
በዓለም ላይ ደም ለግሶ ልትጠፋ አፋፍ ላይ ያለችን የሰዎች ሕይወት ከመታደግ በላይ የሚያስደስትና የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ምንም አይነት ሌላ ሰብአዊ ተግባር ምድር ላይ የለም።
ደም መለገስ ዓለም ላይ ካሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች አንዱና ሕይወት አድን እየተባለ ከሚጠቀሱ መካከል ዋነኛው ነው። አንድ ሰው የሚለግሰው ደም የብዙዎችን ሕይወት ያድናል። ደም የሚለግሰው በዘር፣ በሃይማኖት፣በቀለም፣ በጾታ ለሚያውቀው ሰው ሳይሆን ለማያውቀው ውለታዬን ይከፍለኛል ብሎ ለማያስበው የሰው ልጅ ነው። ምናልባትም የለገሰው ደም ለራሱ ወይም ለቅርብ ዘመዱ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትም አጋጣሚ ይኖራል ።
የደም ልገሳ ለደም ተቀባዩ በሕይወት የመኖር፤ ለለጋሹ ደግሞ ሕይወት የማትረፍ ያህል ዋጋው ከፍ ያለ ነው። የደም ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችን በሌላ በምንም ዓይነት ሕክምና ሕይወታቸውን ማትረፍ አይቻልም። ስለዚህ የደም ሕክምና ለታካሚው በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው።
ለእዚህም ነው የደም ልገሳ በሕክምና ተቋም ውስጥ የአገልግሎቱ የጀርባ አጥንት ናቸው የሚባለው። ይሁን እንጂ በየዓመቱ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በቂ ደም በየደም ባንኮች አለመኖሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ጉዳዩ ከሚመለከተው ተቋም ሲገለጽ ይሰማል።
የሕክምና ተቋማትን የደም ፍላጎት ከማሟላትና የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት አንጻር አንድ ሀገር ካላት ሕዝብ ቁጥር ውስጥ ቢያንስ አንድ በመቶ የሚያህለው ሕዝቧ ቋሚ ደም ለጋሽ መሆን አለበት። ከእዚህ አንጻር ሲታይ ዛሬም በቂ የሆነ ደም ወደ ደም ባንክ እየገባ አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት በዓመት አንድ ሚሊዮን ደም እንዲሰበሰብ ቢመክርም ኢትዮጵያ ግን በዓመት 300 ሺህ ያህል ደም ከለጋሾች ትሰበስባለች።
ለምሳሌ ያህል የኅብረተሰቡን ደም የመለገስ ባህል ከግምት ውስጥ በማስገባት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ግማሽ ሚሊዮን ሚሊ ሊትር ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ ባለፉት ሰባት ወራት 243 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቧል። ነገር ግን የሕክምና ተቋማት ከሚፈልጉትና የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት አንጻር ይሄ በቂ አይደለም።
የደም ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በየጤና ተቋማቱ በሕይወትና በሞት መካከል ሆነው የወገናቸውን ክንድ አንጋጠው እየጠበቁ ይገኛሉ። በመሆኑም ሁሉም ማህበረሰብ በተለይም በእዚህ የፆም ወቅት ክንዱን በመዘርጋት በሚተካ ደም የማይተካ የሰው ሕይወትን ለማዳን ርብርብ ማድረግ ይገባዋል። ይሄ አንዱ ሕይወትን የማትረፊያ የጽድቅ መንገድ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ መጠን ያለው የደም መፍሰስ ያጋጥማቸዋል። የሚፈሳቸውን ደም መተካት ካልተቻለ ደግሞ ሕይወትን ሰጥተው ሕይወታቸውን ያጣሉ። የሀገርን ዳር ድንበር በመጠበቅ ላይ ያሉ የጦር ሠራዊት አባላት በሥራ ላይ በሚገጥማቸው የጦር ጉዳት፣ የአደጋ ተጠቂዎች፣ የካንሰር ታማሚዎች፣ የኩላሊት እጥበት ታካሚዎች፣ የቀዶ ሕክምና ታካሚዎች እንዲሁም ሌሎች በሕይወት እንዲቆዩ ደም ያስፈልጋቸዋል። በየጤና ተቋማቱም የደም መስጠት ሕክምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ስለዚህ ይሄንን ፍላጎት ማሟላት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
ይሄ ደም ከየት ይመጣል ከተባለ መልሱ አንድ ብቻ ነው ከበጎ ፈቃደኞች። እያንዳንዱ ሰው ደም ሲለግስ ዛሬ የተቸገረ ወገኑ ይደርሳል፤ ለራሱ ርካታን ያስቀራል። ይሁን እንጂ አሁን እየተሰበሰበ ያለው የደም መጠን ሲታይ ደም የመለገሱ ባህል ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል።
በመሆኑም የደም ልገሳን ባህል በማድረግ የደም ባንክ ለሚሰጠው ሰብአዊ ተግባር እጥረት እንዳይገጥመው ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት አዳዲስ አሠራሮችንና ስትራቴጂዎችን መዘርጋት ያስፈልጋል።
ይህ ወቅት የኦርቶዶክስ እና እስልምና ሃይማኖቶች አፅዋማት ወር በመሆኑ እና ጾም ደግሞ በጎ ተግባር የሚፈጸምበት እንደመሆኑ በጎ ፈቃደኛ ደም የመለገስ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ይበረታታሉ። ይህንንም በማድረግ የደም አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል ሰፊ ሥራ መሥራት ይገባል። በተለይ የሰንበት ቀናትን እና ከጾም ሰዓት ውጪ ያሉትን ጊዜያት ደም መለገስ እንደሚያስችል ማስገንዘብ ይገባል። በእዚህ ዙሪያ የሃይማኖት አባቶች ሰፊ ትምህርት ሊሰጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም