
ፋሽን እንደግል ምርጫ እንደመሆኑ፤ ውበትና አንድናቆትም እንደየሰው እይታ ነው። በመሆኑም ፋሽን ወጥ የሆነና ይሄ ነው የሚባል ስምምነትም ሆነ ቅርጽ የለውም። ነገር ግን ሁላችንንም ሊያስማማን የሚችል አንድ ነገር አለ። ማናችንም ብንሆን የትኛውንም ፋሽን ስንከተል ዋነኛው ዓላማችንና ግባችን በሰዎች ዘንድ ቆንጆ ሆኖ መታየት ነው። ታዲያ እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ መጠየቅ አለብን፤ ሁሉም ፋሽኖች በእያንዳንዳችን ዘንድ እኩል ውበትን ይሰጣሉ? በእርግጠኝነት መልሱ አይሰጡም መሆን አለበት። ምክንያቱም ደግሞ የምንከተላቸው እያንዳንዱ የፋሽን አይነቶች ውብ ናቸው..አምሮብሃል..አምሮብሻል የሚያስብሉን የፋሽኑ የጥራት ደረጃ፣ የገዛንበት የገንዘብ መጠን ወይንም ሌላ አይደለም። ጉዳዩ የተፈጥሮና የስነ-ውበት ነው።
ፋሽን የግዴታ የሚያስብል ሕግ ባይኖረውም፤ ነገር ግን የስነ-ውበት ሕግ አለው። አብዛኛውን ጊዜ በፋሽንና ሞዴሊንግ ውድድሮች ላይ እነዚህ ሕጎች እንደ መስፈርት ይታያሉ። እነዚህን ሕጎች የተሻለ በጠበቅን ቁጥር የተሻለ ቆንጆ ሆነን እንታያለን። በፋሽናዊ እይታ ውስጥ የሚያምር ፊት ስላለን ብቻ ቆንጆ አያስብለንም። የማያምር ፊት ስላለንም አስቀያሚ አይደለንም። ሁሉም ነገሮች የሚወሰኑት ያለንን ነገር የምንጠቀምበት መንገድ ነው።
ተፈጥሮ የሰጠችንን ጥሩም ይሁን መጥፎ የውበት ገጽታችንን በሚመጥነው የፋሽን አይነት ጠብቆ ማቆየትም ሆነ ማከም እንችላለን። የስነ-ውበት ሕጎቹ ባለን የሰውነት ቅርጽ፣ ቁመት፣ የቆዳ ቀለም፣ አቋም እንዲሁም ባለን የሰውነት ክብደት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እነዚህ ነጥቦች በእያንዳንዱ የፋሽን ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። አንዳንድ ጊዜ ወደ ቡቲኮች ጎራ ብለን የሚያምር ልብስ ገዝተን እንመጣና ስንለብሰው ግን በእኛ ላይ የማያምር አይነት ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። አንዳንዴ ደግሞ እኛ አስጠልቶን የጣልነውን ለሌላ ሰው ሰጥተነው አሊያም ድንገት ካስቀመጥንበት አንስቶ ለብሶት ስናየው እስከዛሬ ያልታየን የልብሱ ውበት ይገለጥልና አዲስ ይሆንብናል። ስለዚህ በአንዱ እያማረ በሌላው ደግሞ ውበቱ የሚደበቅበት ምክንያት የሕጎቹ የስነ-ውበት ሚስጥር ነው።
ታዲያ እነዚህን ሕጎች በመከተል የእኔን የውበት ቁልፍ እንዴት ነው ላገኘው የምችለው አሊያም የማውቀው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። ነገር ግን ምላሹ ቀመር አሊያም ስሌት አይደለም። ይህን ለማግኘት ስለ ተፈጥሮአዊ የቀለማት ውህደት በጥቂቱም ቢሆን ማወቅን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል በእነዚህ ሕጎች ውስጥ የቀለማት ሕግጋቶች ይገኙበታል። ቀይ ሰው ከወገብ በላይ ቀይ ቀለም ያላቸውን አልባሳት ባይለብስ ይመከራል። የፊቱና የልብሱ ቀለም በሚመሳሰልበት ወቅት የሰውየው መልክ ይደበቃል አሊያም የልብሱ ውበት ይደበዝዛል።
ይሄ ደግሞ ለእይታ የማይማርክ ገጽታን ያጎናጽፋል። እግረ ቀጭን የሆኑ ሰዎች ከቁንጣና በጣም ጠባብ ከሆኑ አልባሳት ይልቅ ሰፋ ያሉ ሱሪዎችን ቢያዘወትሩ የተሻለ የውበት ገጽታ ይኖራቸዋል። ሌላው ደግሞ ሱሪ፣ ጫማ፣ ሸሚዝ፣ ኮት ወዘተ..የምንጠቀምበት መንገድ በራሱ እይታዊ ውበትን መፍጠር ይችላሉ። ምን አይነት ሱሪ ከምን አይነት ጫማ ጋር ብንለብሰው የተሻለ ውበት ይኖረዋል…ለመረጥነው ሱሪ አሊያም ሹራብ ከቀለማትም ሆነ ከሌሎች ነገሮች አንጻር የተሻለና አብሮ ሊሄድ የሚችል ነገር መምረጥ ከቻልን አለባበሳችንም ጥሩና ያማረ መሆን ይችላል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት በአንድ ላይ መሰባጠራቸውና ከላይ እስከታች የተሰባጠሩበት መንገድ ለእይታ የተለየ ውበትን ይፈጥራሉ። ነገር ግን ቀለማቱ ለየብቻ ቢሆኑ አሊያም ቅደም ተከተላቸው በእንዲህ አይነት መልኩ ባይሆን ኖሮ ያንን ውበት ላናየው እንችላለን።
የምንከተላቸው ፋሽኖች ስኬታማና ሁሌም ተመራጭ ለመሆን ሁሌም የራሳችንን ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። ስታይሎቻችን የተፈጥሮ ውበታችን አጉልተው የማውጣትም ሆነ የመደበቅም ኃይል አላቸው። አንዲት ጸጉሯ ከፊት ገባ ያለ ቆንጆ ሴት ልጅ፣ ጸጉሯን ሹርባ ብትሰራው የውበት ገጽታዋን ሊያበላሽና ቁንጅናዋን ሊሰውረው ይችላል። ነገር ግን ከዚህ ይልቅ የጸጉሯ ስታይሏ ፓንክ ቢሆን የተሻለ ይሆናል። ጸጉሯን ወደፊት በመድፋት ገባ ያለውን ክፍል የሚሸፍንላትን ስታይል በመጠቀም በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋ የመጣባትን ምልጥና ለሱ በሚመጥነው ፋሽን ክፍተቱን ልትሞላው ትችላለች። አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ጸጉራቸው መመለጥ ሲጀምር ኮፊያ ያዘወትራሉ። ምልጥና ተፈጥሮ ያመጣችብን መጥፎ ነገር መስሎ ሊሰማንና ልናፍርበት እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ተፈጥሮ ለአንዳንዶቹ ውበትና የሚያምር ገጽታን አላብሷቸው እንመለከታለን።
እዚህ ጋር ከላይ ያነሳነውን የሰውነት ቅርጽ የምትለዋን የስነ-ውበት ሕግ እናነሳታለን። ምልጥና የሚያምርባቸውና የማያምርባቸው እነማን ናቸው ካላችሁ፤ ምላሹ የሚገኘው ሰዎቹ ባላቸው የራስ ቅልና የፊት ቅርጽ የሚወሰን ይሆናል። ሁል ጊዜ ባይሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ ትልቅ የራስ ቅል ያላቸው ሰዎች እምብዛም ጸጉር ላያምርባቸው ይችላል። በሴቶቹ ዘንድም ከጸጉር ይልቅ የጸጉር ቁርጥ የሚያምርባቸው እንዳሉ አስተውለን ሊሆን ይችላል። በዚያው ልክ ደግሞ ጸጉራቸውን ከመቆረጥ ይልቅ ሲያሳድጉ፣ ሹሩባና የመሳሰሉትን የጸጉር አሰራሮች ሲከተሉ የሚያምርባቸውም እንዲሁ ሞልተዋል። ይህን ሁሉ ምሳሌዎችን የማነሳው እንዲህ እንሁን ለማለት ሳይሆን ላለን ተፈጥሮ ምን አይነት የፋሽን ሳይንስን መከተል አለብን የምትለዋን ሀሳብ ጠብ ለማድረግ ያህል ነው። ስለዚህ በፋሽኖቻችን ውስጥ ውበትን ለመፍጠር በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁል ጊዜም ተፈጥሮአችንን ያማከሉ መሆን አለባቸው።
ፋሽን ጥበባዊ ሳይንስ እንደመሆኑ የፋሽን ተከታዮች ስንሆን ደግሞ አስቀድመን ሳይንሱን ልናውቅ ይገባል። በሳይንሱ ውስጥ ያሉት እነዚህ ሕጎቹም ከሰው ሰው እንደሁኔታው የሚለያዩ ናቸው። እነዚህን ነገሮች ለማወቅ ማስተዋልን እንጂ ብዙ ማሰብም ሆነ መጨነቅና መጠበብ የሚጠይቁ አይደሉም።
ምናልባትም አብዛኛዎቹ የምናውቃቸው ነገር ግን የማናስተውላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም ሰው ቆንጆና ውብ ሆኖ መታየት ይችላል። ሁሉም ሰው ደግሞ የራሱ የሆኑ የውበት ምንጭና ሊከተላቸው የሚገባው የራሱ የሆኑ ስርዓቶች አሉት። ትልቁ ነገር ላለን ነገር የሚሆን የራሳችንን መንገድ መፈለግ ነው። ታዲያ እኛ የምንወደውን ብቻ ሳይሆን እኛን የሚመስለውን መርጠን እንከተል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም