
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ በሦስት የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በቬትናም የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ማሌዢያ ያመሩ ሲሆን፤ ካምቦዲያም ሦስተኛ መዳረሻቸው ትሆናለች፡፡ የፕሬዚዳንት ሺ ጉብኝት አሜሪካና ቻይና በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ምክንያት ከፍተኛ የንግድ ጦርነት ውስጥ በሚገኙበት ወቅት መከናወኑ የተለየ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ጉብኝት እያደረጉባቸው ያሉት ሀገራት የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር (Association of Southeast Asian Nations – ASEAN) አባላት ሲሆኑ፤ እነዚህ
ሀገራት ደግሞ በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ታሪፍ ከጣሉባቸው ሀገራት መካከል የሚመደቡ ናቸው:: ለአብነት ያህልም የፕሬዚዳንት ሺ የመጀመሪያ መዳረሻ የሆነችው ቬትናም የ46 በመቶ እንዲሁም ካምቦዲያ የ49 በመቶ ታሪፍ ሰለባ ሆነዋል:: የወቅቱ የማኅበሩ ሊቀመንበር ማሌዢያ ደግሞ የ24 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባታል:: ሀገራቱም በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ መከፋታቸውን ገልጸዋል:: የፕሬዚዳንቱ ጉብኝትም ቻይና ከአሜሪካ የተሻለች ጠንካራና ዘላቂ ወዳጅና የንግድ አጋር እንደሆነች የማሳየት ተልዕኮ ያለው ነው ሲሉ ተንታኞች ገልጸዋል::
ባለፈው ዓመት አሜሪካ የ438 ቢሊዮን ዶላር ምርት ከቻይና ያስገባች ሲሆን፤ ቻይና ደግሞ 143 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአሜሪካ ሸምታለች:: ይህ የንግድ ልውውጥ አሃዝ አሜሪካ ለቻይና ምርቶች ትልቅ ገበያ እንደሆነች ያሳያል:: አሜሪካም ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ የሚያጋጥማትን ሰፊ የንግድ ጉድለት ለማስተካከል በቻይና ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣልን እንደ አማራጭ አድርጋ ይዛዋለች::
ከእዚህ መነሻነትም ቻይና በፕሬዚዳንት ትራምፕ የተጣለባትን ታሪፍ ለመቋቋም አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችንና የንግድ አጋሮችን መፈለጓ አይቀርም:: ሺ በሃኖይ ከቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ቶ ላም ጋር ከተወያዩ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ “ቻይናና ቬትናም ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትና መተማመን እንዲሰፍን ማድረግ ችለዋል:: ሁለቱ ሀገራት ከዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ትስስር ተጠቃሚ እንደመሆናቸው፤ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ማጠንከር፣ የአንድ ወገን ማንአለብኝነትን መቃወም እና ነፃ ዓለም አቀፍ ንግድን መጠበቅ ይገባናል፤ የበለጠ ክፍት፣ አካታች፣ ፍትሐዊ የሆነና ሁሉንም ወገን ሊጠቅም የሚችል የምጣኔ ሀብት ሥርዓት እንዲኖር መሥራት ይኖርብናል” ብለዋል::
በፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ቻይናና ቬትናም በርካታ የትብብር ስምምነቶችን የተፈራረሙ ሲሆን፤ የቻይና ገበያ ለቬትናም ምርቶች ክፍት መሆኑንም ተናግረዋል:: ከእዚህ በተጨማሪም የቬትናም የግብርና ምርቶች በቻይና ገበያ የተሻለ መዳረሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ፕሬዚዳንቱ ቃል ገብተዋል::
በቬትናም ፉልበራይት ዩኒቨርሲቲ የቬትናም ጉዳዮች ጥናት መምህር ንጉዬን ታን ትረንግ፣ ቻይና ለቬትናምም ሆነ ለሌሎቹ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር አባላት ብዙ አማራጮችን ማቅረብ እና መሪ መሆን እንደምትችል ይናገራሉ::
ፕሬዚዳንት ሺ በፑትራጃያ ከማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ቻይና ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር ጋር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለመፈራረም ያላትን ፍላጎት አንስተው ተነጋግረዋል:: የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ካዎ ኪም ሆርን ስምምነቱ በቻይናና በማኅበሩ አባል ሀገራት መካከል ያሉ የንግድ ታሪፎችን በማስወገድ የሁለቱን ወገኖች የንግድ ልውውጥ ይበልጥ እንደሚያሳድገውና እንደሚያቀላጥፈው ገልጸዋል::
እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ ቻይና የማሌዢያ ግንባር ቀደም የንግድ አጋር መሆኗ እና ቻይናና ማሌዢያ ባለፈው ዓመት የነበራቸው የንግድ ልውውጥ 212 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሲታሰብ የፕሬዚዳንት ሺ ጉብኝት ለቻይና አማራጭ የገበያ ፍለጋ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል::
በአሜሪካ የቀድሞ የማሌዢያ አምባሳደር መሐመድ ናዝሪ አብዱልአዚዝ የፕሬዚዳንት ሺ ጉብኝት ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ በመግለፅ፣ ጉብኝታቸው ብዙ ነገሮችን የሚያስረዳ እንደሆነ ጠቁመዋል:: “ቻይና ከአሜሪካ የተሻለች አስተማማኝ የንግድ አጋር እንደሆነች እየነገረችን ነው:: በጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም አስተዳደር ማሌዢያ ለቻይና የበለጠ ቅርብ እየሆነች ነው:: ይህ ጥሩ ነገር ነው:: በሂደት የአሜሪካ ተፅዕኖ እንዲቀንስ ያደርጋል” ብለዋል:: የማሌዢያና የቻይና የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የንግድ ትስስር መጠንከሩ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስረድተዋል::
በማላያ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍና ስትራቴጂክ ጉዳዮች መምህር ኮ ዪንግ ሆይ፣ የፕሬዚዳንት ሺን ጉብኝት “በአሜሪካ የታሪፍ ውሳኔ መካከል የታየ የቀጣናዊ ወዳጅነት መፈተኛ ክስተት” ሲሉ ገልፀውታል:: “ይህ ስለወዳጅነት አይደለም፤ ቤጂንግን ዳግም ቀጣናዊ የስበት ማዕከል የማድረግ ጥረት ነው” ብለዋል::
በአውስትራሊያ ታስማኒያ ዩኒቨርሲቲ የእስያ ጥናቶች መምህር ጄምስ ቺን፣ የፕሬዚዳንት ሺ ጉብኝት ቻይና ለአሜሪካ የፖለቲካና የንግድ አጋርነት ሁነኛ አማራጭና ምትክ መሆን እንደምትችል ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ይገልፃሉ:: እሳቸው እንደሚሉት፣ ቻይና የብሪክስ (BRICS)ና ሌሎች አደረጃጀቶችን ተጠቅማ አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት እየጣረች ነው:: “ሁሉን አቀፍ ቀጣናዊ የምጣኔ ሀብት ትብብር›› (Regional Comprehensive Economic Partnership (RCEP) የተሰኘውንና አስሩ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር (ASEAN) አባላት እና ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ አባል የሆኑበትን ነፃ የንግድ ስምምነትም ቻይና ለእዚሁ ዓላማዋ ልትጠቀምበት ትሞክራለች::
የትራምፕ ውሳኔዎች ቻይና በመላው ዓለም፣ በተለይም በታዳጊ ሀገራት ዘንድ፣ የሚኖራትን ተፅዕኖ እንድታሰፋ እድል እየሰጧት ነው:: ቻይናዎቹ እየሠሩት ያለው አንዱ ሥራ የአሜሪካን ዶላር ላለመጠቀም የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ የንግድ ሥርዓት መገንባት እንደሆነም ቺን ጠቁመዋል::
የሲንጋፖር የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኦህ ኢይ ሰን፣ “የደቡብ ምሥራቅ እስያ ቀጣና ሀገራት የቻይና ወሳኝ የንግድ አጋሮች ናቸው:: ቻይናም በእዚህ አካባቢ ያላትን ተፅዕኖ ማስፋትና ማስጠበቅ ትፈልጋለች:: የጉብኝቱ ጊዜ እና ፕሬዚዳንቱ እየጎበኟቸው ያሉት ሀገራት የትራምፕ የታሪፍ ውሳኔ ተፅዕኖ የሚያሳድርባቸው መሆናቸው ቻይና ኃላፊነት የሚሰማት ኃያል ሀገር እንደሆነች ለማሳየት ይረዳታል” ብለዋል::
ፕሬዚዳንት ትራምፕም የቻይናው አቻቸው የሚያደርጉትን ጉብኝት በዓይነ ቁራኛ እያዩት ስለመሆኑ የሚያመለክቱ ንግግሮችን ተናግረዋል:: ለአብነት ያህልም የቻይናና የቬትናም መሪዎችን ውይይት በአሜሪካ ላይ እንደሚሸረብ ሴራ አድርገውም ቆጥረውታል::
በአጠቃላይ የፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ የሰሞኑ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ጉብኝት ቻይና በቀጣናው ያላትን የበላይነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ውሳኔን ተከትሎ ለወጪ ምርቶቿ አማራጭ የገበያ መዳረሻና ዘላቂ የንግድ አጋሮችን ለመፈለግ የምታደርገው እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ ተወስዷል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም