
እ.አ.አ 2023 የዓለም ጤና ድርጅት ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ሰዎች ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ። በተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በወባ፣ በተቅማጥ እና በሙቀት ጭንቀት በ 2030 እና 2050 መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በዓመት በግምት 250 ሺህ ተጨማሪ ሞት ያስከትላል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው ውጤቶች መካከል ከፍተኛ ድርቅ፣ የውሃ እጥረት፣ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ የባህር ከፍታ መጨመር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የበረዶ መቅለጥ፣ አስከፊ አውሎ ንፋስ እና የብዝሀ ህይወት መቀነስን ያጠቃልላል።
ሀገራችንም ችግሩ እንደ ሀገር ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ቅድሚያ በመገንዘብ የአየር ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ አረንጓዴ አሻራን እና ሌሎች መርሃ ግብሮችን ነድፋ እየሠራች ትገኛለች:: በእዚህም የደን ሽፋኗ 17 ነጥብ 2 በመቶ ከነበረበት እ.አ.አ ወደ 23 ነጥብ 6 ማደግ ችሏል::
መንግሥት በቀጣይም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ለመሥራት የሚያስችሉ ስምምነቶች ከተለያዩ አካላት ጋር እያደረግ ይገኛል:: ከእዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው ወር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥ ፎረም ተቋቁመዋል:: የፎረሙ መቋቋም ምን ፋይዳ ይኖረዋል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የዩኒቨርሲቲ መምህራኖችን አነጋግረናል::
ፐሮፌሰር በላይ ስማኒ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የፎረሙ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች በሌሎች ሀገራት ተደራዳሪዎች ሲመጡ በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የደመቀ ተሳትፎ አላቸው:: በኢትዮጵያ ግን በእውቀትና በገንዘብ ችግር ተሳትፏቸው በጣም ቀጭጮ እንደነበር፤ አሁን ላይ ግን በፎረሙ አማካኝነት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተሰባስበው ስለ አንድ ነገር ማውራት መቻላቸው ትልቅ እድል መሆኑን ያስረዳሉ::
የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን፤ ከመደራደር እና ገንዘብ ከማምጣቱ ረገድ ፖለቲካ መሆኑን አመልክተው፤ ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ስትራቴጂዎች ሲዘጋጁ፤ ስትራቴጂውን አርሞ ቅርጽ ከማስያዝ አኳያ የዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ::
ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ከሚገኘ ገቢ እና ኪሳራ ጋር ቀድሞ ምርምር በመሥራት ፖሊሲ ለሚያወጡ ተቋማት፣ የጥናት ሥራዎችን በማቅረብ ዩኒቨርሲቲዎች ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንዳላቸው አመልክተው፤ ይህም ከኢኮኖሚ አኳያ የሚታይ፤ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ እንደሆነ አመልክተዋል::
የአየር ንብረት ለውጥ ማህበራዊ ጉዳይ መሆኑን የሚያመለክቱት ፕሮፌሰሩ፤በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በቦረና፣ ሱማሌ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚታዩ የድርቅ አደጋዎች ትልቅ ማህበራዊ ቀውስ አማጭ ናቸው:: አብዛኛው ሰው ያልተረዳው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አብዛኛው ማህበራዊ ቀውስ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው ይላሉ::
የተፈጥሮ ሀብት ለማግኘት የሚደረግ እሽቅድድም የሰላም ችግር እያስከተለ በመሆኑ፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሰላም እና ደህንነት ጉዳይ ጭምር ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ አፍሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት ከአህጉሪቱ የሰላም ቀውስ 75 በመቶ የሚሆነው ከተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዘ እንጂ የፖለቲካ፣ የዘር እና የቋንቋ ጉዳይ እንዳልሆነ ጠቁመዋል::
ፐሮፌሰር በላይ እንደሚሉት፤ የዩኒቨርሲቲ ፎረሙ የተመሠረተው ፖሊሲዎች ላይ ተጽእኖ ማድረስ የሚችል እውቀቶችን እና ምርምሮችን ማውጣት እንዲችል ነው:: ይህን ማድረግ የሚቻለው በሳይንስ ያልተደገፉ ቅድመ ግምቶችን ማውጣት ሲቻል ነው፤ ለእዚህ ደግሞ አንድ ተቋም ብቻ ለውጥ አያመጣም::
ኢትዮጵያ የተለያየ ሥነምህዳር ያላት ሀገር እንደመሆኗ፤ ይህን የተለያየ ሥነምህዳር፣ ባህል እና ኢኮኖሚ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መሥራት የሚቻለው በተለያየ መንገድ ነው:: በእዚህ መሠረት በየቦታው ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ባለድርሻ አካል አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ያስረዳሉ::
ስለ አየር ንብረት ለውጥ ስናስተምር፤ የምናስተምረው ስለዘላኪ ልማት ነው:: በመሆኑም የዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያው ሥራ በአካዳሚው ዘርፍ ስለአየር ንብረት ለውጥ ተማሪዎችን ማስተማር እንደሆነ ይናገራሉ::
ሁለተኛው በምርምሮች እና ፈጠራዎች ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው:: ለእዚህም እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው የሆነ እድሎች አላቸው:: ለምሳሌም ባህርዳር፣ መደወላቦ እና ባሌ ዩኒቨርሲቲ ብንወስድ፤ የራሳቸው የሆነ ምርምር ለመሥራት የሚያስችል እድል አላቸው ይላሉ::
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፖሊሲ ተሳትፏቸው ደካማ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር በላይ፤ አሁን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እድል ስለሰጠ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚዘጋጁ ፖሊሲዎች ጥናቶችን በማድረግ መሳተፍ ይችላሉ ብለዋል::
አሁን ላይ የሚታየው ትልቁ የዩኒቨርሲቲዎች ድክምት የምዕራባዊያንን እውቀት ቀጥታ አምጥቶ በመጠቀም፤ ሀገር በቀል እውቀትን ኋላ ቀር አድርጎ መተው ነው:: አሁን ግን ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ ተሳትፎን በመጠቀም ሀገር በቀል እውቀቶችን እየተጠቀሙ የሚሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ፕሮፌሰር በላይ እንደሚሉት፤ በተቋቋመው ፎረም መሠረት የከፍተኛ ተቋማት ኃላፊነት “ግሪን ካምፓስ” መመስረት፣ በጥናቶች ፖሊሲ አውጪዎችን መሞገት እና ለአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች የገንዘብ ምንጮችን ማፈላለግ ነው::
የአመራር ቁርጠኝነት፣ የመንግሥት ድጋፍና አግባብ የሆነ ፈንድ እና ተባብሮ በጋራ መሥራት ከተቻለ ፎረሙ በሂደት ብዙ ነገር ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ::
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል አቅማቸው፣ ያላቸው መሠረተ ልማት፣ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸው በጣም የተለያየ ነው:: ከእዛ አንጻር አቅምን አሰባስቦ በአንድ ኃይል ለመሥራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወሰደው ርምጃ ትልቅ ነው ይላሉ::
የፎረሙ መቋቋም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተቀመጠውን ግብ በፍጥነት ለማሳካት ይረዳል የሚል ግምት እንዳላቸው በመግለጽ፤ ፎረሙ ሲመሠረት ሥራዎች በምን መልኩ መሠራት እንደሚገባቸው፤ ሀብት በምን መልኩ መሰብሰብ እንደሚቻል ተመላክቷል፤ ይህም ጥሩ ርምጃ ነው ብለዋል::
ፕሬዚዳንቱ እንዳስታወቁት፤ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ መሥራት ከጀመረ ሰንብቷል:: ከአፍሪካ ልህቀት ማእከል ጋር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ትምህርቶችን ለሀገር ውስጥና ከአፍሪካ ሀገራት ለመጡ ተማሪዎች በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ ነው::
ማእከሉ ከዓለም ባንክ እና ከኖርዌ መንግሥት ደጋፍ ያገኛል:: የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የሚደግፋቸውን ፕሮጀክቶች በማምጣት ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ሀገራት ተማሪዎችን በማስተማር እና ምርምር በመሥራት ላይ እንገኛለን:: የፎረሙ መመስረትም የዩኒቨርሲቲውን አቅም ያጎላዋል የሚል እምነት አላቸው::
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዳዊት አዬሶ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአሁኑ ጊዜ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች አጠቃላይ ዓለም ላይ ከሚሠሩ ሥራዎች ትኩረት በማግኘት ግንባር ቀደም እየሆኑ ነው ሲሉ ይገልጻሉ::
ከእዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ሰፊ ሥራዎችን እየሠራች መሆኑን በማንሳት፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ቀድማ በመተንበይ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አመላክተዋል::
ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፤ የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም መቋቋም ልዩ የሚያደርገው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን የዜጎች ጉዳይ በማድረግ ከመማር ማስተማር፣ ከምርምር እና ከአጠቃላይ ኅብረተሰብ ጋር በማቆራኘት መሥራት የሚያስችል ነው::
የአየር ንብረት ለውጥ የአንድ ትምህርት ክፍል ብቻ ሳይሆን፤ ሁሉም አጀንዳውን ማእከላዊ አድርጎ እንዲወስድና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው:: ዘላቂ ልማትን ከማምጣት አንጻርም፤ አካባቢን በመጠበቅ በዘላቂነት ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል መሆኑ ፎረሙን ለየት ያደርገዋል ሲሉ ይገልጻሉ::
በከፍተኛ የምርምር ተቋማት የሚሠሩት የምርምር ሥራዎች ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው ከተሠሩ እና ለማህበረሰብ የሚሰጡ አገልግሎቶችም አየር ንብረትን ያማከለ ከሆነ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ልማት በጽኑ መሠረት ላይ ለመጣል የሚያስችል መሆኑን ያስረዳሉ::
ዳዊት(ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ዋቸሙ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ መርሃ ግብሮች አረንጓዴ አሻራ እና የኮሪደር ልማትን አካቶ እየሠራ ይገኛል:: በፎረሙ በተደረገው ስምምነት መሠረት ደግሞ፤ በካምፓሶች አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ጠንክሮ በመሥራት፤ ተማሪዎች በግቢው ያዩትን ልምድ ወደ አካባቢው እንዲወስዱ ለማስቻል በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው::
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም