
በተለያዩ የዓለም ከተሞች ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድሮች ከ5 ኪሎ ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች ድረስ ይዘጋጃሉ፡፡ የእነዚህ ውድድሮች ዓላማም ሴቶችን ማበረታታትና በስፖርቱ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ሲሆን፤ ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ገቢ ለማሰባሰብም ይካሄዳሉ። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያም ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን መከበሩን ተከትሎ ሴቶችን ብቻ የሚያሳትፍ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ያከናውናል፡፡
በአፍሪካ ትልቁን የጎዳና ውድድር በማስተናገድ የሚታወቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል “ቅድሚያ ለሴቶች” የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ትናንት በአዲስ አበባ በድምቀት ተካሂዷል፡፡ በውድድሩ ላይም 150 ኢሊት አትሌቶች፣ ከ30 በላይ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የተሠማሩ ተምሳሌት ሴቶች፣ ሴት አምባሳደሮች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሴት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 16ሺ ሴቶች ተሳትፈዋል።
በኢሊት አትሌቶች መካከል በተደረገው ፉክክር በክለብ እንዲሁም በግላቸው በርካታ ስመ ጥርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ ማካበት የቻሉ ብርቱ ሯጮች ተካፋይ ሆነዋል። ከእነዚህም መካከል አንዷ አምና የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው አትሌት ብርነሽ ደሴ በድጋሚ ባለድል ሆናለች። ብርቱ ፉክክር ባስተናገደው ውድድር አትሌት አበዙ ከበደ እና መቅደስ ሽመልስ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ፈጽመዋል። ለአሸናፊ አትሌቶች ከሜዳሊያና ዋንጫ ባለፈ የ50ሺ ብር ሽልማት ያገኙ ሲሆን፤ ክብረወሰን ቢያሻሽሉ ደግሞ ተጨማሪ 50ሺ ብር ይበረከትላቸው ነበር። የውድድሩ ስፖንሰር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በበኩሉ፤ የሳምሰንግ ተንቀሳቃሽ የስልክ ቀፎ ሽልማት ለቀዳሚዎቹ አትሌቶች አበርክቷል።
ከውድድሩ በኋላ ባለድሏ የግሎባል ስፖርት አትሌት ብርነሽ፤ ያለፈው ዓመት ልምዷ ዳግም አሸናፊ ለመሆን እንዳገዛት ተናግራለች። ፉክክሩ ከባድ ቢሆንም ተፎካካሪዎቿን አሸንፋ በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቃለች። ወጣቷ አትሌት 5ሺ ሜትር ላይ ትኩረት አድርጋ የምትወዳደር ሲሆን፤ በቀጣይም ጠንክራ በመሥራት በሌሎች ውድድሮች መሳተፍና ሀገሯን የማስጠራት ህልም እንዳላት ገልጻለች።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት የሆነችው አበዙ ከበደ ዘንድሮ ውድድሩን አሸንፋለሁ ብላ ባትጠብቅም፤ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆና የብር ሜዳሊያ ማጥለቋን ተናግራለች። ወደ ክለብ ከገባች አንድ ዓመት የሆናት አትሌት አበዙ፤ ከእዚህ በኋላ በጠንካራ ሥራ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እንደምትሠራም ጠቁማለች።
ደማቅ የነበረው በእዚህ ውድድር “ሁሉም መብቶች፤ ለሁሉም ሴቶች” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው ውድድር የዕድሜ፣ የትምህርት፣ የሥራና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ራሳቸውን የሚገልጹበት ትልቅ መድረክ መሆኑም ታይቷል፡፡ በተምሳሌት ሴቶች የሴት ልጅ አቅምና ብርታት ከሚንጸባረቅበት የሩጫ ውድድር ዓላማቸውን፣ ስሜቶቻቸውን እንዲሁም ልምዶቻቸውን የሚያካፍሉበትም ነው፡፡
በተለያዩ ዘርፎች በተከናወነው ፉክክርም ብቃቷን ማስመስከር የቻለች ሴት ዕውቅናን አግኝታለች፡፡ በተጨማሪም በውድድሩ ለመሳተፍ አቅም የሌላቸው ተማሪዎችን በኤምባሲዎችና የግል ተቋማት በተደረገ ድጋፍ የሩጫው ተካፋይ ተደርገዋል፡፡
የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ አምባሳደር ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር፤ በርካታ ተሳታፊዎች ርቀቱን ከ35 ደቂቃ በታች በመግባት የተለየ እንደነበር ጠቁማለች። ባለፉት በርካታ ዓመታት እስከ ኦሊምፒክ የደረሰ ተሳትፎ የነበራቸው አትሌቶች ያፈሩበት ትልቅ ውድድር መሆኑንም አስታውሳለች። መሰል ውድድሮች ለሴቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሲሆን፤ ከተሳትፎ ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ የሆኑ ሴቶች የሚሳተፉበት በመሆኑም ለሌሎች ተነሳሽነትን እንደሚፈጥሩ ገልጻለች። በመሆኑም መሰል ውድድሮች ቢጠናከሩ በርካቶችን ለማፍራት እንደሚቻል ያላትን እምነት ጠቅሳለች።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ በበኩሏ፤ ውድድሩ ደማቅና በርካቶችን ያሳተፈ እንደነበር ገልጻለች። ሀገርን በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያስጠሩትን አትሌቶች ጨምሮ በመድረኩ የተሳተፉና በተለያዩ ሙያዎች ነጥረው በመውጣት ተምሳሌት የሆኑ ሴቶች ሌሎችን እንዲበረታቱ የሚያደርግ ነው ብላለች። “ውድድሩ ጀግና ሴቶች የሚከበሩበት ከመሆን ባለፈ ስኬት መለኪያ የሌለው እንደመሆኑ በየትኛውም ዕድሜ ስኬታማ መሆን እንደሚቻልም በግልጽ የታየበት ነው።” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም