ከመሬት ወደ ሰማይ የሚተነው ጉም አካባቢውን የተነደፈ ጥጥ አስመስሎታል። በከፊል ጉም የተሸፈነውን የፓርኩን ክፍል የዓይኔ እይታ እስከቻለልኝ አሻግሬ ወደ መመልከት ተሸጋገርኩ። አካባቢው አስደማሚ ገጽታን የተላበሰ ነው። በአረንጓዴ ልምላሜ ከታደለው አካባቢ ሽው የሚለው ንፋስ፤ በንፋሱ ሽውታ እየተገፋ ከጦስኝ ቁጥቋጦዎቹ የሚፈልቀው መልካም መዐዛ ለአፍንጫ ምግብ ነው።
የአካባቢው ቅዝቃዜ አንጀት ድረስ ዘልቆ በመግባት መላ ሰውነትን ያንዘፈዝፋል። ብርዱ በስፍራው ቆዩ አይልም። ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞቹን፣ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችና የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች ገና በማለዳው በስፍራው ታድመናል።
ከሸዋ እስከ ወሎ ያለው የአማራ ወጣትም በስፍራው ቀድሞን ተገኝቷል። «አማራነት ይለመልማል፣ ኢትዮጵያዊነት ይቀጥላል» የሚል ህብረ ዝማሬን እያሰሙ በሚያስገመግም ድምጽ በህብረት የሚተሙትን ወጣቶች መመልከት ልብን በአንዳች የደስታ መንፈስ ይሞላል። እኛም ሆንን ወጣቶቹ በስፍራው የተገኘንበት ምክንያት ከወራት በፊት በእሳት ቃጠሎ ጉዳት በደረሰበት የኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ማማ በሆነው ከታላቁ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ አረንጓዴ አሻራችንን ለማኖር ነው።
በወጣቶቹ ትዕይንት የተሳበው ቀልቤ አላረፈምና ትዕይንቱ ከፊት በመሆን ወደ ሚመራው ወጣት ጠጋ ማለትን ወደደኩ። ራሴን አስተዋውቄ ስሙንና ከየት አካባቢ እንደመጣ ጥያቄዬን አቀረብኩለት። ከጎንደር ከተማ መምጣቱንና ስሙም ጋሻው አስናቀ እንደሚባል ነገረኝ።
የተከፈተው የንግግር በር እንዳይዘጋ፤ በፍጥነት መርሃ ግብሩ ምን ስሜት ፈጠረብህ ስል? ሰፊ ማብራሪያን ይሰጠኝ ዘንድ ሃሳብ አቀበልኩት። ዕለቱ ከፍተኛ ደስታንየፈጠረበት መሆኑንና በሰሜን ተራራ አናት ላይ በችግኝ ተመስሎ ኢትዮጵያዊ አንድነት የተተከለበት ልዩነት የማይታሰብበት ዕለት ነው ሲል ገለጸልኝ። እኔም እንዴት? ስል በጥያቄ ያዝኩት።
እርሱም ጊዜ ሳያጠፋ «በሰሜን ፓርክ በተዘጋጀው የችግኝ መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ በአንድነት መንፈስ መነሳቱን አሳይቷል። ይሄ ሁኔታ አንድነታችንን የሚያጎለብት ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ ነው የማስበው» ሲል ለችግኝ ተከላ ከዳር እስከ ዳር በነቂስ ወጥቶ የታየው ተሳትፎ ሀገርን ለማልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ነገረኝ።
ከወጣት ጋሻው ጋር የነበረኝን የወግ ምዕራፍ በመዝጋት ሌላ ሃሳብ ሰጪን ፍለጋ ዓይኔን ከግራ ወደቀኝ ማማተር ጀመርኩኝ። ዓይኖቼ ጥቁር በጥቁር ከለበሰች አንዲት ሴት ላይ አረፈ። ጊዜ ሳላጠፋ ከአጠገቧ ተገኘቼ ከስፍራው የመገኘቷን ምክንያት እንድታጋራኝ ጠየኳት። ስሟ መሠረት ቻለው መሆኑን በመግለጽ «ከስፍራው የተገኘነው ሁለት አላማ በመያዝ ነው» ስትል ንግግሯን ጀመረችልኝ።
«አንድም በልምላሜ የተሞላች ሀገርን ለልጆቻችንን ለማውረስ የሚያስችል ሥራን ለመስራት። ሌላው ደግሞ ሰኔ 15 ቀን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሲታትሩ የተሰዉትን መሪዎቻችንን ለማሰብ ነው» ስትል።
መሠረት እንባ ያቀረሩ ዓይኖቿን ከደን ከፈት በማድረግ ስሜቷን ለመቆጣጠር እየሞከረች እንዲህ ስትል ማብራራት ጀመረች፤ «መሪዎቻችን የአማራ ሕዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለመውሰድ እስከ ህልፈተ ሕይወታቸው ታግለዋል፤ ሰርተዋል። የሞቱለት ራዕይን ይቀጥላል። የሰሜን ተራሮች ፓርክን የህብረታችን ምሳሌ በማድረግ በአንድነት ለልማት የተነሳንበት ዕለት ነው» ስትል ነበር በችግኝ ተከላው መርሃ ግብሩ ላይ ለመገኘቷ ምክንያቷን እንደሆናት ያወጋችኝ ።
በሰሜን ተራራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ለመሳተፍ ከደሴ ከተማ ድረስ እንደመጣ የነገረኝ አቶ መልካሙ ይመር ሌላው የእይታዬ ማረፊያ ነበር። አቶ መልካሙ እንደነገረኝ በሰሜን ተራሮች አናት ላይ ችግኝ ከመትከል ባሻገር፤ መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለችውን ሀገራችንን በአንድነት በመቆም ማዳን እንደምንችል ለማሳየት ነው ይላል። የሰሜን ተራሮች ፓርክ የአንድነታችን ማጠንከሪያ ገመድ፣ የብርታታችን ምሳሌ፣ ወድቆ የመነሳቱ ማሳያ እንደሆነ በመግለጽ ነበር የመርሃ ግብሩ አንድምታ ምን ያህል ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን የገለጸልኝ።
ከአቶ መልካሙ ጋር የነበረኝን ቆይታ በመዝጋት አካባቢውን ወደ መቃኘት ተሻገርኩ። በተፈጥሮ መደመምን ፈለኩ። አካባቢው አረንጓዴ ለብሷል። የእሳት አደጋ በቅርቡ ስለመድረሱ ጥያቄን ያጭራል። በተፈጥሮ ሀብቱ ከመደመም ሻገር ስል ደግሞ የአካባቢውን መአዛ ወደማጣጣም ተሻገርኩ። ቅዝቃዜን አሳብሮ ሽው የሚለው ንፋስ ከጦስኝ ቁጥቋጦ የሚፈልቅ መዐዛ ኦህ ….እንዴት ይማርካል። የመልክዓ ምድሩ ገጽታ፤ አፍንጫን ሰርስሮ ልብን ኮርኩሮ የሚገባው የጦስኝ ሽታ፣ የስፍራው በጉም የመሞላቱ ትዕይንት ከሰሜን ተራሮች አስፈንጥሮ ወደ ባሌ ወሰደኝ።
ከትውልድ ከተማዬ ጎባ ከተማ መቶ ኪሎ ሜትር ርቆ የዓለም እይታ የሆነውን ሳነቴን በቅጽበት እንዳስብ ያስገደደኝ ስሜት ወረሰኝ። ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ ብቻ ሳይሆን በመልክዓ ምድሯም ጭምር የመመሳሰል፣ የመወራረስና የአንድነት ገጽታን የተቸረች ምድር ስለመሆኗ እንዳስብ አስገደደኝ።
አጥንት ሰርስሮ በሚገባው የሰሜን ተራሮች ብርድ ሳይበገሩ በርካቶች አሻራቸውን ያሳረፉበት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ወኔን በሰነቀ መንፈስ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ተጠናቀቀ። ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡትን ከሁለት ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያካተተው መርሃ ግብሩ በመጨረሻም ከ38 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መትከል መቻሉ ተሰማ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ዳንኤል ዘነበ