ዋሊያዎቹ ፈርዖኖቹን ለመመከት ተዘጋጅተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብፅ አቻቸው ጋር ነገ ጨዋታቸውን በሞሮኮ ካዛብላንካ ያከናውናሉ:: ዋሊያዎቹ ለተቃራኒ ቡድን የተጋነነ ግምት በመስጠት ወደ ሜዳ እንደማይገቡም አምበሉ አስታውቋል::

አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ ለሚያስተናግዱት የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከግብፅ፣ ከጊኒ ቢሳው፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን እና ጅቡቲ ጋር መደልደሏ ይታወቃል። በዚህም የምድቡን አምስተኛ እና ስድስተኛ ጨዋታ በቀናት ልዩነት ታከናውናለች:: ዋልያዎቹ ነገ ከፈርዖኖቹ ጋር በሞሮኮ ለሚያደርጉት ጨዋታ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ለስድስት ቀናት ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው አንድ ተጫዋች በመቀነስ ከትናንት በስቲያ ሌሊት ወደ ሞሮኮ አቅንተዋል::

በአዲስ አበባ ስታዲየም የነበረው የቡድኑ ቆይታም አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ የተከናወነበት እንዲሁም ባለፉት ጨዋታዎች የነበሩበትን ክፍተት የማረም ሥራ የተከናወነበት መሆኑን አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከቡድኑ ጉዞው በፊት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቁሟል::

በመግለጫው ላይ የተገኘው የቡድኑ አምበል አስቻለው ታመነ በበኩሉ፣ ዋልያዎቹ ከውድድር ላይ ስለተሰባሰቡ ባለፉት ቀናት ጥሩ ዝግጅት ሲያከናውኑ መቆየቱን ገልጿል:: ዋሊያዎቹ ለተጋጣሚያቸው የተጋነነ ግምት ሰጥተው ወደ ሜዳ እንደማይገቡ የተናገረው የዋልያዎቹ አምበል፣ ‹‹በነበረን አጭር ጊዜ በተሟላ የሥልጠና ባለሙያዎች ጥሩ ዝግጅት በመደረጉ ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ላይ ይገኛል:: ከዚህ ቀደም ከግብፅ ጋር የነበረን ጨዋታም መነሳሻ ስለሚሆነን በዚያው ስሜት ጨዋታውን የምናደርግ ይሆናል:: አሁን ላይ ተጋጣሚን አጋነን አናይም፤ እንደከዚህ ቀደሙ ስንት ግብ ይቆጠርባቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ብሔራዊ ቡድን የለንም:: ባሸነፍንባቸውም ሆነ በተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ለግብፆች ቀላል ተፎካካሪ አልነበርንም:: በአውሮፓ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ስላሏቸው የተለየ ግምት አንሰጣቸውም፤ እግር ኳስ የሚፈቅደውን ነገር እናደርጋለን::›› ብሏል::

ከተጫዋቾች ምርጫ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄ የተነሳበት አሠልጣኝ መሳይ በበኩሉ፤ ተጫዋቾች ባላቸው ወቅታዊ አቋምና ቡድኑ ሊተገብረው ላቀደው አጨዋወት የሚሆኑትን እንደመረጠ አስረድቷል።

በደቡብ አፍሪካው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ የሚገኘውና ጨዋታዎች ላይ ሳይታይ የቆየው አጥቂው አቡበከር ናስርን በተመለከተም “ከክለቡ አሠልጣኝ ጋር በመነጋገር የነጥብ ጨዋታዎች ላይ ባይጫወትም ያለው ነገር ጥሩ እንደሆነ ነግሮን ነው መጥቶም በልምምድ ላይ ያለው ነገር ጥሩ ነው በደንብ ያግዘናል ብለን እናስባለን” ሲሉ ገልፀዋል።

ለአሁኑ ጨዋታ የሚረዱ የቀድሞ ጨዋታዎችን ከማየት ባለፈ ክፍተቶችን በመለየት ለማረም የሚያስችል ውይይት በማድረግ መዘጋጀታቸውንም አክሏል። በቴክኒክ፣ በሥነልቦና እና በአካል ብቃት ተጋጣሚን ማዕከል ያደረገ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፤ እንደ ቡድን በጋራ በመሥራት ላይ ትኩረት አድርጎ በምን መልክ ማጥቃትና መከላከል እንደሚቻልም ዝግጅት ተደርጓል::

አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሊቨርፑሉን ሞሐመድ ሳላህን እና የማንቸስተር ሲቲውን ኦማር ማርሙሽን ለማቆም ተዘጋጅተናል በማለትም ተናግረዋል። “እንደ ቡድን እንጫወታለን የተጋጣሚያችንን የፊት አጥቂዎች መሐመድ ሳላህ እና ኦማር ማርሙሽን ለማቆምም ሥራዎችን ሠርተናል” ብለዋል።

ቡድኑ ግብፅን ከገጠመ ከሦስት ቀን በኋላ ከጅቡቲ አቻው ጋር ይገናኛል:: ይኸውም ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳዋ የምታከናውነው ሲሆን፤ በአል ጀዲዳ ቤን መሐመድ አል አብዲ ስታዲየም ሞሮኮ ላይ ይደረጋል:: ጨዋታው የሚከናወንባቸው ስታዲየም እና የቡድኑ ወጪም በሞሮኮ የሚሸፈን ሲሆን፤ ከ40-50ሺ ዶላር እንደሚፈጅም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ጠቁመዋል:: ከዚህ ቀደም በተሠራው ሥራም ከግብፅ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ እስከ 70ሺ ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎም ይጠበቃል::

ግብፅ በአራት የምድቡ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነጥብ በመጋራት ምድቡን በ10 ነጥብ እየመራች ትገኛለች። 3 ነጥብ ያላት ኢትዮጵያ ደግሞ አንድ ነጥብ ያላትን ጅቡቲን አስከትላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች:: በአፍሪካ እግር ኳስ ጠንካራው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪውን የሊቨርፑሎች ኮከብ ሞሐመድ ሳላ፣ የማንቸስተር ሲቲው ኡማር ማርሙሽ እና መሐመድ ትሬዜጊትን ጨምሮ 6 ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ያካተተ መሆኑም ታውቋል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You