
በኢትዮጵያ ምድር የባሕር በር ጥያቄ መስተጋባት ከጀመረ ከራርሟል። ይህ ጊዜውን ሲጠብቅ የነበረ እና በበርካቶች ልቦና ውስጥ የኖረ ጥያቄ እነሆ ጊዜው ደርሶ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኗል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንዴት ተገለለች? ከታሪክ፣ ከዓለም አቀፍ ሕጎች እና ከተፈረሙ ስምምነቶች አንጻር መልሳ የቀይ ባሕር አካል የምትሆንበት ዕድልስ አለ? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ነው፡፡ይህን ጉዳይ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎችም የየራሳቸው ምላሽ አላቸው፡፡
በዓረቡ ዓለም ሚዲያዎች የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት የሚታወቁት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሳ ሼኮ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ ሲገልጹ፤ ግብጾች ዓባይን የግብጽ ስጦታ ይሉታል። እውነታው ግን ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ስጦታ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ በሙሉ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተነጥላ ታሪኳ ሊጻፍ አይችልም። ልክ እንደ ዓይኗ፤ እግሯ የአካሏ አንድ ክፋይ ነው ይላሉ።
የነበረው የተዛባ ትርክት፣ ታሪካችንን አለማንበብና አለማወቃችን እንዲሁም ሕዝባችንን የምናስገነዝብበት መንገድ ነው ስለ ወደብ ሲነሳ ሰዎች ጦርነት ይነሳል በሚል እንዲፈሩ የሚያደርገው የሚሉት አቶ ሙሳ፤ ስለ ቀይ ባሕር ስናነሳ ልንመለከታቸው የሚገቡ ሶስት ነገሮች እንዳሉም ያስረዳሉ። ጣሊያኖች ከወጡ በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴራል እንድትዋሃድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ስምምነት ላይ በተደረሰበት ሰነድ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ወደብ የተጻፈ ነገር አለ። ኤርትራ ስትገነጠልም እንዲሁ የተደረሰው ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ሀቅ እንዲጠበቅ የሚል ሃሳብ ሰፍሯል። ሦስተኛ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በአልጀርስ የድንበር ስምምነት ላይ ስለ አሰብ የተባለ ነገር አለ። ይሄም ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት የለባትም የሚል ነው። አሰብ የማን ናት የሚለው የዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም መጽሐፍ እነዚህን ነገሮች ያመላክታል። በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ገዢዎች የነበሩት ጣሊያን እና እንግሊዝ ምን ጻፉ የሚለውን ብንመረምር ሀቃችን እዚያ ውስጥም ይገኛል ባይ ናቸው።
በወቅቱ ኢትዮጵያን ያስተዳድር የነበረው ሕወሓት አሰብን አሁን አንወስዳትም በኋላ ላይ በድርድር እናመጣታለን ብሎ ወይም ከኤርትራ ጋር ተዋህዶ ሀገር የመሆን ህልም ይዞ አውቆ ስህተት ሰርቶ ሊሆን ይችላል። እንዴት ተደርጎ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተነጥላ ትታያለች ? ብለው የሚጠይቁት የፖለቲካ ተንታኙ፤ እኛ ከቀይ ባሕር መነጠል የለብንም በማለት ለጥያቄው ራሳቸው መልስ ይሰጣሉ።
ቀይ ባሕርን ማጣት ማለት ከኢትዮጵያ አካል አንዱን ማጣት ማለት ነው። ቀይ ባሕር ሲባል ባርነቱ ወይም መውጫ ብቻ አይደለም የተፈለገው። ቀይ ባሕር ላይ ከ120 በላይ የተለያዩ ሚሊተሪ ቤዞች ይገኛሉ። ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ጃፓን እና ሌሎች ሀገራት ከሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት አቆራርጠው መጥተው ቀይ ባሕር ላይ ሰፍረው ኢትዮጵያ አፍንጫዋ ስር የሚካሄደው ነገር አይመለከታም ማለት አይቻልም። ቡሬ ተራራ ላይ ቆመህ ቀይ ባሕርን መመልከት ትችላለህ። አሰብ ከኢትዮጵያ ድንበር 60 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚርቀው። ዓለም በደጃችን ሲፋጭ እናንተ ከቀይ ባሕር ምንም የላችሁም እንዴት ይባላል ? የቀድሞዎቹ ፖለቲከኞች የሠሩት ስህተት ለምን በምሁራን ደረጃ እና በሕግ ባለሙያዎች ዛሬ የማይታየው? ከኤርትራውያን ጋር ሲደረግ የነበረው ንግግር ሁሉ ለምን እንደገና አይታይም ? ሲሉም ይጠይቃሉ።
ከቀይ ባሕር ማዶ በቀጣናው ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ብዙ ጠንካራ ሀገራት አሉ። ከቀይ ባሕር ወዲህ ግን የትኛው ሀገር ነው ትልቅና ጠንካራ ሆኖ ሊታይ የሚችል ሀገር አለመኖሩን ጠቁመው፤ አንድ ዩኒቨርሲቲ የሌለውና በሰላሳ ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የውጭ ዲፕሎማቶችን ሰብስቦ መግለጫ የሚሰጥ ሀገር እንደ ሀገር ይታያል? የትኛው ሀገር ነው እንደ ሀገር ራሱን ችሎ የሚቆመው? የሚለውን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። ከዚሁ ባሻገር አብዛኞቹ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት የሌሎች ሀገራት ጥገኛ ናቸው። ጅቡቲን ብንወስዳት በፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ ድጋፍ የምትኖር ናት። ሶማሊ ላንድ ገና እንደ ሀገር እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ያለች ሀገር ናት። ሶማሊያ ውድቀት ገጥሟት በኢትዮጵያ ድጋፍ ነው ከዜሮ ተነስታ የቆመችው። ከቀይ ባሕር ወደዚህ ያለችው ብቸኛ ጥሩ አቋም ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ናት። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገር እንድትሆን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍላጎት ነው። ምክንያቱም የአልሻባብ አቅም ከሶማሊያ መንግሥት በላይ ነው። ኤርትራ እንደ መንግሥት የሚታይ አስተዳደር የላትም ሲሉ ሙሳ ሼኩ ያስረዳሉ።
አቶ ሙሳ እንደሚናገሩት፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሀገር መሆኗን ተረድቶ ቀይ ባሕር ላይ መገኘቷን ስትራቴጂክ ጉዳይ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ስለዚህ ግብጽና ኤርትራ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የምታነሳውን ጥያቄ ለመቀልበስ የሚያደርጉት ሩጫ የትም የሚደርስ አይደለም።
ኤርትራም ዕድሜ ልኳን ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ልትቀጥል እንደማትችል የሚገልጹት የፖለቲካ ተንታኙ፤ አንዳች ነገር ተፈጥሮ የኢሳያስ አስተዳደር ቢፈርስ አራትና አምስት ታጣቂ ኃይል ከውስጧ ሊወጣ ይችላል። አልሻባብ እየፈጠረ ካለው ችግር ጋር ተዳምሮ ቀይ ባሕር ሌላ መልክ ሊይዝ ይችላል። አሁን እንኳን የሁቲ አማጺያን በአካባቢው ላይ እየፈጠሩ ያሉት ችግር የሚታወቅ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ሁኔታ ስለተረዳ ኢትዮጵያ የግድ ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ መጠጋት አለባት የሚል አቋም ይዟል ብለዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው፤ ቀይ ባሕር ከጥንት ጀምሮ የአበሻ ባሕር በመባል ነው የሚታወቀው። ሥልጣኔያችንም፣ ታሪካችንም፣ እምነታችንም፣ ብልፅግናችንም ሆነ ንግዳችን ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ ነው። ቅኝ ገዢዎች መጥተው አይደለም ይህቺን ሀገር የከፋፈሏት። የኤርትራ ነፃ አውጪዎች አጀንዳ ላይ ሚና የተጫወቱት ሌሎች ናቸው። እውነት የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብስ ተጠይቆ በጉዳዩ ላይ ተወያይቷል? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡
ኤርትራ እንድትገነጠልና ቀይ ባሕርን እንድናጣ የተደረገው በተለይ በግብጾች ሸፍጥ መሆኑን የሚጠቅሱት የታሪክ ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያን የሚመራው የወቅቱ መንግሥት ቀይ ባሕርን እንድታጣ የተደረገበት ደባና ሴራ አሜን ብሎ መቀበሉ አነጋጋሪና አከራካሪ ነው። ሕወሓትም ሆነ ሻቢያ የአንድ ሳምንት ሁለት ገጽታዎች ናቸው። እነሱ የሚታገሉትን የደርግ ሥርዓት ለመጣል የትጥቅ ትግል በሚያደርጉበት ወቅት ከጀርባቸው የነበሩት ግብጾች እንደነበሩ ይናገራሉ።
አክለውም፤ ቀይ ባሕርን እንድናጣ ያደረገው በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ይሠራ የነበረ አንድ ግብጻዊ ዲፕሎማት ነው። ለአራት ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ያገለገለው ይህ ግብጻዊ በጊዜው በሰፊው ሲንቀሳቀስ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ሲንቀሳቀስ የነበረበት ዓላማም የቀይ ባሕርን ምዕራብ ክፍል የያዘችውን ኢትዮጵያ ከባሕር ዳርቻው ማራቅ የሚል ነበር። ‹‹ምንም እንኳን አረብኛ ባይናገሩም ጅቡቲና ሶማሌን የዓረብ ሊግ አባል አድርገናል። የቀይ ባሕርን ዓረባዊነት ለማረጋገጥ ኤርትራ የምትባል ሀገር መወለድ አለባት። ይህች ሀገር 23ኛ የዓረብ ሊግ አባል ሀገር ትሆናለች። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የቀይ ባሕር ምንም ድርሻ ስለማይኖራት ያልቅላታል›› የሚል ህልም ነበረው። ይህን ህልሙን ለማሳካት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎችን በሁሉም መንገድ በመደገፍ ጉዞውን ጀመረ። ኮድ ከሚባል የወቅቱ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ተጠሪ ጋር በመሆን የኤርትራን መገንጠል ተግባራዊ አደረጉ። በዚህም ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን አጣች ይላሉ።
አደም እንደሚያስረዱት፤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ገዢ ፓርቲዎች ውሳኔዎችን አሳለፉ እንጂ በሁለቱም ወገን ያሉ ሕዝቦች አልተወያዩበትም። ሰላሳ ዓመት ታግለናል ነፃነታችንን ማግኘት አለብን አሉ አገኙ። በዚህ ሂደት ቅኝ ገዢዎች ዐሻራ የላቸውም። በዚህ መንገድ ነው አሰብና ምጽዋን እንድናጣ የተደረገው። የኢሳያስ መንግሥት ነፃነቱን ከወሰደ 31 ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የኤርትራን ሕዝብ ድህነት ለመቅረፍ በአሰብ ወደብም ሆነ በመላ ሀገሪቱ የሠራው ምንም ነገር የለም።
የአሰብ ወደብን መጠቀም የምትችለው ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን የሚያነሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ኬንያ ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን ወይም ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ሊጠቀሙበት አይችሉም። አሰብን እንኳን ለኢትዮጵያ በማከራየት መጠቀም ይችል ነበር፤ ይሄንን እንኳን ማድረግ አልቻለም። እኛ የወደብ አማራጮች አሉን። ከፈለግን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልክ የኮሪደር ልማት እንደምንሠራው ከቀይ ባሕር እስከ አሰብ ድረስ ያለውን ቦታ ቆፍረን ባሕሩን ስበን በማምጣት በራሳችን ክልል ውስጥ ራሳችን ወደብ መመሥረት እንችላለን። በዚህ ረገድ የተጠና ጥናት አለ። ነገር ግን የጋራ ተጠቃሚነት እንዲኖር በሰላማዊ መንገድ ተደራድረን ወደቡን ለመጠቀም እየሠራን ነው። ኢትዮጵያ አሁን የ130 ሚሊየን ዜጎች ሀገር በመሆኗ ወደቡን የመጠቀም አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። ወጪያችንን ለመቆጠብ ወደብ ማግኘት አለብን ነው የሚሉት።
አስተያየታቸውን ሲቋጩም የአሰብ ወደብ ከጥንትም በታሪክ ደረጃ የአፋር ንብረት ነው። ይህ ዓለም አቀፍ ሕግ የመሰከረበት ሁኔታ ነው። አሰብ የኢትዮጵያ ንብረት መሆኑ ከጥንትም ጀምሮ የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ በሰላማዊ መንገድ እንጠቀም ጦርነት አይበጅም የሚለው ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
የውሃ ሳይንስ መሐንዲሱ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁም የአሰብ ጉዳይ በአስተዳደርም ሆነ በሌሎች ነገሮች ከአብዛኛው የኤርትራ ክፍል ተለይቶ ኢትዮጵያ ጋር የቆየ ነው። የአፋሮች ባለሥልጣናት ሲያስተዳድሩት የነበረ ነው። በአጠቃላይ በክፍለ ሀገርም ብናየው የወሎ ግዛት ሆኖ የቆየ ነው። ሕወሓት ኤርትራ ስትገነጠል በአሰብ ጉዳይ መደራደር ይችል ነበር። ምክንያቱም ኤርትራም አጥብቃ የኔ ነው የምትልበት ነገር የላትም፣ ኢትዮጵያም ወደ ኋላ የምታፈገፍግበት ምክንያት አልነበራትም ይላሉ።
አሰብ የኢትዮጵያ የነዳጅ ማጣሪያ ማዕከል እና ወደብ ነበረች። ያጣነው ቁልፍ ሚና የነበረውን የባሕር በር ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ የተለያዩ ሀገራት ከርቀት በመምጣት በቀይ ባሕር የጦር ሰፈር ማቋቋም ደረጃ እየደረሱ ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የተዘጋ በር ከፈት እንዲልላትና ከተቀረው ዓለም ጋር መገናኘት እንድትችል መጠየቋ ትልቅ ጉዳይ የሚሆንበት ምክንያት የለም ባይ ናቸው፡፡
ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ደህንነት፣ ልማት፣ ሁለንተናዊ ብልፅግና እና ገናናነት ጋር የሚያያዝ ነው። ከ130 ሚሊየን በላይ የሕዝብ ቁጥር ላላት ሀገር እጅግ ወሳኝ የሆነ አካሏ ነው። ከቀይ ባሕር እንራቅ ብንል እንኳን ምን ጊዜም መዘዙ ሊለቀን አይችልም ያሉት ተመራማሪው፤ በቀይ ባሕር ጉዳይ አርፈን እንቀመጥ የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል ጠቁመዋል።
የወደብ ጉዳይ የሀገር አጀንዳ በመሆኑ የማይነካው ግለሰብ፣ ቡድን እና ተቋም አይኖርም። ስለዚህ ከአንድ መንግሥት ጋር አለመግባባት አለኝ በሚል የምናኮርፍበት ነገር መሆን የለበትም። የመንግሥታት ዕድሜ አጭር ነው። እንደ ወደብ ያለ አጀንዳ ግን ወደፊት የሚመጡ ትውልዶችን ሁሉ የሚመለከት ዘላቂ የሀገር ጥቅም ነው። ስለሆነም በወደብ ጉዳይ ሁላችንም በአንድነት መቆም ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስበዋል።
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም