“በረመዳን ወር የምንተገብራቸውን መልካም ዕሴቶች የሕይወታችን ልምዶች ልናደርጋቸው ይገባል” -ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ

አዲስ አበባ፡- በረመዳን ወር የምንተገብራቸው የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና መሰል መልካም እሴቶችን ሁልጊዜም የሕይወታችን ልምዶች ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ገለጹ፡፡

ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ረመዳን መሠረታዊ እሴት በሰዎች ልብ ውስጥ የፈጣሪ ፍራቻ፣ መተዛዘን፣ ስለሌሎች መኖርን፣ መደጋገፍንና ማሰብን የሕይወታችን አካል እንድናደርግ ለ11 ወራት የሚሆን ስንቅ የሚይዝበት ወር ነው።

በመሆኑም በረመዳን ወር የምንተገብራቸውን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና ለሌሎች መልካም እሴቶች ሁልጊዜም የሕይወታችን ልምዶች አካል ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ረመዳን አንዱ ስለሌላው የሚኖርበት ስለሆነ መልካም ተግባራት በስፋት የሚከናወኑበት ወር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር ደግሞ ሰዎች ዘወትር ሊኖራቸው የሚገባ ባሕሪ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

“እኛ ዋጋ ለማግኘት ብለን በፈቃዳችን ስንፆም ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን ማሰብና አለኝታነታችንን ማሳየት ይገባናል ብለዋል።

የረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ መልካም ነገሮችን የሚለማመድበት ቅዱስ ወር መሆኑን አስታውሰው፤ ረመዳን ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአላህ ወራት ናቸው ብለዋል። ስለሆነም ለፈጣሪ መታዘዝና ሕጉን አክብረን መንቀሳቀስ የሚገባን ዓመቱን ሙሉ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ስንፈጠር ጀምሮ አንዳችን ለአንዳችን እንድንኖር መሆኑን የጠቆሙት ኡስታዝ አቡበከር፤ መስጠት የሚችሉ ሰዎችን የፈጣሪ ትዕዛዝን መሠረት አድርገው እና ያላቸውን ፀጋ ተጠቅመው የሌሎችን ተስፋና ደስታ በመሙላት የመኖር ዋጋቸውን ከፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ዒድ አልፈጥር ከረመዳን ፆም በኋላ ፆሙን በትክክል ስላስጨረሰን ለአላህ ምስጋና የምናቀርብበት የደስታ በዓል ነው ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ በዓሉን ስናከብርም ስለሌሎች በማሰብና ደስታን በመጋራት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዒድ በዓል አስቀድሞም በፆም ወቅት ያጎደልነውንና ያጠፋነውን ነገር ካለ ለማስተካከል ከዒድ ሶላት በኋላም ለተቸገሩት ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You