
አዲስ አበባ፦ የቬትናም ጉብኝት በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ያልታዩና ትምህርት የሚወሰድባቸውን አዲስ ተሞክሮዎች ለመቅሰም ዕድል የሰጠ መሆኑ ተገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በቬትናም ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጎ ተመልሷል።
የልዑኩ አባል የሆኑት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የቬትናም ይፋዊ የሥራ ጉብኝትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቬትናም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ አስቸጋሪ ጉዳዮችን በማለፍ በብዝኅ የኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ ቅኝት ዕድገትን በማስቀጠል ምቹ ዕድል የፈጠረች ሀገር መሆኗን አብራርተዋል።
ቬትናም ከግብርና መር ኢኮኖሚ በመላቀቅ ስኬት እያስመዘገበች የምትገኝበት የከተማና ገጠር ልማት ተግባርም በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የቬትናም መደበኛና ኢ-መደበኛ የትምህርትና ሥልጠና የሰው ሀብት ልማት በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሰጠው ተልዕኮ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
በእዚህ መነሻነትም በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮ-ቬትናም መካከል የሰው ሀብት ልማት ምርታማነትን የሚያሳድግ የትምህርትና ሥልጠና የትብብር መግባቢያ ስምምነት መደረጉን አስረድተዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቬትናም ከ1984 ጀምሮ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄዷ እና ይህን ተከትሎም በ1990ዎቹ 70 በመቶ የነበረውን የዜጎቿን ድህነት ሙሉ በሙሉ ቀርፋ፤ ዛሬ በዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ሩዝ፣ ቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በቅታለች ብለዋል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍም ከዓለም የንግድ ድርጅት እና ሌሎች በቀጣናው ከሚገኙ ጋር ባደረገችው ስምምነት ከፍተኛ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቧን ገልጸው፤ ከቬትናም መሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ከስንዴ ቀጥላ ለሩዝ ከፍተኛ ግምት መስጠቷ ተነስቷል ነው ያሉት።
ቬትናም በሩዝ ምርት ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ላይ የደረሰች በመሆኑ ሩዝን ለማስፋፋትና በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ልምድ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡና ምርቶች ልምድ የሚገኝባት ሀገር መሆኗንም አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ እያከናወነች ያለው ተግባር ከቬትናም ጋር የሚያመሳስለው ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። ቬትናም በኤሌክትሮኒክስ፣ በጨርቃጨርቅና ጫማ ምርቶች የኤክስፖርት ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። ከእዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ተኪ ምርቶችን ለማምረት እያደረገችው ላለው እንቅስቃሴ ልምድ ተገኝቶበታል ብለዋል።
በከተማ ግንባታ፣ በኮሪደር ልማት ሥራ፣ በድህነት ቅነሳ እና በቱሪዝም ዘርፉም ሀገራቱ ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችላቸው ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል፡፡ በቅርቡ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቬትናምን ከአፍሪካ ለማገናኘት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬትናም ቆይታቸው ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል። በእዚህም የቬትናም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ቬትናም በብዛት የምትታወቀው መዋዕለ ንዋይ በመሳብ ነው። ከእዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ልምድ ቀስማለች። የቬትናም ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃኖይ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ያደረጉት ጉብኝትም ኢትዮጵያ እያከናወነችው ከሚገኘው የኮሪደር ልማት ጋር ለማስተሳሰር እና ልምድ ለመቅሰም እድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የዘመናዊ ከተማ ፕሮጀክቶችን ነባራዊ ሁኔታውን በማገናዘብ ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም