ዲጂታላይዝድ የትራፊክ ቅጣትን በመተግበር በዓመት 17ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ ፡- አውቶማቲክ የቁጥጥር ሥርዓትን በመዘርጋትና እና የትራፊክ ቅጣት አፈጻጸምን ዲጂታላይዝድ በማድረግ በዓመት ለደረሰኝ ሕትመት ይወጣ የነበረውን 17 ሚሊዮን ብር ማስቀረት መቻሉን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ገለጸ::

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ የአውቶማቲክ ቁጥጥር ሥርዓትን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙኅን በሰጡት ማብራሪያ፤ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ቀደም ሲል በነበረው አሠራር ለደረሰኝ ሕትመት በዓመት ይወጣ የነበረውን 17 ሚሊዮን ብር ማስቀረት ተችሏል::

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ኋላ ቀር የትራፊክ ቅጣት አፈጻጸምን ዘመናዊ በማድረግና ለብልሹ አሠራር ያለውን ተጋላጭነት በመቀነስ፣ የተገልጋዮችን የሰዓት ብክነትና ይገጥማቸው የነበረውን እንግልት በማስቀረት ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ነው::

ዲጂታል የትራፊክ ቅጣት አፈጻጸም መተግበሪያ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 2ሺህ 461 ደንብ የተላለፉ ተሽከርካሪዎች የተስተናገዱ መሆኑን አመልክተው፤ አንድ ሺህ 458 የሚሆኑት በእዚሁ አገልግሎት መክፈል የቻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል::

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤የቅጣት አፈጻጸም ዲጂታላይዝ በመሆኑ ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸውን አሽከርካሪዎች በሲስተም ውስጥ እንዲመዘገቡ ተደርጓል:: በእዚህም ፎርጂድ የብቃት ማረጋገጫ እና ሰሌዳ የያዙትን መለየት ተችሏል:: በከተማዋ 772 ሺህ 740 ተሽከርካሪዎች የተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህጋዊ የአሽከርካሪነት ሙያ ማረጋገጫ ፍቃድ ያላቸው አንድ ሚሊዮን 104 ሺህ 126 አሽከርካሪዎች በሲስተሙ መመዝገብ እንደቻሉ ተናግረዋል::

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ደንብ ተላልፈው ከተገኙ አሽከርካሪዎች 600 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል::

የዘመናዊ የትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓት ዲጂታላይዝ መሆኑ ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች የአሽከርካሪነት የብቃት ማረጋገጫቸውን እና ሰሌዳ መያዝ ሳያስፈልጋቸው በእዚሁ ሥርዓት በ10 ቀን የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲከፍሉ የማድረግ እድል ፈጥሯል ብለዋል:: በ10 ቀናት ውስጥ መክፈል ያልቻሉ አምስት በመቶ የቅጣት ወለድ እንደሚከፍሉና ስድስት ወር ሲቆዩ ደግሞ የአሽከርካሪውን ብቃት ማረጋገጫ እስከማገድ የሚደርስ ቅጣት የሚጣል እንደሆነ አመልክተዋል::

ዲጂታላይዝ የቅጣት አፈጻጸም ተግባራዊ መሆኑ በተቆጣጣሪውና ደንብ በተላለፈው አሽከርካሪ መካከል የሚፈጸመውን ብልሹ አሰራር የሚቀንስ እንደሆነና ያለምንም ንክኪ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ አማራጮች መክፈል የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል::

የትራፊክ ቅጣት አፈጻጸም ዲጂታላይዝ መሆን ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት ችግሩን በፍጥነት ለመፍታት እንደሚያስችልም አንስተው፤ መንገዱ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆንና የየእለት የትራፊክ ቁጥጥርን ለመመዝገብ እንዲያመች ያደርጋል ብለዋል:: አሠራሩ ለሌሎች ጥናቶች ግብዓት በመሆን እንደሚያገለግልም አቶ ክበበው ጠቁመዋል::

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You