ ወንጀል የተበራከተባቸው ምክንያቶች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዋናነት ግን ለውጥ ላይ እንደመሆናችን በግርግር ተጠቅመው ባልተለፋበትና የራሳቸው ሃቅ ባልሆኑ ሃብቶች ለመክበር የሚያስብ ኃይል ከመበራከቱ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እናም ይህ አይነቱ ወንጀል ከራሳቸው ከግለሰቦቹ ሁኔታ የሚመነጭ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ባለፉት 27ዓመታትም ቢሆን መጠኑ ይለያይ እንጂ የተደራጀ ዝርፊያ ሲጋጥም ነበር፡፡ አሁን የበለጠ ያደረገው ግን መንግስት በለውጥ እንቅሳቀሴ ውስጥ በመሆኑ በዚህ ቀዳዳ ገብቶ የህዝብና የመንግስትን ንብረት በስፋት ለመመዝበር ያለመ መሆኑ ነው፡፡
እውነት ነው በተጠቀሰው ሁኔታ ህብረተሰቡ ከምንጊዜውም በተለየ ወጥቶ ለመግባት የተቸገረበትና ስጋት ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ለውጡን ተከትሎ በተለይም የመንግስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚገነቡበት ሳይቶች የግንባታ ግብዓቶችን እንዲሁም የቴሌኮሙኒኬሽን ኬብሎች ዘረፋ ከዋና ዋናዎቹ መካከል ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር አዳዲስ አመራሮች መምጣታቸውን ተከትሎ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካና ቦሌ ክፍለከተሞች አጋጣሚውን ተጠቅሞ የመሬት ወረራዎች ተካሂደዋል፡፡ ኪስ ቦታዎችን የማስፋፋትና የማጠርና ወደ ግል ይዞታ የማስገባት ዝንባሌ በስፋት ታይቷል፡፡ ስለዚህ የዝንባሌው አይነት ይለያይ እንጂ በድርጊቱ ሰፊ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ተዘርፏል፡፡
እኛም ወደዚህ ተቋም ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ በሶስትና አራት ዙር እርምጃዎች ወስደናል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የመፈፀም አቅማችንን ስርነቀል በሆነ መልኩ ለማስተካከል ያስችለን ዘንድ መልሶ የማደራጀት /የሪፎርም/ ስራ መስራት አለብን ብለን የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን፡፡ በዋናነት የአባሎቻችንን ጥራት በማሻሻልና አቅማቸውን በማሳደግ ህብረተሰቡ የሚረካበት፣ በክህሎትና እውቀትን መሰረት ያደረገ ፖሊሳዊ አገልገሎት መስጠት የሚያስ ችለንን አደረጃጀት ነው ለመፍጠር ያቀድነው፡፡ ህበረተሰባችን በሰላም ወጥቶ ለመግባት ምን እሆናለሁ ብሎ መጨነቅና ማሰብ የለበትም፡፡ የሰላሙ መሰረት እኛ መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥም ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በውስጥ ያለንን ቁመና ማስተካከል ወሳኝ በመሆኑ አመራሮቹን የመለወጥ፣ የተሻለ አደረጃጀት የመፍጠርና የማስፋት ሥራ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው፡፡
በሌላ በኩልም አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረትና የተለያዩ አለምዓቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ ይህንን መነሻ በማድረግ ሰላማዊ ከተማ ለመፍጠር ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው፡፡ እስካሁንም በዚህ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ስጋቶችን ለማስቀረት በስፋት ተንቀሳቅሰናል፡፡ ይህ ማለት ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልቋል ባንልም የተለያዩ እርም ጃዎች እየወሰድን ነው፡፡ ይህም ህብረተሰቡን ካላሳተፈ እውን ሊሆን ስለማይችል ከነዋሪውና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የግንኙነት መርሃግብር ፈጥረን የመከላከሉን ስራ በትብብር ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡
በቅርቡ ከከተማ አስተዳደሩና ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን የተወረሩና በልማት ሰበብ ለዘመናት የታጠሩ መሬቶችን የማስመለስ ስራ አከናወኗል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ታጥረው መቆየታቸው ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ስለነበሩ ከመናፈሻነት ባሻገር ለፓርኪንግ አገልግሎት እንዲውሉ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለወንጀሎቹ መበራከት የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት መዳከም እንደ ዋና ምክንያት ይነሳል፡፡ ህብረተሰቡም በቦታው የተመደቡ አባላት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያሰ ማል፡፡በተለይ ወንጀል ሲፈፀም ክልሌ አይደለም በሚል ቸልተኝነት እንደሚታይባቸውና የነፃ ስልክ አገልግሎቱም በተጨባጭ እንደማይሰራ ይጠቅሳሉ፡፡ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ም/ል ኮሚሽነር ዘላለም፡- ትክክልነው እንደ ተባለው የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የመፋዘዙ ነገር በስፋት ታይቷል፡፡ በሚፈለገው ደረጃ እየሰራ አለመሆኑን እኛም ገምግመን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየሰራን ነው፡፡ በተለይም በብህረተሰቡ ጥሩ ተቀባይነት ያላቸውን በስነምግባር የታነፁ ፖሊሶችን የመመደቡን ስራ የመልሶ አደረጃጀቱ አካል አድርገነዋል፡፡ ብቃት ያላቸውና ማዕረጋቸው በመኮንንነት ደረጃ የሆኑ አባላትን መመደብ አለብን የሚል አዲስ አቅጣጫ ይዘን ምደባ ጀምረናል፡፡ በቅርብ ጊዜ ከህብ ረተሰባችን ጋር እንገናኛለን፡፡ እነርሱንም የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን፡፡
ሁለተኛ የህብረተሰቡን የባህል፣ ያኗኗርና የኢኮኖሚ እድገት የሚመጥን የግኑኙነት መርሃግብር እጥረት እንደነበረብን ገምግመናል፡፡ በመሆኑም ይህንን ሊመልስ የሚችል ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት መኖር አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህ ረገድ ህብረተሰቡ ያነሳው ትክክል ነው፡፡ ግን እርምጃው የዘገየው ከዚህ ቀደም ቦታውን ተላምደውና ከወንጀለኞች ጋር አብረው በህብረተሰቡ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ የፖሊስ አባላትን የማጥራት ስራ አስቀድመን መስራት ስለነበረብን ነው፡፡ ስለዚህ ፈትሸን በብቃታቸው የተሻሉ፤ ታማኝ የሆኑ፤ ህዝብን ማገልገል የሚፈልጉና ስነምግባር ያላቸውን አባላት በቦታው ለመመደብ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ ይህንንም ህብረተሰቡ ሊገነዘብልን ይገባል፡፡
የነፃ የስልክ ጥሪ ቶሎ ምላሽ አለማግኘት ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ዋነኛ ምክንያት ከቴሌ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዋናነትም መስመሮች በቁፋሮ ሲበጠሱ ቶሎ ስለማይቀጠሉ አገልግሎቱ የሚቆረጥበት ሁኔታ አለ፡፡ በእኛ በኩል በርካታ ሰው መድበን ለዚህ አገልግሎት ብቻ እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ ይህንንም በአካል መጎብኘት ይቻላል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ የመደራረብ ሁኔታ ያጋጥማል፤ ምክንያቱም ያው ወንጀል ተጠብቆ የማይመጣ እንደመሆኑ በተመሳሳይ ሰዓት ከተለያየ አቅጣጫ ወንጀል ሲከሰት በእኩል ፍጥነት መድረስ ላይ አሁንም የሚቀረን ነገር አለ፡፡
ከዚያ በተረፈ ግን «ክልሌ አይደለም» በሚል ወንጀልን በቸልተኝነት የሚመለከቱ ፖሊሶች ስለመኖራቸው ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ ባይቻልም ካሉ ግን እነዚህ አካላት ኃላፊነታቸውንም ሆነ የሙያ ስነ-ምግባራቸውን የዘነጉ ናቸው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን ሁሉም በተመደበበት ቦታ የመስራት ሃላፊነት ቢኖርበትም የኔ ክልል የሚባል ነገር የለም፤ ነገር ግን ይህ ችግር ከፖሊስ ግለሰባዊ እንዝህላልነት የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር የደንብ ልብሱን ለብሶ የሚንቀሳቀስበት ቦታ የራሱ ክልል ነው፡፡ ባይሆን እንኳ ወንጀል ተፈፅሞ ቀጠናዬ አይደለም በሚል ቸል ማለት አይችልም፡፡ ቢያንስ ለሚመለከተው አካል ወዲያውኑ በሬዲዮ ማስተላለፍ ይችላል፡፡
ማንኛውም ፖሊስ መለዮውን እስከለበሰ ድረስ ወንጀልን የመከላከል ህብረተሰቡን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት፡፡ ይህ የፖሊስ ዲሲፕሊን አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የአመለካከት ችግር ያለባቸውን አባላት የማጥራት እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ ህብረተሰብ ከሚሰበሰብ ታክስ ነው ደመወዝ የሚከፈለኝ ብሎ የሚያስብ አባል መፍጠር ላይ ብዙ ይቀረናል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ፅሁፎች አዘጋጅተን ሁሉንም አባላት ከህዝቡ ጋር የማወያየት ስራ ለመስራት አቅደናል፡፡ ነገር ግን አስቀድሜ እንዳልኩት አዲስ አመራር እንደመሆናችን ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን እያጠራን መሄድ ጊዜ ይጠይቀናል፡፡ በቅርቡ ሪፎርሙን አጠናቅቀን ወደ ትግበራ ስንገባ ችግሮቹ ደረጃ በደረጃ ይቃለላሉ የሚል እምነት አለን፡፡ በዚህ ሁለት ወር መንግስት ያወጣው የ100 ቀን እቅድ ውስጥ እንደ ኮሚሽን የ60 ቀን እቅድ አውጥተናል፡፡ ይህንን በአስሩም ክፍለ ከተማ አዘጋጅተን ከሁሉም ጋር መግባቢያ ተፈራርመናል፡፡
ይህም በክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚስተዋሉ ወንጀሎችን ለይቶ በምን መልኩ መከላከል የሚያስችል ግልፅና ተጠያቂነት የሚያመጣ እቅድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እቅዳችሁ ከሌሎች መንግሥ ታዊ ተቋማት በተለየ ቀኖቹ ያነሱበት የተለየ ምክንያት ይኖር ይሆን?
ም/ል ኮሚሽነር ዘላለም፡- አዎ የ60ቀን እቅድ ለእኛ እንደ ፖሊስ ፓይለት ፕሮጀክት ነው ያየነው፡፡ምክንያቱም ያልተለመደ እንደመሆኑ የ60 ቀኑን አፈፃፀም ገምግመን ውጤቱን ካየን በኋላ ለማስቀጠል ነው ያሰብነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከተደራጀ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ታርጋ በሌላቸው ሞተሮች ዝርፊያን ለመከላከል ከትራንስፖርት ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር እየሰራችሁበት ያለው አግባብ ምን ይመስላል?
ም/ል ኮሚሽነር ዘላለም፡- ወንጀል የሚፈፀ ምበት አንዱ መንገድ ሞተር ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ሶስት ወራት ከ2ሺ500 ያላነሱ ሞተሮች በቁጥጥር ስር አውለናል፡፡ አንዱም ወንጀል የቀነሰው በዚህ ደረጃ በሁለት ሶስት ዙር ሞተረኞችን የማደን ስራ ስለሰራን ነው፡፡ ታርጋ የሌለው ሞተር የለም ለወንጀል እንዲመቻቸው እየፈቱት ነው፡፡ ጨርቅ ይሸፍኑታል፤ ጭቃ ይቀቡታል፤ ያጣምሙታል፡፡ እነዚህን አጥንተን የሚገኙበትንና የሚያንቀሳቅሱበትን ቦታ ሁሉ ለይተናል፡፡
እንደምሳሌ ብንጠቅስ እንኳ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተያዘ አንድ ግለሰብ እስከ10 ሞተር ሳይክል ገዝቶ ለተለያዩ ወንጀል ስራዎች የሚያሰ ማራበት ሁኔታ እንዳለ ደርሰንበታል፡፡ አንዳንዱ በገቢ ምንጭነትም ለታክሲ ስራ የሚሰራበት መኖሩንና ሌላውም የተለያዩ የንግድ እቃዎችን የሚያመላ ልስበት ሁኔታ መኖሩን አረጋግጠናል፡፡ በነገራችን ላይ የሞተር አገልግሎት ለድርጅትና ለመንግስት ተቋማት ካልሆነ በስተቀር ሞተርን የታክሲ አገልግሎት ማዋል በህግ የተከለከለ ነው፡፡ ለዚህ አላማ እየዋሉ ያሉትን ሞተሮች የመለየቱን ስራ የምንሰራው ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ነው፡፡ እኛም በተለይ ትራፊኩን የመቆጣጠር ሃላፊነትም ስላለብን በአስሩም ክፍለ ከተሞች ላይ ባደረግነው ዘመቻ እንደዚህ አይነት ችግሮች ያለባቸውን ሞተሮች ይዘናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የተሰረቁ፤ አንዳንዶቹ ባለቤት የሌላቸው ናቸው፡፡ አሁንም ህገ-ወጥ ሞተረኞችን የማደን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ጋር ተያይዞ የህገ-ወጥ መሳሪያና የሰዎች ዝውውር መጠን ከምንጊዜውም በላይ መጨመሩ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህን ወንጀሎች ከመከላከል አኳያ ኮሚሽኑ ምን እየሰራ ነው?
ም/ል ኮሚሽነር ዘላለም፡- እንደተባለው በዋናነት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት የሚደረግ ከፍተኛ ጥረት መኖሩን በምናደርገው ማጣራት ለማወቅ ችለናል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች ቦታዎችም ለማሸጋገር ሲባል የተያዙ በርካታ የጦር መሳሪያዎች አሉ፡፡ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በሚመለከት እኛ እንደ አዲስ አበባ ከፌዴራልና ከክልሎች የፀጥታ አካላት ጋር ሆነን በተለያዩ ጊዜ አብረን በጋራ ሰርተናል፤ ሰሞኑንም እየተያዘ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 1ሺ599 ሽጉጦች፥ 28ሺ209 የተለየዩ አይነትና 18ሺ717 የክላሽ ጥይቶች እንዲሁም አንድ ብሬን ጠመንጃ ተይዟል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎችም በዚህ ጉዳይ ተይዘው በፍርድ ቤት በምርምራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኮሚሽናችን በራሱ መንገድ በዚህ መልኩ የሚደረጉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የከባድ ወንጀል ጥናት ቡድን ያጠናውን መሰረት አድርገን በአስሩም ክፍለከተማ ላይ የቁጥጥር ስራ እየሰራን ነው፡፡ ሁለተኛ ድንገተኛ ፍተሻዎች በተለያዩ ጊዜያት እናደርጋለን፡፡ በተለይም በመግቢያ በሮችና በማዕከላዊ የከተማዋ ክፍል የፍተሻና የቁጥጥር ስራ በስፋት ይከናወናል፡፡
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይሰጥ የነበረው የጦር መሳሪያ የምዝገባ ስርዓት እንዲስተካከል አድርገናል፡፡ መመዝገቡ ራሱ የሚያበረታታ በመሆኑ ካቆምን አራት ወራት ሆኖናል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ክልሎች ላይ እያስመዘገቡ የመያዝ ዝንባሌ በመኖሩ የማሸጋገር ሁኔታው አሁንም ቀጥሏል፡፡ እነዚህ ላይ ለህዝቡ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት በአሁኑ ወቅት እየተፈፀሙ ያሉት አብዛኞቹ ወንጀሎች በህገወጥ መሳሪያ የተፈፀሙ መሆናቸውን ተገንዝቦ ለራሱም ሆነ ለአካበቢው ደህንነት ጠንቅ የሆኑ ህገወጦችን የማጋለጥ ሚናውን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ ነው፡፡
ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርም አስቀድሜ እንዳልኩት በእቅድ አስገብተን አስተላላፊዎች፣ ደላሎች፣ ኤጀንሲዎችና ተቀባባዮች ላይ ከሶስት ወራት በፊት እርምጃ የተወሰደባቸው አሉ፡፡ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉም በርካቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁንም ከአገር አቀፉ ግብረሃይል ጋር በመሆን እንደ አዲስ አበባም ከተደራጀው የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ኮሚቴ ጋር በጋራ እየሰራን ነው፡፡ ስለዚህ ከመሳሪያ ዝውውሩ ጋር ባልተናነሰ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሌላው ለወንጀል መበራከት አንዱ ተደርጎ በተደጋጋሚ የሚነሳው የፖሊሱ የያገባኛል ስሜት ያለመኖር እንደሆነ ነው፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ አባላቱን የሚመለምልበት መንገድ የከተማዋን ተወላጆች ማዕከል ያደረገ አለመሆኑ ይተቻል፡፡ በዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ይኖር ይሆን?
ም/ል ኮሚሽነር፡- በፖሊስ ውስጥ የባለቤትነት ስሜት ማጣትነው በሚለው ሃሳብ አልስማማም፡፡ እንደማንም ፈፃሚ አካል በፖሊስ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ ድክመቱ የሚመነጨው ስራውን ካለመውደድ ወይም ደግሞ የራሱ የግል ችግር ሲኖርበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ መነሻቸው ብዙ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰራቸው ውጤታማ ስራዎች ያሉትን ያህል በዚያው ልክ እጥረት አለበት፡፡ ያልደረሰባቸውና ያልተሻገራቸው ችግሮች አሉበት፡፡ ይህንን በሚዛኑ ነው መናገር የምፈልገው፡፡ ምክንያቱም በአዲስ አበባ ውስጥ ያለው ኑሮ በጣም ውስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ከስነ-ምግባር አኳያ እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በእርግጥ ሁልጊዜ የሚነሳው ክፍተት ምልመላችን ላይ ነው፡፡ ይህ ማለት የአዲስ አበባ ልጆች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ግን በበቂ ደረጃ ነው? አይደለም? የሚለው ጉዳይ አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡ በተለይ እስከ መኮንንነት የሚደርስ መልምሎ ያለማፍራት ክፍተት ነበረብን፡፡ በነገራችን ላይ ማስታወቂያው ለሁሉም ነው የሚወጣው የደመወዙ ስኬል ሳቢ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም አንዳንዴ ዝም ብሎ ከአዲስ አበባ ስላልመጡ ነው ለህዝቡ ተቆርቋሪ ያልሆኑት እያሉ በጅምላ የመጨፍለቁ ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡
አሁን ምልመላው የሚካሄድበትን አግባብ በአዲሱ ሪፎርም አካትተን ይዘናል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ትምህርታቸው፤ አቅማቸውና ብቃታ ቸው በተሻለ ደረጃ ላይ ያሉ አባላትን የመመደብ ስራ ይሰራል፡፡ የደመወዝ ስኬሉንም ሳቢ በማድረግ የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በዚህ ላይም ከፌዴራል ጋርም ተነጋግረን በዚህ ደረጃ ሊመጥን የሚችል አባል ለመመልመል ታቅዷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- መደብደብን እንደመብት የሚቆጥሩና ከፍተኛ የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው የፖሊስ አባላትን የማጥራትና አስተሳሰብ ቀረፃው ላይ ለመስራት ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል?
ም/ል ኮሚሽነር፡- የተቋም ግንባታ ሲባል የህንፃ ግንባታና ግብዓት የማሟላት ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ በተመሳሳይም በሰው አዕምሮ ላይ የምንሰራው ስራ ከአንድ ጫፍ ወደ አንድ ጫፍ የማምጣት ስራ ይጠይቃል፡፡ በመደብደብ የሚያምንና መብት አድርጎ የሚወሰድ ልምድ ሊቆም እንደሚገባ በሁሉም አመራር ዘንድ ታምኖ ነው የማጥራቱ ስራ እየተሰራ ያለው፡፡ በተለይም መንግስት በግልፅ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ማንኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ሲውል ሰብአዊነቱን በጠበቀ መልኩ ነው መያዝ ያለበት ብለን በአዲስ መልክ የጀመርነው ስራ አለ፡፡ ግን ብዙ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ስርነቀል የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣትም መስራት ይጠይቃል፡፡
መደብደብ ለማንም ፖሊስ የተሰጠ መብት አይደለም፡፡ የተሰጠ መብት ቢኖር ጥቃት በሚፈፀምበት ጊዜ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ ብቻ ነው፡፡ ደግሞም አባሉ ግለሰብን በመያዝና በማንገላታት የሚፈጠር ሰላም አለመኖሩን ተገንዝቦ ሚናውን ሊወጣ ይገባል፡፡ በመደብደብ አናገለግልም፡፡ ከዚህ የዘለለ የሰውን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት እንዲሁም በሰውነቱ የመኖር መብቱ ላይ ማንም ጥቃት የመሰንዘር ኃላፊነትም ተልዕኮም የለውም፡፡ ባለፉት ዓመታት ከፖሊስ መርሆ ውጭ የሆኑ ህገ-ወጥ ተግባራት ተፈፅሟል፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ለማስቀረት ግን ብዙ ስራ ይፈልጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሰነድ የመቅረፅ ስራ እየሰራን ነው፡፡ በቀጣዮቹ ወራት ከህዝቡ ጋር ውይይት እናደርጋለን፡፡ሥራችንን ህዝቡ እንዲገመግመውና እንዲፈርደው ነው የምንፈልገው፡፡ በነገራችን ላይ ሌላ የመገምገሚያ መስፈርትም አያስፈ ልግም፡፡ ምክንያቱም ተልዕኳችን ህዝብን ማገልገል በመሆኑ ህዝብ ያልተሳተፈበት ደግሞ የፖሊስ ስራ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል፤ ደግሞም ለህዝብ እየሰራን ህዝቡን ባዕድ ማድረግም አይቻልም፡፡ይህ አስተሳሰብ በሳይንስም ደረጃ እርስበርስ የሚጣረስ በመሆኑ ይህንን ሙሉ ለሙሉ ማስተካከል ይገባናል ብለን እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት አንዳንድ የፖሊስ አባላት መንግስታዊ በዓላትን ለማክበር በሚል ከነጋዴው ህብረተሰብ ስፖንሰር ይጠይቃሉ፡፡ ይህም የፍትህ ስርዓቱን እምነት እንዲያጣ ያደረገው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ይህንን አይነቱን ችግር ለማስወገድ የማጥራቱ ስራ እነዚህን አያካትትም?
ም/ል ኮሚሽነር፡- ያካትታል እንጂ! በነገራችን ላይ ፖሊስ ከማንኛው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ገለልተኛ ሊሆን እንደሚገባ ህገደንቡ ያስገድደዋል፡፡ በዓላትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ይሳተፋሉ ያልሻቸው ነገሮች እኔ አላውቃቸውም፡፡ አሁን ከመጣን በኋላ ግን እንደዚህ አይነት በዓልም አላከበርንም፡፡ በዚህ ደረጃ ሄደው ስፖንሰር እንዲያመጡም አይፈለግም፡፡ የኛ ስራ ፀጥታ የማስከበር ስራ ነው፡፡ በምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን የለብንም፤ የሆነ የፖለቲካ ድርጅትም አስፈፃሚ መሳሪያ መሆን አይገባም፡፡
ፖሊስ ዘብ ሊቆም የሚገባው ለህገመንግስቱና ለህዝቡ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ባለፉት ጊዜያት ጉራማይሌ የሆነ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ግን አላውቅም፡፡ እንዲያውም ካነሳሽው አይቀር በአንዳንድ ፅህፈት ቤቶቻችን አካበቢ ለንግድ የተከራዩ ሱቆች አሉ፡፡ እነዚህ ሱቆች ለፅህፈት ቤቶቹ ድጎማ የሚውሉ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የሚያስፈልገው እንዲመደብላቸውና ሱቆቹ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሱ አድርገናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ዝንባሌው እንደነበረ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ በፍትህ ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አያጠያይቅም፡፡ የያዝነው ትጥቅና የተቀመጥንበት ወንበር የህዝባችንን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እንጂ ህዝብ የምናስፈራራበት አይደለም፡፡ ህዝብ የሚፈራን ሳይሆን የሚወደንና የሚያከብረን ነው እንዲሆን የሚፈለገው፡፡ ፖሊስ ሲያይ የሚሮጥ ሳይሆን ፖሊስ የኔ ነው ብሎ የሚያስብ ማህበረሰብ ነው መፍጠር ያለብን፡፡ እዚህ ላይ ትልቅ ስራ ይጠብቀናል፡፡ አሁን ከደረስንበት የእድገት ደረጃ የሚመጥን ስራ መስራት ይገባናል፡፡ የጀመርናቸው ውጤታማ ስራዎች አሉ፡፡ አሁንም የሚቀሩን ብዙ አሉ፡፡ ላሉብን ችግሮች ዙሪያ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በመልሶ አደረጃጀታችን የጀመርነው ነገር አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰ ግናለሁ፡፡
ም/ል ኮሚሽነር ዘላለም፡-እኔም አመሰግ ናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
ማህሌት አብዱል