የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታት ለኢትዮጵያ ብልፅግና መሠረት ነው !

ዓለማችን አሁን ላይ ለደረሰችበት ሁለንተናዊ እድገት የፈጠራ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው የማይተካ አስተዋጽኦ ነበራቸው ፤ አላቸውም ። በቀጣይም የሰው ልጅን ሆነ የዓለማችንን እጣ ፈንታ በመተለም ሂደት ውስጥ የፈጠራ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው ወሳኝ አቅሞች እንደሆኑ ይታመናል። ለዚህም ሲባል አሁን ላይ ዓለማችን ለጥናት እና ምርምር በተለይም ለፈጠራ ሥራዎች ከፍተኛ ሀብት ለመመደብ የተገደደችበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል።

እንደሚታወቀው ዓለማችን አሁን ላይ በብዙ የውድድር መድረኮች የተሞላች ነች ። በያንዳንዱ መስክ ያለው ተወዳዳሪነት የህልውና ጉዳይ እየሆነ የመጣበት እውነታም በተጨባጭ እየተስተዋለ ነው ፤ ውድድሩን በአሸናፊነት ለመወጣት ሀገራት ከፍተኛ ሀብት ከመመደብ ባለፈ የትምህርት ሥርዓታቸው ይህንን ታሳቢ አንዲያደርግ ፤ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው። ዘመኑን የሚመጥን እና የሚዋጁ የትምህርት ሥርዓት በመቅረጽም ነገዎቻቸውን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ እየተጉ ነው።

ይህ ተጨባጭ ዓለም አቀፋዊ እውነታ የማይመለከተው ሀገር ሆነ ማህበረሰበ የለም። በተለይም በማደግ ላይ ያሉት ፤ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ለመውጣት በብዙ ትግል ውስጥ የሚገኙ ሀገራት እና ሕዝቦች ይህ እውነታ በብዙ መንገድ ነገዎቻቸውን የሚወስን ከሆነ ውሎ አድሯል። ዓለም አቀፋዊ ከሆነው ውድድር ተጠቃሚ ለመሆን ሆነ በውድድሩ ከጨዋታ ውጪ በመሆን ለሚፈጠር አደጋ እራሳቸውን ለመታደግ ፤ ለፈጠራ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው።

ለዚህም አንድም የፈጠራ ሰዎችን እና ሥራዎቻቸውን በማበረታታት ፤ እንደ ሀገር ሆነ ማህበረሰብ የራስን አቅም መገንባት የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ስትራቴጂክ እይታ መፍጠር ፤ ከዚያም ባለፈ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ሀገራዊ ዝግጁነት መገንባት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ትውልድ በፈጠራ ሂደት ውስጥ የራሱን ዐሻራ አስቀምጦ የሚያልፍበትን መንገድ መቀየስ ፤ የራሱን ሆነ የመጪ ትውልዶችን እጣ ፈንታ ብሩህ ሊያደርግ የሚችል የአስተሳሰብ መሠረት ላይ እንዲቆም ማስቻል ወሳኝ ነው።

በተለይም ከፈጠራ እና ከፈጠራ ሥራዎች ጋር የተያያዙ የተዛቡ አመለካከቶችን እና ድባቴዎችን ሰብሮ በመውጣት ሂደት ውስጥ ትውልዱ የተሻለ ግንዛቤ እና መነቃቃት እንዲኖረው የአስተሳሰብ ህዳሴ መፍጠር ያስፈልጋል ። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ለዘርፉ ጎታች የሆኑ አስተሳሰቦችን እና አስተሳሰቦቹ የወለዷቸውን የአይቻልም መንፈስ መስበር የሚያስችል በፖሊሲ የተደገፈ ሀገራዊ መነቃቃት መፍጠር ያስፈልጋል።

እንደኛ አይነት በአንድ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ከፍያለ ሥልጣኔ ባለቤት የሆኑ ሕዝቦች ፤ ከሁሉም በላይ ከትናንት ሥልጣኔ ከፍታቸው ለመውረዳቸው ምክንያት የሆኑ እሳቤዎችን በአግባቡ ማጥናት ፤ ከእሳቤዎቹ በስተጀርባ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን ማረም ያስፈልጋቸዋል። በአዲሱ ትውልድ አእምሮ እና ልብ ውስጥ የይቻላል መንፈስን የሚያሰርጽ አዳጊ አስተሳሰብ መፍጠርም ወሳኝ ነው።

በተለይም አዲሱ ትውልድ ዓለም አሁን ከደረሰችበት የላቀ የፈጠራ እድገት አንጻር ፤ ለራሱ እና ለራሱ የፈጠራ ሥራዎች የሚኖረው ግምት ዝቅተኛ እንዳይሆን ፤ ከዚህ ይልቅ ራሱን ለመሆን ለሚያደርጋቸው ጥረቶች አቅም የሚሆን የይቻላል መንፈስን የሚያጎለብት ቀጣይነት ያለው የሥነ ልቦና ግንባታ ማካሄድ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው።

አሁን ያለው ዓለም የፈጠራ እድገት በጥቂት አስር ዓመታት ውስጥ የተስተዋለ ፤ዓለም አሁን ከደረሰችበት የፈጠራ ልህቀት አኳያ ሁኔታዎች ከዚህም በፈጠነ መንገድ ሊጓዙ እንደሚችሉ ፤ ትውልዱ በደረሰበት ደረጃ ከዓለም ጋር ተቀራርቦ መጓዝ የሚያስችለው የመረዳት እና የመፍጠር ባለአቅም መሆኑን በተጨባጭ የሚረዳበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠርም ያስፈልጋል።

ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር ከመጣንበት ያልጠራ መንገድ እና በአግባቡ ያልተገራ አስተሳሰብ አኳያ ገናብዙ መሥራት የሚጠበቅብን ቢሆንም አሁን ላይ እንደ ሀገር ፈጠራን ከማበረታታት ጀምሮ ለፈጠራ የሚሆን ማህበረሰባዊ መደላድሎችን ለመፍጠር እየሄድንበት ያለው መንገድ የሚበረታታ ነው። በራሳችን ለመቆም ለጀመርነው ሀገራዊ መነቃቃትም ትርጉሙ ብዙ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን የፈጠራ ሰዎቻችን ወደ አደባባይ ይዘዋቸው የሚመጧቸው ሥራዎቻቸው ሀገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው በማስቻል ሂደት ውስጥ ባለሀብቶች አጋዥ አቅም በመሆን እንደ ዜጋ ያለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት እንደ ጅማሮ የሚበረታታ ቢሆንም ፤ በቀጣይ ብዙ የሚጠበቅባቸው ስለመሆኑ በአግባቡ ሊረዱና ራሳቸውን በተሻለ መልኩ ሊያዘጋጁ ይገባል።

በተለይም ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ፤ የፈጠራ ሥራዎችን ከማበረታታት ጀምሮ ሥራዎቹ በስፋት በሀገር ውስጥ ተመርተው ወደሥራ እንዲገቡ የባለሀብቶች እና የፋይናንስ ተቋማት አበርክቶ ከፍተኛ በመሆኑ ራሳቸውን ለዚህ አይነቱ ሃላፊነት ማዘጋጀት ለነገ የሚሉት የቤት ሥራቸው ሊሆን አይገባም ።

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You