“የብዝኃ ሕይወት ጥፋትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሃኖይ እየተገነባ ያለውን የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ጎበኙ

አዲስ አበባ፡- የብዝኃ ሕይወት ጥፋትን እና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ አፋጣኝ ርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቬትናም በሃኖይ እየተገነባ የሚገኘውን ትልቅ የዘመነ ከተማ (የስማርት ሲቲ) ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል ጭብጥ እየተካሄደ ባለው የ2025 ፒ4ጂ ቬትናም ጉባኤ ላይ የአየር ንብረት ጥበቃን ለማራመድ አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ቁልፍ የተግባር ነጥቦችን አፅንዖት ሰጥቼ አንስቻለሁ ብለዋል።

አንደኛ የአየር ንብረት ጥበቃ የገንዘብ አቅርቦትን የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት በቂ፣ ተገማች እና ዘላቂ በሆኑ ምንጮች ማረጋገጥ ይኖርብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁለተኛ ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ እና የአኅጉሩን ወሳኝ ሥነምኅዳር ጥበቃ ለማድረግ በዓለም የኃይል ምንጭ ኢንቨስትመንት ሽፋን ውስጥ የአፍሪካን ድርሻ በአሁኑ ወቅት ካለበት ሁለት ከመቶ በ2030 ወደ ሃያ ከመቶ ማሳደግ ይገባናል በማለት ተናግረዋል።

እንዲሁም በሦስተኛ ነጥባቸው የብዝኃ ሕይወት ጥፋትን እና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ አፋጣኝ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ሲሉ አስገንዝበው፤ ይህም እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ሕዝባዊ ሥራዎችን በገንዘብ መደገፍን በእዚህም ለየአካባቢው ኅብረተሰብ ከአድልዎ የፀዳና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ያካትታል ብለዋል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በቬትናም የጀግኖች እና ሰማዕታት መታሰቢያ ብሎም በሆ ቺ ሚን የመቃብር ሥፍራ ጉንጉን አበባ አኑረዋል።

እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የይፋዊ ጉብኝታቸው አካል የሆነ ውይይት ከቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጋር በፓርቲው ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት አካሂደዋል። በውይይታቸውም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳዮች ብሎም በሀገራዊ ልማት እና አስተዳደር ጉዳዮች መክረዋል።

በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቬትናም ፕሬዚዳንት ጄነራል ሉዎንግ ኩዎንግ እና ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ትራን ታንህ ማን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በሁለቱም ውይይቶች ስለ ሀገረ መንግሥት ቀጣይነት፣ የፖለቲካ ትብብር፣ የለውጥ ጥረቶች የተነሱ ሲሆን፤ በብዙ ዘርፎች የሁለትዮሽ ትስስሮችን እና ትብብሮችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚቻልባቸው መንገዶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሃኖይ እየተገነባ የሚገኘውን ትልቅ የዘመነ ከተማ (የስማርት ሲቲ) ፕሮጀክት ጎብኝተዋል። ይህም ለኢትዮጵያ የከተማ ልማት ሥራ የሚሆን ተሞክሮ የመቅሰም ተግባር አካል እንደሆነ ተገልጿል።

ጉብኝቱ ዓለምአቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በመላው ሀገራችን እየተካሄዱ ያሉ የዘመናዊ ከተማ ፕሮጀክቶችን ለማላቅ የሚደረግ ፍላጎትና ጥረትን ያሳያል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቬትናም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሠረተ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የመንግሥት መሪ ያደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የኦፊሴላዊ ጉብኝት እንደሆነ ታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You