«የዓባይ ግድብ መገባደድ እና የባሕር በር ጥያቄ ተያያዥ ናቸው»- አቶ ሙሳ ሼኮ የፖለቲካ ተንታኝ

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሳ ሼኮ ባለፉት አራት ዓመታት በዓባይ ግድብና በሌሎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በሆኑ ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ የተለያዩ ቃለ መጠይቆችን በመስጠት ይታወቃሉ። በዛሬው ወቅታዊ ጉዳይ ዝግጅታችን ቀይ ባሕርን እና ዓባይ ግድብን አስመልክተን ያደረግነውን ቆይታ እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን።

አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ የተጀመረበት 14ኛ ዓመት በያዝነው ሳምንት ይከበራል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የፓርላማ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅ ተናግረዋል። ከጅማሮ አንስቶ የግድቡ ግንባታ ያለፈባቸውን ሂደቶች በማንሳት እንጀምር?

አቶ ሙሳ፡- የዓባይ ግድብ ከዓድዋ ወዲህ ኢትዮጵያኖችን ከዳር እስከዳር በማነቃነቅ አንድ ያደረገ ታላቅ ፕሮጀክት ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች የዓባይ ግድብን እና ዓድዋን አብረው ያነሳሉ፤ ምሁራንም ሁለቱን አያይዘው ይጽፋሉ። ምክንያቱም መጀመሪያ የዓባይ ግድቡን ለመሥራት ዝግጅት ሲደረግ ኢትዮጵያውያኖች ወደ ግብጽ ሀገር ተጉዘው ይሄ ፕሮጀክት ምስራቅ አፍሪካን የሚያስተሳስር መሆን አለበት፤ ሁላችን ተባብረን እንሥራ የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር። ግብጾች ኢትዮጵያውያንን የበታች አድርገው ስለሚመለከቱ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ይቀርብልና በሚል በንቀት ነው የሸኟቸው።

በወቅቱ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሁስኒ ሙባረክ ነበር። መልስ ያልሰጡት ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግድቡን መሥራት አትችልም ብለው አስበው ነው። ይህም ልክ ጣሊያኖች እንደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያውያኖችም በቅኝ ግዛት ይገዙልናል ብለው እንደናቁን ሁሉ ግብጾችም በተመሳሳይ መንገድ ነበር ኢትዮጵያውያንን ያዩን። በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዓድዋ ላይ የነበረው እልህ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ እንደገና ተመልሶ ወደ ዝግጅት በመግባት በአውሮፓውያኑ 2010 ፕሮጀክቱ ይፋ ሆነ።

ግብጾች ከእኛ ጋር ሲፋለሙ የነበሩት በአቋም ሳይሆን በታክቲክ ነበር። መጀመሪያ ግድቡን መገደብ እንደማይቻል ነበር ሊያሳዩን የሞከሩት። እንደምንችል በተግባር ስናሳምናቸው ደግሞ የግድቡ መጠን ከ74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ወደ 14 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲቀንስ ነው ሃሳብ ያቀረቡት። ይሄም ሳይሳካ ሲቀር የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮች ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳያደርጉልን ተግተው ሠርተዋል፤ ይህ ተሳክቶላቸዋል። ኢትዮጵያውን በራሳቸው አቅም ለመገንባት ሲንቀሳቀሱ ደግሞ ለስምምነት ግድቡ እንዳይጀመር የአፍሪካ በተለይም የናይል ተፋሰስ ሀገራትን እየሄዱ እየቀሰቀሱ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ጫና ቀጥለው ነበር። ይሄም አልተሳካም።

በአውሮፓውያኑ 2015 የሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ መሪዎች የመነሻ ስምምነት ተፈራረሙ። ይሄ በዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ላይ ኢትዮጵያውያኖች በግብጽ ላይ ያስመዘገቡት ትልቅ ድል ነው። የመጀመሪያው ምሽግ የተሰበረበት ስምምነት ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም እስካሁን ድረስ በየትኛውም መድረክ የምንጠቅሰው መብት የሰጠን ስምምነት ሆኗል። ዓድዋና ዓባይ ግድብን የማመሳሰሉ ባሕል መነሻው ይህ ነው። ሁለቱም ኢትዮጵያውያንን አንድ አድርገዋል። በውስጣቸው እልህና ቁጭትን ፈጥረዋል። በመጨረሻም ድል ተገኝቶባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ዓባይን በራሷ አቅም መገንባት መጀመሯን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ በልማት ዜና ተደጋግሞ በመነሳቱ ገጽታዋን በመገንባት ረገድ አትርፋለች ማለት እንችላለን ?

አቶ ሙሳ፡- የዓባይ ግድብ ለረጅም ጊዜ በዓመት አንድና ሁለት ጊዜ ስሟ ይነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የምትጠቀስ ሀገር እንድትሆን አድርጓል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ብቻ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ 12 ጊዜ ክስ አቅርባ ሁሉንም በኢትዮጵያ የተረታችበት ታሪክ ተጽፏል። ዓለም ሁሉ ከጎናችን የቆመበትና የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ማግኘት ሳይሆን የኢትዮጵያ ስም ከፍ ብሎ ትልቅ የዲፕሎማቲክ ድል የተመዘገበበት ሆኗል።

የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት የተጠነሰሰው በ1932 ንጉሡ ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ንግግር ነው። ያን ጊዜ መሠረቱ የተጣለ ሃሳብ እየተንከባለለ መጥቶ ለአንድ መቶ ዓመታት ከቆየ በኋላ እውን ሆኖ ዛሬ መሬት ላይ መውረድ ችሏል። በዓረቡ ዓለም ያሉ አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ስሟ የታወቀ ነው የሚመስላቸው። የነበረው ትርክት እንደዛ ስለነበር ማለት ነው። እውነታው ግን አውቶማን ቱርክና የፖርቱጋል ንጉሥ በነበሩበት ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነበራቸው። ይሄ ትክክለኛ የሆነ እውነታ ነው። ምዕራባውያንም ጭምር ይህንን መናገር አይፈልጉም። እኛ ጣሊያኖች መጥተው ሳይሞክሩን በፊት የዓለማችን የጥንት ሥልጣኔ ካላቸው ቱርክ እና ፓርቱጋል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበረን ታላቅ ሀገር ነን።

ግድቡ በዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግና የሚያስከብር ፕሮጀክት ነው። በዚህ ልንኮራ ይገባል። ትላልቅ ሀገሮች ሁሉ በሀገራቸው ውስጥ የሚንከባከቡትና የሚጠብቁት ትልቅ ሀብት አላቸው። ከአሁን በኋላ እኛ ልንከባከበው የሚገባን ሀብታችን ዓባይ ግድብ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጠንክሮ መውጣት ከዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ጋር ይያያዛል ?

አቶ ሙሳ፡- የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲን ስንመለከት የሕዳሴ ግድብ ወደ መገባደዱ ሲመጣ ነው የባሕር በር ጥያቄ ከበፊቱ ይልቅ ጠንክሮ እየገፋ የመጣው። የኤሌክትሪክ ኃይሉን ወደ ውጭ እንደምንልክ ሁሉ በኤሌክትሪከ ኃይል አቅርቦት መሻሻል ምክንያት የሚገኘው ተጨማሪ ምርትም ወደ ውጭ መሄዳቸው አይቀሬ ስለሆነ ነው የባሕር በር ግዴታ ነው የምንለው። ስለዚህ የሕዳሴ ግድብ መገባደድና የባሕር በር ጥያቄ ተያያዥ ናቸው።

ሕዳሴ ግድብ በሙሉ ተርባይኑ ሲሠራ የሚመረተው ኤሌክትሪክ ኃይል በከፊል ወደ ውጭ የሚላክና ምንዛሬ የሚያመጣ ነው። የቀረው ደግሞ በሀገር ውስጥ በየክልሉ ተገንብተው በሙሉ አቅማቸው ለማምረት የኤሌክትሪክ ኃይል እየጠበቁ ወዳሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲደርስ ተደርጎ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ ምንዛሬ የማግኘት ዕድል ይፈጥራል። በየክልሉ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው በማምረታቸው የምርት መጨመር ይኖራል። ይህም ወደ ውጭ ሀገራት የሚላከውን ምርት ያሳድጋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷ ወደብ ያስፈልጋታል፡፡

ሙሉ ተርባይኖቹ ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ ስምንት ሀገራት ከዓባይ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሱዳን እየተጠቀመች ትገኛለች። 124 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ አለበት። በጦርነቱ ምክንያት ነው ሳትጠየቅ የቀረችው። ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያም በዚያው መንገድ ላይ ናቸው። በቀጣይ ምናልባትም ራሳቸው ግብጾችም ሊፈልጉ ይችላሉ። በሀገር ውስጥም 65 በመቶ ጨለማ ውስጥ ለሚኖረው ሕዝባችን ብርሃን እንዲገኝ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እና ጥቂት ዓረብኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ግብጾች ለዓረቡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ የሚያስተጋቡትን የሀሰት ትርክት በታዋቂ የዓረብ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ አንገት ለአንገት በመተናነቅ የኢትዮጵያን እውነት በማስረዳት ያደረጋችሁት ትግል በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እንድትገቡ አድርጓቸኋል። ይህ ትግላችሁ ያስገኘውን ውጤት እንዴት ይገመግሙታል ?

አቶ ሙሳ፡- ግብጾች 25 አባላት ያሉትን የዓረቡን ዓለም ሚዲያ በሙሉ በግል ተቆጣጥረውታል ማለት ይቻላል። ግብጾች በትንሹ ሁለት መቶ የሚደርሱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የያዘ የሚዲያ ኢንዱስትሪያል ዞን (የተሟላ የሚዲያ ከተማ) ነው ያላቸው። ከዚህ ውጭ ያሉትን ዌብሳይቶችና ዲጅታል ፕላትፎርሞች ከጨመርን አንድ ሺህ ገደማ ይደርሳል። ይሄ ሁሉ መድረክ በአንድ ጊዜ እኛ ኢትዮጵያውያኖች ላይ ነው የሚዘምተው። የተወሰንን ሦስትና አራት ሰዎች ይሄን ያህል የተደራጀውን ሚዲያ ነው የሰበርነው ማለት ይቻላል። እኛ ጥቂት ሆነን እነዚህን ሰዎች ማሸነፍ የቻልነው ሀቅ ስለያዝን ነው። ይሄ ሀቅ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከእኛ ጋር እንዲቆም አድርጓል። ነገር ግን ሀቁ ከእኛ ጋር ስለሆነ ሁልጊዜ እንደዚህ ይቀጥላል ማለት አይቻልም። ብዙ ፈተናዎች ይኖራሉ ምክንያቱም ግብጾች ምንጊዜም ለኢትዮጵያ አይተኙም።

እኛ ወደ መድረክ ከመምጣታችን በፊት ትላልቅ የሚባሉት እንደ አልጀዚራ፣ ስካ ነውስ ዓረቢያ፣ አልዓረቢያ እና አልዓረቢያ ላሃደስ ያሉ ትላልቅ የዓረቡ ዓለም ሚዲያዎችን በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ሌሎች ቢሆኑም በሙያተኝነት ተቀጥረው የሚዘውሯቸው በሙሉ ግብጾች ናቸው። እስካሁንም ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ የቀጠለው ይህ ነው። አልጀዚራ ውስጥ ነገሮችን ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የሚያንቀሳቀሱት ግብጻውያን ናቸው። 22 የዓረብ ሀገራት ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ባሕል የሚከተል ትልቅ ተደራሽ ነው። የእነዚህ ሀገራት ሕዝብ ሁሉ በዋነኝነት መረጃ የሚያገኘው ከአልጀዚራ ነው። ግብጻውያን ይህን የሚያክል መድረክ ላይ ፕሮግራም አቅራቢም አዘጋጅም እንግዳም ሆነው መጥተው ስለኢትዮጵያውያን የፈለጉትን አውርተው ደምድመው ይሄዱ ነበር። የሚቃወማቸው አካል ስላልነበር የ22 ሀገራት ሕዝብ በዚህ መንገድ የሚያገኘውን የውሸት መረጃ ተቀብሎ ነው ሲኖር የነበረው። ባለፉት አራት ዓመታት መሐመድ አል አሩሲን ተከትለን በጣት የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን እነዚህ ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ በመቅረብ የሀገራችንን አቋም በሰፊው ማንጸባረቅ በመቻላቸውን የብዙዎችን ዓይን መግለጥ ችለናል።

አዲስ ዘመን፡- በዓባይ ግድብ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ በግብጽ ላይ የተቀናጀችውን ድል እንዴት ይገልጹታል ?

አቶ ሙሳ፡- ዓለሙን ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያሰለፈው ሀቅ የ1929 እና የ1959 ስምምነት ነው። በእነዚህ ስምምነቶች ሱዳን እና ግብጽ ካርቱም ላይ ቁጭ ብለው የዓባይን ውሃ 55 ነጥብ አምስት ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ለግብጽ እንዲሁም 18 ነጥብ አምስት ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ለሱዳን ብለው 86 ቢሊየን ሜትር ኪዩቡን ውሃ ለብቻቸው መከፋፈላቸው ነው። ወንዙ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ በሌለሁበት የተደረገው ስምምነት ትክክል አይደለም ወንዙ ይመለከተኛል ብላ በተደጋጋሚ ጥያቄ ስታቀርብ ነበር። ግብጽና ሱዳን በድርድሩ ሂደት ታሪካዊ የውሃ ድርሻችን እያሉ ሲያነሱ የሚሰሙት ይህን ኢፍታዊ ስምምነት የሚጠቅስ ነው። ታሪካዊ ድርሻችንን የማትቀበሉ ከሆነ መፈራረም አንችልም ይላሉ። በአጭሩ የድርድር ጭብጣቸው ይሄ ነው። ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለውም በዚህ ምክንያት ነው።

በሌላ አነጋገር እንድንፈራረምበት የሚፈልጉት ስምምነት ግድቡ እንዲሠራ ተስማምተናል ነገር ግን ግድቡ ተሠራም አልተሠራም ታሪካዊ ድርሻችን የሆነው 55 ነጥብ አምስት ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የውሃ ድርሻችን እንዳይነካ የሚል ነው። ግድቡ ተሰርቶ እነሱ እንደሚፈልጉት ታሪካዊ የውሃ ድርሻችን የሚሉት እንዲከበር ከተስማማን የሚከሰተው ምንድን ነው፣ ግድቡ ይሠራል የሚይዘው ውሃ የግብጾች ይሆናል ማለት ነው። እነርሱ በሚፈልጉበት ሰዓት ውሃ እንከፍታለን ይበቃናል ውሃ በዝቶብናል ዝጉልን ሲሉን ደግሞ እንዘጋለን ማለት ነው። ድርድሩ ውስጥ ያለው ይሄ ነው።

ኢትዮጵያ ከ150 ዓመታት በላይ የዲፕሎማሲ ልምምድ ያላት ሀገር ናት። በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ቅኝ ገዢዎች መጥተው የነበረውን ሥርዓት አፈራርሰው ከዜሮ ጀምረው ሲሠሩ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ነገር አልተደረገም። ኢትዮጵያ ስትመሠረት የጀመረችው ዲፕሎማሲ እስካሁን ድረስ ቀጥሏል። ግብጾች ይህንን በትክክል አልተረዱትም ወይም መረዳት አልፈለጉም። ግብጾች በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያን ለመጫን እንቅስቃሴ ያድርጉ የነበሩት በአቋም ሳይሆን ይሄ አልተሳካም ያንን እንሞክር በሚል ታክቲክ ነው። ከአፍሪካውያን ጋር ያላቸው ትስስር ደካማ ነው። ምክንያቱም ለ40 ዓመታት ያህል የአፍሪካን አህጉር ትተው ወደ ዓረቡ ዓለም ነው የዞሩት። ከእስራኤል እና ፍልስጤም ጋር ተያይዞ ወደ እስራኤል እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመዞር አፍሪካውያንን ረስተዋል። የረሷቸው አፍሪካውያን ከጎናቸው መቆም አልቻሉም።

ከሁሉም አፍሪካ ሀገራት የግብጾችን ዲፕሎማሲ ውድቀት የሚያሳየው የደቡብ ሱዳን ሁኔታ ነው። ደቡብ ሱዳን ሀገር ሆና እንድትገነጠል ሁሉን ነገር ሲደግፉ የነበሩት ግብጾች ናቸው። የናይል ወንዝ ትብብር ማሕቀፍን በፓርላማ አጽድቃ ለአፍሪካ ህብረት በማስገባት የናይል ኢኒሼቲቭ የትብብር ማሕቀፍ ወደ ኮሚሽን ደረጃ እንዲሸጋገር ስድስተኛዋ ፈራሚ ሀገር በመሆን በሩን የከፈተችው ደቡብ ሱዳን ናት። ግብጾች በዓለም ላይ በዚህ ደረጃ የተከዱበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። ግብጾች ከዓባይ ጉዳይ የሚያስበልጡት ምንም ነገር የለም። በመሆኑም ይህ የመጨረሻ የዲፕሎማሲ ውድቀታቸው ማሳያ ነው። ይህ የሆነው ኢትዮጵያ ያላትን የረጅም ዓመታት የዲፕሎማሲ ልምድ ተጠቅማ ማሳመን እና በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛ ርምጃ መውሰድ በመቻሏ ነው።

እኛ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ርዳታ ከውጭ እንጠብቃለን እንጂ አሜሪካን ሀገር ሄደን ለአግባቢ ድርጅቶች የምንከፍለው ዶላር የለንም። ነገር ግን ልምዱ ስላለን ማንን እንደምናናግር እና እንዴት ጉዳያችንን እንደምናቀርብ እናውቃለን። ስለዚህም በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግብጾችን በዲፕሎማሲ አሸንፈናቸዋል። የመጨረሻው ድላችን ከሶማሊያ ጋር የተያያዘው ነው። ግብጾች በሶማሊያ ምድር ወታደር በማሰማራት በጦርነት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ተንቀሳቅሰው ነበር። ከኢትዮጵያ ጋር የረዘመ የወዳጅነት ታሪክ ባላት ቱርክ እገዛ ከሶማሊያ ጋር የነበረንን ግንኙነት ወደነበረበት በመመለስ ግብጽን አሸንፈናል።

ይሄ ሁሉ የግብጽ እንቅስቃሴ ከዓባይ ግድብ ጋር የሚያያዝ ነው። እነርሱ አሁንም ስለዓባይ ግድብ የሚያስቡት ኢትዮጵያ ላይ ጫና አድርገን የምንፈልገውን ስምምነት ካላስፈረምናት አይሆንም የሚል ነው። በኤርትራም ይሁን ሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንም ሆነ ኬንያ ግብጾች ችግር የሚፈጥሩ ከሆነ ከኋላው የሚኖረው ግብ ኢትዮጵያውያን ተጨንቀው ወደ ስምምነት እንዲመጡ ለማስገደድ ነው። እንዲህ ያለው እንቅስቃሴያቸው እካሁን አልተሳካላቸውም፤ ወደፊትም ቢሆን ካሉበት ሁኔታ አንጻር አይሰካላቸውም። ግብጾች ዛሬም ድረስ በሚያራምዱት የቅኝ ግዛት ዘመን የውሃ ድርሻችን ይከበርልን የሚል ጥያቄ ምክንያት መቼም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ ሊደርሱ አይችሉም።

ግብጾች በአስዋን ግድብ 162 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ አላቸው። ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን የኛን ግድብ ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ ነው። ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትም አላቸው። በተጨማሪም የባሕር ውሃን አጥርተው እየተጠቀሙም ይገኛሉ። ስለዚህ እነርሱ ነገሩን ወደ ፖለቲካ ስለሚወስዱት እንጂ የውሃ ችግር የለባቸውም ማለት እንችላለን። የልማት ፕሮጀክት ወደ ፖለቲካ ከተወሰደ ሁልጊዜም ስምምነት አይመጣም።

ዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ህልውና ከቀይ ባሕር ነጥሎ መመልከት ይቻላል ?

አቶ ሙሳ፡- ግብጾች ዓባይን የግብጽ ስጦታ ይሉታል። እውነታው ግን ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ስጦታ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ በሙሉ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተነጥላ ታሪኳ ሊጻፍ አይችልም። ዓይኗ እግሯ አንድ አካሏ ነው። ለምን እንፈራልን የነበረው ትርክትና ታሪካችንን አለማንበብ አለማወቃችን ነው ሰዎች እንዲፈሩ የሚያደርገው። ሕዝባችንን የምናስገነዝብበት መንገድ ነው የተበላሸው።

ስለ ቀይ ባሕር ስናነሳ ልንመለከታቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮች አሉ። ጣሊያኖች ከወጡ በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴራል እንድትዋሃድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ስምምነት ላይ በተደረሰበት ሰነድ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ወደብ የተጻፈ ነገር አለ። ኤርትራ ስትገነጠልም እንዲሁ የተደረሰው ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ሀቅ እንዲጠበቅ የሚል ሃሳብ ሰፍሯል። ሦስተኛ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በአልጀርስ የድንበር ስምምነት ላይ ስለ አሰብ የተባለ ነገር አለ። ይሄም ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት የለባትም የሚል ነው። አሰብ የማን ናት የሚለው የዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም መጽሐፍ እነዚህን ነገሮች ያመላክታል። በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ገዢዎች የነበሩት ጣሊያን እና እንግሊዝ ምን ጻፉ የሚለውን ብንመረምር ሀቃችን እዚያ ውስጥም ይገኛል።

እኛ ከቀይ ባሕር መነጠል የለብንም። በወቅቱ ኢትዮጵያን ያስተዳድር የነበረው ሕወሓት አሰብን አሁን አንወስዳትም በኋላ ላይ በድርድር እናመጣታለን ብሎ ወይም ከኤርትራ ጋር ተዋህዶ ሀገር የመሆን ህልም ይዞ አውቆ ስህተት ሰርቶ ሊሆን ይችላል። እንዴት ተደርጎ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተነጥላ ትታያለች ?

ቀይ ባሕርን ማጣት ማለት ከኢትዮጵያ አካል አንዱን ማጣት ማለት ነው። ቀይ ባሕር ሲባል ባርነቱ ወይም መውጫ ብቻ አይደለም የተፈለገው። ቀይ ባሕር ላይ ከ120 በላይ ሚሊተሪ ቤዞች ይገኛሉ። ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ጃፓን እና ሌሎች ሀገራት ከሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት አቆራርጠው መጥተው ቀይ ባሕር ላይ ሰፍረው ኢትዮጵያ አፍንጫዋ ስር የሚካሄደው ነገር አይመለከታትም ማለት አይቻልም። ቡሬ ተራራ ላይ ቆመህ ቀይ ባሕርን መመልከት ትችላለህ። አሰብ ከኢትዮጵያ ድንበር 60 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚርቀው። ዓለም በደጃችን ሲፋጭ እናንተ ከቀይ ባሕር ምንም የላችሁም እንዴት ይባላል ? የቀድሞዎቹ ፖለቲከኞች የሠሩት ስህተት ለምን በምሁራን ደረጃ እና በሕግ ባለሙያዎች ዛሬ የማይታየው? ከኤርትራውያን ጋ ሲደረግ የነበረው ንግግር ሁሉ ለምን እንደገና አይታይም ?

አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ዳርቻ ተዋሳኝነት ለመመለስ እያደረገች ላለችው ጥረት ድጋፍ መቸሩን እንዴት ይመለከቱታል ?

አቶ ሙሳ፡- ከቀይ ባሕር ማዶ በቀጣናው ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ብዙ ጠንካራ ሀገራት አሉ። ከቀይ ባሕር ወዲህ ግን የትኛው ሀገር ነው ትልቅና ጠንካራ ሆኖ ሊታይ የሚችለው? አንድ ዩኒቨርሲቲ የሌለውና በሰላሣ ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የውጭ ዲፕሎማቶችን ሰብስቦ መግለጫ የሚሰጥ ሀገር እንደ ሀገር ይታያል? የትኛው ሀገር ነው እንደ ሀገር ራሱን ችሎ የሚቆመው? አብዛኞቹ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት የሌሎች ሀገራት ጥገኛ ናቸው። ጅቡቲን ብንወስዳት በፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ ድጋፍ የምትኖር ናት። ሶማሊላንድ ገና እንደ ሀገር እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ያለች ሀገር ናት። ሶማሊያ ውድቀት ጥሟት በኢትዮጵያ ድጋፍ ነው ከዜሮ ተነስታ የቆመችው። ከቀይ ባሕር ወደዚህ ያለችው ብቸኛ ጥሩ አቋም ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ናት። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገር እንድትሆን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፍላጎት ነው። ምክንያቱም የአልሻባብ አቅም ከሶማሊያ መንግሥት በላይ ነው። ኤርትራ እንደ መንግሥት የሚታይ አስተዳደር የላትም።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሀገር መሆኗን ተረድቶ ቀይ ባሕር ላይ መገኘቷን ስትራቴጂክ ጉዳይ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ግብጽና ኤርትራ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የምታነሳውን ጥያቄ ለመቀልበስ የሚያደርጉት ሩጫ የትም የሚደርስ አይደለም። ኤርትራም ዕድሜ ልኳን ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ልትቀጥል አትችልም። አንዳች ነገር ተፈጥሮ የኢሳያስ አስተዳደር ቢፈርስ አራትና አምስት ታጣቂ ኃይል ከውስጧ ሊወጣ ይችላል። አልሻባብ እየፈጠረ ካለው ችግር ጋር ተዳምሮ ቀይ ባሕር ሌላ መልክ ሊይዝ ይችላል። አሁን እንኳን የሁቲ አማጺያን በአካባቢው ላይ እየፈጠሩ ያሉት ችግር የሚታወቅ ነው። ይህን ሁኔታ ስለተረዳ ነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የግድ ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ መጠጋት አለባት የሚለው።

አዲስ ዘመን፡- ሰፊ ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን ማብራሪያ ስለሰጡን እናመሰግናለን!

አቶ ሙሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ!

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You