506 ሺህ ቱሪስቶች ሀዋሳ ከተማን ጎበኙ

ሀዋሳ፦ ባለፉት ስድስት ወራት 506 ሺህ ቱሪስቶች ሀዋሳ ከተማን መጎብኘታቸውን የሀዋሳ ከተማ ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ። “በሀዋሳ ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል” ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስና ከእውነት የራቀ መሆኑንም አመለከተ።

የሀዋሳ ከተማ ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ሁሪሶ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በተያዘው ዓመት የከተማዋ የቱሪዝም ፍሰት ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ ለእዚህም በከተማዋ የሚካሄዱ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ትልቁን ድርሻ አበርክተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከሀገር ውስጥና ከውጭ 506 ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ወደ ሀዋሳ ከተማ መግባታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ መቅደስ፤ ከእነዚህ ውስጥ 265 ሺህ አዳዲስ ጎብኚዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከተማዋን ከጎበኙ ቱሪስቶች 267 ሚሊዮን ብር በላይ በኢኮኖሚው መንቀሳቀሱን አስታውቀዋል። ገቢው ከማረፊያ ብቻ የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

በሀዋሳ ከተማ እና አካባቢው ያለው ሰላም ለቱሪዝም ፍሰቱ መጨመር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያመለከቱት ወይዘሮ መቅደስ፤ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለቱሪዝም እድገቱ የራሱን አስተዋፅዖ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ሰዓት ከሀዋሳ ሳውዝ ስፕሪንግ ሆቴል እስከ ሻፌታ አደባባይ ድረስ 2 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት እየተሠራ ይገኛል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ አመልክተዋል። ግንባታው ሲጠናቀቅ ለከተማዋ የተለየ ውበት ከመጨመር ባለፈ የጎብኚዎችን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀዋሳ ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል” ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስና ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

ከተማውና አካባቢው ምቹና ፍፁም ሰላማዊ በመሆኑ የትኛውም ግለሰብም ሆነ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲጎበኙ ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅድስት ገዛኸኝ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You