
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ፍልስጤምን የሚደግፍ ሰልፍ ያዘጋጀው ሞህሰን ማህዳዊ ለአሜሪካ ዜግነት ቃለ ምልልስ በሚያደርግበት ወቅት መታሰሩ ተገለጸ።የአሜሪካ መኖሪያ ‘ግሪን ካርድ’ ያለው ሞህሰን በስደተኞች ጉዳይ በባለሥልጣኖች ተይዟል። በቀጣይ ወር ከኒውዮርክ ሲቲ ኮሌጅ ይመረቃል።ጠበቃው እንዳሉት ሞህሰን በዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ተቃውሞ ምክንያት ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ የተሳተፈው የመብት ተሟጋች ማሕሙድ ካሕሊል እና በቱፍትስ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ የተሳተፈው የመብት ተሟጋች ሩምያሳ ኦዝቱክ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ቪድዮዎች ሞህሰን በሁለት ፖሊሶች ታጅቦ ሲወጣ ያሳያሉ። ጠበቃው ሉና ድሮቢ “የትራምፕ አስተዳደር ሞህሰንን ያሰረው ለፍልስጤማውያን ድምጹን ስላሰማና ፍልስጤማዊ ስለሆነ ነው። በጋዛ እየደረሰ ያለውን ቀውስ የሚቃወሙ ሰዎችን ዝም ማስባል ነው ዓላማቸው። ይህም ሕገ ወጥ ነው” ብለዋል።
ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ዐቃቤ ሕግ ሞህሰን በባለሥልጣኖች ከቬርሞንት ግዛት ወይም አሜሪካ እንዳይወጣ አግደዋል።ሞህሰን የተወለደው በዌስት ባንክ ሲሆን በ2014 ነው አሜሪካ የገባው።ፍልስፍና የሚማረው ሞህሰን ቡዲስት እንደሆነ፤ በሃይማኖቱ ነውጥን እንደሚጠላና ሀዘኔታን እንደሚያስቀድም ተገልጿል።
አሁን ላይ የት እንደተያዘ አለመታወቁን ጠበቃው ገልጸዋል።በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፍልስጤም ተማሪዎች ኅብረት መሥርቷል። የእስራኤልን የጋዛ ጥቃት ሲቃወምም ነበር።የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ማርኮ ሩብዩ ቢያንስ 300 የውጭ ተማሪዎች ቪዛቸው እንደሚነጠቅ ገልጸዋል። ይህም “ፀረ ሴማዊነትን” ለመታገል ነው ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር “ፀረ ሴማዊነት” በሚል ሽፋን የንግግር ነጻነትን ማፈኑን ተንታኞች ይናገራሉ።የቨርሞንት ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ሞህሰን “በሕገ ወጥ መንገድ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው። የዜግነት ጥያቄው የመጨረሻ ዙር ላይ ነው የሚገኘው። በአፋጣኝ ተለቆ በሕግ መሠረት ጉዳዩ መታየት አለበት” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም