“ህዳሴ ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት በ2017 ዓ.ም የስድስት ወር የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም እና በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል ።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከልም፣ በትግራይ ክልል እየታየ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ወደግጭት እንዳያመራ ምን እየተሠራ ነው ፣ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተነጋግሮ የመፍታት ባህል በማጎልበት በተሠሩ ሥራዎች እና የተገኙ ውጤቶችን ቢያብራሩልን?

ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከአሥር ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅዱ አንፃር ያላቸው አፈፃፀም ምን ይመስላል፣ በስድስት ወር ውስጥ የመንግሥት ወጪና ገቢ ምን ይመስላል፣ የባሕር በር ጥያቄ ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ምላሽ እንዲያገኝ የተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ ?

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ሕግ የማስከበር ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል፤ ሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ በመስጠትና ሁለቱንም አቀናጅቶ ከመተግበር አንጻር መንግሥት ምን እየሠራ ይገኛል ምንስ ውጤት ተገኝቷል?

የቤት አቅርቦቱ በአዲስ አበባ ውስጥ በ1997 ዓ.ም ጀምሮ ተደራጅተው ገንዘብ ሲቆጥቡ የነበሩ ነዋሪዎችም ሆኑ አጠቃላይ የቤት ፈላጊዎች ጋር እየተጣጣመ እንዲሄድ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?

ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የሀገራችን ከተሞች እየተሠሩ ያሉ የኮሪዶር ልማት ሥራ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና በኅብረተሰቡ ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዴት ተገምግሟል?

መንግሥት የኮሪዶር ልማት ሥራዎችን መሠረት ተደርገው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍና አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ምን እየሠራ ይገኛል? ታላቁ የህዳሴ ግድብ መቼ ይመረቃል የሚሉ ጥያቄዎች በዋንኛነት ተጠቃሽ ናቸው። እኛም ለነዚህ እና ለሌሎች ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡-

አመሰግናለሁ የተከበሩ አፈ-ጉባዔ! የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት ከእረፍት ቆይታችሁ እንኳን በሰላም ተመለሳችሁ! ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንድችል በድጋሚ ዕድል ስላገኘሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!

ከቀረቡት ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ በስድስት ወር አልፎ አልፎ በሰባት ወር መረጃዎች/ዳታዎችና ሪፖርቶች ላይ ተንተርሰው የቀረቡ ናቸው፣ የበለጠ ወቅታዊ የሆነ መረጃ እንዲሆን በአንዳንድ ጉዳዮች ተጠቃለው የቀረቡልኝን የስምንት ወር ሪፖርቶች እንደማጣቀሻ ልጠቀምባቸው እችላለሁ።

በመጀመሪያ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን አስመልክቶ መንግሥታችን የ10 ዓመት የልማት እቅድ ማዘጋጀቱ ይታወሳል፤ ከዚያ እቅድ የተቀዳ/ካስኬድ የተደረገ የአምስት ዓመት፣ የአንድ ዓመት፣ በየሴክተር እና ተቋማት ደግሞ ከዚያም ባነሰ ጊዜ የተግባር እቅድ ተዘጋጅቶ፤ እነዚያን አሰናስሎ በማሳካት ትልቁን እቅድ ከግብ የማድረስ ጥማት፣ ጉጉትና ትጋት እንዳለ ይታወቃል።

ይህንን እቅድ ስናዘጋጅ፤ በይሆናል የገመትናቸው አልፎ አልፎ ደግሞ ያልገመትናቸው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሀገር ደረጃም፤ በዓለም አቀፍ ሁኔታ ያጋጠሙ ቢሆንም፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ባለፈው ዓመት ከሰሐራ በታች ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት አራት ነጥብ ሁለት በመቶ እንደሚሆን ገምተው ነበር። ይሁንና በባለፈው ዓመት ሪፖርት እንደተመላከተው ኢትዮጵያ ስምንት ነጥብ አንድ በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች።

በዚህ ዓመት ከሰሐራ በታች ለሚገኙ ሀገራት የተሠጠው ግምት ከአምናው እምብዛም የራቀ ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ በስምንት ነጥብ አራት በመቶ ለማደግ አቅዳ ይህንን ለመተግበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

ባለፉት ስምንት ወራት የነበሩ የኢኮኖሚ እቅዶቻችን አፈጻጸም፤ እንደሚያመላክቱትም፤ በሚቀጥሉት ሁለትና አራት ወራት ይህንኑ ተግባር አጠናክረን መድገም ከቻልን፤ ዘንድሮ ካቀድነው ከስምንት ነጥብ አራት በመቶ በላይ ልናሳካ እንደምንችል ይጠበቃል።

ያለፉት ስምንት ወራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎቻችን በሙሉ በእያንዳንዱ አመላካች /ኢንዲኬተር/ በብልፅግና፣ በኢሕአዴግ፣ በደርግ፣ በሚባል ደረጃ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተወሰነ ደረጃ በሴክተር ለማንሳት፤ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አምስት ዋና ዋና ሴክተሮች አንደኛ የሆነው ግብርናን እንመልከት። የኢትዮጵያ ግብርና ከሌሎች ሀገራት የሚለየው አብዛኛው የእርሻ ማሳ የአነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሳ ነው። እርሻው ወደ ኮሜርሻል እርሻ ያላደገ በመሆኑ፤ ለውጥ ለማምጣት እነርሱን ማዕከል ያደረገ ጣልቃ ገብነት “ኢንተር ቬንሽን” ይፈልጋል።

ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ዘንድሮ ብቻ የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሰብል ሽፋን፤ ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 20 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ማደግ ችሏል። ይሄ ትልቅ እመርታ ነው።

ኩታ ገጠም የሚል እንቅስቃሴ መጀመራችን በግልጽ ይታወቃል፤ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የተሸፈነ ቢሆንም፣ ይህን አኀዝ ዘንድሮ ወደ 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል። የመሬት ሽፋን ብቻ ሳይሆን ኩታ ገጠምም በከፍተኛ ደረጃ እመርታ አሳይቷል።

ስንዴን ብቻ እንደ አንድ የሰብል ምርት ብንወስድ፤ በመኸር አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ለምቷል፤ በበጋ መስኖ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ታርሷል። በድምሩ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ መሬት በስንዴ ሰብል የሸፈነች ሲሆን፣ ከዚህም ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይጠበቃል።

ይሄ ሴክተሩን ለሚያውቁ ሰዎች ስንዴ ከውጭ ማስገባት የለባትም፤ ኢትዮጵያ ማምረት አለባት ብለው ለወሰኑ ሰዎች እንደ ተዓምር ሊወሰድ ይችላል። ይህ ስኬት ዛሬ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራች ሀገር አድርጓታል።

ይህ ጉዳይ የሚያማቸው፤ የሚያቀረሻቸው፤ የሚያቃጥላቸው ሰዎች ያሉ ቢሆንም፣ እውነታው ይሄ ነውና መዋጥ ይኖርበታል። በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች ዛሬ ኢትዮጵያ ናት።

በስንዴ ብቻ ሳይሆን በቡና፣ በሻይ፣ በቅባት እህሎች ያየን እንደሆነ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመጣው እመርታ ይበል፣ ይበርታ፣ ይቀጥል የሚያስብል ነው።

ለምሳሌ ቡና በለውጡ ማግስት 700 ሚሊዮን ገደማ ዶላር በዓመት ከቡና ኤክስፖርት እናገኝ ነበር፤ ያለፈው ዓመት ብዙ እመርታ የመጣበት ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ዓመት ስለሆነ ከቡና ኤክስፖርት አንጻር አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ የቡና ኤክስፖርት ተብሎ የተመዘገበ ነበር።

ዘንድሮ ግን አምና ያልገቡ ወደ ምርት ያልገቡ ቀድመን የተከልናቸው ቡናዎች ስለተጨመሩ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከቡና ኤክስፖርት ማግኘት ተችሏል።

የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ በመጣው የሕዝብ ቁጥር እና የቡና ፍጆታ ዝርዝር ጥናት ሳታካሂዱ በግርድፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቡና ፍጆታ እያደገ መምጣቱን መገመት አያስቸግርም።

የዛሬ አምስት ስድስት ዓመት ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር በዚህ ዓመት ከሞላ ጎደል ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ታደርጋለች ማለት ቡና ላይ ስር ነቀል ለውጥ መጥቷል ማለት ነው፤ የሚጨበጥ ውጤት መጥቷል ማለት ነው።

ከሁለት እጥፍ በላይ ኤክስፖርት በአንድ ማኅበረሰብ ማሳደግ የሚቻለው በዛው ልክ ያደገ ምርት ያለ እንደሆነ ብቻ ነው። ቡና ከሌላው ነገር የሚለየው በሀገር ወስጥም ከፍተኛ ተፈላጊ በመሆኑም ጭምር ነው።

በሻይ ምርት በቡና ልክ ለመናገር የምንችልበት ጊዜ ገና ቢሆንም በርካታ የኢትዮጵያ ገጠር አካባቢዎች ባሕር ዛፍ እያነሱ በሻይ ለመተካት እየተሠራ ያለውን ሥራ ለመስክ ጉብኝት ስትወጡ እንደታዘባችሁት እገምታለሁ፤ በጣም ተስፋ ሰጪ ሥራ እየታየ ነው።

ሻይን ከቡና የሚለየው፤ እንደቡና ለቅመን የምንሸጠው ሳይሆን የግድ ሂደት (ፕሮሰስ) ማድረግ የሚጠይቅ ስለሆነ በግብርናው ብቻ ሳይሆን “በአግሮ ፕሮሰሲንግ” ተጨማሪ ሥራዎች የሚጠይቅ ይሆናል።

በሩዝ በቅባት እህሎች በተለይም በሌማት አዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ አይደለም። ጅግጅጋ፣ ባሕርዳርም፣ አሶሳም ቢኬድ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ጥረት በእጅጉ ተስፋ ሰጭ ነው። በወተት፣ በእንቁላል፣ በሥጋ ምርት ኢትዮጵያ ቀድማ የጀመረችው እንቅስቃሴ ትክክለኛ እንደሆነ አሁን ዓለም ላይ ያለው የገበያ ቀውስ በራሱ ጥሩ አመላካች ሊሆን ይችላል።

በሌማትም፣ በስንዴም፣ በቡናም፣ በሻይም ኢትዮጵያ በቂ የሆነ ሥራ ሠርታለች ብለን ግን አናምንም፤ አስደናቂ እመርታ አለ፤ አንክደውም። እውነት ስለሆነ። ከዚያ በላይ ሊሠራ የሚገባው ሥራ ስላለ በቂ ነው ብለን አናምንም።

ተጨማሪ ጥረት፣ ትጋት እንደሚጠበቅብን እናምናለን። በተለይ መስኖን፤ በርካታ አነስተኛ ግድቦች ተገንብተዋል። በየቦታው እንደምታዩት በርካታ ግድቦች ተገንብተው፣ ካናል ተዘርግቶ በመስኖ ከዚህ ቀደም በሴፍቲኔት የምናቃቸው አካባቢዎችም ጭምር ምርት እያመረቱ ይገኛሉ።

ግን መስኖ ላይ የሚሠራው ሥራ ቀደም ሲል እንደተነሳው ተጨማሪ ጥረት፤ ተጨማሪ የፕሮጀክት አፈጻጸም እድገትን ይጠይቃል። መሬት ማስፋት፤ አሁንም ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ መሬት ለማስፋት ዕድል አላት። ያልታረሱ ቦታዎች በስፋት ስላሉ እነዚያን ማስፋት ያስፈልጋል። አሲዳማ መሬቶችን በኖራ ማከምና መልሰው ምርት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል።

ማሽነሪ መጠቀም በሚቻልባቸው አካባቢዎች ማሽነሪ ማስፋት ያስፈልጋል። በዚህ ዓመት ከ500 በላይ የሚሆኑ ለእርሻ ሥራ የሚሆኑ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተደርጓል። ለማሽነሪ የማይመቹ በተባሉ ቦታዎችም ሰፋፊ የእርከን ሥራዎች በመጀመራቸው የግድ ስንዴ ባይሆንም ፍራፍሬ ለዚያ የሚመቹ ምርቶች ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው።

ለምሳሌ በቅርቡ በምሥራቅ ሐረርጌ በነበረን ቆይታ እንኳን ሊታረስበት፤ ሊወጣ የሚያዳግትን ተራራ የሐረርጌ አርሶ አደሮች በእጃቸው ተዓምር ሠርተው የሚያስደንቅ የእርከን ሥራዎችን አሳይተዋል። እነዚያ የእርከን ሥራዎች አሳይተዋል፡፡ እነዚህ የእርከን ሥራዎች ከወዲሁ ውሃ መያዝ ጀምረዋል፤ እዚያ ላይ በርካታ ፍራፍሬዎች ይተከላሉ፤ ከነዛ ፍራፍሬዎች የደከመው አርሶ አደር እና ልጆቹ በሂደት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የግብርና ዘርፍ በዚህ ዓመት ሊያመጣ ከሚጠበቀው እድገት አንጻር በስምንት ወር ያየናቸው ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከግብርና ሴክተር ወጣ ብለን የኢንዱስትሪን ብንመለከት፤ ኢንዱስትሪ በግብርናው ልክ ውጤታማ እንዲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ ጥናቶች፣ ግምገማዎች ሲካሄዱ ቆይተው፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ደረጃ ‘ናሽናል ስትሪም” ኮሚቴ ተቋቁሟል።

የተቋቋመው ኮሚቴ ዋናው ሥራ ኢንዱስትሪን እንደ አንድ ምሰሶ፤ ከኢንዱስትሪ ባሻገር ደግሞ በንዑስ ሴክተር፣ በሴክተር፣ በፋብሪካ ደረጃ ምን አይነት ማነቆዎች እንዳሉ የሚለይና ድጋፍ የሚሰጥ ኮሚቴ ነው። ይህ ኮሚቴ ባለፉት አንድ ዓመት ገደማ ጊዜያት በሠራቸው ሥራዎች የለያቸው ዋና ዋና ማነቆዎች አንደኛው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ነበር።

ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚቀርበው የውጪ ምንዛሪ በበቂ ማቅረብ ባለመቻሉ በዘርፉ ሊገኝ የሚገባው ውጤት እንዲቀዛቀዝ አድርጓል። ያንን ለመቀነስ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል፤ ይህን ተከትሎም ከፍተኛ ባይባልም መሻሻሎች አሉ፤ አቅርቦት አድጓል።

ሁለተኛው ችግር የኃይል አቅርቦት ነበር። ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግር ነበረባቸው። ይህን ችግር ለመፍታት በእያንዳንዱ ፋብሪካና በእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ሥር ባሉ ሴክተሮች በተደረገ ጥናት መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የኢነርጂ አቅርቦት ችግር ተቀርፎላቸዋል። በዚህም በዚህ ዓመት ለኢንዱስትሪው ሴክተር ብቻ የቀረበው ኢነርጂ ከአምናው ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል። በአንድ ዓመት ከ50 በመቶ በላይ የኢነርጂ አቅርቦት ጨምሯል ማለት ይህ በየዓመቱ የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ የሆነ የኢነርጂ ዝግጅት እንደሚያስፈልግም ከወዲሁ ያመላክታል።

በሀገር ደረጃ ዘንድሮ 47 በመቶ ኢነርጂ ጨምሯል።

በኢንዱስትሪ ሴክተር ከዚያ ከፍ ይላል። በየዓመቱ ከ40 እስከ 50 በመቶ የኢነርጂ ፍላጎት እያሟሉ መሄድ ከፍተኛ የማመንጨት አቅም ይጠይቃል፤ ያለው ፍላጎት ሌሎች ሥራዎች መታሰብ እንዳለባቸው እግረ መንገዱን አመላክቷል።

በኢንዱስትሪ ሴክተር ከመሬት አቅርቦት ከግብዓት ጋር ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። የተከበረው ምክር ቤት፡- አንዳንድ በኢንዱስትሪ ሴክተር ስር ያሉ ሁነኛ ጠቃሚ የሸቀጥ ዓይነቶችን በተወሰነ አነሳለሁ።

ለምሳሌ ብረትን ብንወስድ ኢትዮጵያ “በፎርዋርድ ሊንኬጅ” ወይም ወደ መጠቀም ደረጃ ወዳሉ ብረት ሥራዎች ብረት አቅልጦ ለኢትዮጵያ ልማቶች የሚያስፈልገውን የብረት አይነት በማምረት ደረጃ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ሀገሪቱ አቅም ፈጥራለች።

በብረት ሴክተር ኢትዮጵያ አሁን ያላት ችግር “በኦር በአልትሜት” ጥሬውን ጨምቆ ለብረት ግብዓት ማዋል አለመቻል ነው። ከተለያየ ሀገር “እስክራፕ” ማግኘት ከቻልን ያንን ጨፍልቀን ለልማት የሚውሉ ብረቶች ማምረት የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ፈጥራለች።

ቀጣይ ትኩረት የሚሆነው ኦሩን እንዴት በሀገር ውስጥ በማምረት ሙሉ በሙሉ ከሀ እስከ ፐ የብረት ምርትና ግብዓት በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል ካሳሳን ትልቅ እመርታ ይሆናል።

ሲሚንቶ፤ እናንተም ከዚህ ቀደም እንዳነሳችሁት ከጥቂት ወራት በፊት ሲሚንቶ ከፍተኛ ችግር ነበር። አሁን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኤክስፖርት ጥያቄ እያነሱ ነው። ዋጋ መቀነሱ ብቻ ሳይሆን ምርቱ ከፍተኛ ስለሆነ ወደ ውጭ ወጥተን ብንሸጥ የሚሉ ጥያቄ እያነሱ ነው፡ መንግሥትም እየመረመረው ይገኛል።

ያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የቤት ፍላጎት ገና አዳጊ ስለሆነ ግንባታ ገና አዳጊ ስለሆነ ተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቋቋምና ያሉትን ማስፋት ላይ በተለይ በቅርቡ እንደሰማችሁት የዳንጎቴን አቅም በእጥፍ ለማሳደግ ሥራ ተጀምሯል።

ከእነዚህ ጋር የሚያያዝ በጣም አስፈላጊው አንዱ ነገር መስታወት ነው። መስታወት ማምረት ልክ እንደብረቱ በመቁረጥ ከዚያ ቅርጽ በማውጣት ደረጃ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። መስታወትን እንደብረት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥቂት የግል ባለሀብቶች የጀመሩት ሥራ በመንግሥት ድጋፍ አግኝቶ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ከተጠናቀቀ ከሲሚንቶውም ቀድሞ ሙሉ ለሙሉ መስታወት በሀገር ውስጥ ከጅምሩ እስከ መጨረሻ ምርት ማምረት የሚያስችል ዕድል እየተፈጠረ ነው።

ሴራሚክስ፣ ግራናይት እና ማርብል ሌሎች ናቸው። ኢትዮጵያ ያላት አቅም በቅርቡ ባደረግናቸው የመስክ ምልከታዎች በተለይ ሶማሌ ክልል ያየነው ግራናይት ምርት ማንም ሰው የምርቱን የመጨረሻ ደረጃ ምርት አይቶ ይሄ ከኢትዮጵያ ነው ቢባል ለመቀበል ይቸገራል። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም አላት። እነዚህን ምርቶች ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በቂ በሆነ ልክ ማምረት ከዚያም ባሻገር ሲል ለውጭም ገበያ ማዋል ይጠበቅብናል።

እነዚህ ያነሳኋቸው የብረት፣ የሲሚንቶና የመስታወት፣ የግራናይት፣ ሴራሚክስ ምርቶች በውጭ መመረታቸውና በውጭ ምንዛሪ ብቻ ማምጣታቸው ብቻ ሳይሆን ከባድ ስለሆኑ የሎጀስቲክ ሥርዓቱንም በእጅጉ የሚያውኩ ናቸው።

ብረት እንዲሁም አፈር /ሲሚንቶ/ ጭኖ ማምጣት፣ ድንጋይ ጭኖ ማምጣት ከባድ ስለሆነ እነዚህ በሀገር ውስጥ እያመረትን ስንሄድ፣ በቴክስታይል፣ በምግብ ማቀነባበሪያ ከጀመርናቸው ሥራዎች ጋር ተደማምሮ የኢንዱስትሪ ሴክተር በከፍተኛ ደረጃ ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

የማምረት አቅም ስንጀምር 47 የነበረው ዘንድሮ 61 በመቶ ደርሷል። ይህ በጣም ትልቅ እመርታ ነው፤ አሁንም ማደግ አለበት፤ ከነበርንበት አንጻር ኢንዱስትሪዎቻችን 61 በመቶ የማቅረብ አቅማቸው ተሻሽሎል። በዚህ ዓመት ብቻ ከ55 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል። ከ120 በላይ አዳዲስ ፋብሪካዎች አዳዲስ ፍቃድ አውጥተዋል። ይሄ ተደማምሮ ሲታይ ኢንዱስትሪው ልክ እንደግብርናው በዚህ ዓመት የተቀመጠለትን ግብ እንደሚያሳካ ሙሉ እምነት አለ።

በግብርናው እና በኢንዱስትሪው ከምናገኘው ውጤት በተጨማሪ የሰርቪስ ዘርፉን ደግሞ በከፊል ስንመለከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን እንዲሁም በመዳረሻ ብዛት፣ ኤርፖርቶችን አስመርቆ ሥራ በማስጀመር፣ የበረራ ምልልስ /ፍላይት ፍሪኬዌንሲ/ በመጨመር እድገት እያመጣ እንዳለ ታውቃለችሁ።

በዚያው ልክ ትርፋማነቱን ጨምሯል። በተለየ አሁን በአፍሪካ ትልቁን አየር ማረፊያ ኤርፖርት ለመገንባት ጥረት ጀምሯል። በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በሚቀጥሉት አምስት ስድስት ወራት አብዛኛው የዲዛይን የፋይናንስ ጉዳይ ከተጠናቀቀ ሥራው እንደሚጀመር ይጠበቃል።

ይህ ቅድም የተነሳው አንዱ ሀገራዊ ስትራቴጂክ ፕሮጀክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በፋይናንስ ደረጃ ከህዳሴ የሚበልጥ ይሆናል እንጂ አያንስም፤ እንደ አንድ ትልቅ ኢንቨስትመንት ተወስዶ ሊሠራበት የሚገባ ይሆናል።

የመርከብ መስመር ላይም በተመሳሳይ ተጨማሪ መርከቦች እየተጨመረ ሥራውን ለማዘመን እና ትርፋማነቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የባቡር ትራንስፖርት አምናም ከነበረው በእጅጉ ውጤናማነቱ እያደገ መጥቷል። የዲጂታል ግብይት ከ100 በመቶ በላይ አድጓል።

በተለይ በቅርቡ የጀመርነው የካፒታል ገበያ ከአምስት በላይ ለሚሆኑ ኩባንያዎች ፍቃድ ሰጥቷል። የዲጂታል ግብይቱ እና የንግድ ሥርዓቱ በዚያው ልክ እየዘመነ ለመሄድ ሰፊ ዕድል አግኝቷል።

የፋይናንሻል ሴክተር በተደጋጋሚ በዝርዝር እንዳቀረብኩት እነሱም ከፍተኛ እድገት እያረጋገጡ ይገኛሉ። የአቅም ውስንነት እንደተጠበቀ ሆኖ። የፋይናንስ ዘርፎቻችን አሁን ባለው ፍላጎት እና ውድድር ልክ ለመሆን ሰብሰብ ማለት ይጠበቅባቸዋል። የአቅም ውስንነቶች እንዳለ ሆኖ በሚታዩ አመላካቾች ሲታዩ ግን ከፍተኛ እድገት እያመጡ ይገኛሉ።

የቱሪስት ፍሰት ቅድም እንደተገለፀው በዚህ ዓመት ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች አካሄደናል። በጣም በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ይንቀሳቀሳሉ። ከዓምናው አንፃር ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል።

በአፍሪካም በቱሪስት ፍሰት በንፅፅር እድገት ካመጡ ሀገራት በቀዳሚነት ኢትዮጵያ ትቀመጣለች። አምና ከነበራት ዘንድሮ ያመጣችው እድገት ማለት ነው እንጂ አጠቃላይ የቱሪስት ፍሰት ማለት አይደለም። ያለው ዕድገት ሲታይ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች።

የሰርቪስ ሴክተር አጠቃላይ እንዲለወጥ የሕዝብ ምሬት እንዲቀንስ፣ መንግሥት የሚሰጠው አገልግሎት ያደገ እንዲሆን ሁለት በጣም ጠቃሚ ጉዳዮችን በግርድፉ አመላክቼ አልፋለሁ። አንደኛው በቀበሌ ደረጃ መንግሥት ገቢራዊ ይሁን፣ ቀበሌን እናጠናክር ብለን የጀመርንው ሥራ፤ በቅርቡ በምዕራብ ሸዋ አንድ ቀበሌ በድንገት ባደረግነው ጉብኝት እጅግ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ አይተናል።

የዚያ ቀበሌ ሊቀመንበር በቢሮ ውስጥ የተለጠፉ መረጃዎች አሉት። በሱ ቀበሌ ስንት አባወራ እንዳለ፣ ስንት ወንድ እንዳለ፣ ስንት ሴት እንዳለ፣ ስንት ምንጭ እንዳለ፣ ስንት ሀገር በቀል ዛፎች እንዳሉ፣ ምን ምን እንደሚመረት፣ በስንት ሄክታር እንደሚመረት፣ ስለቀበሌው ከሞላ ጎደል ልማት ለማሳለጥ የሚያስፈልጉ በቂ የሚባሉ መረጃዎች /ዳታዎች/ ለጥፎ ይዟል።

የሰው፣ የከብት፣ እንዲሁም የበሬ ቁጥር ያውቃል፣ ምን ያህል ዶሮዎች በቀን ማርባት እየተቻለ መሆኑን ያውቃል። በዚያ ያየነው ይህ ጅምር በቀበሌዎች፣ በሁሉም ወረዳዎች፣ በሁሉም ዞኖች በዚያ ልክ የተመለሰ እንደሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዳታ ጨዋታ፣ የቁጥር ጨዋታ፣ ከመሠረቱ የሚቀይር እና የሕዝብን የመገልገል መሻት ለማሟላት በእጅጉ የሚያግዝ ጅማሮ ሥራ ነው።

ቀበሌዎች በብዙ ዞኖች እየተስፋፉ እንዳሉ አውቃለሁ። በመላ ኢትዮጵያ ግን ቀበሌ ላይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መንግሥታዊ አቅም መገንባት ቀዳሚው ትኩረት ተደርጎ በተጠናከረ መልኩ ቢሠራ ለሕዝባችን የዕለት ተዕለት አገልግሎት እፎይታ ስለሚሰጥ ሁሉም የመንግሥት አካላት የተጀመረውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከወዲሁ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።

ከቀበሌ በተጨማሪ እስካሁን በይፋ ሥራ ያልጀመረው መሶብ የሚባለው የአንድ መስኮት አገልግሎት ሥራ ነው። ምናልባት በአንድ ወር አንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ይጠበቃል። በዚህ በኩል ሲቪል ሰርቪስ፣ በፕላን ኮሚሽንና ሌሎችም ተቋማት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

መሶብ የተሰኘው በሀገራችን በመሶብ እንጀራ፣ ልዩ ልዩ ወጦች የሚቀርቡበት ባህል ስላለ ከአንድ ቦታ አገልግሎት የሚገኝበት ነው፤ አሁን የምንጀምረው በስምንት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ከ20 በላይ በሚሆኑ አገልግሎቶች ነው።

ቀስ ቀስ እያለም ሁሉም ሚኒስቴሮች ከአንድ ሰርቪስ ከአንድ ቦታ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ የሚያስችል ነው፤ በመሆኑም ሰው ንግድ ፍቃድ ለማውጣት ንግድ ቢሮ፣ ገቢ ለመክፈል ገቢዎች፣ ባንክ መሄዱ ቀርቶ ከአንድ አካባቢ የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት ዕድል የሚሰጥና በብዙ ሀገራት ስናየው ስንቀናበት የነበረ ነው።

በሀገራችንም ሲስተሙ በልጆቻችን ተገንብቶ ቦታ ተዘጋጅቶ፣ ሥልጠና ተሰጥቶ፣ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ያለ ሲሆን፤ ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ የተከበሩ የምክር ቤት አባላት እንደሚያዩት፣ እንደሚደግፉት ተስፋ አለኝ። ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ብሥራት የምሥራች ነው።

በሲስተም ታግዞ በበይነመረብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ከሄድን ያ አቅም ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ልጆች የተሠራ ስለሆነ እያደገ ስለሚሄድ ከአገልግሎት ጋር ታያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ስሞታዎች እየተቀረፉ እንደሌላው ዓለም የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም እየፈጠርን እንሄዳለን ማለት ነው።

በግብርና በኢንዱስትሪ በአገልግሎት ደምረን ስንመለከት ዘንድሮ ያቀድነው የ8 ነጥብ አራት በመቶ እድገት ካለምንም ጥርጥር ከዚያ በላይ ልናሳካ እንደምንችል ያለፉት ስምንት ወራት ውጤቶች ያመላክታሉ።

ገቢን ስንመለከት ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል። ይሄ ገቢ በንጽጽር ጥሩ የሚባል ቢሆንም ከወጪ አንጻር ግን ቀደም ሲል በእናንተም እንደተነሳው ሰፋፊ ድጎማዎች እና የደመወዝ ጭማሪ በዚህ ዓመት ስላደረግን ወጪያችን አሁንም ከገቢያችን ከፍ ያለ ነው። ነዳጅ፣ ማዳበሪያ ለክልሎች የሚሰጠው ድጋፍ፣ የደመወዝ ጭማሪ ተጨማምሮ ትንሽ ሰፋ ያለ የወጪ ጫና ያለበት ዓመት ስለሆነ ገቢያችን ሙሉ በሙሉ ወጪያችንን መሸፈን ባይችልም በራሱ ግን መጠነኛ መሻሻሎች ይታዩበታል።

ያም ሆኖ ያም ሆኖ አሁንም ኢትዮጵያ እየሞከረች ያለችው ከጂዲፒዋ 7 ፐርሰንት ገደማ ገቢ ለማስገባት ነው። ኬኒያ ከ15.5 በላይ ታስገባለች። ከኬኒያ በግማሽ ከጂዲፒያችን ነው ገቢ የምንሰበስበው እና ጫና የሚለው ጉዳይ የምክር ቤት አባላት በደንብ ብታስቡበት ጥሩ ነው። ገቢ ካልተሰበሰበ በስተቀር እዚህ ጋ ገቢ ጫና አለ ብለን እዚህ ጋ መንገድ ይሠራ፣ ጤና ይስፋፋ ብንል አይሄድም አብሮ።

መንግሥት መሠረተ ልማት የሚያስፋፋው በቂ ገቢ ከሰበሰበ ብቻ ነው። እና የዘንድሮው ውጤት ይበል ይቀጥል የሚያስብል ቢሆንም አሁንም ኢትዮጵያ ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት አንጻር ከጂዲፒዋ የምትሰበስበው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን ሁሉም በወጉ ሊገነዘበው የሚገባ ጉዳይ ይሆናል። ከዕዳ አንጻር ባለፈው የደረስንበትን ገልጬ ነበር አሁን አዲሱ ልገልጽላችሁ የምፈልገው እና የተከበረው ምክር ቤት ቢያውቀው ጠቃሚ የሚሆነው ከዘንድሮው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በነበረው ድርድር የዕዳ ሽግሽግ ለማካሄድ ባለፈው ወራት ስንደራደር ቆይተናል አሁን ወደመቋጫው ደርሷል።

በዚያም የዕዳ ሽግሽግ ኢትዮጵያ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ሴቭ አድርጋለች። ባለፉት ዘመናት አላግባብ ኮሜርሻል ሎን ጀምረን ለማንጨርሳቸው ፕሮጀክቶች በቅጡ ገንዘቡ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ባልተረጋገጠ ሁኔታ ሰፊ ዕዳ ነበረብን። ያ ዕዳ ትክክለኛ አይደለም ብለን አምስት ስድስት ዓመት ስንሟገት የነበርንው ጉዳይ ፍሬ አፍርቶ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሽግሽግ አግኝተናል።

ይሄም በዕዳ ሽግሽግ ጫናችን ላይ የሚያመጣው አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖራል። አሁንም የእኛ አቋም የዕዳ ስረዛ መደረግ አለበት አላግባብ የሆኑ ዕዳዎች በአፍሪካ ተጭነዋል የሚል ቢሆንም ይሄን ውጤት እንደትልቅ እመርታ እንወስደዋለን። እነዚህ ተደምረው ሲታይ አንዱ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ችግር የነበረው “ሪዘርቭ” ነው። የኢትዮጵያ “ሪዘርቭ” ውስን ነበር።

የተከበረው ምክር ቤት ዝርዝሩን ከሚመለከታቸው ጋር እንዲነጋገር ትቼ በጥቅሉ ግን 2011 ኢትዮጵያ ከነበራት “ሪዘርቭ” ከእጥፍ በላይ አላት። ከእጥፍ በላይ “ሪዘርቭ” ይዘናል። ከእጥፍ በላይ መሆኑ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባለፉት መቶ ዓመታት አልታየም። ይሄ ትልቅ እመርታ እና እፎይታ ነው። የማይጠበቁ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለተወሰነ ጊዜ ለውጪ ግብይት የሚያግዝ የውጪ ምንዛሪ እንደሀገር ማከማቸቱ ጠቃሚ ስለሆነ።

ከኤክስፖርት አንጻር ባለፉት ስምንት ወራት ኢትዮጵያ ከኤክስፖርት ያገኘችው ገቢ ከየትኛውም ዓመት ስምንት ወር ሳይሆን ከየትኛውም ዓመት የአንድ ዓመት ሙሉ “ኤክስፖርት” ይበልጣል። 4.5 ቢሊዮን ዶላር “ኤክስፖርት” አድርጋለች። ከአምናውም ከካቻምናውም ከዛሬ አስር ዓመቱም ከዛሬ ሃምሳ ዓመቱም ጋር አይወዳደርም።

ከሁሉም የበለጠ “ኤክስፖርት” በስምንት ወር አድርገናል። የበለጠ ማለት ግን ስምንት ወር አይደለም በዓመት አምና ዓመቱን ሙሉ “ኤክስፖርት” ካደረግነው በዚህ ዓመት ስምንት ወር “ኤክስፖርት” ያደረግነው ይበልጣል። በሚቀጥሉት አራት ወራት ይሄንኑ ፔስ ጠብቀን የምንሄድ ከሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ኤክስፖርት የሚመዘገብበት ዓመት ይሆናል።

ይሄም በአስር ዓመት እቅዳችን ካስቀመጠነው “አምፒሽየስ” ከተባለው እቅድ ጋር የተቀራረበ አፈጻጸም ነው። ያ እቅድ ትክክለኛ እንደነበረ የሚያመላክት ነው። በዚሁ ማስቀጠል ከቻልን የኢትዮጵያን ብልፅግና የምናይበት ዘመን ቅርብ እንደሆነ ያመላክታል።

ከሰርቪስ ኤክስፖርት 4.7 ቢሊዮን ዶላር በዚህ ስምንት ወር ተገኝቷል። ከ”ሬሜንታንስ” 38 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ከውጪ ቀጥተኛ “ኢንቨስትመንት” ከሞላ ጎደል 2 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ከሌሎች “ሶርሶች” ከተገኙት ጨምሮ በዚህ ስምንት ወር የተሻለ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ተገኝቷል።

ለ”ኢንፖርት” ክፍያ ያዋልነው የውጪ ምንዛሪ ተመን 10.5 ቢሊዮን ዶላር ነው ባለፈው ስምንት ወራት። ከነዚህ ውስጥ ለጥሬ እቃ ከ3 ፐርሰንት በላይ አውጥተናል። ለ”ኢንዱስትሪያል ካፒታል ጉድስ” ከ21 ፐርሰንት በላይ ክፍያ ተፈጽሟል። እና ለ”ኢምፖርት” ያዋልነው ገንዘብ ጠቃሚ በሆኑ “ሴክተሮች” ለማዋል ጥረት ተደርጓል።

የዋጋ ንረትን በሚመለከት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ እንደስብራት የለየው ጉዳይ የዋጋ ንረት ወይም “ኢንፍሌሽን” ነው። በተደጋጋሚ ባለፉት ዓመታት ለየት ያለ “ሰርጀሪ” ካልሠራን በስተቀር ጥረቶቻችን በሙሉ በ”ኢንፍሌሽን” ምክንያት ያሰብነውን ያክል ስኬታማ እንዳንሆን አድርጎናል ስንል ነበር።

በዚህ ዓመት ያለን ዜና ግን የተቃረነ ነው። ዓምና ከነበረው 29 ፐርሰንት ገደማ አሁን በዚህ ወር 15 ፐርሰንት ደርሷል። ይህ ትልቅ ድል ነው። በተሠራው “ኢንተርቬንሽን” ከፍተኛ ውጤት መጥቷል “ኢንፍሌሽን” ላይ። ምን ማለት ነው ይሄ በገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው የበጀት ጉድለት ከብሔራዊ ባንክ የሚሟላበትን መጠን በመገደባችን ወደ ኢኮኖሚው እሚፈሰው ገንዘብ ቁጥጥር ስለሚደረግበት ከዛ ባሻገር የምርት እድገት ስላለ፤ በግብርናው በተደረገው ማሻሻያ የምርት እድገት ስላለ በገበያ ትስስር በተለይ የሰንበት ገበያ “ሰንደይ ማርኬት” ላይ አርሶ አደሮች በቀጥታ መጥተው ገበያ ላይ በሚያውሏቸው አካባቢዎች አዲስ አበባም እንዳያችሁት በአንዳንድ ሴንተር ግንባታዎች ቀላል የማይባል ጠቀሜታ አስገኝቷል። ከዛ በተጨማሪ ለእጅ አጠሮች የማዕድ ማጋራት፤ ማዕድ ማጋራት ብዙ ቤተሰብ፣ ብዙ ጎረቤት የሚጠቅም ተግባር ነው። እኛ ለምናጋራው ጥቅሙ እምብዛም ላይገባን ይችላል።

ለተቸገሩ ሰዎች ግን በእንደዚህ አይነት ፆም ወቅት የተወሰነ ነገር ስናጋራ የፆም ጊዜውን ሳይሰቃዩ እንደቤተሰብ ለማሳለፍ ዕድል የሚሰጥ ነው። ይህም የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አስገኝቷል። ነገር ግን የዋጋ ንረት ሲቀንስ የፍጆታ እቃዎች ዋጋም በዛው ልክ ይቀንሳል ማለት አይደለም። የዋጋ ንረት ቀነሰ ማለት የእድገት ምጣኔው ቀነሰ ማለት ነው።

“ኢንክሪሲንግ አት ዲክሪዚንግ ሬት” ማለት ነው እንጂ እድገት የለም ማለት አይደለም። የዋጋ ንረት መቀነስና የኑሮ ውድነትም አንድ አይደሉም። እስካሁን ያለው ዋጋ በራሱ ገቢ ካላደገ ምርት በብዛት ካልተመረተ በራሱ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 20 ዓመታት በቀጣይነት “ደብል ዲጂት” እድገት ስለነበረው የዛ “ኩሚሊቲቭ” ውጤት ድምር ውጤት እያንዳንዱን ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰው ጫና ይፈጥርበታል።

ምንም ጥያቄ የለውም። ለዛ ነው መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ድጎማ የሚያደርገው፤ “ኤንፍሌሽንን” ዜሮ ማድረግ እድገትን ዜሮ ማድረግ ነው እድገት ባለበት ቦታ ኢንፍሌሽን አይቀርም። “ኢንፍሌሽኑ” ግን ተጋኖ “ደብል ዲጂት” ሲሆን ከሰው ገቢ በላይ ከሚያገኘው በላይ እድገት ስለሚኖረው በሰው ኑሮ ላይ ጫና ይፈጥራል። ያን ለማድረግ የሰው ገቢ ማሳደግ አለብን። ዘንድሮ በደመወዝ ጭማሪ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ዝቅተኛ ደመወዝ ያላቸው ሰዎች እስከ 300 ፐርሰንት ድረስ ጭማሪ ያደረግነው በዛ ምክንያት ነው። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች፣ ዝቅተኛ ደሞዝ ያላቸው ሰዎች ተጎጂ ናቸው ከሚል እሳቤ ነው።

ምርት ማሳደግ፣ ሸቀጥ ከሚመረትበት ወደገበያ የሚሄድበትን መንገድ ማስፋት፣ የንግድ ሥርዓትን ማዘመን የሚጠበቅብን ይሆናል። እነዚህን በማድረግ የተገኘውን የ15 ፐርሰንት ውጤት በዚሁ መንገድ ካስቀጠልንና መጠነኛ ማሻሻል ካደረግን እንደትልቅ እመርታ ሊወሰድ ይችላል። ዳታ ላይ የሚያስፈልገንን መረጃ/ዳታ ወስደን የማያስፈልገንን በመተው ሳይሆን ዳታን መቀየር ስለማይቻል ጥሬ ሐቁን እንዳለ መውሰድና ክፍተት ካለበት መሥራት ነው የሚያስፈልገው።

አሁን ያለው “ኢንፍሌሽን” እስካሁን ከሠራናቸው በጣም በእጅጉ የተሻለ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። አሁንም ግን ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ጫናው ከፍተኛ ስለሆነ በድጎማ፣ ማዕድ ማጋራት፣ ገቢያቸው እንዲያድግ፣ ልጆቻቸው ሥራ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደ መንግሥት እንደሕዝብ ይጠበቅብናል። ይህን አሳይመንት የምንዘነጋ ሆኖ ሳይሆን በተሠራው ሥራ የመጣው ውጤት ግን ይበል የሚያስብል ነው ማለት ይቻላል።

ከድጎማ አንጻር ማዳበሪያ 84 ቢሊዮን ብር ነው የምንደጉመው። በአንድ ኩንታል 3ሺ 700 ብር እንደጉማለን። እኛ ማዳበሪያ ስለማናመርት የማዳበሪያ ዋጋ አንወስንም። አምራቾች ዋጋ ተምነው ለእኛ ሲያቀርቡ አርሶአደሩ እንዳይጎዳ አቅም በፈቀደ መጠን እንደጉማለን እንጂ ዋጋ አንወስንም። ነዳጅ በሚመለከት 72 ቢሊዮን ገደማ ተደጉሟል።

ነዳጅን በሚመለከት የተከበረው ምክር ቤት መጠነኛ ግንዛቤ እንዲይዝ በዓለም ገበያ ቤንዚን ኢትዮጵያ በሊትር 129 ብር ትከፍላለች። 129 ብር ኢትዮጵያ ውስጥ ግን 101 ብር እንሸጣለን። 28 ብር በሊትር ድጎማ አለ። 28 ብር በሊትር የሚደጎመው ደሃ ብቻ አይደለም። ኤምባሲዎችም ጭምር ናቸው። ምክንያቱም ሀገር ውስጥ ያለው ገበያ ለይተን ለደሃ የምንልበት አሠራር አስቸጋሪ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሀብታሞች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እነርሱ እንኳን ቀርተው ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ስደተኞችና የውጪ ሀገር ዜጎች ርዳታ የሚያመጡ የዩኤን ኤጀንሲዎች ሳይቀሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያጓዙት ትራንስፖርት በሊትር 20 ብር አካባቢ ኢትዮጵያ ትደጉማለች።

 

ቤንዚን ብቻ ሳይሆን ነጭ ጋዝ 129 ብር ነው የምንገዛው። እኛ የምንሸጠው ግን 99 ብር ነው። 30 ብር በሊትር እንደጉማለን። ሌሎች የነዳጅ ዓይነቶችም እንደዚሁ። ይህ ዋጋ በእኛና በእኛ አከባቢ ካሉ ሀገራት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ልዩነት አለው። 0 ነጥብ 7፣ 0 ነጥብ 8 ሳንቲም ዶላር በሊትር ነው እኛ የምንሸጠው። እኛ አካባቢ ጋር ግን ቢያንስ 1 ነጥብ 4 እስከ 2 ዶላር በሊትር ይሸጣል።

ኢትዮጵያ በብዙ ትደጉማለች። ኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ መወሰን አትችልም። ስለማታመርት። አምራች የወሰነውን ገዝታ ግን ዜጎቿ እንዳይጎዱ በአንድ ሊትር ከ25 ብር በላይ እየደጎመች የምታሠራበት ዋናው ምክንያት አብዛኛው እጅ አጠር ሰዎች በዚህ ሂደት ጉዳት ስለሚደርስባቸው ያን ለመቀነስ ነው። መድኃኒት፣ የምግብ ዘይት 350 ሚሊዮን ገደማ እንደጉማለን።

“ሴፍቲ ኔት” ወደ 22 ቢሊዮን ገደማ እንደጉማለን። ድጎማው ሲደመር የምናገኘውን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ ስለሆነ ኢትዮጵያ ከምታስገባው ገቢ በላይ ድጎማ ሁሉም ዜጎች በነፃ እንዲመገቡ ማድረግ አሁን አትችልም። ማምረት፣ መሥራት አለብን። ይህን ችግር በመድረክ ንግግር ብቻ አንፈታውም። በተግባር ማሳያዎቻችን ላይ በምናስገኛቸው ውጤቶች የሚፈታ ይሆናል። በዚህ አግባብ ድጎማ ለማድረግ እየሞከርን ያለንበት ሂደት በአርሶ አደሩም በነጋዴው ላይም ያለውን ጫና ለመቀነስ የሚያግዝ ነው።

ማዳበሪያ 24 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ የሚያስፈልገን ሲሆን በአንድ ቀን 150 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ከወደብ እናጓጉዛለን። 150 ሺ ኩንታል አፈር ጭነን ወደ ሀገር ውስጥ እንስገባለን። የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን ከወደብ 150 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ በቀን ጭነን ማምጣት ብቻ ሳይሆን ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደር በወታደር አጅበን እንወስዳለን።

አምና አማራ ክልል 7 ሺ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ነው መከላከያ ያጀበው። መከላከያ የገደለው ሳይሆን ለእያንዳንዱ አርሶ አደር ማዳበሪያ ለማድረስ 7 ሺ የጭነት ተሽከርካሪ አጅቦ ወስዷል። ከውጪ እንገዛለን፣ እንደጉማለን፣ ወደብ ስለሌለን ከወደብ ማጓጓዙ ጣጣ ነው፣ ከገባ በኋላ ወደእያንዳንዱ አርሶ አደር እንዲደርስ በአጃቢ እንዳርሳለን። ይህ ሁሉ ወጪ ነው።

አሁን ቀደም ብሎ የመናገር ፍላጎት ባይኖረንም ለአንድ ዓመት ገደማ ማዳበሪያ ኢትዮጵያ ማምረት ካልቻለች በርካታ አርሶ አደር የሚነካ ጉዳይ ስለሆነ፣ ከምግብ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ስለሆነ በዘላቂነት መፍትሔ ልናገኝ አንችልም በሚል ስናጠና ቆይተናል። አሁን የህዳሴው ጉዳይ የምታውቁት ስለሆነ የህዳሴ ፊታችንን ወደ ማዳበሪያ እንዞራለን።

በተደረገው ጥናት ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ይፈልጋል። በጣም በርትተን ከሠራን ቢያንስ ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይፈልጋል የማዳበሪያ ፋብሪካውን በበቂ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ አቋቁሞ ለመሥራት። አሁን ሁለተኛው ህዳሴያችን የሚሆነው ማዳበሪያ ፋብሪካውን ከተቻለ በ‹‹ጆይንት ቬንቸር›› ከግሉ ሴክተር ጋር ከዚያም ከፍ ብሎ ከተገኘ በግሉ ዘርፍ “ኢንቨስትመንት”፤ ካልተቻለ ግን በመንግሥት በራሱ የግድ የማዳበሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያን ፍላጎት ሊመልስ በሚችል መልኩ መፍጠር ይኖርብናል። ምናአልባት የሚቀጥለው ዓመት ሁነኛው ተግባራችን የሚጀምር ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

የሥራ ዕድልን በሚመለከት የስምንት ወር ዳታ የሚያመላክተው በሀገር ውስጥ ወደ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አግኝተዋል። በውጪ ሀገር ከ300 ሺ በላይ ሰዎች ሥራ አግኝተዋል። በ”ሪሞት ጆብ” ወይም “ቢ ፒ ኦ” በሚባለው ከ45 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን እዚሁ ሀገር ውስጥ ተቀምጠው ለውጪ ሀገር ኩባንያዎች ሥራ የሚሠሩ ሥራ አግኝተዋል። ድምር ሲታይ ከ3 ሚሊዮን ከፍ ያለ ሰው በስምንት ወር ውስጥ ሥራ ይዟል። ይህ ትልቅ ቁጥር ነው። ፍላጎት ምንም ያህል ያደገ ቢሆንም በዚህ ልክ ሥራ መፍጠር ቀላል ነገር አይደለም። ግብርና ከ40 ከመቶ በላይ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ኢንዱስትሪ ከ20 ከመቶ በላይ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የአገልግሎት ዘርፍ 38 ከመቶ ገደማ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

በከተማና በገጠር የኮሪዶር ሥራዎችና ልዩ ልዩ “ኢንሺዬቲቮች” በርካታ ወጣቶችን በቀን ብቻ ሳይሆን በማታ በፈረቃ ይሠራሉ። የሥራ ባህላችንም ተቀይሯል። እናንተም የምትታዘቡት ስለሆነ እዛ ውስጥ አልገባም። በዚህ ውስጥ ጥሩ ጅማሮ ነው ያለው ነገር ግን አሁንም ሰፋፊ ጥረቶች ያስፈልጋሉ። በድምሩ የዋጋ ግሽበት ከአምናው በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። የወጪ ንግድ ከአምናው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። ገቢም ተሻሽሏል። የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ ውጤቶታችን በጣም እመርታ አሳይተዋል።

ኢኮኖሚው ከምንግዜውም በላይ ጤነኛ የሚባልና ተስፋ ሰጪ ነገር ይታይበታል። ይህን እውነት ማየት የማይችል፣ ይህን እውነት መገንዘብ የማይችል ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም። ዓለም የሚናገረው ጉዳይ ስለሆነ። በፓርላማ የሚነገር የ10 ከመቶ እድገት ሳይሆን ከዚህ ከአራት ኪሎ ተነስተን ካዛንቺዝ ስንደርስ የምናየው እድገት ስለሆነ ነው። ብዙዎች ገንዘቡን ከየት አመጣችሁት በሚሉበት ሰዓት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ልማት የለም ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ አስቸጋሪ ነው።

ኮሪዶርን በሚመለከት፣ ዋና እሳቤው ለልጆቻችን መልካም ሀገር፣ መልካም ከተማን ጥሎ መሄድ ነው። ልጆቻችን ሌላ ናፋቂ ሳይሆኑ በሀገራቸው የተሻለ ከባቢ ኖሯቸው እንዲኖሩ ለማስቻል ነው። የደቀቁ ሰፈሮች (ሰፈር ማለት አይቻልም የደቀቁ ናቸው)፣ ለዓይን ለማየት የሚያስቸግሩ ሰፈሮች ነው እየተቀየሩ ያሉት። አዲስ አበባ ብቻ አይደለም፤ ከአዲስ አበባ ውጪ።

በቅርቡ ሐረር ሄጄ ጀጎል ውስጥ ያየሁት ተዓምር ነው። የሐረር ሕዝብ ይሰማኛል፤ ሐረርን የምታውቁ ሰዎች ትሰማላችሁ፤ በሐረር ከተማ የተሠራው ሥራ፣ በጀጎል የተሠራው ሥራ ለልጆቻችን ያማረን ስፍራ ጥሎ የማለፍ መሻት ፍሬ እያፈራ መሆኑን ያመላክታል። መስፋት አለበት፤ ብዙ ጋር መድረስ አለበት የሚለውን እቀበላለሁ። ግን ጅማሯችን ተስፋ ሰጪ ነው።

ለዚህ ነው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አሁን ላይ ልምድ ስጡን እያሉን ያሉት። እኛም እንጀምር ነው እያሉ ያሉት። በተለይ ስፔስን በሚመለከት በቤት ላይ ቤት በአጥር ላይ አጥር ፣ በአጥር ላይ ሰርቪስ የነበረውን የኑሮ ዘዬ ቀይረን፤ ልጆቻችን ወጣ ሲሉ ወክ የሚያደርጉበት፣ ኳስ የሚጫወቱበት ከባቢ መፍጠር ከባቢን ለኑሮ ምቹ ማድረግ በጣም በጣም አስደሳች ጉዳይ ነው።

ከዚያ ባሻገር ግን መሠረተ ልማት ግንባታው ግምት እንዲሰጠው እፈልጋለሁ። አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ200 በላይ ኪሎሜትር መንገድ ተሠርቷል። ሰፋፊ “ዎክ ዌዮች” ተሠርተዋል። የውሃ ፍሳሽ፣ የመብራት መስመሮች ድሮ ዝናብ ሲዘንብ አራት ኪሎ እንደዚህ አልነበረም፤ ዘነበ ማለት ጨቀየ ማለት ነው፤ አሁን ዘነበ ሲባል በንጽጽር ፀዳ ብሎ ያየነው አንዳንድ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎችን በመሻሻሉ ምክንያት ነው። ከዚያ ባሻገር የኮሪዶር ሥራ ሥራ ፈጥሯል፤ የዜጎች ያላቸው የሀብት (እሴት) ከፍ አድርጓል። ለዓይን የሚማርክ ከተማ ፈጥሯል፤ የትራፊክ ፍሰት አሻሽሏል።

ቤቶች ግንባታ በሚመለከት የንጽጽር መረጃ ባያስፈልግም በኢሕአዴግ ዘመን ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም፤ 160 ሺህ ገደማ ቤቶች ተገንብተዋል።

ባለፉት አስራ ምናም ዓመታት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት 167 ሺህ ቤት ገንብተን ለጥቅም አውለናል። የአምስት ዓመት ሥራችን ከ15 ዓመት ሥራ ሊነጻጸር ይችላል። አሁንም በመንግሥት፤ በመንግሥት እና የግል አጋርነት እንዲሁም በግሉ ሴክተር እየተገነቡ ይገኛሉ። የቤት ፍላጎታችን ሰፊ ስለሆነ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም የተገኘው ውጤት በጣም ተስፋ የሚሰጥ ነው።

እናንተም እንዳያችሁት ከነበሩበት ከባቢ ተነስተው ሌላ ቦታ የሰፈሩ ወገኖቻችን በከባቢያቸው የሌለ ቤት፣ የሌለ ትምህርት ቤት እና የሌለ ፓርክ ተሠርቶላቸዋል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕጋዊ ማስረጃ ኖሮት ወይም መሬት ወይንም ካሣ ሳይከፈለው የተነሳ አንድም ሰው እኔ እስከማውቀው የለም። ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ካሣ ተከፍሏል። ማላዘን የሚፈልጉ ሰዎች ሊያላዝኑ ይችላሉ።

ከእኛ በላይ ግን ለኢትዮጵያ ድሀ ሊቆረቆሩ አይችሉም እኛ ድሀአደጎች ነን። የተነሳንበትን ሕዝብ ልንጨፈልቀው አንችልም፤ መደብ ላይ አድገን ሕልማችን ልጆቻችን አሁንም መደብ ላይ እንዳያድጉ ማድረግ ነው። ለድሀ መቆርቆር ለድሀ ማዘን፣ ከድሀ ጋር መኖር ለዚህ መንግሥት የሚነገረው ነገር አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ያየዋል ይገነዘበዋል።

በውሃ፣ በሪቨርስ ሳይድ የሚሠራው ሥራ የተከበረው ምክር ቤት ጊዜ ወስዶ እንደሚመለከተው እፈልጋለሁ። የሐረር እና የኮንሶ አርሶ አደሮች እዚህ አዲስ አበባ ላይ እየሠሩ ያሉት ተዓምር፤ እንጦጦ ላይ እየሠሩ ያሉት ተዓምር ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን የሚተርፍ ነው። ውሃ አለ ማለት ሽታው የማያስኬድበትን ከተማ፤ የውሃ መስመሮችን ለማፅዳት እየተሠራ ያለው ሥራ፡ የሚከላ አፈርን ለመከላከል እየተሠራ ያለው ሥራ እናንተን ካላስደመመ ማንን ያስደምማል።

ፓርኪንግ ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ፓርኪንግ በውስጥና በውጭ ተገንብቷል። ፓርኪንግ ነበረ እንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርኪንግ ማለት አስፋልት መንገዱ ማለት ነበር፤ አሁንም በቂ አይደለም ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋል ነገር ግን እስካሁን የመጣው ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው።

በድምሩ ኮሪዶር በጎንደር፣ በባሕርዳር፣ በደሴ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋ፣ በጅማ፣ በአምቦ፣ በነቀምት፣ በአርባምንጭ፣ በሀዋሳ፣ በሶዶ፣ ከቦታ ቦታ ቢለያይም ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች አሉ። በእርግጥ የሐረር ከሁሉም በላይ “ኢምፕረስ” ያደርጋል። ምክንያቱም ሐረርን የቀየረው ከገንዘብ አይደለም ከሌሎች ከተሞች ሁሉ ያነሰ ገቢ ያለው ሐረር ነው ግን ፍቅር የተሞሉ እና ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ሰጥተው የማይጠግቡ ነዋሪዎች ያሉበት ከተማ ስለሆነ በትንሽ ብር ከሁሉም ከተማ የተሻለ ሥራ ሠርተዋል። ይህ ሥራ በሁሉም ጋር እንዲለመድ ሁሉም የዚህ ሥራ አካል እንዲሆን ጥሪዬን እያቀረብኩ የጀመርነው የልማት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ልማት በማንኛውም ኢኮኖሚን በሚያውቅ ተቋምም ሆነ ግለሰብ ዓይን ምሳሌያዊ ነው። አይ.ኤም ኤፍ ጋር፣ ዓለም ባንክ ጋር፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር እንነጋገራለን፣ ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች ጋር፣ የአፍሪካ መሪዎች ጋር እንነጋገራለን፤ ሁሉም በአርዓያነት የሚመለከቱት ተግባር ነው። ይህ እንዲጠናከር እንዲሰፋ ጥረት እንናድርግ ቢባል ካልሆነ በቀር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፈተና ውስጥ እየመጣ ያለው ውጤት ታይቶም አይታወቅም፤ እስካሁንም አልነበረም። በዚህ መነጽር ማየት ቢቻል ጥሩ ይሆናል።

ግጭትን በሚመለከት፤ የግጭት ተፈጥሮና እድገት ከመሠረቱ የማየት ልምምድ ካልፈጠርን፤ ላይ ላዩን ብቻ የምናይ ከሆነ እንስታለን። ግጭት ንጣፍ አለው። እያንዳንዱን ንጣፍ፤ እያንዳንዱን “ሌየር” እያነሱ ማየት ይፈልጋል። “ትሪገሪንግ ፖይንቷን” ብቻ አይቶ የሚናገር ሰው ግጭት ሊፈታ አይችልም። “ከትሪገሪንግ ፖይንቱ” አንድ ዝቅ ስንል “ፕሮክሲሚቲ” አለው። ከእርሱ ዝቅ ስንል “ስትራክቸራል” ችግር አለው። “ስርታክቸራል” ችግሩን ያልተገነዘበ፤ የትኛውም አካል ችግር ሊፈታ ቢያስብ ይቸገራል።

ምክንያቱም ግጭት ከሁሉም ኩነቶች በላይ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር ከሞላ ጎደል እኩል የነበረ ነው። ሰው ተፈጠረ ግጭት ተጀመረ። እንደምታውቁት ግጭት በአቤልና በቃየል ነው የጀመረው ማለት ነው። ከሰው ልጅ እድሜ ጋር ነው ግጭት የኖረው፤ መጠኑ ከፍ ዝቅ እያለ። በጣም ብዙ ፈላስፋዎች፣ ተመራማሪዎች፣ አዋቂዎች ግጭትን ለማስቀረት ብዙ ጥናት፣ ብዙ ምርምር አካሂደዋል፤ ብዙ ፅፈዋል።

ሰላም በጣም በጣም ውድ የሆነ “ኮሞዲቲ” ነው፤ መገንባት ያለበት ነው። ግን ሁለት አከራካሪ ጉዳዮች አሉ ሰላምን በሚመለከት። አንደኛዎቹ ወገኖች ፍፁም ሰላማዊነት ወይም “ፖሲቭዝም” የሚባለው ምንም አይነት ትንኮሳ፣ ምንም አይነት ሙከራ ቢደረግብህ ግብረ መልስ አትስጥ፤ ስትመታም፣ ስትሰደብም፣ ስትነጠቅም ዝም በል። ግብረ መልስ ካልሰጠህ ግጭት በሁለት አካላት ይሁንታ የሚፈፀም ስለሆነ ልታስቀረው ትችላለህ የሚል እሳቤ ያላቸው ፈላስፋዎች፣ አዋቂዎች አሉ።

ፖሲቪዝም ለግለሰቦች ጥሩ እሳቤ ነው። መጥፎ አይደለም። አሁን ታገሰ ነካ ነካ ቢያደርገኝ ብተወው ችግር የለውም፤ ለግለሰቦች። በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በብቸኝነት ሃይል የመጠቀም ሥልጣን ያለው መንግሥት፤ የወል ፍላጎት፣ የወል “ኢንተረስት ፕሮቴክት” ማድረግ ያለበት ተቋም ሲሆን ግን ያስቸግራል። መንግሥት መሬትህን ሲወስዱብህ፤ በቃ ይውሰዱት ብሎ እተዋለሁ ሊል አይችልም። በምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንጥላለን ሲሉ ዝም ብዬ አያለሁ ማለት አይችልም፤ ያስቸግራል። ተፈጥሮ እንደዛ አይደለም።

ይልቁንስ መንግሥት ሰላም ያስቀደመ መሆን አለበት። ሰላምን በይፋ የሚናገር፣ ለሰላም የሚተጋ መሆን አለበት። ሰላም የሚያደፈርስ ነገር ሲኖርም ግልፅ መመዘኛዎች ያስፈልጉታል። ዝም ብሎ ዘሎ ውጊያ አይገባም። አንደኛ ፍትሀዊና በቂ ምክንያት አለ ወይ? ውጊያውን ለማድረግ፣ ግጭቱን ለመፈፀም በቂ ምክንያት አለ ወይ? ሁለተኛ ያንን ግጭት በሃይል ለማስቀጠል ተገቢ ቅቡልነትና ሥልጣን ያለው አካል ነው ወይ፤ ማንም ተነስቶ በሃይል ጉዳይ ልፍታ ቢል ተገቢ ስላልሆነ።

በግጭት ዓላማውን ያሳካል ወይ? ከመነሻው ሊያሳካ የፈለገውን ዓላማ ሊያሟላ ይችላል ወይ? አራተኛ ተመጣጣኝ ሃይል ይጠቀማል ወይ? ሌሎች የሚጨመሩ ነጥቦችም አሉ። እነዚህን የሚያሟላ በሚሆንበት ሰዓት መንግሥት በብቸኝነት ሃይል የመጠቀም ሥልጣን ያለው አካል ስለሆነ ለዘላቂ ሰላም፤ ለፍትህ ሊጋጭ ይችላል። የምንዋጋው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ነው የሚባለው ለዚያ ነው። ለጦርነት ብቻ ከሆነ የተሟላ ሰላም ለማምጣት ሥልጣን ያለው አካል፤ ሃይል መጠቀም እንደሚችል የዓለም አቀፍ ክፍት እውቀት ነው፤ ማንም ሰው የሚያውቀው ነገር ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ከዚህ ይለያል። ሁለት መሠረታዊ የፖለቲካ ስብራቶች አሉ። አንደኛው ነባሩ የመጠፋፋት ባህል ነው፤ ነባር ባህል ነው። ልጅ እያሱ ሲነሱ አልጋ አልፀናም ብለው የሚነሱ ሃይሎች አሉ። መንግሥቱ ሲመጣ አልጋ አልፀናም ጊዜው አሁን ነው ብለው እዚህም እዚያም የሚቧደኑ ሰዎች አሉ፤ በኢህአዴግ ዘመንም አሁንም ይሄው ነው። ባህል ነው፤ አዲስ መንግሥት ሲመጣ አልጋው ሳይፀና እናፍርሰው የሚባል የነበረ ባህል አለ። አንድም መንግሥታት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ሽግግር አድርገው በረጋ መንገድ የሄዱበት ታሪክ የለንም። ይሄ የራሱ የሆነ ጉዳት አለው።

ሁለተኛው ከሶሻሊስት እሳቤ ጋር በስፋት ወደ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ የገባ በሽታ ነው። ሶሻሊዝም እንደ “ዌቭ ዘ ሆል አፍሪካን ” የወረረ በሽታ፣ የወረረ እሳቤ ነው ፤ በሆነ ዘመን ውስጥ። ይሄ በሽታ በተለይ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያመጣው ችግር ደግሞ ፍረጃ ነው። ሶማሊያም ነበረ፣ ታንዛኒያም ነበረ፣ ዙምባቡዌም ነበረ፤ ብዙ አፍሪካ ሀገራት በሶሻሊዝም እሳቤ ተውጠው ተንቀሳቅሰዋል። በእኛ ደረጃ ግን ፍረጃ መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም። ጠላት ስንል እንፈርጃለን፤ በጠላት መቃብር ላይ ካልሆነ ቤት አንሠራም። ቆሞ በሰላማዊ መንገድ ተደራድሮ የሚባል ነገር፣ ልምምዱ የለም።

የኢትዮጵያ ፖለቲካል ፓርቲ እና እሳቤው ከተጀመረበት ከ1960 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ ያለውን ብንመለከት ተማሪዎች ሁሉም አንድ እሳቤ “አይዲዮሎጂ” ይዘው በሆነ በሆነ ምክንያት ግራና ቀኝ ከቆሙ በኋላ መሣሪያ ሳይኖራቸው እስኪርቢቶ ያላቸው ተማሪዎች በፅሁፍ በንግግር ከመጨቃጨቅ ይልቅ፤ መሣሪያ ተውሰውና ገዝተው መገዳደል ጀመሩ፤ ተማሪዎች። መንግሥት አይደለም፤ ተማሪዎች እነዚህ ተማሪዎች ከመንግሥት ጋር በነበረው ግጭት ከተማ ውስጥ መቆየት ሲያቅታቸው በረሃ ሲሄዱ፤ ከመንግሥት ጋር አይደለም፤ አንድ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ ተማሪዎች በረሃ ላይ በውስጣቸውም ከሌሎች ሃይሎች ጋርም ባደረጉት ውጊያ ተባሉ።

ከተማ ውስጥ ኢህአፓና መኢሶን መውሰድ ይቻላል፤ ኢህአፓና ቲፒኤልኤፍ በአሲምባ መውሰድ ይቻላል። ከበርሃ ከወጡ በኃላ ተሰደው ትግሉ እንደማያዋጣ አውቀው ወደ ውጭ ሀገር ከሄዱ በኋላ አሁንም ባሉበት ሀገር አይን ለአይን መተያየት አይችሉም፤ ከአስር ሃያ ሰላሳ ዓመት በኋላም። ከዚያ አልፎ አንዳንዶቹም ሲጽፉ መጽሃፎቻቸውን ያያችሁ ከሆነ ዛሬም ከሃምሳ አርባ ዓመት በኋላ እዛው ቆመው ይወቃቀሳሉ እንጂ ይሄን ማድረግ ሲገባን አይሉም።

ፍረጃው በጉርምስና እና ስሜት ከፍ “ኢሞሽን ሃይ” በሆነበት ጊዜም በስተእርጅና ጊዜም እምብዛም ሲቀየር አይታይም። ይሄ የፍረጃ ችግር በሁሉም አፍሪካ ሀገሮች መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም። እኛ ጋር ይበረታል ትንሽ። ትንሽም ጭላንጭል መልካም ነገር ስናይ ለመናገር በሚያስቸግር ደረጃ ነው እኛ ጋር ያለው ፍረጃ። እግዜር ያሳያችሁ ካዛንችስን ያን የአሽሽ መንደር እንዲህ ለውጠነው “ትራንስፎረም” አድርገነው ሲያይ በስሱ እንኳን ለማድነቅ የሚቸገር የፖለቲካ ፓርቲ፣ ምን ተስፋ አለው ከመፈረጅ ውጪ። ፍረጃ!

ይሄ ጉዳይ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለማፍረስ ዘለን አራት ኪሎ ፤ አራት ኪሎ የሚል መፈክር ተራ ልምምድ ሆኗል። በርሃ ለገቡት አይደለም፣ በአንድ እግራቸው በርሃ በአንድ እግራቸው ፓርላማ ላሉትም ጭምር ማለት ነው። በኃይል ሥልጣን መያዝ አቅልሎ የመመልከት ችግር በስፋት አለ። በዓለም ታሪክ በኢትዮጵያም ታሪክ እንደምንመለከተው እነዚህ ነውጠኛ ነጻ አውጪ ታጣቂዎች በመጀመሪያ ደረጃ ሰለባ የሚያደርጉት እንታገልልሃለን የሚሉትን የራሳቸውን ሕዝብ ነው።

ስለምታገልልህ አግትሃለሁ፣ ስለምታገልልህ ገልሃለሁ፣ ስለምታገልልህ ሳትፈቅድልኝ ገብቼ ቆርሼ በላለሁ ፤ እድፍርሃለሁ። እኔ የማደርገው ማንኛውም ነገር ታጋይ ስለሆንኩ ሀላል ነው ይፈቀዳል ብለው ያስባሉ። ይህ ኦሮሚያ አለ ፤አማራም አለ ፤ወደ ትግራይም ሁሉም ጋር ነው ያለው። ኢትዮጵያም ሌላም ሀገር አለ። አስቡት “ኢማጅን” አልሻባብን ብትወስዱት አንድ የሱማሌ ዜጋ አንድ ሙስሊም በረመዳን ወር ሌላ የሚጾምን ሙስሊም፣ ሌላ ሱማሌ፣ ሌላ እስላም ምንም ባላደረገው ምክንያት ቦንብ ታጥቆ አፈንድቶ ይገለዋል። ለሰሱማሌ እየታገለ ሱማሌን ይገላል ማለት ነው። ሁሉም ጋር ያለ ልምምድ ነው። ነውጠኞች እንደዛ ናቸው ለሚታገሉለት ሕዝብ እዳ ናቸው።

በሀገራችን አንድ አባባል አለ። “ለበሬው ሲሉ በሬውን አረዱት” የሚል አባባል አለ። ምን ማለት ነው፤ በዚህ ሰፈር ያሉ ሰዎች እዚያ ማዶ ያሉ ሰዎች በሬያችንን ወስደውታል አርደው ሊበሉት ስለሆነ፣ ሄደን ተጋጭተን ነጥቀን በሬያችንን መመለስ አለብን ልክ እንደ አሁኑ ቅስቀሳ ይደረጋል። ከተደረገ በኋላ ሰዎች ይሰበሰባሉ፣ ለውጊያ ይዘጋጃሉ ለውጊያ ስንሄድ ስንቅ ስለሚያስፈልገን ስንቅ እንያዝ ብለው በሬ አርደው ስንቅ ይከፋፈላሉ። መንገድ ከጀመሩ በኋላ ለካ ያን የሚዋጉለት በሬ አርደው ስንቅ አድርገውታል። ለበሬው ሲሉ በሬውን አረዱት ይባላል። ለአማራ ሕዝብ ሲባል ለኦሮሞ ሕዝብ ሲባል መልሶ አማራን ኦሮሞን የሚያርድ ነውጠኛ ፋይዳ የለውም ማለት ነው።

ክቡር ዶክተር ደሳለኝ፤ ሰፋ ያለ የጥያቄ መቅደም ካነበቡልን በኋላ አንድ ጥያቄ ጠይቀዋል። ለዚያ ጥያቄቸው ራሳቸው ምላሽ ሰጥተዋል። ጠይቀው ስለመለሱ እንዲሁ ማለፍ ይቻላል። ነገር ግን ለእርሳቸው ክብር፣ ለዚህ ምክር ቤትም ክብር ሲባል አንዳንዶቹን ነገሮች በግርድፉ አንስቼ አልፋለሁ።

አንደኛ ይሄን ጦር ሰባኪ መንግሥት በዚህ ልክ ሲተቹት “ክርቲሳይዝ” ሲያደርጉት ሕዝብ እንዳይወጣ እንዳይገባ፤ እንዳይማር እንዳያርስ፤ ማዳበሪያ እንዳይወስድ ያደረገውን ኃይል ምነው አላየሁም ፤ አልሰማሁም አሉት? በሕዝብ መሰብሰቢያ ፤ በእርስዎ ከተማ ቦንብ ንጹሃን ሰዎች የሚንቀሳቀሱበት ቦታ ላይ የሚያፈነዳን ኃይል ምነው ዝም አሉት? ሽማግሌ ላስታርቅ ብሎ ሲሄድ፣ ቄሶች አሮጊቶች በእንብርክክ የሚያስኬደውን ከኢትዮጵያ ባህል ውጭ የሚገለውን ኃይል ምነው አላውቅህም አሉት? ከሁሉ ደግሞ የገረመኝ በእርሶ እና በእርስዎ ፓርቲ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የነበረውን የትግራይ ውጊያ ምነው የትግራይ ውጊያ አሉት? አዝማች አልነበሩ እንዴ እርስዎ? እነዚህ እሳቤዎች የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንዳለው ስጋ በሊታ ያስመስለዋል።

ይሄ ተገቢ አይመስለኝም። በእኛ በኩል ያለውን ክሪቲክስ ግድየለም እንፈትሸዋለን፤ እርስዎ ግን ትንሽ ሚዛን ቢጠብቁ ጠቃሚ ነበር ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ለሰላም ምን ያህል ጥሪ እንዳቀረብን በዚህ ቤት ጭምር ስለሚያውቁ።

ሌላው በጣም የገረመኝ ጉዳይ የእርስዎ መንግሥት በቄስ ሞገሴዎች ውዳሴ ያሉት፤ እኛ ሰፈር ፊትአውራሪ መሸሻ የሉም ፤ቄስ ሞገሴዎች ምን ያደርጋሉ? ቄስ ሞገሴ መሸሻ ከሌሉ ህልውና እንደሌላቸው ስለሚታወቅ፤ ባይሆን እኛ ጉዱ ካሳዎች ብንባል ያምር ይሆናል እንጂ፤ በየት በኩል ነው ቄስ ሞገሴዎች እኛ ሰፈር የሚታዩት? ምክንያቱም እኛ ትናንትናን ናፋቂዎች፣ ትናንትናን ለማጽናት የምናሸረግድ ሰዎች ሳንሆን ነገን ለልጆቻን ለመሥራት መጋፈጥ የማይገባንን ጉዳዮች የምንጋፈጥ ለውጥ ፈላጊዎች ነን። ጉዱ ካሳዎች ነን። ይሄንን እሳቤዎን እዚህ ቤት የነበሩት ሀዲስ አለማየሁ ለአፍታ ተነስተው ጥያቄውን እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ቢመለከቱ ምነው የአብዬን ወደ እምዬ የሚሉ ይመስለኛል።

መንግሥታችን ለትችት “ለክርቲክስ” በጣም በጣም ክፍት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ስልክ ያለው ማይክ የያዘው ሁሉ የሚናገርበት ነው ይሄ ዘመን። ሃሳብ በመግለጽ ሰው ይታሰራል ላሉት። እርስዎ እዚህ ፓርላማ አካባቢ ከመቅረብዎ በፊት የዚህ ፓርላማ አባል ነበርኩኝ። ቅድም እንዳደረጉት አይነት ግላጭ ስድብ አይፈቀድም ፓርላማ ውስጥ። ነበርንበት፤ እናውቀዋለን።

ሰው በንግግሩ የሚታሰር ከሆነ ጦረኛ፣ ግጭት ጠማቂ፣ ጆሮ የሌለው ከሚል በላይ ስድብ ምን አለ? እዚህ ፊትለፊታችን ሆነው እየተናገሩ እንኳን ካልታሰሩ ሰው በንግግሩ ብቻ አይታሰርም ማለት ነው። ጦረኛ ግጭት ጠማቂ ጆሮ አልቦች ካሉ በኋላ ልክ እናስገባችኋለን በትጥቅ በሁለት ሳምንት አራት ኪሎ እንገባለን ብለው ቢጨምሩበት ግን እርስዎም አይቀርልዎትም ነበር። በመሳደብ አይደለም ፤ ከዚህ አልፎ በኃይል በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት መናድ ሲጨመርበት ነው ጸብ የሚመጣው።

“ዩቲዩብ” ላይ የተናገረው ሁሉ ጋዜጠኛ ሆኖ፤ ጋዜጠኞች ታሰሩ ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይታዘባል፤ እንደዚህ ዘመን ከፓርላማ ውስጥ ከፓርላማ ውጪ ሰው እንዳሻው የሚናገርበት ዘመን፤ ሁሉም ጉዳይ ፖለቲካ የሆነበት ዘመን ያለ አይመስለኝም። ይሄ ሲባል ይሄ መንግሥት ቅዱስ ነው፣ ምንም አይነት እንከን የለውም፣ ሥራው ሁሉ የተቀደሰ ነው ብዬ ልመፃደቅ አልፈልግም። እርሶ ካቀረቧቸው እሳቤ ውስጥ መፈተሽ ያለባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። በእስርም፣ በክስ ሂደትም በሌላም ጉዳይ መንግሥት ሁልጊዜ እራሱን ክፍት አድርጎ መፈተሽ አለበት። እንከን የለኝም የሚል መንግሥት አያድግም።

ነገር ግን ሚዛን ሲጠፋ፣ ለሚሰማውም ትውልድ፣ ለእርስዎም ፓርቲ ጉዳት ያለው ስለመሰለኝ ነው። ምክንያቱም አሁን ያለው መንግሥት የእርስዎ ፓርቲ መንግሥት ሆኖ ያቋቋመው ነው። የእርስዎ ፓርቲ ሊቀመንበር የእኔ ካቢኔ አባል ናቸው። የእርስዎ ፓርቲ አመራሮች በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ አመራሮች ናቸው። በጋራ የምንመራው መንግሥት ነው። እናንተም ስላመናችሁበት፣ እኛም ስላመንበት፣ ሰዎችም ስለሆንን ስንፍናዎች ይኖራሉ፤ ድካሞች ይኖራሉ። መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ።

ለምሳሌ ጦርነትን በሚመለከት ወደ ኋላ መለስ ብለው የኢትዮጵያን የመቶ ዓመት ታሪክ ይመልከቱ። በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሰባት ዓመት ሙሉ ከአንድም ጎረቤት ሀገር ጋር ያልተዋጋ ብቸኛ መንግሥት የኛ መንግሥት ነው። ባለፉት ሰባት ዓመታት ከየትኛውም ጎረቤት ጋር አንድ ጥይት አልተኮስንም። እኔ በታሪክ የማውቀውን ሳይሆን በአካል የማውቀውን ላስታውስዎ በ1983 ዓ.ም ገበቶ በ1984 ዓ.ም መንግሥት የመሠረተ ነው የኢህአዴግ መንግሥት። እስከ 1990ዓ.ም ባለው ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መጀመሪያ ከደቡብ ሱዳን ኢታንግ ላይ ቀጥሎ ከሱዳን ቀጥሎ ከኤርትራ ውጊያ አካሂዷል። በኋላ ላይ የሱማሊያውን ሳይጨምረው ማለት ነው። በደርግም የሚያውቁት ታሪክ ነው። በንጉሡ ጊዜም እንዲሁ።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ከአንድም ጎረቤት ጋር ያልተዋጋነው የሚያጋጩ ነገሮች ስለሌሉ ሳይሆን ግጭት ጉዳት አምጪ እንደሆነ ስለምናውቅ፤ ስላደግንበት ነው። በሀገር ውስጥ ቤኒሻንጉል ያሉ ታጣቂዎችን በሰላም ተደራድረን አላስገባንም? ይሄ አይታወቅም? ምክር ቤቱ አያውቀውም? ኦሮሚያ ውስጥ በርካታ ሴክቶች እንደገቡ አይታወቅም? በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ሶስት ቀናት ብቻ ከሰባ በላይ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ገብተዋል። ሁለት ሶስት ቀን ብቻ። በአፋር ክልል፣ በሶማሌ ክልል በርካታ የሰላም ድርድሮች ተካሂደዋል። ለዚህም ነው መጠነኛ ለውጥ፣ መሻሻሎች ያሉት።

ስለታሰሩት እስረኞች ያነሱት፤ ይህ ፓርላማ እነዚህን እስረኞች ስንቴ ጎበኛቸው? ሄዳችሁ አላያችሁም? አልጎበኛችሁም? ስትጎበኙ በሚዲያ አይቻለሁ። ድሮ እንኳን ፓርላማ በእንደዚህ አይነት ጉዳይ የታሰሩ ሰዎች መጎብኘት ይቅርና ታሳሪዎቹ እራሳቸው ከእስር ሲፈቱ የት ቦታ እንደታሰሩ አያውቁም። ተሸፍነው ገብተው

ተሸፍነው ይወጣሉ። ይሄማ ተቀይሯል፤ ተሻሽሏል ለውጥ አለ። የሚቀር ነገር አለ? አዎ አለ። ጀማሪዎች ስለሆንን ማረም አለብን። ግን ለውድድር የሚቀርብ አይደለም።

ብልፅግና በየትኛውም መመዘኛ ከኢህአዴግ ጋር አይወዳደርም። በአደረጃጀቱ፣ በእሳቤው፣ በተግባሩ፣ በሚመራበት መርህ ለውድድር የሚቀርብ አይደለም። ይሄን ለእናንተ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ያህል ስለሆነ አልፈልገውም። እኛ ተመርጠን ሳለ፣ ሙሉ ለሙሉ ብቻችንን መንግሥት መሆን ስንችል፣ በሕግም በሞራልም የለም ለሰላማችን ስንል ከሚፎካከሩ ሃይሎች ጋር በጋራ መንግሥት እንፍጠር ያልነው ሰላም ፍለጋ ነው። የታጠቀ ሃይል ሁሉ በነፃነት ሳይጠየቅ ይግባ ብለን ያወጅነው ሰላም ፍለጋ ነው። በየመድረኩ ሰላም ሰላም የምንለው የሰላም ፋይዳ ስለሚገባን ነው።

አካታች ብሄራዊ ምክክር ኢትዮጵያ ውስጥ ሲለመን የከረመ አጀንዳ ነው። ጠቃሚ ነው ፤ በሺህ የሚቆጠር ሰው ማንኛውንም ሃሳብ በነፃነት እያነሳበት ያለ አውድ ነው። ይሄ መጠናከር አለበት፤ ጠቃሚ ነው። በአንድ በኩል ችግር አለ፣ ሕገመንግሥቱ ይቀደድ ይባላል። የለም እኛ አንቀድም ሕዝብ አወያይተን አማክረን የሁሉንም ይሁንታ አግኝቶ ነው የሚቀየረው ሲባል ሂደቱን /ፕሮሰሱን/ አንፈልግም ይባላል። አብሮ አይሄድም ።

ለምሳሌ ከፍትህ ሥርዓት ጋር ተያይዞ የተነሳው በአንድ በኩል ክስ አቅርባችሁ ክሱ ተጓተተ ይባላል። የእኛ ሥራ ወንጀለኛ ላልነው ሰው ክስ ማቅረብ ነው። መልሰን ፍርድ የምናስፈርድ ከሆነ የሚታሰበው “የቼክ ኤንድ ባላንስ” ጠፋ ማለት ነው። ባይከሰሱ ሳይከሰሱ ታሰሩ ይባላል። ታስረው ከተከሰሱ ግን መንግሥት ሚናውን እየተወጣ እንዳለ ቢወሰድ ጥሩ ይመስለኛል።

ይሄ ሆኖ ነፃነት ለማስተዳደር ችግር አለ። ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ሕግን በቅጡ ልምምድ ስላልነበረን አሁን እንቸገራለን። ለዛም መንግሥት በብዙ መታገስ ይኖርበታል። ባለፈው ፓርላማ ላይ ድርድር እያካሄድን ነው ከተቃዋሚዎች ጋር ብያችሁ ነበር። ከኦነጎችም ፣ ከአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎችም ጋር ድርድሮች ነበሩ። በነገራችን ላይ በአማራም፣ በኦሮሚያም፣ በየትኛውም ጎጥ ያለ የጎበዝ አለቃ፣ በየትኛውም ጎጥ ያለ በግራም በቀኝም ይደራደራል። እኔ አደለሁም እሱ ነው ይባባላል እንጂ፤ ሲወጣ የትኛውም ቦታ ይደራደራል። ሽማግሌ ይልካል። ልክ እኔ ካልኩ በኋላ የሚደራደረው “ኤክስ” ነው፤ የምደራደረው እኔ አይደለሁም ብሎ የሚከራከረው እራሱ ተደራዳሪው አካል ነው።

መንግሥት ሁልጊዜ እጁ የተዘረጋ ነው። በድርድር በሰላም ጉዳያችንን ለመፍታት ትልቅ ፍላጎት አለን፤ ግጭት ጥቅም ስለሌለው። ዓላማውን ስለማያሳካ አምስትም ዓመት ሆነ ስድስትም ዓመት ሆነ ብንዋጋ ዓላማውን ስለማያሳካ፤ ማንም ሰው አራት ኪሎ ስለማይደርስ ዋጋ የለውም። ዓላማ ለሌለው ነገር ደግሞ መጋደል ተገቢ ነው ብለን አናስብም። ሰላሙን ከማንም በላይ እኛ የምንፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ቢታሰብ።

ሁሉ ነገር ጨለማ ነው፣ ሁሉ ነገር ጥፋት ነው፤ ሁሉ ነገር አዘቅት ነው፤ ሁሉ ነገር የለም ላሉት ክቡር ዶክተር ደሳለኝ እኔ ለእርስዎ ነው ያዘንኩት። ምክንያቱም በዚህ ሁሉ ጨለምተኝነት በዚህ ሁሉ “ፔሲስሚዝም” ድንገት ዕድል ቢቀናዎት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንድን ነው የሚሰጡት፤ እርስዎ በጨለማ ተውጠው። ከጨለማ ብርሃን አይወጣ፤ ከጭንቀት ብርሃን አይወጣ፤ ተስፋን እንዴት አይሰንቅም።

ይሄን ይሄን አልቻላችሁም እኔ መጥቼ እቀይረዋለሁ እንኳን ቢሉን ነው የሚሻለው እንጂ፤ ሁሉ ነገር ጭለማ ከሆነ ጥሩ አይደለም። ፖሊቲካ የሚፈለገው በጭለማ ውስጥ፣ በችግር ውስጥ ተስፋን ማሳየት ነው። ለውጥን ማሳየት ነው። ወደዚያ ሰውን መምራት ነው። መጨበጥ ነው። እንጂ ችግር ብቻ መናገር አይደለምና የምንውልበት፣ የምንሰማው፣ የምንነጋገርበት ጉዳይ በገደል ማሚቶ ተመልሶ እያስተጋባብን እሱን ነገር እየኖርነው እንዳይሆን ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው ለማለት ነው።

ይሄን ሁሉ የመለስኩት እርስዎ ምላሽ እንደማይፈልጉ ቢናገሩም ለተከበረው ምክር ቤት ክብር ሲባል አንዳንድ ጉዳይ ቢታይ ብዬ ነው። ካነሷቸው ጫፍ የወጡ ሂሶች መካከልም ቢሆን ለእኛ ጠቃሚ የሆኑትን ጉዳዮች ፈትሸን እንወስዳለን፤ ማደግ ስለምንፈልግ፣ መለወጥ ስለምንፈልግ። ከማንም ወገን የሚነሳ ሂስ በግርድፉ መጣል አንፈልግም። ሚዛናዊነት ግን ከእርስዎና ከመሰሎችዎ እንጠብቃለን ለማለት ነው።

የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚመለከት ታሪካዊ ስምምነት ነው። ለብዙዎች ልምድ የሚሰጥ ስምምነት ነው። ያለቀ ጦርነት፣ ያሸነፍነውን ጦርነት ነው አቁመን ሰላም ያመጣነው። ለሰላም ያለንን ከፍተኛ ጉጉት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ማንም ሰው ቢያገላብጥ ፤መንግሥት እየተዋጋ ፤ እያሸነፈ መቀሌን ለመቆጣጠር አንድ ሁለት ቀን ሲቀረው ለሰላም ድርድር አይቀመጥም። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የለም። ይህ ለምን ሆነ ሰላም ስለሚያስፈልግ። በዚያ ሂደት ውስጥ በቀሩት ቀናት ውስጥ አምስትም፣ አስርም፣ ሃያ ሰው የሚሞት ከሆነ ወገን ነው የሚሞተውና ያ መቅረቱ ጠቃሚ ስለሆነ ነው ድርድሩ ያስፈለገው።

ድርድሩ በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታዎች አምጥቷል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም አይነት ውጊያ አልነበረም፤ ትልቅ ነገር ነው። የትግራይ ሕዝብ በውጊያው ጊዜ አገልግሎት አያገኝም። መብራት አልነበረውም፤ የባንክ አገልግሎት አያገኝም፤ የትራንስፖርት አገልግሎት አያገኝም፤ በርካታ ችግሮች ነበሩበት። መንግሥት እንደ መንግሥት ፈርሷል። ያንን መልሶ የሚያቋቁምና መሠረታዊ አገልግሎቶችን የሚያስቀጥል አስተዳደር መፈጠሩ በጣም ጠቃሚና ውጤታማ ተደርጎ ይወሰዳል።

ያም ሆኖ በስምምነቱ መሠረት የሚጠበቁ በበቂ ያልተፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። አንዱ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሥራ /ዲዲአር ነው፤ የተወሰኑ ሙከራዎች ቢኖሩም ዲዲአር በተሟላ መንገድ አልተፈጸመም። ዲዲአር አለመፈጸሙ በመጀመሪያ የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ነው። ማስተማር፣ መቆፈር እና ሀገር ማልማት የሚችሉ ወጣቶች በወታደር ስም ተቀምጠው ለትግራይ ክልል የሚሄደውን በጀት እንዳለ ለቀለብ የሚያውሉት ከሆነ ትግራይ ውስጥ ልማት አይመጣም ማለት ነው።

በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው ለእነዚህ ሰዎች የሚውለው በየዓመቱ፤ በየወሩ። ያ ገንዘብ ለልማት ቢውል በርካታ ጠቀሜታ ሊያመጣ ይችላል። ዲዲአሩ ለአጠቃላይ ሰላም ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ በተሟላ መንገድ መፈጸም ይኖርበታል።

የተፈናቀሉትን በሚመለከት በራያና በጸለምት ጥሩ ሥራ ተሠርቷል። በወልቃይት አካባቢ የተጀመሩ ጉዳዮች በተፈለገው ደረጃ አልሄዱም። አሁን በእኛ በኩል ማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት የፌዴራል መንግሥት ከነገ ጀምሮም ቢሆን የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመመለስ ዝግጁ ነው፤ በዚያ ወገን “ሳይድ” በቂ ትብብር ከተደረገልን፤ ፍላጎታችን ዜጎች ወደ ቀዬ፣ መንደራቸው ሄደው የተለመደ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ነው።

ያ እንዳይሆን እያደረገ ያለው ሰዋዊነትና ፖለቲካ በጣም በመቀላቀሉ ነው ። በተፈናቀሉ ሰዎች ላይ የሚሠራ ፖለቲካ ጉዳት አለው። ይሄን ከፖለቲካ ነጥለን እንደ ሰው ዜጎች ናቸው የሚጎዱት ብለን በትብብር መንፈስ ወደ ነበሩበት ቢመለሱ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ቦታ ስላላት አሳሳቢ አይደለም። ከዚያ በኋላ የሚከተሉ ጉዳዮች ደግሞ በድርድር በውይይት እንደፈጸሙ ማድረግ ይቻላል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ በምክትል ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ እና ጻድቃን ገብረትንሳኤ የሚመራው አስተዳደር ሁለት ዓመት ተጨማሪ ጦርነት እንዳይፈጠር፤ ሁለት ዓመት ያሉ ጥያቄዎች በንግግር እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ምንም እንኳን ቀድሞ በነበረው ውጊያ ብንወቅሳቸውም፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰጡት አመራር ግን ማድነቅ ማመስገን እንፈልጋለን። ተጨማሪ ውጊያ እንዳይነሳ ሙከራ አድርገዋል፤ ጥሩ ነገር ነው እሱ።

ያ የሰጠናቸው የሁለት ዓመት ጊዜ አልቋል። ስላለቀ የሕግ ማሻሻያ የሚፈልግ ጉዳይ አለ። ተጨማሪ ጊዜ ስለሚጠይቅ ሕግ መሻሻል አለበት። ሕግ ሲሻሻል ደግሞ እስከ አሁን የነበረው አፈጻጸም መገምገም አለበት። ተገምግሞ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎ የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚያከብር መንገድ አስተዳደሩ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ሥራውን እየሠራ ሕዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀትና ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት የማድረግ ሂደት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።

ይሄን ለማድረግ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ እንዲሁም ጻድቃን ገብረትንሳኤ ጋር ልዩ ልዩ ውይይቶች ስናደርግ ቆይተን የተለያዩ ፕሮፖዛሎች ቀርበዋል። ከእነሱ በተጨማሪ ከፓርቲዎች ጋር ከቲፒኤልኤፍም ከሌሎች ጋር እያደረግን ነው። በዚህ ንግግር መሠረት ህግ አሻሽለን ለሚቀጥለው አንድ ዓመት መጠነኛ ማሻሻያ አድርገን አስተዳደሩ ይቀጥላል የሚል እምነት ነው በእኛ በኩል ያለው። ሲቀጥል በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ሊካሄድ ይችላል። ግለሰቦች ሊቀያየሩ ይችላሉ፤ የነበረው ሥራቸው ተገምግሞ። በጠንካራ ጎናቸው ተሞግሰው በደካማ ጎናቸው ተወቅሰው የሚቀያየሩ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ።

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደማይፈልግ እኔም ሳወያያቸው በተለያየ መንገድ ገልፀዋል። ጦርነት ለትግራይ ከእንግዲህ አያስፈልግም። ማንኛውም ጉዳይ ካለ በንግግር በውይይት መፍታት ይቻላል። ትግራይም ሆነ መላው ኢትዮጵያ ጦርነት አይፈልጉም፣ አይፈጠርም ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።

አልፎ አልፎ በግለሰቦች ደረጃ መከላከያ በአማራና ኦሮሚያ ተበትኗል ተወጥሯልና ጊዜው አሁን ነው ብለው የሚያስቡ ግለሰቦች እንዳሉ እንሰማለን። ምክሬ አይመስለኝም፤ አያዋጣም ተውት ነው። እንደዛ አይመስለኝም። አያዋጣም፤ ድሮም አላዋጣም አሁንም አያዋጣም። የሚያዋጣው መነጋገር ብቻ ነው። በንግግር ውስጥ ይመለሳል።

በእኛ በኩል ነገር ማጋጋል ብንፈልግ ፍላጎታችን እንደተባለው ጦርነት ጨማቂዎች ብንሆን ኖሮ በቂ ምክንያቶች ነበሩን፤ ግን አንፈልግም። ከእያንዳንዷ ቀን ሰላም ስለምናተርፍ አብዝተን የምንሠራው ለሰላም ነው።

በትግራይ ያለው ሁኔታ በንግግርና በውይይት በቅርቡ ከገመገምን በኋላ የሚቋቋመው መንግሥት እስከ ምርጫ የተሻለ ሥራ እንደሚሠራ በተለይም ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለሱ ሥራ /የዲዲ አሩን/ እና የተፈናቀሉ በመመለስ የሕዝብ የልማት ጥያቄ በመመለስ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተስፋ ይደረጋል። ከሁሉም ሃይሎች ጋር እየተነጋገርን ነው። ስናጠቃልል በሚቀጥሉት ጊዜአት ለሕዝብ የሚገለጽ ይሆናል።

ፍትህን በሚመለከት ፍትህ አሁናዊና ውርስ ችግር አለበት። በውርስም የምታውቁት ችግር አለበት፤ አሁናዊም ችግር አለበት። ሕግ ማሻሻያ ለማድረግ በጣም ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለውጦች በትንሹም ቢሆን እየታዩ ነው። በተለይ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም “አይሲቲን” ለመገንባትና “ዋይድ ኤሪያን” ለመሥራት ፍርድ ቤት አመራሮች ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። በቅርቡም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። ያ የፍትህ ሥርዓቱን በተለይ ከችሎት ጋር ተያይዞ ያለውን ከዳታ ጋር ተያያይዞ ያለውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በኛ በኩል ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለማስፋት ሞክረናል። ችግሩን ለመፍታት። ሪፎርሙን ግን በበቂና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት ከኔ ይልቅ እናንተን መጠየቅ የሚሻል ይመስለኛል። ፍርድ ቤት የምትመሩት እናንተ ስለሆናችሁ በቅርበት፤ ጉዳዩ እንዲሻሻል ብታደርጉ በኛ በኩል የፍትህ ሚኒስቴር ፣ፖሊስ እና አቃቤ ሕግ በኩል ያለውን ነገር ለማየት እየሞከርን ነው ፣ እኛ እንቀጥላለን። ፍርድቤትን በሚመለከት ግን የእናንተ ድጋፍ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ትምህርትን በሚመለከት የተነሳው ትክክለኛ ጥያቄ ነው። የተከበረው ምክርቤት እንዲገነዘብ የምፈልገው ነገር በየአካባቢው የምንዋጋቸው ሰዎች የድንቁርና ጌቶች ናቸው። የምንዋጋው ከድንቁርና ጌቶች ጋር ነው። እነዚህ ሰዎች አትማሩ፤ አትታከሙ፤ አትረሱ የሚሉ ናቸው። የሚገርመው አንድ አካባቢ ላይ የኤችአይቪ ፣ የስኳር እና የወባ መድሃኒት ከፋርማሲ አውጥተው የሚደፉ፣ ግን ለዛ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ሃይሎች ያሉበት ነው።

ማዳበሪያ ለሕዝቡ እንዳይደርስ የሚጥሩ ናቸው። ትምህርት ምን ያደርግላቸዋል የሚሉ ናቸው ፤ የጅብ ቆዳ እጃቸው ላይ አስረው ጥይት አይመታንም ብለው የሚታገሉ ሰዎች ትምህርት ምን ያደርግላቸዋል።

በቅርቡ አንድ ቦታ ላይ የጅብ ግልገል ተሸክመው ሲሄዱ ተገኙ ፤ ለምን ሲባል ጥይት እንዳይመታን አሉ። እና እነዚህ የድንቁርና ጌቶች ትምህርት እንዳይስፋፋ በብዙ እየጎዱን ይገኛሉ።

ልጆቻችን እንዳይማሩ ፣ የድሮ ሽፍቶች እንኳን በየአካባቢያቸው ያሉ መድረሳና አብነት ትምህርት ቤቶችን አይነኩም። ሽፍቶች ናቸው መድረሳና የአብነት ትምህርት ቤት አይነኩም። የአሁኖቹ ከነሱም የባሱ ናቸው።

ሎሬት ፀጋዬ “እንዳይነግርህ አንዳች እውነት” የሚል ግጥም አለው። በግርግር ፣ በጩኸት ፣ በመረበሽ ፣ዝግ ብሎ ባለማሰብ ከእውነት ለመደበቅ የሚደረግ ሙከራ ስለላ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ነው።

በእኛ በኩል በተገኘው አጋጣሚ ሰፋፊ የትምህርት ቤት ጥገናዎችን፤ በተለይ ሁላችሁም እንደምታውቁት … “ኪንደርጋርደን” ላይ ዜሮ ክፍል ላይ ሰፋፊ ሥራ እሠራን ነው። ከመፅሀፍ ሽያጭም ሳይቀር በአብዛኛው የገነባነው ትምህርት ቤት ነው። ትምህርት ያስፈልጋል የሚል የፀና እምነት ስላለን ነው። ይሄን ወደፊም በሚቻል አጋጣሚ ሁሉ ከሕዝባችን ጋር በመሆን እያሰፋን የምንሄደው ጉዳይ ይሆናል።

ጤናን በሚመለከት ስጋት አመራር /”አርሊ ዋርኒንግ”/ ላይ ችግር አለ ለተባለው ችግር አለ ግን ችግሩን ለመሻገር ሰፋፊ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ቀድመው የሚተነብዩ ማእከሎች /ሴንተሮች/ አሉ። በ “ሲዲሲ” ጨምር ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። በዚህም የብዙ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ድጋፍ እየተደረገ ነው። ነገር ግን መድሃኒት ስለማናመርት፣ ፈጥነን የመድረስ አቅማችን ውስን ስለሆነ ፣ ቴክኖሎጂን በበቂ ሁኔታ ስለማንጠቀም አሁንም ችግሮች አሉ ፣ ገምግመናል።

አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ሰፋፊ ሥራዎች ተጀምረዋል ውጤት እንደሚመጣ ይጠበቃል።

መድሃኒት ግን የማያመርት ሀገር ነዳጅ የማያመርት ሀገር ማዳበሪያ የማያመርት ሀገር ሁልጊዜም ቢሆን ወይ በግዢ ፣ወይ በትራንስፖርት ፣ወይ በጊዜ መሰቃየቱ አይቀርም። መፍትሔው ደረጃ በደረጃ እያመረቱ የራስን ችግር በራስ እየመለሱ መሄድ ይሆናል።

ተፈናቃዮችን በሚመለከት ገፊ የተግባርና የአመለካከት ችግሮች አሉ። በርካታ ዜጎች እየተመለሱ ነው፣ አሁንም የተፈናቀለ ቁጥር ማጋነን ፣ የተሳሳተ መረጃ መስጠት ፣ እንዳይመለሱ መቀስቀስ የተለመደ የወል ተግባር ሆኗል። ብዙ ቦታ ላይ የሚታይ ተግባር ሆኗል። በየቦታው ያሉ ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ ጥረቶች ይደረጋሉ።

የሚመለሱትን እየደገፍን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት ይደረጋል። እስካሁን የተገኘውን ውጤት በዚያው መንገድ እያጠናከርን እንሄዳለን።

ፕሮጀክቶችን በሚመለከት በየወረዳው ከመንገድ፣ ከግድብ ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎቹን እንመረምራቸዋለን፤ ችግር ይኖራል ብለን ስለምናስብ እንፈትሻቸዋለን።

ነገር ግን የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘብ የሚያስፈልገው ያዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ የተዘራው የድንጋይ መዓት ብዙ ነው። የወረስነው እዳና መሠረተ ድንጋይ ነው።

መጀመር እንደ ሥራ ተወስዶ መጨረስን ታሳቢ ያላደረጉ በጣም በርካታ ሥራዎች በየቦታው ተጀምረዋል። ስንሄድ መንግሥት ቃል ገብቶ ፣ መንግሥት እንዲህ አድርጎ እንባላለን። ያን ሁሉ መመለስ ጊዜም ገንዘብም ይጠይቃል። ያም ሆኖ ግን እኛ የጀመርናቸውን ሥራዎች ባፋጣኝ ለመጨረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው።

አዋጅ 1210 የ2012ቱ ፕሮጀክትን በሚመለከት ፖሊሲዎቻችን ከነሱ የተቀዱት መመሪያዎቻችን አጥንተን እንድንገባ ጀምረን እንድንጨርስ የሚያስገድዱ ናቸው። ግን አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮጀክት ጀምሮ በመጨረስ ዙሪያ በጣም ብዙ መማር የሚገቡን ነገሮች እንዳሉ ያሳያል።

ማንኛውም ሥራ ፕሮጀክት ነው፤ አስቀድመን አጥንተን አቅማችንን አውቀን ጀምረን ተከታትለን የማንጨርሰው ከሆነ መልሰን ዕዳ ይሆናል ፣መልሶ ኪሳራ ይሆናል።

ውጤቶች ያየንባቸው ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚጠበቁ እናምናለን። በዚያው አግባብ እየፈተሽን፣ እያረምን የሕዝቡን ጥያቄ እየመለስን ለመሄድ አቅም በፈቀደ መጠን ጥረት እናደርጋለን።

ህዳሴን በሚመለከት እንደተባለው ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው። አንድ ብር ርዳታም ሆነ ብድር ከውጪ ያልተገኘበት ነው፤ ብዙ ፈተና አይተንበታል።

ቅድም ማዳበሪያ ላይ እንዳነሳሁላችሁ ለህዳሴ የሚውሉ ግብዓቶች ከሁለት ወር ተኩል ያላነሰ ከጅቡቲ እስከ ህዳሴ አጅበን እየወሰድን እየሠራን ነው። ሁለት ወር ተኩል እያንዳንዱን መኪና የገንዘቡ ሳያንስ የውጪ ጫናው ሳያንስ ከተገዛና ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ያንን ነገር ማድረስ በጣም አስቸጋሪ ነበር።

ፕሮጀክት ላይ ቅድም አንስቼ የተውኩት ጉዳይ አንዱ ፤ያለብን ፈተና ሁሉም ጋር ሳይሆን አንዳንድ አካባቢ ሕዝቡ መንገድ ካልተሠራልኝ፣ ድልድይ ካልተሠራልኝ ብሎ ከጠየቀ በኋላ ፕሮጀክቱ ጨረታ ወጥቶ ሥራው ሲጀመር ፤ ሰዎች ከዚያ አካባቢ መቅጠር አለባችሁ፤ ለአካባቢው ሰዎች ሥራ መፍጠር አለባችሁ ስለሚባል አንዳንድ ቦታ የተቀጠሩ ሾፌሮች የተቀጠሩበትን ኩባንያ መኪና ይዘው ወጥተው ከመኪናው ውስጥ ነዳጅ በጀሪካን ቀድተው ይሸጣሉ። የከፋው ደግሞ ሾፌር መኪናውን አቁሞ ሁሉንም ጎማዎች ፈትቶ መኪናውን ጥሎ ጎማውን ይዞ የሄደበት ቦታም አለ። አንዳንድ ቦታ ደግሞ እርሻ ያቃጥላሉ፤ የግለሰብ የእርሻ ኢንቨስትመንት ያቃጥላሉ።

የእኛ የልማት ፍላጎት ለካሳ ጥያቄ፣ የእኛ የልማት ፍላጎት ጎማ ለመስረቅ አይደለም፤ ይህንን ማህበረሰቡ መፈተሽ አለበት። ገንዘቡ የራሱ ነው ፤የራሱ ሀገር ሀብት በሌላ መንገድ ሲዘረፍ እያየ መተው የለበትም።

ህዳሴ ላይም ብዙ መከራ ታይቷል። ክቡር አቶ መሃመድ እንዳነሱት ህዳሴን በተመለከተ ቢበዛ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በጋራ ሪቫን እንቆርጣለን። ለእዚህ ጊዜ የምንወስድበት ምክንያት ዝግጅት ስለሚፈልግና አካባቢውም ሞቃታማ ስለሆነና የክረምቱን ዝናብ ስለምንፈልገው ብቻ ይሆናል። በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ታሪክ ሆኖ የሚያልፍ ይሆናል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከግብጽ ጋር ባለው ሁኔታ የቀድሞውን የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና የደህንነት ሹም ከአንዴም ሁለቴ አናግሬያቸው ነበር። ህዳሴ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ ላይ የተለየ ችግር የሚያመጣ አይደለም፤ የእኛ ዓላማ ኢነርጂ ማምረት ነው፤ እናንተን መጉዳት እኛ አንፈልግም ስላቸው ስጋታቸው ድርቅ እንደሆነ አነሱልኝ።

ድርቅ ቢያጋጥመን የሚል ስጋት አነሱ፤ ድርቅ እኮ ያጋጥማል የሚባለው በኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ደርቆ ግብጽ ቢዘንብ ዋጋ የለውም የዓባይ ውሃ ከዚህ ስለሚሄድ። ግብጽ ድርቅ ኖሮ ኢትዮጵያ ደግሞ ዝናብ ካለ ውሃው ሁሌም አለ ማለት ነው። ድርቅ እንዳይኖር መከላከል ያለብን እዚህ ነው። ውሃው በበቂ እንዲሄድ።

ለዚያ ደግሞ አረንጓዴ ዐሻራ /ግሪን ሌጋሲ/ ብለናል፤ እኛ “ክላውድ ሲዲንግ” ብለናል፤ እኛ የዝናብ መጠን እንዲጨምር። ጉዳት አይደርስባችሁም፤ በዚህ መንገድ መንግሥታችሁን አሳምናችሁ በትብብር እንሥራ የሚል ፕሮፖዛል በተደጋጋሚ ቀርቦላቸዋል፤ እኔም አናግሬያቸዋለሁ፣ አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎችም ለፕሬዚዳንት አልሲሲ ካይሮ ላይ ቃል ገብተህ ነበር ይላሉ።

ያው እንደምታውቁት ቃል መግባት ብቻም ሳይሆን ቃል መፈጸም ባህላችን ለማድረግ ካለን ቁርጠኛ ፍላጎት ለፕሬዚዳንት አልሲሲ ያልኳቸው ህዳሴ ሲሞላ አንድ ሊትር ውሃ እንኳን ከአስዋን ግድብ አይጎድልም ነበር ያልኳቸው።

ህዳሴ መቶ በመቶ ሞልቷል ፤ አስዋን ግድብም መቶ በመቶ ሙሉ ነው፤ ቃሉ ተፈጽሟል ፤ የተካደ ነገር የለም ማለት ነው። እነዚያ ሚኒስትሩና የደህንነት ሃላፊው በወጉ ሥራቸውን ሠርተው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ትብብር መፍጠር ይቻል ነበር። አሁንም ከግብጽ ወንድሞቻችን ጋር በውይይት ይበልጥ አብረን መሥራት መደጋገፍ እንዳለብን እናምናለን።

የሚያጣላን የሚያጨቃጭቀን ገንዘባችንን እዚያና እዚህ የሚያስበትነን ጉዳይ አለ ብለን አናምንም። በትብብር አብረን ብንሠራ ሁለቱም ሕዝቦች ሀገራት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ግብጽና ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት አብረው የኖሩ ናቸው፤ አሁንም እስከ መጨረሻው ዘመን አብረው መኖራቸው አይቀርም ።

ይህን ዕውነት ተቀብለው በትብብር መንፈስ ቢሠሩ የእኛ መሻትና ፍላጎት ነው። አሁንም ለንግግርና ለውይይት አሁንም ህዳሴ ያለበትን ሁኔታ ለማየት በእኛ በኩል ክፍትና ፍላጎት ያለን መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እገልጻለሁ።

ህዳሴ የአፍሪካ ኩራት ነው፤ ህዳሴ ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት ነው። ህዳሴ ስህተትን ያረምንበት ነው፣ ህዳሴ በውስጣችን ያለውን ውድቀት ጨክነን ወስነን ያረምንበት ነው።

74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ የያዝንበት ነው፣ ከፍተኛ ኢነርጂ የምናመርትበት ነው። አፍሪካውያን ብድር ቢከለከሉ አፍሪካውያን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ቢደረግባቸው የራሳቸውን ሀብት በገዛ ዜጎቻቸው ማልማትና መቀየር እንደሚችሉ በተግባር የሚያስተምር ሥራ ነው።

ብልፅግና ለዚህ ሥራ ስኬት ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ኩራት እና ክብር ይሰማዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ለእናቱ ወግ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲ አንድ፣ ላሊበላ አንድ፣ አክሱም አንድ ወግ ስለሆነ ያን ወግ ሰብረን ማባዛት ደግሞ የዚህ ትውልድ ተግባር እንደሆነ እተማመናለሁ።

ዲፕሎማሲን በሚመለከት የባሕር በር ጉዳይ ዋናው ዓላማ ቀድሜ ከእናንተ ጋር እንደተወያየሁት የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ማንሸራሸር ነውርነቱ አክትሟል።

ከማንም ዓለም ጋር ስንነጋገር ትክክል ነው፣ በዓለም ላይ የእናንተን ያህል ቁጥር ኖሮት ትልቅ ሀገር ሆኖ የባሕር በር/ አክሰስ የሌለው ሀገር የለም። ነገር ግን በንግግርና በውይይት በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆን አለበት። ግጭት ውስጥ እንዳትገቡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይላሉ እንጂ አያስፈልግም የሚል ሰው በአብዛኛው ጠፍቷል።

ይሄ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው። ስለዓባይም ስለቀይ ባሕርም ማውራት ይቻላል፤ ስለዓባይም ስለቀይ ባሕርም “በዊን ዊን” መጠቀም ይቻላል። በጋራ መጠቀም ይቻላል የሚለው ትርክት/ ናሬሽን፣ ግልጽ ሆኗል።

አንዳንድ ሰዎች ይሄ መንግሥት ይሄንን ጉዳይ ያነሳው ለአጀንዳ ነው፣ ለፖለቲካ ነው፣ ለምርጫ ነው፣ እያሉ ሲያሙ ይሰማል። ግን ይሄ ሀሜት ውሃ አይቋጥርም፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የወደብ፣ የባሕር በር/ የሲ አክሰስ ጥያቄ ላለፉት አሥር አሥራ አምስት ዓመታት እንደ ፖለቲካል ዲስኮርስ ስንወያይበት የቆየንበት ጉዳይ ቢሆንም ቢያንስ ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት በመንግሥት ደረጃ ንግግር ከማድረጋችን በላይ ከመደመር ተከታታይ መጽሐፎች፣ የመጨረሻው የመደመር ትውልድ በ2014 የወጣው የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ሳይወጣ በፊት የታሸ ሥራ ነው፤ በመጨረሻው አካባቢ 240 ገጽ ላይ መልሳችሁ እዩት ። ‹‹የጂኦ ፖለቲካል ዕይታ ለውጥ›› ይላል ርዕሱ። የጂኦ ፖለቲካል ዕይታ መለወጥ አለበት የሚል እሳቤ ያነሳል።

ቀይ ባሕርን እና ዓባይን እያነሳ ቆይቶ ገጽ 245 ላይ ‹‹በሁለት የውሃ አካላት ሥር›› ይላል። መጽሐፍ እኮ ነው! ሦስት ዓመቱ ነው! ያን መጽሐፍ ለሁሉም ሰው አድለናል፤ ለጎረቤትም ለሁሉም ሰው አድለናል፤ ያውቁታል። የመንግሥት እሳቤ ሁለቱን ውሃ በሚመለከት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

የተከበረው ምክር ቤት ግን አንድ “ክሪቲካል” ነገር አስቦ እንዲገነዘበው የምፈልገው የዚህ የሁለቱ ውሃ ትርክት /ናሬሽን/ መደመር ከመጻፉ በፊትም ነበር፤ መደመር ላይ አልተቀመጠም፤ የመደመር መንገድ ላይ አልተቀመጠም፣ የመደመር ትውልድ ላይ ነው የተቀመጠው። የትውልድ ጉዳይ ስለሆነ ነው። “ኮንሺየስ” ነበርን! ትውልዱ ይሄንን ጉዳይ በሚገባ አይቶ ምላሽ መስጠት አለበት የሚል እምነት ነበር፤ በምሥጢር ሳይሆን በግልጽ የተጻፈ ነው፤ ማንም ሰው ማየት ይችላል።

የቀይ ባሕር ፍላጎታችን፤ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራ፣ ከኬንያ የሚያጣላ የሚያዋጋ መሆን የለበትም። የጋራ ሀብት ነው፤ 5 ሺህ የባሕር ጠረፍ / ሲ ሾር አለ እዚች ቀጣና ውስጥ። ለሁላችን በቂ ነው፣ ተነጋግረን፣ ተግባብተን፣ ሁላችንንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መፈጸም ይቻላል።

ሰሞኑን ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግጭት ይፈጠራል የሚሉ ስሞታዎች ይሰማሉ። ለተከበረው ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለኤርትራ ሕዝብና መንግሥት በዚህ ምክር ቤት ፊት ቆሜ ላረጋግጥ የምወደው ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም። ያላት ፍላጎት እንነጋገር ነው። በሰጥቶ በመቀበል መርህ፣ ሕዝቦችን በሚጠቅም መርህ፣ በገበያ መርህ ይሄንን ችግር እልባት እናብጅለት፤ ዛሬ ዝም ብለን ብናልፈው ነገ ጦስ ያመጣብናል።

እንጋፈጠው፣ እንወያይ ነው እንጂ እንዋጋ አይደለም! ውጊያ አያስፈልግም!

ብዙ ብዙ ክሶች ይሰማሉ፤ አብዛኛው ክስ ውሃ አይቋጥርም። የኤርትራ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው፣ የኤርትራ ሕዝብ ምስኪን ሕዝብ ነው፤ እንደ ኢትዮጵያ ለማደግ የሚፈልግ ሕዝብ ነው፤ የሚያስፈልገው ልማት ነው፤ ውጊያ አይደለም! ተባብረን መሥራት፣ ተባብረን መልማት ነው እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ ዕቅድ አይደለም።

በሌላ መንገድ፤ ኢትዮጵያ ላይ ማንም ሀገር ወረራ ሊፈጽም እና ከጀመርነው ሕልም ሊያስቆመን ይችላል የሚል ስጋት ደግሞ የለብንም። ጭራሽ ሥጋት የለብንም፤ ይሄም መሰመር አለበት። ማንም ደፍሮ አይሞክረውም! በቂ ዝግጅት ስላለን! የምንዘጋጀው ግን ውጊያ ለማስቀረት ስለሆነ በእኛ ተነሳሽነት/ ኢኒሼቲቭ /ከማንም ጋር የመዋጋት ፍላጎት የለንም።

እንደምታስታውሱት ከሶማሊያ ጋር ይዋጋሉ የሚሉ ብዙ ንግግሮች ነበሩ፤ የፈታንበትን መንገድ አይታችኋል። በሶማሊያና በኬንያ መካከል ችግር ሲፈጠር ዘለን የገባነው እኛ ነን፤ በሱዳን ወንድሞች መካከል ችግር ሲፈጠር ዘለን የገባነው እኛ ነን፣ ሳውዝ ሱዳን ችግር ሲፈጠር ዘለን የገባነው እኛ ነን፤ በአካባቢያችን ሰላም፣ ልማት እንዲመጣ ስለምንፈልግ! እስከዛሬ ከማንም ጋር አንድ ጥይት ተታኩሰን አናውቅም፤ ወደፊትም የእኛ ፍላጎት ይሄው እንዲቀጥል ነው።

ምንም አይነት ትንኮሳ ከየትኛውም ወገን መኖር የለበትም፤ ትንኮሳ ካለ ምላሹ ከፍተኛ ስለሚሆን! በእኛ ወገን ግን ትንኮሳ እንደማይኖር እያረጋገጥኩ የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው። ብልፅግና ኖረ አልኖረ፣ ይሄ ምክር ቤት ኖረ አልኖረ፣ 130 ሚሊዮን ሕዝብ፣ ኢኮኖሚው እያደገ ያለ ሕዝብ፣ መለወጥ እና ከድህነት መውጣት የሚፈልግ ሕዝብ፣ ጫፍ ጫፉ ተሰምሮ ተዘግቶበት እስር ቤት ሊቀመጥ አይችልም።

ይሄን ማንም ሰላም ወዳድ ነኝ የሚል የዓለም መንግሥት፣ ግለሰብ፣ ቡድን ከወንድሞቻችን ጋር አነጋግሮን በሕግ አግባብ፣ በቢዝነስ ተርም፣ የኢትዮጵያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ፣ ወንድሞቻችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል “አሚኬብል ሶሊዩሽን” እንዲፈጠር ለመላው ዓለም ጥሪ እናቀርባለን። እኛ የምንፈልገው በሰላም ችግራችን እንዲፈታ ማድረግ ነው።

የቀይ ባሕር ጉዳይ የማይፈታ ሕልም ነው፣ የሩቅ ጊዜ ህልም ነው፣ እንዴት እንደዚህ አይነት የሩቅ ጊዜ ህልም ይሄ መንግሥት ያስባል የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች አልፎ አልፎ ይደመጣሉ። ይሄ ዓለም አንድ ግለሰብ፣ የአንድ ግለሰብ ኩባንያ ማርስ ላይ ወጥቼ እወርሳለሁ በሚልበት ዓለም ውስጥ እየኖርን 30 እና 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለችን ቀይ ባሕር ለመንካት አናልምም ማለት የሚቻል አይመስለኝም።

እኛ ህልመኞች ነን፤ ሕልማችን ግን ብልፅግና ነው። ሕልማችን ልማት ነው፣ ህልማችን ውጤት ነው፣ ህልማችን ማደግ ነው፤ ብቻችንን አይደለም፤ እንደ አፍሪካ ማደግ ነው። ለዚህ ዕድገት ከአፍሪካ ወንድሞቻችን ጋር በትብብር በዓባይም፣ በስንዴም፣ በማዳበሪያም፣ በጋዝም፣ በወርቅም፣ በሌላውም ጉዳይ ተባብረን በጋራ እንድንለማ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

የጀመርነው የብልፅግና ጉዞ ይቀጥላል፤ ሰላማችን ይበልጥ እያደገ ይሄዳል። ለኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት የበለጠ የሚጓጉ የትኛውም ግለሰብና ቡድኖች ለንግግር መንግሥት ክፍት መሆኑን ተገንዝበው ሁልጊዜም በንግግር በውይይት ጉዳያቸውን ለመፍታት እንዲዘጋጁ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ሚዛን ሳንስት ለአዳዲስ ልማት በጋራ እንድንቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ፤ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You