የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ እምነት እና ብልፅግና ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው

የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ እምነት እና ብልፅግና ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ አደም ካሚል (ረ/ፕ) ገለጹ፡፡

የታሪክ ተመራማሪው አደም ካሚል (ረ/ፕ) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ እምነት እና ብልፅግና ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ቀይ ባሕር ከጥንት ጀምሮ የአበሻ ባሕር በመባል የሚታወቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደነበራት ከጥንትም ጀምሮ የተረጋገጠና ዓለም የሚመሰክረው ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት አደም ካሚል (ረ/ፕ) ፤ ያለን አማራጭ ይህን ታሪካዊ ንብረታችንን በሰላማዊ መንገድ ማግኘት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተዋሳኝነቷን በሰላማዊ መንገድ መልሳ ማግኘት እንዳለባትና ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከባሕሩ ተጋሪ ሀገራት ጋር ተጠቃሚ መሆን የምንችልበትን ዕድል መፍጠር እንደሚገባት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችው በወቅቱ በነበረው በራሷ መንግሥታዊ አስተዳደርና ተመሳሳይ ፍላጎት ባላቸው ሌሎች ሃይሎች እንደነበር አስታውሰው፤ በዚያ የተሳሳተ ውሳኔ ላይ የሕዝቦች ይሁንታና የቅኝ ገዢዎችም ጫና አለመኖሩን አደም ካሚል (ረ/ፕ) አስታውሰዋል። ኢትዮጵያን የሚመራው የወቅቱ መንግሥት ሀገሪቱ የባሕር በር እንድታጣ ያደረገው ደባና ሴራ ዛሬም ድረስ አስገራሚና አከራካሪ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት ጀርባ የራሷ መንግሥታዊ አስተዳደር እና የኤርትራ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይም የግብጾችን ሚና ወደ ኋላ ሄዶ መፈተሽ ቢቻል የተሠራብንን ሸፍጥ መረዳት እንችላለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሰብን ያጣችበት ሁኔታ አነጋጋሪና ምክንያታዊ ያልሆነ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የ130 ሚሊዮን ዜጎች ሀገር በመሆኗ የባሕር በር የማግኘት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች ያሉት አደም ካሚል (ረ/ፕ) ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በተለይም በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር ተጠቃሚ የሚደርጋትን አድል መፍጠር አለባት ብለዋል። ኢትዮጵያ ለወደብ የምትከፍለውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስና የሕዝቦቿን ፍላጎት ለማስተናገድ ወደብ እንደሚያስፈልጋት የሚያጠራጥር አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር የባሕር በር ባለቤትነቷን ማረጋገጥ ይኖርባታል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም አንዱ መፍትሄ የቀይ ባሕርን ውሃ ወደ ግዛቷ በመሳብ ልክ እንደኮሪደር ልማቱ አልምታ የእኔ የምትለውን ወደብ መሥራት ግድ እንደሚላት አመላክተው፤ በዚህ ረገድም የተጠና ጥናት ስለመኖሩ ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ በሰላማዊ መንገድ ተደራድሮ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉም አደም ካሚል (ረ/ፕ) አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You