“የሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ ነው” – አቶ ያለው ከበደ

– አቶ ያለው ከበደ የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል የሕዝብ ግንኙነት፣ አጋርነት እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር

ከ129 ዓመታት በፊት፤ በ1888 ዓ.ም ከዓድዋ ተራሮች ሰማይ ስር የሀገራቸውን ሉዓላዊነት፤ ከነሙሉ ማንነቱ ለማስጠበቅ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ የኢትዮጵያ ልጆች ተሰበሰቡ:: እናም በጋራ የኢትዮጵያውያንን አንገት ሊያስደፋ የመጣውን ኃይል በመመከት ለመላው ጥቁር ሕዝብ የድል ብስራት ዓድዋ! ብለው አበሰሩ::

ከዚያ ጊዜ በኋላ ዓድዋ የቀኝ ተገዢዎች ልብ በማሞቅ፤ ለነጻነት መታገልን አስተማረ:: በወቅቱ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ባይኖራትም፤ ለሀገሩ ክብር ወደ ኋላ የማይለው ትውልድ “ሆ!” ብሎ በመውጣት በኢትዮጵያ በኩል 100 ሺህ ሰራዊት ተሰለፈ::

ከጣሊያን በኩል ደግሞ 20 ሺህ ሰራዊት ተሰልፎ ነበር:: በጦርነቱም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በሀገር ፍቅር ስሜት በመነሳሳት፤ የአካባቢውን መልክዓ ምድር በመረዳት እና ያላቸውን የጦር መሳሪያ በአግባቡ በመጠቀም ስድስት ሰዓት በፈጀ ጦርነት ድል ተቀዳጁ::

የዛሬው የወቅታዊ እንግዳችን፤ የግሎባል ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል የሕዝብ ግንኙነት፣ አጋርነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በተጨማሪም፤ የአፍሪካ ባሕል እና እሴቶች ተመራማሪ አቶ ያለው ከበደ ናቸው:: ከእርሳቸው ጋር በነበረን ቆይታ ስለ ዓድዋ የድል ታሪክ፣ በወቅቱ ስለነበረው አንድነት እና ስለባሕር በር አንስተናል::

አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ እና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ያለው አስተዋፅኦ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ያለው፡– ዓድዋ የሚገለጸው በተለያየ መልኩ ነው:: የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የነጻነት መሰረት የተጣለበት ነው:: ዘመናዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ከዛ በኋላ የተቀረጸ በመሆኑ፤ ዓድዋ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንም መሰረት ነው::

ሌላኛው የዓድዋ ድል በዘመናዊ መንገድ ሀገርን የመከላከል እና የሉዓላዊነት ትርጉም በወጉ የጸናበት ነው:: በዚህም በሀገራችን የመከላከል ታሪክ ውስጥ ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት የተመሰረተበት ነው:: ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያላት ቦታ የታየበት እና በዓለም ላይ ያሉት ጥቁሮች የነጻነት ተስፋ የተንጸባረቀበት ነው:: ስለዚህ የአንድነት፣ የሕብረት ማሳያና እና ለመጀመሪያ ግዜ በዘመናዊ መልክ አዋጅ ታውጆ የሀገርን ሎአላዊነት ከጠላት ለመከላከል መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው::

እንደ ሀገር ከዓድዋ በፊት ብዙ ጦርነቶችን አካሂደናል:: አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ያደረጉት፣ አፄ ዮሐንስ ከማሀዲስቶች ጋር ያደረጉት እና ቀደም ብሎም በዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል:: ነገር ግን የዓድዋ ጦርነት ልዩ ነው:: ልዩ የሚያደርገው አንደኛ ጠቅላላ እንደ ሀገር ከጫፍ እስከ ጫፍ በቡድን ለጦርነት የወጣንበት ነው::

ሌላው የዓድዋ ጦርነት ለጣሊያን ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ፤ ጣሊያንኛ ተናጋሪ እንሆን ነበር:: የራሳችን ጽሁፍ አይኖረንም ነበር፤ ፍራንኮ ፎን ሀገሮች ቋንቋ አላቸው፤ ነገር ግን ጽሁፍ የላቸውም:: ቀደም ብሎ ነበራቸው፤ ነገር ግን በቀኝ ግዛት ጠፍቷል:: አንግሎ ፎን ሀገሮችም ብዙ ቋንቋ አላቸው፤ ግን እነሱም ጽሁፍ የላቸውም:: ለእኛ ዓድዋ ማለት ጽሁፋችን፣ የቀን እና የዓመተ ምህረት አቆጣጠራችን ማለት ነው::

በአውሮፓ አንድ ሴት ስታገባ ቤተሰቧ ባለቤቷ ተደርጎ ስለሚቆጠር የምትጠራው በባሏ ስም ነው:: የአፍሪካ አገሮችም በእነሱ ስለተገዙ አጠራራቸው ተመሳሳይ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ቀጥታ መስመሩን ጠብቆ ይሔዳል:: ይህ ሁሉ የተጠበቀው በዓድዋ ነው:: ነገር ግን ይህንን ሁሉ አንወያይበትም::

በዚህ ዓመት (ግሎባል ብላክ ሄርቴጅ ኤዱኬሽን ሴንተር) ተቋቁሟል:: ይህን መክፈት ያስፈለገው ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ማዕከል እንድትሆን ነው:: ይህ ማዕክል አሁን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ተሰጥቶት እየሰራ ነው:: ስለዚህ ዓድዋ ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ቅርስ ነው:: ዓላማችን ዓለም ጥቁር ሕዝብን ማክበር አለበት የሚል ነው:: ይህንንም ሀሳብ አሁን ላይ ለፓርላማ ያቀረብን ሲሆን፤ ቀጣይ ዓመት ደግሞ ለአፍሪካ ሕብረት የሚቀርብ ይሆናል::

በተጨማሪ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ቅራኔን ወደ ኋላ ትተው ጠላትን መከላከል የሚቻል መሆኑ ያረጋገጥንበት ነው:: ስለዚህ ዓድዋ አሁን ላለነው ማንነታችን ሁሉ መሰረት የሆነ ነው:: በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቦታ እንዲኖራት እና የዓለም ሀገሮች ከዓድዋ በኋላ ዲፕሎማሲ እንዲመሰርቱ አስችሏል::

ቀደም ብሎም ከሀገራት ጋር ግንኙነት የነበረ ቢሆንም፤ መደበኛ ዲፕሎማሲያው ግንኙነት የተጀመረው የዓድዋ ድልን ተከትሎ ነው:: ዓድዋ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የተጀመረበት ነው:: የዓድዋ ጦርነት ከተቋጨ በኋላ ሌሎች ሀገሮች ለኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ሰጥተው፤ ጣሊያንን የማይወዷት ሀገሮች ሁሉ ግንኙነት የመሰረቱበት ነው:: ዘመናዊ የመከላከያ መስሪያ ቤት የተቋቋመው ከዛ በኋላ ነበር::

አውሮፓውያኑ እያደጉ መሆናቸው ይታወቅ ስለነበር እኛም እንደነሱ ማደግ አለብን የሚለው መንፈስ የመጣው በዓድዋ ጦርነት ማግስት ነው:: ከጦርነቱ በኋላ ወደ ልማት ተገባ፤ ስለዚህ ድሉ ለልማት መሰረት የሆነ እና ለዘመናዊ ስርዓት ግንባታ አንኳር መሰረት የጣለም ነው:: ዓለም ላይ የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት የተጣለበት ነው:: በዚህም ዓድዋ የፓን አፍሪካኒዝም የተጀመረበት እና የመንግሥት ስርዓት ግንባታዎች ወደ ዘመናዊነት የተቀየረበት ነው::

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረው አንድነት እና መተባበር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ያለው፡– በኢትዮጵያ ከዓድዋ በፊት የነበሩ ጦርነቶች በተካሄዱበት ጊዜ ብዙ የውስጥ ችግሮች ነበሩ:: ከዘመነ መሳፍንት ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች የመጡበት፣ ንጉሰ ነገስቶች የሚገዙበት እና ብዙ ንጉሶችም የነበሩበት ነበር:: እናም ቀደም ሲል ከነበሩ ጦርነቶች ብዙ ትምህርት ተወስዶ፤ በዓድዋ ጊዜ አጠቃላይ የነበረው ጦርነት ማንንም የማይምር ስለሆነ እና ከቀደመው ልምድም ስለተወሰደ ሁሉም ሰው ያለውን ልዩነት ትቶ አዋጁን ሰምቶ ሊወጣ ችሏል::

የዓድዋ ጦርነት አዋጅ በጣም የሚገርም ነው:: ንጉሱ ያሉት ሁሉንም “ምሬያለው ” ነው:: ምክንያቱም ቀደም ብሎ ልዩነት ስለነበረ ነው:: በወቅቱ በወጉ ክርክር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ ስላልነበረ የጥቅም ልዩነት ነበር:: የአገዛዝ፣ የግብር እና ሌሎች ልዩነቶች ስለነበሩ፤ ይህን ተከትሎ በጣም ብዙ ችግሮች ነበሩ::

በጦርነቱ ወቅት ሁሉም የነበረውን ልዩነት ትቶ በጋራ ጉዳይ ላይ በአንድ የተቆመበት ነው:: ዓድዋ የውጭ ኃይል ሲመጣ የግል ጉዳይ ተትቶ፤ የጋራ ጠላትን ከመከትን በኋላ እንቀጥላለን በሚል፤ በአንድነት የተቆመበት ነው:: በዚህም የኢትዮጵያውን የአንድነት ስነ-ልቦና የተረጋገጠበት ነው:: ምንም አይነት ልዩነት ቢመጣ፤ የውጭ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያውያን አንድ እንደሚሆኑ ያረጋገጡበት ታሪክ ነው:: ስለዚህ ዓድዋ ለእኛ የአንድነት፣ የይቅርታ፣ ቅራኔን የመፍታት ምሳሌ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ከነበረው አንድነት እና መተባበር የአሁኑ ትውልድ ምን መማር አለበት?

አቶ ያለው፡- እንግዲህ የአሁኑ ትውልድ ማየት ያለበት በሶስት መንገድ ነው:: አንደኛ የዓድዋ ታሪክ አሁን ላለው እና ወደፊት ለሚመጣው ኢትዮጵያዊ፤ የነጻነት እና የአይበገሬነት ስንቅን ነው:: ኢትዮጵያዊ ለሆነ ግለሰብ የትም ዓለም ቢሄድ የአባቶቹን ታሪክ እየዘከረ የሚኖርበት፤ ነጻነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ፤ እናም ለእዚህ ነጻነት ሲሉ እራሳቸውን መስዋዕት ለአደረጉ አባቶች ክብር የምንሰጥበት ነው:: አሁን ላለን የነጻነት መንፈስ በጣም ትልቅ እና ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው::

ዓድዋ እና ኢትዮጵያዊነት አንድ ናቸው:: ኢትዮጵያዊነት ዓድዋ ነው፤ ዓድዋ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው:: በዚህም ዓድዋ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያውያን ያላቸው ግምት መሰረት የተጣለበት እና ሌሎች ጥቁሮች ነጻነትን በእኛ ውስጥ እንዲያዩ ያስቻለ ነው:: የጥቁር ሕዝቦች ችግር ምን እንደሆነ፤ ሰው ሊረዳው የሚችለውም ከሀገሩ ወጥቶ በሌላ የዓለም ሀገር ላይ ሲኖር ነው::

አሁን ደግሞ ዓለም ሌላ ፈተና ውስጥ ገብቷል:: ቀደም ብሎ የነበረው የዓለም ስርዓት ፈርሶ አዲስ እየተሰራ

ነው:: በዚህን ጊዜ ዓድዋ፣ ኢትዮጵያዊነት እና የነጻነት መንፈስ መነሻ አድርገን በኢኮኖሚ ለመበልጸግ መሥራት ያስፈልጋል:: የዚን ጊዜ ያስጠበቅነው የፖለቲካ ነጻነታችንን ነው:: መተባበር ለፖለቲካ ነጻነት ብቻ ሳይሆን፤ ለኢኮኖሚ ነጻነትም የሚጠቅም ነው:: ዓድዋ ለእኛ ቱሪዝም ነው፤ ዓድዋ ለእኛ የባሕል ማሳያ ነው:: ዓድዋ ለእኛ የጥረት ምሳሌ ነው:: በአጠቃለይ ዓድዋ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ገንዘብ ነው::

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌሎች አፍሪካውያን በዓድዋ ድል በጣም ይነቃቃሉ:: የዓለም ጥቁር ሕዝቦች በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚያዩት በዓድዋ ነው:: ስለዚህ አሁን ላለው ትውልድ ኢትዮጵያዊነት እና ዓድዋ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው:: ሆኖም ያለፍንበት የሀገራችን ታሪክ በጣም ውስብስብ ነው:: ዓለም አቀፍ ወዛደራዊነት የሚባል በ “ኮሚኒዝም” ስርዓት ውስጥ ያለፍን ዜጎች ነን:: በዚህም እንደ ዓድዋ አይነት ያሉ ታሪኮች እየተረሱ ቆይተዋል:: በተጨማሪ ዓድዋ ጎልቶ እንዳይወጣ የሚያደርጉ ብዙ ችግሮች ነበሩ::

ዓድዋ የግለሰብ፣ የቡድን እና የመላው ጥቁር ሕዝብ ነጻነት ማለት ነው:: ስለዚህ የአሁኑ ትውልድ ዓድዋን በደንብ እንዲረዳው በትምህርት ቤት እና በተለያዩ መንገዶች ትምህርት መስጠት አለበት:: በትምህርት ስርዓቱ የተጻፈው ስለአንደኛው የዓለም ጦርነት፣ ስለሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና ከጦርነቱ በኋላ ስለነበሩ ነገሮች ነው:: የእኛ የትምህርት ስርዓት እራሱ ችግር ያለበት ነው:: ሀገር በቀል እውቀት በሙሉ ተረስቶ የምዕራባውያን ትረካ የትምህር ስርዓታችንን ከላይ እስከታች ወሮታል::

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በተደረገ ጊዜ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ነበረች:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜም ጣሊያን አርባ ዓመት ቆጥሮ መጥቶ ጦርነት ላይ ነበርን:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓለም ታሪክ ተነጥሎ አይታወቅም:: እርሱ ብቻ አይደለም፤ የዓድዋ ጦርነት አባይን የመቆጣጠር አጀንዳ የነበረበት ነው:: አሁን ጥናቶች እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያን የመውረር ብቻ ሳይሆን ናይልን የመቆጣጠር አጀንዳ በውስጡ የያዘ ነበር::

የምዕራባውያኑ እውቀት በትምህርት ስርዓቱ ገብቶ፤ የእኛ ሀገር በቀል እውቀት እየቀጨጨ ነው:: በዚህም አዲሱ ትውልድ አይፈረድበትም:: በአንደኛው የዓለም ጦርነት ስለጀርመን፣ ስለሩሲያ የሚያጠና ሕዝብ ስለሆነ፤ ከዛ መላቀቅ አለበት:: ትምህርቱ ሀገር በቀል እውቀት ላይ፣ እምነት ላይ የተመሰረተ እና እኛ ማን ነን? የሚለውን ማስረዳት የሚያስችል መሆን አለበት:: ስለዚህ ዓድዋ የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚያስረዱ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው::

በምዕራባውያን ታሪክ አብዛኛው የጦርነት ታሪክ፤ የወንዶች የጦርነት ታሪክ ነው:: ዓድዋ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ የሴቶች ጦርነት ጭምር ነው:: በየትኛውም ዓለም በሴቶች የተመራ ጦርነት አልነበረም:: በዓለም ታሪክ ውስጥ ሴቶች አዋጊ ሆነው የተዋጉበት ጦርነት ቢኖር ዓድዋ ነው:: የጦር ሜዳ እቅድ በመንደፍ ሴቶች የተሳተፉበት በመሆኑ፤ ዓድዋ የሴቶች እኩልነት የተረጋገጠበት፤ ስለዚህ የድሉ ታሪክ የሁሉም ነገር መገለጫ ነው:: ግን ይሄ በወጉ ለአሁኑ ትውልድ አልተነገረም:: ምናልባት አሁን ጥሩ እየሆነ ያለው የማሕበራዊ ሚዲያ ታፍኖ የነበረውን የዓድዋ ታሪክ፤ ግለሰቦች እየገለፁት በመሆኑ ነው::

የሚዲያው መሳሪያ በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ ስላለ በግለሰብ ደረጃም እየተሰራ ነው:: እንግሊዝ ሀገር 33 ዓመት በኖርኩበት ጊዜ፤ ኢትዮጵያውያን ተሰብስበን በየዓመቱ ዓድዋን እናከብራለን:: ዓድዋን በለንደን ጎዳናዎች ላይ እናከብራለን::

በቀጣይም ዓድዋን በወጉ ለትውልዱ ለማስረዳት ዘጋቢ ፊልም መሠራት አለበት:: የሴቶችን፤ የሃይማኖት አባቶችን፣ የወጣቶችን እና የሽማግሌዎችን ድርሻ ለብቻ መስራት ያስፈልጋል:: ዓድዋ ጸሎት ምን ያህል ኃይል እንዳለውም የሚያሳይ ጭምር ነው:: የዛኔ የተደረገው አዋጅ በጸሎት መርዳትንም ያካተተ ነው:: አዋጁ “ምትችል በጉልበትህ፤ ማትችል በጸሎትህ እርዳኝ” የሚል ነበር:: ስለዚህ ዓድዋ እንደዚህ አይነት ማሕበራዊ እሴቶቻችን ጎልተው የወጡበት እና ኃያል የሆኑበት ነው::

በሂደት ዘመናዊ የትምህርት ስርዓት ተባለና የነበረን እሴት እየተሸረሸረ መጣ:: የመተባበር አንድነታችን ዞሮ ዞሮ አደጋ ላይ ወደቀ:: አሁን ባለንበት ዘመን የብሔር ፖለቲካ መጣ:: አዲስ የተፈጠረ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያ ጊዜ አይዶሎጂ አልነበረም:: አሁን ግን ዓድዋ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ለመሻር ስንቅ ይሆነናል::

አሁን ላይ የዓድዋ ምሳሌ ብዬ የምወስደው የዓባይ ግድብን ነው:: የሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ ነው:: ኢትዮጵያውያን ለዓድዋ በጋራ እንደዘመቱት በኢኮኖሚው ዘርፍ ለሕዳሴ ግድቡ በተመሳሳይ ርብርብ አድርገዋል::

ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት በሆነው ዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ገንዘብ ጠይቃ ተከልክላለች:: ዓለም ባንክ እና ሌሎች የገንዘብ ተቋማት የተቋቋሙት ሀገሮች የሚሰሩትን የልማት ሥራ ለማገዝ ነው:: ነገር ግን እኛ ገንዘብ እንዳናገኝ ተከልክለን፤ በመሰረትነው ዓለም አቀፍ ተቋም ብንከዳም፤ አሁንም በድጋሚ ልክ በዓድዋ እንደሆነው ኢትዮጵያውያን ከላይ እስከታች ብሔር ሳይወክለን፤ ቋንቋ ሳይገድበን የአባይ ግድብን ለመገንባት ቻልን::

ትውልዱ የመተባበር አቅሙን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሳይቷል:: ስለዚህ እሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ወደፊት ዓድዋን የበለጠ እያጠናከሩ፣ ለሕዳሴ ግድብ የተደረገውን ርብርብ መሰረት አድርጎ በኢኮኖሚው ወደፊት አብሮ መስራት ያስፈልጋል:: በተለይ በአፍሪካ እና በአካባቢያችን ላይ ጠንክረን እንድንሰራ ማድረግ ይቻላል::

አዲስ ዘመን፡- የኢጣሊያን ወረራ አባይንም የመቆጣጠር አጀንዳ እንደነበር አንስተዋል:: አጀንዳ የነበረው እንዴት ነበር?

አቶ ያለው፡- ዓባይን የመቆጣጠር ጉዳይ ፖለቲካ ነው:: ከዓድዋ በፊት ዓባይን ለመቆጣጠር ከግብጾች፤ ማሀዲስቶች ጋር ጦርነት ተካሂዷል:: ጦርነት የተካሄደው ሰሀቲ ላይ ከግብጾች ጋር ነው፤ አፄ ዮሐንስ አንገታቸው የተቆረጠው ከማህዲስቶች ጋር በነበረው ጦርነት ነው::

ግብጾች መጀመሪያ ምጽዋን ወረው ተሸንፈው ሄደዋል:: በኋላ ደግሞ ከማሃዲስቶች ጋር መጡ:: በዚህም ዓላማቸው የነበረው ዓባይን መያዝ ነው:: በኋላ እነሱ ሳይችሉ ሲቀሩ ከጣሊያን ጋር በመተባበር እና ጣሊያኖችን በመገፋፋት ጥረት አድርገዋል:: በዚያ ጊዜ ግብጽ ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት እየወጣች ስለነበር፤ ከጣሊያን ጋር ሆነው ዓባይን ይቆጣጠራሉ ማለት ነው::

አዲስ ዘመን፡- ዓድዋ ስናከበር የድል ቀን ብለን ነው እንጂ የነጻነት ቀን ብለን አይደለም:: የሁለቱ ልዩነት ምንድነው?

አቶ ያለው፡- ድል እና ነጻነት ሁለቱ የተያያዙ ነገሮች ናቸው:: ጠላትን ድል ማድረግ ማለት ነጻነታችንን የጠበቅንበት ማለት ነው:: ጣሊያን 40 ዓመት ጠብቆ መጥቷል:: አምስት ዓመት ለመግዛትም ችሏል:: ነገር ግን የቀድሞ የዓድዋ ትግል ስለቀጠለ አልተሳካም:: በዚያ ጊዜ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መስርታ ነበር:: ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ላይ ታውጆ ስለነበር፤ ኢትዮጵያ ለመቀራመት ፈረንሳይ፤ ጣሊያን እና እንግሊዝ ስምምነት ነበራቸው:: ልክ ያንን ሲያደርጉ፤ ሂትለር ጦርነት አወጀ:: በወቅቱ ደግሞ ጣሊያን ኤርትራ ላይ ስለነበረች ኢትዮጵያን ለመጠቅለል አስልታ መጣች::

ከዚያ ግን ጀርመን ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ሲመታ፤ ሞሶሎኒ ለሂትለር እጁን ሰጠ:: እናም በዚያ ምክንያት እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ኢትዮጵያን ረዱ:: ሞሶሎኒ ስለከዳቸው ሁለቱ ተባብረው ኢትዮጵያን ለመርዳት መጡ:: በዚያ ምክንያት የእንግሊዞች ትምህርት ቤት ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከፈተ፤ ኮሎኔል ሳንፎርድ የተከፈተውም በወቅቱ ስላገዙን ነው:: ጀርመን አውሮፓን ባትወር ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር:: ቀኝ ገዢዎች ይከፋፈሏት ነበር:: ስለዚህ በተዘዋዋሪ ጀርመንም ባለውለታችን ናት::

አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ሙዚየም መገንባቱ ኣድዋን በአግባቡ እየተጠቀምንበት ነው ብሎ ለማንሳት ያስችላል?

አቶ ያለው፡– እጅግ በጣም! የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከዚህ ዘመን በኋላ ወቅቱን ጠብቆ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባቱ የአንድነታችን ማሳያ ነው:: በፊትም ቢሆን በውክልና ስንጠቃ ነበር:: አብዛኛው የተማረው ሕዝብ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካኝነት፤ በዲቪ፣ በጋብቻ እና በሌሎች ሁኔታዎች ሀገሩን ጥሎ ስለሄደ ስልጣኔ ከየት ይመጣል? የተማረው ሕዝብ እየለቀቀ ሲሄድ ሌላኛው እስኪማር ድረስ ስልጣኔ የሚባል አይኖርም::

አሁን የነበረው አሰራር ተቀየረ:: በዚያ ጊዜ በርካታ ሕዝብን በስደት እንዳልወሰዱ አሁን ደግሞ ታቡ ሆኗል:: እንደ ዓድዋ አይነት ድሎች ብቅ ማለት ጀመሩ፤ ሕዝቡም ሀገር በቀል እውቀት ላይ ማተኮር ጀመረ:: አሁን ዓድዋን የምንጠቀመው በሰብል ምርት እና በሌሎች እድገቶች ነው:: ለእዚህም ተግባራዊ ማሳያ የዓባይ ግድብ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሕልውና እና እድገት ምን አስተዋጾኦ ይኖረዋል?

አቶ ያለው፡-ኢትዮጵያ አሁን ዋና አጀንዳዋ የባሕር በር ማግኘት ነው:: በየሀገሩ አፍሪካን የሚያገናኝ አውሮፕላን አለን:: አንድ ነገር ቢሆን፤ ሌሎችን ድረሱልን ልንል ነው? ከ30 በላይ የኢትዮጵያ መርከቦች የሚጠገኑት በየሀገሩ ሄደው ነው:: ለእዚህም መፍትሔ ያስፈልገዋል:: ስለዚህ የባሕር በር አስፈላጊ ነው::

ሌሎች ጎረቤት ሀገሮቻችን እኮ እስካሁን ባለመጠ የቃችን ይገረማሉ:: ምክንያቱም እነሱም በኢትዮጵያ ቦታ ቢሆኑ መጠየቃቸው አይቀርም:: ኢትዮጵያ የባሕር በር ስትጠይቅ በጎረቤት ሀገራት ፖለቲከኞች አካባቢ አንዳንድ ችግሮች ተፈጥረዋል:: ግን ሕዝቡ እስካሁን ባለመጠየቃችን ተገርሟል::

ከሩቅ ሀገራት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ጃፓን መጥተው ቀይ ባሕር ላይ ጦራቸውን ሲያሰፍሩ፤ ኢትዮጵያ ቅርብ ሆና የባሕር በር አለመጠየቋ የጎረቤት ሀገራትን አስገርሟል:: ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ በቀጣናው ያለውን ስጋት ያጠፋል:: ምክንያቱም እነሱም ኢትዮጵያ ጥያቄ ማንሳቷ እንደማይቀር ስለሚያውቁ ስጋት አለባቸው::

ጥያቄው የወደብ አይደለም፤ የባሕር በር ነው:: ወደብ አሁንም አላጣንም ካስፈለገ ከኬኒያ፣ ከሱማሊያ ኬላዎች መጠቀም ይቻላል:: እንዲያውም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሁለት የባሕር በር ነው:: ቀይ ባሕርን ብቻ ሳይሆን፤ ከሕንድ ውቅያኖስም የባሕር በር መጠየቅ ያስፈልጋል::

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

አቶ ያለው፡- በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ስለ ዓድዋ በዓመት አንድ ቀን ብቻ ሳይሆን፤ ወሩን በሙሉ መነገር አለበት:: በዚህ በኩል ሚዲያዎች በደንብ እንዲሰሩ እላለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ::

አቶ ያለው፡– እኔም አመሰግናለሁ::

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You