
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ ነው። ጀግንነታችንን
ያሳየንበት የዚህ ትውልድ ልዩ ዐሻራ በመሆኑ ሁላችንም በባለቤትነት ስሜት እናየዋለን፤
እንኮራበታለን። ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንንና ዕውቀታችንን አዋሕደን «አይችሉትም፤ አይሞክሩትም»
የተባለውን ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ተጠቃሽ የሆነውን ግዙፍ ግድብ ገንብተን ብርታታችንን
ለዓለም አስመስክረናል።
ልዩነቶቻችንን ጌጥ አድርገንና አንድነታችንን አስቀድመን የጀመርነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ
ግድብ አሁን ላይ ፍጻሜውን ሊያገኝ ጫፍ ላይ ደርሷል። «አይችሉምን» በይቻላል ለውጠን ሪቫን
ለመቁረጥ በጣት የሚቆጠሩ ወራቶች ቀርተውናል።
ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ብርቅዬ የዘመኑ
የጀግንነት መገለጫ፤ ከደሃ እስከ ሀብታም፤ ከሕፃን እስከ አዋቂ ከደቂቅ እስከ ሊቅ የሁሉም
ኢትዮጵያውያን ደማቅ ዐሻራ ያረፈበት መለያ ዓርማችን ነው። ይቻላል በተግባር የተመሰከረበት፤
ኢትዮጵያውያን የጦር ሜዳ ኅብረትና ጠላትን ድል የነሱበትን ጀግንነታቸውን በልማት የደገሙበት ልዩ
የሆነው የአንድነት መኩሪያ ምልክት ነው።
የሁሉም ዜጋ የልብ ትርታ በመሆኑ እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ፤ መቼ ባለቀ ተብሎ በጉጉት
የሚጠበቅ፤ የእያንዳንዱ ዜጋ ዐሻራ ያረፈበት የጀግንነት መለያችን ነው። ከሀገር አልፎ ለጎረቤት
ሀገራት የሚተርፍ ዕንቁ ሀብታችን። በመሆኑም ሁሉም ሰው የራሴ ብሎ የመጠናቀቁን ብሥራት
የሚያበስረውን ዜና ሰምቶ ደስታውን በጋራ ለማጣጣም በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል።
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሠረት ተጥሎ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተገባው የኢትዮጵያ
ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራውን ከተጀመረ እነሆ አስራ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። ፕሮጀክቱ
በታሰበለት ጊዜ መጠናቀቅ ባይችልም በመዘግየቱ ማንም ተስፋ ሳይቆርጥ የተበላሸው ተስተካክሎ፤
የጎበጠው ተቃንቶ ዛሬ ላይ ወደ ማ ጠናቀቂያ ምዕራፍ ማቃረብ ተችሏል።
በግድቡ ግንባታ ወቅት ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ግን ተስፋ ያልቆረጥንባቸው ተግዳሮቶች
ከውስጥም ከውጪም አጋጥመውን እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ከፕሮጀክቱ መጠንሰስ ጀምሮ
ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እንዳይገኝ የተሄደበት ርቀት አንዱ ለፕሮጀክቱ
ማደናቀፊያ ታስቦ የተደረገ ነበር።
ያም ሆኖ በራስ አቅም፣ ሀብትና እውቀት ወደ ሥራ በተገባበት ወቅትም በርካታ መሰናክሎች
ገጥመውናል። ከግንባታው ጥራት አንስቶ የሌሎችን ሀገራት ሰብዓዊ መብት ይጋፋል እስከሚለው
የዲፕሎማሲ ጫና የማድረግ ሂደት ታልፏል። በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጭምር
ተደጋጋሚ ክሶች ቀርበውበታል።
ሆኖም ሁሉም በጥንካሬና በአንድነት በመቆም ማክሸፍ ተችሏል። የነበሩብንን እንደመርግ የከበዱ
ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ አሁን ላይ ወደ ፍጻሜው ተቃርቧል። በከሳሾቻችን ሴራ ሳይሆን
በመንግሥትና በዜጋው ብርቱ ጥረት የድሉ ባለቤት መሆን ተችሏል። የብርሃን ሻማ ልንለኩስም
ከጫፍ ደርሰናል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን ግዙፍ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል። የኢትዮጵያን
አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ ይሆናል። የፋይናንስ ምንጭ ከሆነው
ሕዝብ ባለፉት 13 ዓመታት ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል።
ይሄ የሕዝቡ የፋይናንስ አቅም እውቀትና ጉልበት በቀጣይ የታሰበውን የማዳበሪያ በጨለማ
ውስጥ ያሉ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከዚህ ችግር ከመታደግ አንስቶ በርካታ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች
ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆንም ይታመናል፡፡
በቅርቡ ለምርቃት የሚበቃውን ታላቁ ህዳሴ ግድባችንን አጠናቀን ድሉን እያጣጣምን ለዳግም
ህዳሴ መዘጋጀት ደግሞ ይጠበቅብናል። ህዳሴ ግድብ የይቻላል አቅም ማሳያችን፤ ዳግማዊ ዓድዋችንም
ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም