ዓይናችንን ከፍተን ያላየነው ባለብዙ በረከት

እንሰት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢኖርም በምግብነት የሚጠቀሙት ደቡብ ምዕራብ የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው። ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ኮባውን ድፎ ዳቦ ለመጋገር ከመጠቀም በዘለለ በምግብነት አያውቁትም። የሚተከለውም ቅጠሉ ሰፋፊ ስለሆነ የተቦካውን ዱቄት በኮባ ሸፍኖ ዳቦ ለመጋገር ስለሚረዳ ነው። ደቡብ የሚኖሩ ሕዝቦች ግንዱም ቃጫ (ገመድ፣ ዘንቢል ፣ጆንያ) ኮባውን ድፎ ዳቦ ለመጋገር ከመጠቀም ባሻገር ለዘወትር ምግብነት ይጠቀሙታል።

ከእንሰት ስር ቆጮ ፣ቡላ(ገንፎ የሚመስል)፣ አሚቾ የተቀቀለ (ድንች የሚመስል ) ጓርየ፣አስተርና እና ቅብናር፣ አተካና የሚባሉ ምግቦች ይዘጋጃሉ። ቅብናርና አስተርና ስብራት ለደረሰበት ሰው የመጠገን አቅም አላቸው ይላሉ ። እንሰት በሚያዘወትርበት ቦታዎች አራሶችም የሚታረሱት ቡላ እየተመገቡ ነው። በሲዳማ ቡርሳሜ የሚባል ከቆጮና ከቅቤ የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ አለ። በገጠር የእንሰት ምግብ ግማሽ ዓመት ሳይበላሽ በመሬት በመቅበር ያቆዩታል።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ክትፎ፣አይቤና ጎመን ክትፎ በኮባ ተጠቅልሎ ለተመጋቢው ይሰጣል። ኮባው እንደ ሳህን አገለገለ ማለት ነው። ከእንሰት ግንድ እየተገነጠለ በእንጨት፣በአጥንት ፣በቢላ ነገር እየተፋቀ ቃጫ ይወጣዋል። ከቃጫው ደግሞ ገመድ፣ጅራፍ፣ጆንያ፣ ዘንቢል እና መሰል ነገሮች በመሥራት ይገለገሉበታል። በተጨማሪው ግንዱ እንዳለ ሆኖ ጅባ የተባለ ሰሌን የሚመስል ምንጣፍ ተዘጋጅቶ በገጠር ለቤት ወለል ይጠቀሙበታል።አንዳንዶቹም ለመኝታ ይገለገሉበታል። በከተሞች የባሕል ምግብ ቤቶች ለኮርኒስና ለግርግዳ ይጠቀሙበታል። በገበያም ይሸጡታል።

በጥንቱ ዘመን የኮባ ተክል ለምግብነት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ያገለግል ነበር፤ በእርሻና አዝርዕት መስፋፋት ሂደት የእንሰት ምግብነት እየተራባ መሄዱን የዊኪፒዲያ ድረ ገፅ ያስረዳል። ኮባ ከሌሎች ተክሎች በተለየ መልኩ ዳገታማ ቦታ ላይ ስለሚበቅል ለተራራማ ቦታዎች ምቹ ነው። አንድ ኮባ ከተተከለ ከ4-7 ዓመት ውስጥ ለምግብነት ይደርሳል። እያንዳንዱ የኮባ ስር (እንሰት) እስከ 40 ኪሎ ግራም ዱቄት ይወጣዋል።

እንሰት ከ20 ሚሊዮን በላይ የሀገሪቱ ዜጎች ለዘወትር ምግብነት ይገለገሉበታል። በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሰባት ቤት ጉራጌ፣ ሶዶ ፣ ዶቢ ፣ስልጤ ፣ሀላባ፣ ከምባታ ፣ወላይታ፣ኦሮሞ፣ ሀዲያ፣ ሲዳማ፣ዳውሮ፣ጋሞጎፋ ከፊቾ በብዛት ይጠቀሙታል። ቂጣ የሚመስለው ቆጮውን በአይቤ፣በክትፎ፣በቅቅል፣በሥጋ መረቅ ይመገቡታል። ቆጮውን በጎመን ክትፎ፣ በወጥ፣ በድንች ወጥ፣ በድንች እንዲሁም ቆጮን በወተት ፣በቡና፣ በሚጥሚጣ እያጣጣሙ የሚመገቡ አሉ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ እንሰት ከዘወትር ምግብነት አልፎ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያለው ተክል ነው። ለተጠቃሚዎቹ ባሕላዊ ፣ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚና አለው። በክስታኔ እንኩሳ የሚባል ለበዓል የሚዘጋጅ የቆጮ ዓይነት አለ። ዘወትር የሚበላውን የቆጮ ዓይነት ጪሳራ ይሉታል፤ፈጣም የሚባል ደግሞ ጥቁር ለአገልጋዮች የሚሰጥ የቆጮ ዓይነት ነው። ከእ ዚሁ ቆጮ ደግሞ ዣንዣ የሚባል ገንፎ (ቡላ አይደለም) ይሠራል። በዲላ፣በጉራጌም ‹‹ወርቄ ›› ተብሎ የሚጠራ የእንሰት ዓይነት አለ። በኦሮሞም እንሰት ‹‹ወርቄ›› እየተባለ ይጠራል። የእንሰት አብዛኛው ምግብ እንደ ወርቅ ከመሬት ተቆፍሮ ስለሚወጣም ሊሆን ይችላል።

እንሰት የመሬት ከፍታቸው ከ2ሺህ እስከ 2ሺህ 750 ቦታዎችና ዓመታዊ የዝናብ መጠናቸው 1ሺህ100 እስከ 1ሺህ 500 ሚሊ ሜትር ለመብቀል በጣም ምቹ መሆኑን (Journal of Plant Studies; Vol. 10, No. 2; 2021) ያወጣው መረጃ ያስረዳል። እንደ ዛፍ የሚያድገው እንሰት ቁመቱ ከ4 እስከ 11 ሜትር ሲሆን፤ የዙሪያው ውፍረት ደግሞ ከ1ነጥብ 5 እስከ 3 ሜትር ይደርሳል።

ብዙ የኮባ ወይም እንሰት ዓይነቶች በአፍሪካ ደጋማ ክፍሎች ይብቀሉ እንጂ ለምግብነት የሚያገለግለው በኢትዮጵያ ብቻ ነው። የኮባ ተክል በጥንቱ የግብጽ ስልጣኔ ይበቅል እንደነበር ማስረጃዎች አሉ። ዝርያው በአፍሪካና በእሲያ ይገኛል። የዊኪፒዲያ መረጃ ከምዕራብ ትሮፒካል አፍሪካ እስከ ማላዊ ፣ከደቡብ ምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እስከ ሰሜን ዛምቢያ፣ በማዳስካር በእሲያ የሚመሳሰል የእንሰት ዝርያ መኖሩን፤ ከህንድ እስከ ኒው ጊኒ Papua New Guinea ፣ በቻይና ፣በታይላንድ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ እንደሚገኝ ያስረዳል።

የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንሰትን ፣ የኮባና የሙዝ ዓይነት ቅጠል፣ ሴቴ ኮባ ጒናጒና የጒራጌ መና በሚል ይፈታዋል። እንሰት በሳይንሳዊ ስሙ እንሰቴ ቬንትሪኮሱም (Ensete vetricosum) ይባላል። ምዕራባውያንም የአቢሲኒያ ቀይ ሙዝና የአቢሲኒያ ሙዝ በሚል ይጠሩታል። በብዛት ፎልስ ባናናም የሚሉት አሉ። የሙዝ ተክል ስለሚመስል።

በዘመናችን እንሰትን ለማዘመን ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ ተቋማት እየሠሩ ነው። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከእንሰት የሚዘጋጁ ምግቦች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ በጥናትና በተግባር መረጋገጡንና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የመከረበት መረጃ ይገልጻል። ሚኒስቴሩ እንሰትን ስትራቴጂክ ሰብል መሆን አለበት ብሎ ናሽናል ፍላግሽፕ ፕሮግራም ቀርፆ፣ ኮሚቴ አቋቁሞ ዶክመንት በማዘጋጀት እስኪፀድቅ እየጠበቀ ነው።

ሲፀድቅ እንሰት እንደ ጤፍና ስንዴ ታይቶ ትኩረት ያገኛል፣ የመንግሥት ዕገዛ ይኖረዋል። ዩኒቪርሲቲው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የእንሰት ፓርክ ሠርቶ፣ ሳይንሳዊ ግኝቶችንም እያወጣ ነው። አቻ ዩኒቨርሲቲዎችን ተጠቃሚ ለማድረግም አዋሳ፣ ወልቂጤ፣ ወላይታ፣ ወሎ፣ ሀዋሳ፣ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎችን ልምድ አካፍሏል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከእንሰት የሚገኘውን ምግብ ለማዘመን፣ የእናቶችን ድካም ለመቀነስና የእንሰትን የምግብ ይዘት ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲዎች እየሠራ ነው። እንሰትን ከቆጮ ባለፈ ዳቦና ጣፋጭ ምግቦች እንዲሆን

አንድ ርምጃ ወደፊት ሄዷል። ዩኒቨርሲቲው በባህላዊ መንገድ የሚሠራውን የእንሰት አመራረትና አዘገጃጀት ሂደትም ሙሉ በሙሉ የቀየረ ፕሮጀክት ተግብሯል።

በዩኒቨርሲቲው የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና ተመራማሪ አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር)፤ በፕሮጀክቱ በባህላዊ መንገድ ከእንሰት ለሚሠሩ ምግቦች ሳይንሳዊ መፍትሔ አምጥቷል ይላሉ። ዩኒቨርሲቲው እንሰት የሚፋቅበትን መንገድ ወደ ዘመናዊ የቀየረ ሲሆን፤ ለአርሶ አደሩ ምቹ፣ ቀላልና ዘመናዊ የእንሰት ማዘጋጃ ማሽኖችን (ወፍጮ) በማምረት የማስተዋወቅና የማዳረስ ሥራ እያከናወነ ነው። በፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእንሰት ዱቄት መመረቱን፣ ዱቄቱ ለቆጮ፣ ለኬክ፣ ለኩኪስና ለዳቦ መሆን እንደሚችል እያስተዋወቀ ይገኛል።

እንሰት ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ረዥም ጊዜ የሚቆይበትን ዘዴ በመቀየርም፣ በማብላያ እንስራ ወይም ሮቶ በመጠቀም እንሰት ጉድጓድ ውስጥ የሚቀበርበትን አሠራር ለማስቀረት ተችሏል። እንሰት ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ለመብላላት እስከ ሦስት ወራት እንደሚቆይ፣ ነገር ግን በምርምር ከሰባት እስከ አሥር ቀናት ውስጥ ለምግብነት ማድረስ መቻሉን አዲስ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ‹‹እንሰት ከኢትዮጵያ አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ ብሎም ለዓለም ምግብ ይሆናል›› የሚል ዓላማ ይዞ የእንሰት ዱቄት በሰፊው ተመርቶ ወደ ገበያ የሚገባበት አካሄድ ተዘጋጅቶና ወጣቶች ተደራጅተው የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ከእንሰት የሚሠሩ ጣፋጭ ምግቦች ባህላዊውን ቃና ያልለቀቁ፣ ነገር ግን ዘመናዊ የምግብ ሥርዓትን ተከትለው የሚመረቱ፣ ጤናማ ከማንኛውም ኬሚካል የፀዱና ግሉቲን የሌላቸው ናቸው።

በጋሞና ወላይታ ዞኖች እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ማኅበረሰብ አቀፍ የእንሰት የሙከራ ወፍጮ ቤት ማሽኖች ተተክለዋል። ይህም እንሰትን ለመፋቅ ሁለትና ሦስት ቀናት ይፈጅ የነበረውን አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲፈጭ፣ ከአፈር ያልተነካካ፣ በእንጨትና በአጥንት ያልተፋቀና ጉድጓድ ያልተቀበረ ንፁህ ምግብ ለማዘጋጀት አስችሏል። የእንሰት አዘገጃጀት ለእናቶች አድካሚ ነበር። ፕሮጀክቱ ግን የእናቶችን ድካም አስቀርቷል።

ወፍጮው ለአርሶ አደሮች ቃጫውን፣ ቆጮውንና ቡላውን ለየብቻ ጨምቀው እንዲወስዱ የሚያስችል ነው። የተፈጨውን ከሰባት እስከ አሥር ቀናት በእንስራ አብላልተው ለምግብ የሚያደርሱት ሲሆን፤ በዚህም እንሰት በባህላዊ ዘዴ ሲዘጋጅ የነበረውን 45 በመቶ ምርት ብክነት ማስቀረት ተችሏል። ከክርስቲያን ኤይድና ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ድጋፍም በወላይታ ሁለት ወረዳዎች ወፍጮ ቤቶች ተተክለው፣ ወጣቶች ሠልጥነው ምርቱን ወደ ገበያ ማውጣት ጀምረዋል።

ከአሜሪካ ካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር በተሠራ የጋራ ጥናት እንሰት ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚሆን ኦርጋኒክና ከግሉቲን ነፃ ብስኩት ተዘጋጅቶ ከተጠቃሚዎች ቃናውን በሚመለከት አስተያየት ተሰብስቧል። ለዓለም አቀፍ ገበያ ኦርጋኒክ፣ ከግሉቲን ነፃ ምርት ይዘው ለማውጣት እየተሠራ ነው። ዓለም አቀፍ የምግብ ኩባንያዎችም ፍላጎት አሳይተው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመሥራት ውል ተፈራርመዋል።

በሐምሌ 2016 አዲስ ዘመን የወጣ ዘገባ በጌዴኦ ዞን ከእንሰት ምርት ለማግኘት እስከ አምስት ዓመት በላይ ይወስድ የነበረውን ጊዜ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደ አንድ ዓመት ተኩል ማጥበብ ተችሏል ይላል። እንሰት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ትልቅ ድርሻ አለው። በዞኑ የእንሰትና ቡና ተክል በስፋት የሚገኝበት በመሆኑ ምርታማነትን ሊያረጋግጥ በሚችል ደረጃ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።

ፕሮፌሰር አበበ መንገሻ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ዶክተር ጀምስ ቦሬል ከሮያል የዕፅዋት አትክልት መካን (Royal Botanic Gardens Kew) ፣ከሪፕል ኢፌክት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አክሊሉ ዶጊሶ በጋራ ያወጡት ምርምር የተለያየ የዓየር ንብረት የሚቋቋሙ ከ1ሺህ 200 በላይ ዝርያ ያለው የእንሰት ዓይነት መመዝገቡን ያሳያል።

በአፍሪካ ከገበሬዎች ማኅበረሰብ ጋር የሚሠራው ሪፕል ኢፌክት፤ በድረ ገፁ ባወጣው መረጃ እንሰት እስከ 10 ሜትር ሊረዝም እንደሚችልና ‹‹ ፀረ ረሀብ የሆነ እጽዋት›› እንደሚባል ይጠቅሳል። የምርምር ተቋሙ ላለፉት 40 ዓመታት እንሰት ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ያለውን ጥንካሬ በተመለከተ ጥልቅ ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል። ሮያል የዕፅዋት አትክልት መካን ኢትዮጵያ በዓለም ልዩ የሆነው የእንሰት ምርት መገኛ መሆኗን ያስረዳል። እንሰት ወቅት ሳይጠብቅ በማንኛውም ጊዜ መመረት የሚችልና ለረዥም ጊዜ በማስቀመጥ ለምግብነት የመዋል ከፍተኛ አቅም እንዳለውና በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ትልቅ ሚና አለው።

ከእንሰት ውስጥ ለምግብነት የማይፈለገው ዘሩ ብቻ ነው። ቅጠሉ ተደራርቦ ተደራርቦ ቅጠሉን ያቆመው ግንዱ በቀላሉ ነጥሎ በመገንጠል በመቆራረጥ ከቅጠሉ ጋር ከብቶች ከመመገብ አልፎ ለማደለብ ይጠቀሙበታል። በተለይ ድርቅ በሆነ ጊዜ ግንዱ እርጥበት እና ውሃ አዘል ስለሆነ ለከብት ከምግብነት አልፎ የውሃ ፍላጎታቸውን እንደሚያረካም ጥናቱ ያስረዳል። የከብቶችን የውሃ አምሮታቸውንም የሣር ፍላጎታቸውንም በአንድ ጊዜ ያረካል። ያነጋገርኳቸው ሰዎችም የእንሰት ግንዱ እርጥብና ውሃ አዘል ስለሆነ ከብቶችን ከመቀለብ አልፎ ለማደለብ ይረዳል ብለውኛል። በተለይ ለእርድ የሚታሰብ ከብት የእንሰት ቅጠሉን ነጥለው፣ ግንዱን ቆራርጠው ቢሰጡት በፍጥነት እንደሚደልብ ይነገራል።

ዋና መቀመጫውን እንግሊዝ ሀገር ያደረገው ሮያል በተሰኘው የእጽዋት ምርምር ተቋም የዘርፉ ተመራማሪዎች፤ እንሰት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም አቅም እንዳለውና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ። በተቋሙ የእጽዋት ባህሪና ጥቅም ጥናት ቡድን መሪ ጀምስ ቦሬል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በግብርና ብዝኃ ሕይወትና አዝርት ስብጥር እምቅ አቅም ካላቸው ሀገሮች አንዷ ነች።

የምርምር ተቋሙ ላለፉት 40 ዓመታት እንሰት ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ያለውን ጥንካሬ በተመለከተ ጥልቅ ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በዓለም ልዩ የሆነው የእንሰት ምርት መገኛ መሆኗን ከተቋሙ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። እንሰት ወቅት ሳይጠብቅ በማንኛውም ጊዜ መመረት የሚችልና ለረዥም ጊዜ በማስቀመጥ ለምግብነት የመዋል ከፍተኛ አቅም እንዳለውም ጠቁመው፤ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ትልቅ ሚና አለው።

እንሰትን ከሌሎች ሰብሎች የሚለየው ኢትዮጵያ አንድም ዶላር የማታወጣበት፣ ማዳበሪያም ሆነ ኬሚካል ከውጭ የማይገባለት፣ ‹‹ዜሮ ዶላር ፕሮጀክት›› መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ በደቡብ ምዕራብ፣ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያና በመካከለኛው ኢትዮጵያ አካባቢዎች ያላትን ከፍተኛ የእንሰት ክምችት ለምግብ ዋስትና እንድትጠቀምበት ለማስቻል ፕሮጀክት እየተሠራ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ላይብረሪ ኦፍ ሜዲሲን በሲዳማ የበቀሉ እንሰት ዝርያዎች ላይ ባካሄደው ጥናትም እንሰት በብዛት በፖታሲየም፣በካልሲየም ዋና ማዕድን የበለፀጉ፤ማግኒዚየም፣ ዝቅተኛ ሶዲየም ያላቸው የተወሰኑት በብረትና ማንጋኒዝ ማዕድ የበለጸጉ መሆናቸውን ያስረዳል።

እንሰትን ከምግብነት አልፎ ለመድኃኒትነት ለማዳበሪያነት ፣ለከብቶች መኖ፣ ለቤት መሥሪያ ፣ ለቁሳቁስ አገልግሎት ይውላል። ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት መጀመሩንም አዳል ኢንዱስትሪ የተገኘ መረጃ ያሳያል። ኢንዱስትሪው በአማካይ በዓመት 30 ሺህ ቶን ወረቀት የማምረት አቅም እንዳለውና ለወረቀት ግዥ የሚወጣውን የጭ ምንዛሪ ለማስቀረት እየሠራ መሆኑንም በአዲስ ዘመን በመጋቢት 2016 ዓ.ም ተዘግቦ ነበር።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማቴሪያል ኢንጂነሪንግ መምህርት ወይዘሮ ፋይዛ ሸምሱ በገጠር የጉራጌ ሴቶች የእንሰት ቅርንጫፍ አድርቀው በማንጠፍ የሚተኙበት እና ለንፅህና መጠበቂያ ሲገለገሉበት የነበረውን በማዘመን ከእንሰት የእንሰት ንፅህና መጠበቂያም ሠርታለች። አንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ ውሎ ከሚጣለው የንፅህና መጠበቂያ በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ እየታጠበ አገልግሎት መስጠት የሚችል የሴቶች ንፅህና መጠበቂያም ነው የሠራችው።

በኢትዮጵያ የእንሰት ምርት ከምግብነቱ ባሻገር ዘምኖ ዱቁት ሆኖ ኬክ፣ ኩኪስ፣ ዳቦ የሚሠራበት ተረፈ-ምርቱ ለመድኃኒት፣ ለእንስሳት መኖ እንዲሁም ለወረቀት ማምረቻና ሌሎች አገልግሎቶች እንሰት ዘምኖ ዱቁት ሆኖ ኬክ፣ ኩኪስ፣ ዳቦ የሚሠራበት የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ዘምኖ የተሠራበት፣ ከተረፈ ምርቱም ወረቀት ማምረት መቻሉ ሁሉ እንሰት ምሉዕ በኩልሄ ጠቀሜታ እንዳለው ማሳያ ነው።

ድርቅ ለመቋቋም ድርቅ በሚያጠቃቸውና እንሰት ሊበቅልባቸው በሚችልባቸው አካባቢዎች እንሰትን ተክለን የምግብ ዋስትና መሆኑን በተግባር ማሳየት አለብን። እንሰት ተተክሎ እንዲበቅል የከብቶች እበት ከሥሩ ማድረግ ብቻ በቂ መሆኑን ሰዎች ይናገራሉ። ተረቱም ‹‹አንቺ እንሰት መገኛሽ ከገነት፣ ማደጊያሽ ከእበት፣ መበያሽ በወተት›› ይላል።

በሰሜን የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የእንሰት ምግብ እስኪለምዱ ቢያንስ ለከብቶቻቸው ኮባውንና ግንዱን እየነጠሉ እየቆራረጡ በመስጠት ከብት ማደለብ የሚችሉበትና የሚረዱበት ነገር ቢኖር ሸጋ ነው። ግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮዎች፣ መገናኛ ብዙኃን ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ መስጠት አለባቸው።

ድርቅ ‘ለሚያፈቅራትና አልለይሽም እያለ ለሚያስቸግራት ኢትዮጵያ በሰሜኑ አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎቻችን የእንሰትን ምግብ ማስለመድ ይገባናል። ይህም ኢትዮጵያ ‹‹የድርቅ ‹ፍቅር ወዲያ ይቅር›› እንድትል ያደርጋታል። እንሰት ድርቅን ለመቋቋም እንደሚረዳ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ሲነገር አስታውሳለሁ።

ክፋቱ እንሰት ድርቅን እንደሚቀናቀን ከማቀንቀን በስተቀር ለመትከል አለመነቃነቃችን ነው። እንሰትን በመትከል የምግብ አጠቃቀሙን ለገበሬው በማስገንዘብ ድርቅንም መግታት አልቻልንም። እንሰትን ይዘን ግን ድርቅን መዋጋት ተሳነን። በብሂላችን ‹‹በጊዜ የገባ እንግዳ እራቱ ፍሪዳ ›› እንደሚባለው እንዲሆንልንና ድርቅ መቋቋም እንድንችል ድርቅ በሚያጠቃቸው እንሰት ሊበቅልባቸው በሚችልባቸው አካባቢዎች እንሰትን ተክለን የምግብ ዋስትና መሆኑን በተግባር ማሳየት አለብን።

ይቤ ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You