መደጋገፋችን የበዓል ሰሞን ብቻ አይሁን!

ባለፉት ሁለት ወራት በኢትዮጵያ በክርስትናውም፣ በእስልምናውም እምነት ተከታዮች ዘንድ የነበረውን ፆም ተከትሎ፤ የሰዎች የርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቱ ከፍ ብሎ ታይቷል። በተለይ ፆም ወራቱ ምዕመናን በየእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ በትህትና ውስጥ ሆነው የሚፈጽሙበት፤ በፆም፣ በፀሎትና በስግደት ውስጥ ራሳቸውን በፍጹም መታዘዝ ስለ ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡበት ጊዜ ነው፡፡

ለምሳሌ፣ በረመዳን ወር የነበረው የርስ በርስ መረዳዳት፤ የኢፍጣር መርሃ ግብሮች እንዲሁም ያለው የሌለውን በመጎብኘት በፆሙ ወቅት እንዳያዝንና እንዳይቸገር ለማድረግ የነበረው መልካም ተግባር፤ በዒድ ዕለትም እንዲሁ ከፍ ብሎ የተገለጠ ነበር። ምክንያቱም፣ በዓሉ ያለውም የሌለውም እኩል ማክበር ባይችል እንኳን፤ የሌለው ተቸግሮ እንዳይውል ለማድረግ በግለሰቦችም፣ በተቋማትም፣ በቤተ እምነቶችም፣ በመንግሥት ተቋማት ጭምር ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡

በክርስትናው እምነት ተከታዮች ዘንድ የነበረው የዐብይ ፆም ወቅት፣ እንዲሁ በብዙ መደጋገፍና መረዳዳት ተግባራት ያለፈ ነበር። በተለይ በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስን አርነት በመግለጥ ውስጥ የሚታሰብ እንደመሆኑ፤ የትንሳዔው በዓል ከመድረሱ በፊት ባሉት የኅማማት ሰሞን የነበረው ትህትና፣ መታዘዝ፣ ደግነትና መደጋገፍ፣ የኢየሱስን ቤዛነት አጉልቶ መግለጥን ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ፡፡

ከዚህም በላይ በትንሳዔው ዕለት ሁለት ወር በፆም ላይ የቆዩ ምዕመናንን ፆም ከማስፈታት፣ የተቸገሩ ወገኖችን ከመርዳት፣ ያለው ለሌለው ከማካፈል አኳያ ከፍ ያለ ሰብዓዊነት የተሞላባቸው ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም ግለሰቦች፣ ቤተ እምነቶች፣ የግብረሰናይ ድርጅቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ስለ ሰው ልጆች ደስታ ፋይዳ ያላቸውን የማካፈል ተግባራት ሲከውኑ ታይተዋል፡፡

ይሄን አይነት የመደጋገፍ እና ለሰው ደራሹ ሰው መሆኑን የሚያመለክቱ ተግባራት መከወን ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም። እንዲህ እንደዛሬው በአደባባይ የሚነገርለት ባልነበረበት ወቅትም ዜጎች እርስ በእርሳቸው ሲደጋገፉ፤ ጎረቤት ጎረቤቱን ሲጎበኝና ጉድለቱን ሲሞላ ዘመናትን አሳልፈዋል። ዛሬም ይሄው ተግባር ከመቀጠሉም በላይ፤ ምሳሌነቱ ለሌሎች ይደርስና ያነሳሳ ዘንድ ልገሳን በገሃድ ወደመከወን ተሸጋግሯል፡፡

ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት የመደጋገፍና የመረዳዳት ተግባራት የአንድ ሰሞን ያውም የበዓላት ወቅት እና የዘመቻ ተግባር ወደመምሰል እያጋደለ ይገኛል። ሆኖም ችግር ቀን አይመርጥም፤ ድጋፍም ወቅት አይታከክም። ምክንያቱም ሰው በዓል ጠብቆ አይቸገርም፤ ችግርም ወቅት ጠብቆ ወደ ሰው አይመጣም። ሁሌም በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሰዎች ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡

መልካም ማድረግም በጊዜ የሚታጠር አይደለም፤ ሁነትን ጠብቆም በደቦ መከወንን የግድ የሚልም አይደለም። ምክንያቱም እኛ ሁኔታዎችን ስንጠብቅ በየጓዳው የሚቸገሩ ወገኖች ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ። እኛ ለታይታ የሚሆን አመቺ ጊዜን ስናማትር በወቅቱ ልንደርስላቸው የሚገባቸው ወገኖች ልንደርስላቸው ስላልቻልን ብቻ ያልተገባ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡

በዚህ በኩል መንግሥት እንደ መንግሥት በርካታ ዜጎችን የሚደግፍባቸው መርሃ ግብሮችን ዘርግቷል። የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን በወጉ ለመምራት የሚያስችለውን አሠራር መዘርጋቱም ዜጎችን በጊዜና በቦታ ሳይወሰን ደርሶ ለመደገፍ ያለው ቁርጠኝነትን አመላካች አንዱ አብነት ነው። ከዚህ ባሻገርም፣ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ብናይ በየክፍለ ከተሞቹ የገነባቸው የምገባ ማዕከላት የከተማዋ ነዋሪዎች ፆም ውለው እንዳያድሩ ለማድረግ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ እንዲመገቡ ዕድል የሰጠ ነው፡፡

የትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብርም መንግሥት ዜጎቹን በየትኛውም ሁኔታና ቦታ ለመደገፍ ያለውን ከፍ ያለ መሻት፤ መሻቱን ወደ ተግባር የመቀየር ቁርጠኝነት የሚናገሩ ሕያው ተግባራት ናቸው። ከዚህ ባሻገር ያሉት የበዓላት እና የአንዳንድ ሁነቶች ሰሞን የሚደረጉ መንግሥታዊ ድጋፎች፣ የማዕድ ማጋራትና የምገባ ፕሮግራሞች ግን፤ በራሳቸው ከሰብዓዊ ተግባር መገለጫነት ባሻገር በሌሎች ዘንድ መነሳሳትን የመፍጠሪያ ኹነቶች ተደርገው ሊወሰዱ የሚገባቸው ናቸው፡፡

ይሄን ተከትሎም በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች መሰል ተግባርን ሲከውኑ፤ የበዓላት እና የሁነት ክዋኔዎችን ተከትሎም በርካታ ወገኖች በሚደረግላቸው ድጋፍ ደስታቸውን በእንባ ሲገልጹ መስማትም፤ ማየትም እየተለመደ መጥቷል። ሆኖም፣ ይህ ልግስናና መረዳዳት ከአንድ ሰሞን ተግባርነት፤ ከበዓል ሰሞን ደግነት የዘለለ ሊሆን፤ የተቸገሩ ወገኖች ደስታና ፈገግታም ከበዓላት ሰሞን ድምቀት የተሻገረ እንዲሆን ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ድጋፉም፣ ሰብዓዊነቱም ከበዓል ሰሞን ተግባርነት ተሻግሮ የሰርክ ልምምድ እንዲሆን ማስቻል ከሁላችንም ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You