ዓርብ አልፎ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ልናይ በዋዜማው ላይ ነን!

ትንሳዔ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣዔ የፍቅር ጥግ የታየበት፣ የዕርቅና የይቅርታ ትርጉም የተገለጠበት፣ ምሕረትና ደኅንነት የተረጋገጠበት ታላቅ በዓል ነው፤ ፍጹም ፍቅር ከክብር ዙፋን ላይ መውረድን እንደሚጠይቅ፤ እውነተኛ መውደድ በቅድመ ሁኔታዎች እንደማ ይታጠር ክርስቶስ በተግባር አስ ተምሯል።

በጸሎተ ሀሙስ ዝቅ ብሎ እግር አጥቦ ትህትናን አሳይቶናል። በዕለተ ዓርብም የአምላክነት ክብሩን ትቶ ለሰው ልጆች በደል መሥዋዕት የከፈለበት የትንሣዔ በዓል የዕርቅና የይቅርታ በዓል ነው፤ በትንሣዔው አዲስ የምሕረት ምዕራፍ ተከፍቶ የሰው ልጆች የርግማን ሰነድ ተሰርዟል። ይህን የአምላክን ይቅርታ እያሰብን በሁላችን በኩል በዳይ ይቅርታ የሚጠይቅበት ተበዳይም ይቅር የሚልበት ጊዜ እንዲሆንልን ቅሬታዎቻችንንና በደሎቻችንን በይቅርታ መተላለፍ አለብን።

የዕርቅ ዓላማው ሰላም በማውረድ መከራን ማጥፋት ነውና ተበዳዩ ይቅር ቢል ታላቅነቱን ያሳያል ፤ ተሸናፊ እንደማያደርገው የትንሣዔው ታሪክ ያስተምራልና ። የትንሣዔን በዓል እያከበርን ባለንበት ወቅት በሀገራችን የተፈጠሩ ግጭትና አለመግባባቶችን በዕርቅ ስለመቋጨት ማሰብና መወሰን ይገባል። ቅሬታዎችን አለመግባባቶችን በንግግር በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይጠበቅብናል። አሁን በየቦታው የሚታዩ ግጭቶች የነገ ተስፋችንን እንዳያጨልሙ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መክረንና ዘክረን ልንቋጫቸው ይገባል።

መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በሠለጠነ አካሄድ በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ አስታውቋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም የመወያያ አጀንዳዎችን ሁሉ ከየክልሎቹ አሰባስቧል። አሁን አጀንዳ ማሰባሰቡ ሥራ የቀረው የትግራይ ክልል ላይ ብቻ ነው። ይህን አጠናቅቆ በሁሉም ክልሎች በኩል ልንወያይበትና ልንግባባበት ይገባሉ ያልናቸውን ከውስጣችን አውጥተንና በሀቅ እና በቅንነት በመነጋገር አስካሁን የመጣንበትን አክሳሪ መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ መፍታት ያስፈልጋል። እንደ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ሁሉ ከቂምና በቀል ራስን ነጻ ማድረግ ይገባናል።

አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የምናያቸው ጦረኝነት፣ ሽፍትነት ፣ ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉ የውንብድና ተግባራት በየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ ኃጢያት ተብለው የተፈረጁ ናቸው። በዓለማዊውም የአዕምሮ እረፍትን የሚያሳጡ ናቸው። በዚህ የሚጠቀምም ሕዝብም ሆነ ሀገር አይኖርም። አሁን ጊዜው 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ቀዳሚ መሆን ያለበትም መነጋገር ነው። ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ለሁሉም የሚበጀው ነውና እንደ ክርስቶስ ሁሉ የህመሙን ጊዜ በይቅርታ ማለፍ ተገቢ ይሆናል። የሃሳብ ልዩነቶች የአውደውጊያ መነሻ እንዳይሆኑ ከስሜታዊነት መውጣትና ሆደ ሰፊነትን ይጠይቃል።

ሀገራችን ብዙ መከራዎችን እንደክርስቶስ ሁሉ ብዙ ህመማቶችን አሳልፋለች አሁን ግን ይሄ ህመም በሀገራችን ትንሳኤ ድል ሊመታ ይገባል። ሀገራችን አሁን በልማቱ ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች፤ የኢኮኖሚ እድገቱ በ8.4 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል እየተረጋገጠ ነው። በቱሪዝሙ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ነው። በግብርና በቡና ኤክስፖርት በመሳሰሉት የተገኙት ውጤቶች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። ይሄ ሁሉ የሆነው ሀገር ሰላም በመሆኗ ነው። በቀጣይም በአንዳንድ ክልሎች በኩል ያሉ ችግሮቻችንን ፈትተን ወደ የጋራ ብልፅግናችን ልንጓዝ ይገባል። አሁን ሀገራችን ዓርብን አልፋ የትንሣዔዋ ዋዜማ ላይ ነች። የምናያቸው ፈተናዎች የሕማማት ሰሞን ፈተናዎች ናቸው። እንደ ክርስቶስ ትንሣዔ ሁሉ የሀገራችን ብልፅግና እውን እንደሚሆንና የኢትዮጵያችን ትንሣዔ እንደሚሳካ ትልቅ እምነት አለን፤ ይህ የሚሆነው ግን እንደ ኒቆዲሞስ ተስፋን ሰንቀው ወደ ትንሣዔው ብርሃን የሚገሠግሡ፣ እንደ ዮሐንስ ውዥንብሩን ሁሉ በጽናት የሚያልፉ፣ እንደ ሮማዊው መቶ አለቃ እውነትን በድፍረት የሚመሰክሩ ዜጎች ሲበዙ ነው።

ፈተናዎች ሁሉ በጥንካሬ በኅብረት ማለፍ አለና የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም በቅንነት፣ በታማኝነት በየተሰማራበት ሙያና ተግባር ሁሉ ሀገርንና ወገንን በታማኝነት ማገልገል አለብን። ሀገራችንን የምናበለፅገው እኛ ዜጎች እንጂ የውጪ ኃይሎች አይደሉም። ሀገራችንን ወደ ከፍታው ማማ የምናሻግራት ራሳችን ብቻ መሆናችንን ሠርተን ባሳየነው ታላቁ የዓባይ ግድብ አሳይተናል። ለሀገራችን ለራሳችን ያለነው ራሳችን ነን ። የሰው ወርቅ አያደምቅ እንዲሉ ትልልቅ ርዳታ ሰጪ ሀገራት ዛሬ እጃቸውን ሲሰበስቡ በዓለም ላይ የተፈጠረውን አይተናል ። እናም ለራሳችንም ለሀገራችንም ያለነው ራሳችን መሆናችንን ተረድተን የእርስ በርስ መቆራቆሱን በንግግር በውይይት መፍታት እና ወደሰላም መንገድ መምጣት አለብን። ሰላም አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ሁሉም ልንገነዘበው ይገባል። በሀገራችን ያየናቸው መከራዎች ሁሉ እንደ ክርስቶች ህመሞች አልፈው ትንሳኤውን ለማየት የተቃረብንበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የሀገራችንን ትንሳዔ በጋራ እንድናይ ሁላችንም ችግሮቻችንን በይቅርታና በእርቅ ልንፈታ ይገባል!

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You