
– ሥርዓቱ 150 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል
አዲስ አበባ:– የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድን ለማሳለጥ፣ የምርቶችን ጥራት ለማስጠበቅ እንዲሁም የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓትን ለማጠናከር ያግዛል ያለውን ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ ፕሮጀክቱ 150 ሺህ አርሶ አደሮች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቆመ፡፡
ፕሮጀክቱ ትናንት ይፋ በሆነበት ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ውሃብረቢ፤ የእቃ ደረሰኝ ሥርዓት ትግበራው ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንባታው ከፍ ያለ፣ አርሶ አደሩ ለግብዓት ለሚያወጣው ወጪ ተመጣጣኝ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በድህረ ምርት 30 በመቶ ምርት እንደሚባክን በማስታወስም፤ በአግባቡ በመጋዘን መቀመጡ ይባክን የነበረውን ምርት እንዲቀንስ እና አስፈላጊው ጥራት እንዲጠበቅ እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ለጊዜው አምስት ባንኮች ይሳተፉበታል በቀጣይ እየሰፋ እንዲሄድ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተይዞ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱንም አመልክተው፤ ከእዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብሩ ዘንድሮ የተሰጠ ብድር መሆኑን አስታውቀዋል። ብድሩ በቀጣይም እየሰፋ እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡
በመጋዘን ኦፕሬተርነት አራት ድርጅቶች ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን፤ ሁለቱ የመንግሥት ቀሪዎቹ ደግሞ የማህበራት መሆናቸውንም ጠቁመዋል። ማህበራቱ አዋጭነቱን በመገንዘብ በቀጣይ ትላልቅ መጋዘኖችን እንዲገነቡ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
የአግራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ይሄነው ዘውዴ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው መርሃ ግብር በተለይ የግብርና ምርቶች በመጋዘን ሥርዓት ሆነው እንደ መያዣነት ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡ ምርቶቹ በአግባቡ ተቀምጠው የድህረ ምርት ችግሮችን በሚቀርፍ መልኩ የተደራጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ አሠራር ዘመናዊ የግብይት ዘዴ ሲሆን፤ አርሶ አደሩ በቀጥታ ከባንክ ብድር የሚያገኝበት ሳይሆን የምርቱ ጥራት ተገምግሞ መጋዘን ውስጥ በሚያስቀምጠው የምርት ልክ የሚቆረጥለትን ደረሰኝ በማስያዝ ብድር የሚያገኝበት አሠራር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለማስጀመሪያ ያህል ስንዴ፣ በቆሎና አኩሪ አተርን ጨምሮ ስድስት የሚሆኑ ምርቶች እንደተለዩ ጠቁመው፤ በሂደት እየታየ ሌሎች የግብርና ምርቶች የመጋዘን ግብይት አስተዳደር ላይ እንደሚካተቱ ተናግረዋል፡፡
የወጪ ንግድ ፕሮሞሽንና ግብይት ማሳለጥ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በረከት መሰረት፤ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ በምርት ወቅት የሚደርስበትን ጫና በማስወገድ ምርቱን በማስያዣ በማቅረብ ብድር የሚያገኝበት ሥርዓትና የገበያ ዋጋው ሲስተካከል መሸጥ የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአርሶ አደሩ ዘንድ ሊፈጠር የሚችልን ጥርጣሬን በማስወገድ መተማመን የሚያስችል ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ የሚሠራበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሚቆይባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 15 ባንኮች እንዲሳተፉ እንደሚደረግ፣ እስከ 45 ሺህ ቶን የሚደርስ የተለያዩ ምርቶችን ለአገልግሎቱ ጥቅም ላይ እንዲውሉና በወቅቱ የገበያ ዋጋ እኩል የሆነ ብድር ማግኘት የሚችሉበት ብድር እንዲፈጠር እንደሚሠራም ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ “ቅንጅት ለአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት” (አግራ) ፕሮጀክትና የኢንተርናሽናል ፋይናንሻል ኮርፖሬሽን በጋራ ተግባራዊ የሚያደርጉት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም