
ዜና ሀተታ
በመዲናዋ ከአንድ ሚሊዮን 253 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንደሚገኙ የትምህርት ቢሮው የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ያሳያል፡፡ ተማሪዎችን ከመደገፍ አንጻር ደግሞ ከ835 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የመመገብ ሥራ የሚሠራ ሲሆን፤ የደብተር እና የዩኒፎርም በሺዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ድጋፍ ይደረጋል፡፡
በእነዚህ የድጋፍ ሂደቶች በመጨረሻ ተማሪዎች የሚያመጡት ውጤት እና የሥነ-ምግባራቸው መሻሻል ትልቁና ዋነኛው ነገር ነው፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ደግሞ የክፍለ ከተማዎች፤ ወረዳዎች እና በየደረጃው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ኃላፊነታቸውን በአግባብ የመወጣት አቅም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ከተማሪዎች ውጤት ማሻሻል፣ የሪፎርም ሥራዎችን በብቃት ከመወጣት እና የትምህርት አካባቢን ምቹ ከማድረግ አንጻር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በየደረጃው ለሚገኙ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች የስድስት ወር አፈጻጸማቸውን በመገምገም እውቅና ሰጥቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የትምህርት ቤቶቹ እና የክፍለ ከተማዎቹ ተሞክሮ ምን ይመስላል፤ እንደ ሀገር ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን ምን መሠራት አለበት? በሚሉ ጉዳዮች እውቅና ያገኙ ትምህርት ቤቶች እና ክፍለ ከተማዎችን ተወካዮችን አነጋግሯል፡፡
ገላን የወንዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ዕርሰ መምህር አቶ ካሳሁን መርጋ እንደሚናገሩት፤ አዳሪ ትምህር ቤቱ ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን መቶ በመቶ ያሳለፈ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዚህ ዓመትም በቁልፍ ውጤቴ አመልካቾች እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የመዲናዋ የትምህርት ቢሮ በተለያየ መልኩ የግምገማ መስፈርቶችን በመያዝ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ የድጋፍ ሂደት ውስጥ ትምህርት ቤቱ ደረጃውን ያለቀቀ ሲሆን፤ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ የመጨረሻ ግምገማ ተደርጎ ከአዳሪ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያውን ደረጃ በማምጣት እውቅና እንደተሰጠው ያስረዳሉ፡፡
ትምህርት ቤቶች አመራራቸውን ይመስላሉ የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት፤ አመራሩ በግምባር ቀደም የሚመራውን ተቋም ቁርጠኛ ሆኖ ሊመራ ይገባል ይላሉ፡፡
የትምህርት ሥራ አንድ ጊዜ ብቻ ተሠርቶ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም፡፡ በሂደት ውጤት ለማምጣት የበርካታ ሰዎችን ርብርብ እና ቅብብሎሽ የሚጠይቅ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የተለያዩ አሠራሮች ሲዘረጉ የአመራሩ ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ፤ መምህራኑን እና ሠራተኛውን በማሳተፍ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት መቻሉን ያስረዳሉ፡፡
ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት መለወጥ የሚቻለው በትብብር፣ በቅንነት እና በእውቀት መሥራት ሲቻል ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ተጠያቂነት ያለው አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡ አዳሪ ትምህር ቤቱ ከዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ ነው እዚህ ሊደርስ የቻለው፡፡ እናም መተባበር ካለ የማይለወጥ ነገር የለም ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቡርቃዋዮ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ዕርሰ መምህር አቶ አዲሱ ግዛው በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ በበጀት ዓመቱ በተቀመጠው ምዘና መሠረት፤ አጠቃላይ ባስመዘገባቸው የተማሪዎች ውጤት እና በተሠሩ የለውጥ ሥራዎች ነው እውቅና ማግኘት የቻለው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ዋና ዕርሰ መምህሩ እንደሚሉ፤ ትምህርት ቤቱ ይህን እውቅና ለማግኘት የቻለው፤ የመማሪያ ግብዓቶችን በማሟላት፤ ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና የክፍለ ጊዜ ብክነት እንዳይኖር በመሥራት ነው፡፡ በተረፈ ደግሞ ተማሪዎች ማርፈድና መቅረትን ወደ ዜሮ ለማምጣት ተችሏል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ትምህርት የአንድ አካል ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ የጋራ ሥራ እስከሆነ ድረስ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት፤ ተማሪዎች ላይ ክትትል በማድረግ በትምህርት ሥርዓቱ ያጋጠመውን ስብራት መፈወስ እንደሚገባ ሃሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ ግርማ እንደሚሉት፤ በበጀት ዓመቱ ታቅዶ ወደ ሥራ ከተገባባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል እና የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ ነው፡፡
ይህን መሠረት በማድረግ ትምህርት ቢሮ በተለያየ ወቅት ክትትልና ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም የስድስት ወር አፈጻጸም በ11 ክፍለ ከተሞች ምን ይመስላል? የሚለው ግምገማ የተደረገ ሲሆን፤ ጽህፈት ቤቱ በግምገማው የተሻለ ውጤት በማምጣት ሁለተኛ ደረጃ ለመያዝ ችሏል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ክፍለ ከተማው ከሠራቸው ተግባራት በተሞክሮነት የተወሰዱት የሂሳብ እና የእንግሊዝኛ ትምህርት ስትራቴጂዎችን ወደ መሬት በማውረድ ተማሪዎችን በማጠናከር ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው፤ የሪፎርም ሥራዎችን ቆጥሮ በመረከብ ሠራተኛው አመራር ኖረም አልኖረም በአንድነት መሥራት በመቻሉ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ትምህርት ማህበረሰብ የሚገነባበት እንደመሆኑ፤ የሁሉ ነገር መሠረት ነው ሲባል ከቃል በዘለለ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በትምህርት ዘርፍ ያሉ ሥራዎች ሲሠሩ፤ ትውልድን እንደመሥራት መታሰብ አለበት፡፡ ልጆች አብዛኛውን ሰዓታቸውን የሚያሳልፉት በትምህርት ቤት ነው ያሉት፡፡
ሁሉም በትምህርት ዘርፍ የሚገኙ ባለድርሻ ተቋማት የተማሪዎች ውጤት ማሻሻል፣ የተማሪ ሥነ-ምግባር ማሻሻል እና ሰላማዊ የመማር ሁኔታ መፍጠር ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ልደታ ክፍለ ከተማ ሲታይ ትምህርት ቤቶቹ ማእከል ላይ እንደመሆናቸው ብዙ አሉታዊ ተጽእኖዎች አሉት፡፡ ይህን በማሸነፍ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በሚደረግ ጥረት ውጤት ለማምጣት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ከእኛ መውሰድ የሚቻለው በምን አይነት ሁኔታ ነው ተግዳሮቶችን መጋፈጥ የሚቻለው የሚለው እና በትብብር መሥራት መቻልን ነው ይላሉ፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም