አዲስ አበባ፡- «ሚዛናዊነቱን የሳተ ውሳኔ» በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በቀረበው ዘገባ የቀበሌ ቤታቸው ለዳኛ ተከፍሎ በመሰጠቱ ለችግር ለተጋለጡት ወይዘሮ ፅጌ በሻህ በነፃ ጥብቅና የሚቆምላቸው የሕግ ባለሙያ አገኙ፡፡
አቤቱታቸውን መነሻ አድርጎ የተስተናገደውን ዘገባ የተመለከቱት በፌዴራል ማንኛውም ፍርድ ቤት ጠበቃ አቶ አባይነህ ባደግ በነፃ ጥብቅና እንደሚቆሙላቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ አባይነህ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የቅሬታ አቅራቢዋን መረጃዎች በመመልከት ነፃ የጥብቅና አገልግሎት ሊሰጧቸው ዝግጁ ናቸው። ሆኖም ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር በማምራት ይህንኑ የማሳወቅና ፈቃድ የማግኘት ሥራ ቀዳሚው ይሆናል፡፡
ይህም ወደ ፍርድ ቤት ሲያመሩም ሆነ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት ጋር ሲሄዱ ውክልና ሳያስፈልግ ለመንቀሳቀስ ይረዳቸዋል፡፡ ይህ ካልተደረገ ሥልጣኑን ከየት እንዳገኙት ጥያቄ ማጫሩ ስለማይቀር እርሳቸው ሙሉ ፈቃደኛ እንደሆኑና ሌላው ሒደት በሚመለከተው አካል የሚያልቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ ፅጌ በበኩላቸው ከ30 ዓመታት በላይ የኖሩበትን የቀበሌ ቤት የወረዳው አስተዳደር ከፍሎ ለዳኛ በመስጠቱ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በመግለጽ ቅሬታቸውን ይዘው የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ፍትሕ እንዲሰጧቸው ቢመላለሱም ሚዛናዊ ውሳኔ ግን ማግኘት አለመቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በቤታቸው ውስጥ በደረደሩት ወንበር በእንብርክክ ሲወጡና ሲገቡ ለበርካታ ጊዜያት የመሰበር አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡ ራሳቸው ያስገቡት የቧንቧ ውሃ፣ ያሠሩት ማዕድ ቤትና መፀዳጃ ቤታቸውም ተወስዶባቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን በተመ ለከተ በጋዜጣው በመውጣቱ በአሁኑ ወቅት ነፃ ጥብቅና አገልግሎት የሚሰጣቸው የሕግ ባለሙያ እንዳገኙና ዳግም የመኖር ተስፋን እንዳ ለመለ መላቸው ለዝግጅት ክፍላችን በደስታ ገልጸ ዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ፍዮሪ ተወልደ