
በሀገራችን የሚገኙት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች በወንድ ፕሬዚዳንቶች የሚመሩ ናቸው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ዩኒቨርሲቲዎችን የመምራት ዕድል የገጠማቸው ሴቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከእነዚህ ብርቅዬ ሴት ምሑራን አንዷ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኡባ አደም (ዶ/ር) ናቸው። የዛሬዋ እንግዳችን ከሆኑት ኡባ አደም (ዶ/ር) ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የምንቆይበት ጉዳይ አብዛኛው ከትምህርት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ ከትምህርት ዝግጅትዎ ብንጀምር?
ኡባ አደም (ዶ/ር)፡– የመጀመሪያ ዲግሪዬን የያዝኩት በአካውንቲንግ ነው። ከዚያ ማስተርስ ዲግሪዬን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝቻለሁ። ሦስተኛ ዲግሪዬንም ያጠናሁት ሁለተኛ ዲግሪዬን በሠራሁበት ዘርፍ አካባቢ ነው።
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ1999 ዓ.ም. ተቋቁመው ወደ ሥራ ከገቡት ሁለተኛ ትውልድ ከሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው። በአጋጣሚ እኔም ያን ጊዜ ነው ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀልኩት። ዩኒቨርሲቲው አዲስ በነበረበት ወቅት የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ ሳገለግል ነበር። በወቅቱ ብዙ ልምድ አልነበረኝም። ምክንያቱም ከዲግሪ በኋላ አንድ ቦታ ነው ሥራ የሠራሁት። ማስተርሴን ከያዝኩ በኋላ ነው ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጣሁት። የሥራ ልምድና የተሻለ ብቃት ያላቸው አመራሮች አብረውኝ ስላሉ እኔም ከፍተኛ የማገልገል ፍላጎት ስለነበረኝ እነርሱ መሐል ሆኜ ስሠራ ነበር። በኋላም ወደ ትምህርት ተመልሼ ፒኤችዲ ጨርሼ ስመጣ ለሦስት ዓመታት ምንም ዓይነት ኃላፊነት ሳልይዝ በመምህርነት አገልግያለሁ። ቀጥሎም የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ስሠራ ቆይቻለሁ።
ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በነበረ ችግር ምክንያት በወቅቱ የነበሩት ፕሬዚዳንት ከኃላፊነት ሲለቁ ከጥር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በተጠባባቂነት እንዳገለግል ትምህርት ሚኒስቴር በቦታው ላይ መድቦኛል። ቆይቶም በውድድር ከመስከረም ስምንት ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሆኛለሁ። ወደ ኃላፊነት የመጣሁት የዩኒቨርሲቲው የሰላም ሁኔታ ጥሩ ባልነበረበት የግርግር እና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ስለነበር ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ። ነገር ግን ፍላጎቱ ካለ አብረውህ ከሚሠሩ ሠራተኞች ጋር በመሆን ነገሮችን መግፋትና መቀየር እንደሚቻል አይቻለሁ። በትብብር መንፈስ መሥራት ከምንም በላይ ለአንድ አመራር ስኬት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው በዚህ ሂደት ውስጥ ተምሬያለሁ።
በቋሚነት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሆኜ ከተመደብኩ አሁን አራተኛ ዓመት እያለፈኝ ነው። የኛ ዩኒቨርሲቲ በብዙ መልኩ ወደኋላ የቀረባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ቢኖሩም ከመምህራን፣ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች እና ከሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ተባብረን እየሠራን ነው። ጥሩ ውጤቶችን እያስመዘገብንም እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በአራት ዓመታት የአመራርነት ዘመንዎ ዩኒቨርሲቲው እንዴት ያሉ ፈተናዎችን ተሻግሮ ምን አይነት ውጤቶች አስመዝግቧል?
ኡባ (ዶ/ር)፡– ከምንም በላይ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት በጣም ከፍተኛ ችግር የነበረበት ነው። አሁን ግን ወደተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ መሸጋገር ችሏል። የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን ከመሥራት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራኖችና ተመራማሪዎች ምርምር ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ከማድረግ አንጻር በሠራናቸው ሥራዎች ጥሩ ውጤቶች አስመዝግበናል። ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጆርናል አልነበረውም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተሠራ ሥራ ጆርናል እንዲኖረው ሆኗል። ዘመናዊ ስቱዲዮ በመገንባት የራሱ የሆነ የማኅበረሰብ ሬዲዮ አገልግሎት እንዲኖረው ተደርጓል።
አመራር ቅብብሎሽ እንደመሆኑ ተጀምረው በእንጥልጥል የቀሩ ነገሮች በማጠናቀቅ ረገድ ብዙ ነገሮችን ሠርተናል። በተለይ በአይሲቲ መሠረተ ልማት ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርገናል። በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሻለ የአይሲቲ መሠረተ ልማት እንዲኖረው ለማድረግ አልመን ተንቀሳቅሰን ማሳካት ችለናል። በኢለርኒንግ የኦንላይን ትምህርት ከመስጠት አንጻር ደግሞ በከፍተኛ ትጋት በመሥራት ላይ ይገኛል።
በግቢው ውስጥ የነበረውን ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር ሁለት ጉድጓዶችን በማስቆፈር የመስመር ዝርጋታውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንዲገባ አድርገናል። ግንባታው ለረጅም ጊዜ ተጓትቶ የተረከብነውን ሆስፒታል በከፊል ሥራ አስጀምረናል። በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ተጀምረው የነበሩ የተለያዩ ግንባታዎች እንዲጠናቀቁ አድርገናል። ተዘግተው የቆዩ ሕንጻዎችን አድሰን ወደ ሥራ አስገብተናል። አንድ ግዙፍ ቤተመጽሐፍት ተገንብቶ ተጠናቋል። ለተማሪዎች የሕክምና አገልግሎት የሚውል የከፍተኛ ክሊኒክ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል። ከአጋሮች ጋር በመሥራት የጋራ ፕሮግራሞችን በመክፈት የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት እጅግ ወሳኝ የሆኑ ሥራዎችን ሠርተናል። ከዜሮ ተነስተን የስትራቴጂ ፓርትነርሺፕ እና ዓለም አቀፋዊነት የሚል ዳይሬክተሪ በማቋቋም ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና አሜሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ፕሮጀክቶችን በማምጣት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ሚኒስቴር የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መለየቱ ይታወቃል። ሙሉ ለሙሉ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያደርገው ጉዞ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ኡባ (ዶ/ር)፡– ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለአፕላይድ ሳይንስ ከተለዩት 15 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ነው። ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት ተግባር ተኮር የሆነ ትምህርት መስጠት ይጠበቅበታል። እኛም ወደዛ ነው ጉዞ እያደረግን ያለነው። ይበልጥ ተግባርን ማዕከል ያደረግ ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም ነው። ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለይ ለተግባር ትምህርት ብዙ ዕድሎችን የሚሰጥ ነው። ኢንጂነሪንግ፣ ቴክኖሎጂ፣ ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ እና ጤና ላይ ነው አተኩረን እየሠራን የምንገኘው። በተለይ በኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ዞን ከመሆኗ አንጻር ተማሪዎች በቀላሉ ልምምድ የሚያደርጉባቸው ቦታዎች ያገኛሉ። በቢዝነስና ኢኮኖሚክስም ድሬዳዋ በጣም ብዙ የንግድ ተቋማት የሚገኙባት ከተማ ናት። የፋይናንስ ተቋማትም እንደልብ ስለሚገኙ ተማሪዎች በቀላሉ የተግባር ትምህርት እንዲማሩ ሰፊ ዕድል ያገኛሉ። ከቴክኖሎጂ አንጻርም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ መሠረተ ልማት ያለው በመሆኑ ዘመኑን የዋጀ የትምህርት አሰጣጥ ለመተግበር ነው እየሠራን ያለነው።
ዩኒቨርሲቲያችን ወደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ለሚያደርገው ሽግግር የሚያግዙ አራት ጥናቶችን በቂ የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ባላቸው የዩኒቨርሲቲው ምሑራን እየተሠሩ ይገኛሉ። ጥናቶቹ የዩኒቨርሲቲውን ጥንካሬ፣ ድክመት፣ አስቻይ ሁኔታዎች እና ፈተናዎች ዳሰሳ፣ ስልተ ሽግግር፣ የአተገባበር ሂደት ስልት እና የግብዓቶች ልየታ እና ቆጠራ ናቸው። እነዚህ ጥናቶች በአብዛኛው የተጠናቀቁ ናቸው። የጥናቶቹን ውጤት የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። በቀጣይም ጥናቶቹ ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት የቀረቡትን ገንቢ አስተያየቶች መሠረት በማድረግ እርማት ከተደረገባቸው በኋላ ለትግበራ ዝግጁ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል። ዩኒቨርሲቲያችን ከመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት የአጭር፣ መካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ እየሠራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን ቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር እስካሁን የሠራችሁትን ሥራ እንዴት ይገመግሙታል ?
ኡባ (ዶ/ር)፡- የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ እና በምርምር የተደገፉ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች የተለያዩ ሲስተሞችን በማበልፀግ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው። ዩኒቨርሲቲው በሁሉም መስኮች አሠራሩን በማዘመን እና የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ መተግበሪያዎችን በማበልፀግ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። በምክትል ፕሬዚዳንት በሚመራው የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ መምህራን ያላቸውን እውቀት በተግባር ለማኅበረሰቡ እንዲያውሉ ከማድረግ አንጻር ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠርና በማበረታታት እገዛ እየተደረገላቸው ነው።
ዩኒቨርሲቲው በ2015 ዓ.ም. ብቻ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ አምስት መተግበሪያዎችን በማበልፀግ የባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝቷል። የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል በማቋቋም ተማሪዎች ያላቸውን ሃሳብ እንዲያበለፅጉና የሥራ ፈጠራን ባሕል እንዲያዳብሩ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
የዩኒቨርሲቲውን አሠራር በማዘመን ዲጂታላይዝድ የሆነ ወረቀት አልባ የአገልግሎት አሰጣጥን ለመተግበር የሚያስችል መተግበሪያ በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በልፅጎ ወደ ሥራ ገብቷል። በተመሳሳይ መልኩ በከፊል ሥራ የጀመረው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታልን አሠራር ሙሉ ለሙሉ ወረቀት አልባ ለማድረግ የሚያስችል ሶፍትዌር በልፅጓል።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ግቢ የትኛውም ቦታ ላይ ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ የሚያስችል የኔትወርክ ዝርጋታ ተደርጓል። ይህም ተማሪዎች ዓለም ያለበትን ሁኔታ በቀላሉ ማየት እንዲችሉ ዕድል በመፍጠር የመማር ማስተማር ሂደቱን ያግዛል። በድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ በሚመራው ድሬዳዋን ስማርት ሲቲ የማድረግ ፕሮጀክት ውስጥም ዩኒቨርሲቲው አንድ ባለድርሻ አካል ሆኖ እየሠራ ይገኛል። ዩኒቨርስቲው የራሱን ትልቅ ዳታ ሴንተር ገንብቶ በ2014 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር አድርጓል።
ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት ተፈራርመናል። ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል ትብብርን በማጠናከር የጥናትና ምርምር ሥራን ለማሳደግ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መስኮች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በጋራ ለማልማት ያለመ ነው። የተደረገው ስምምነት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በአጋርነት እንድንሠራ ከማስቻሉም በላይ ለዩኒቨርሲቲያችን ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው። በለውጥ ጎዳና ላይ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲያችን ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ከመተዋወቅ፣ ከመጠቀም እና ከማበልፀግ አንጻር ልዩ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
ስለዚህ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲያችን ቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር ያከናወናቸው ተግባራትና በቀጣይ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች የተጣለበትን አደራ ለመወጣት በሚያስችል መንገድ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ትምህርት ሥርዓት እንዲተገብሩ ትምህርት ሚኒስቴር ከመረጣቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም አንዱ እንደመሆኑ ምን ዓይነት እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል?
ኡባ (ዶ/ር)፡– ትክክል ነው። ትምህርት ሚኒስቴር የዲጂታል ትምህርት ሥርዓት (ኢለርኒንግ) እንዲተገበርባቸው ከመረጣቸው አምስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው። የዲጂታል ትምህርትን በዩኒቨርሲቲው ለማስጀመር የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ የመልቲ ሚዲያ ስቱዲዮ ግንባታ ተጠናቋል። የተገነባው ስቱዲዮ ዩኒቨርሲቲውን የኦንላይን ትምህርት መስጠት ያስችለዋል።
የዲጂታል የትምህርት አሰጣጥን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። የዲጂታል ትምህርቱን ለሚሰጡ መምህራንም ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ለተማሪዎችም መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና እየተሰጠ ነው፤ መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሴት ተመራማሪዎችን የምርምር ተሳትፎ ለማሳደግ ምን እየሠራ ነው ?
ኡባ (ዶ/ር)፡- ዩኒቨርሲቲያችን በአጠቃላይ የሴቶች ተሳትፎን ከማጉላት አንጻር የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ። በግቢያችን የሴት መምህራን ቁጥር 16 በመቶ ነው። ሴቶች በአመራርነት፣ በምርምርም እና ዩኒቨርሲቲው በሚሠራቸው በሁሉም ሥራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ እናደርጋለን። ወደምርምር ስንመጣ በልዩ ሁኔታ ነው ድጋፍ የሚደረግላቸው። ፕሮፖዛል እንዴት መጻፍ እንዳለባቸው ሥልጠና እንሰጣለን። በተጨማሪም በልዩ ሁኔታ ሴቶች ብቻቸውን ፕሮፖዛል አቅርበው ተገምግሞ በጀት ተመድቦላቸው የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ይደረጋል። ከወንዶች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሚሳተፉባቸው የምርምር ሥራዎች አሉ። ነገር ግን ሴቶች ተፈጥሮ የሰጠቻቸው ፀጋ ለመወጣት ኃላፊነት ስላለባቸውና በቤት ውስጥም ጫና ስለሚበዛባቸው የግድ ተጨማሪ ዕድሎችን በመፍጠር ሴቶችን መደገፍ ይጠበቅብናል።
ሴት መምህራን በምርምር ሥራዎች ውስጥ የሚያደ ርጉት ተሳትፎ እንዲጨምር በየጊዜው ለሁሉም ተመራማሪዎች ከሚደረገው ጥሪ ባለፈ በየጊዜው ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የምርምር ጥሪ ማቅረባችንን እንቀጥልበታለን። ትኩረታችን ከመሠረታዊ ምርምር ይልቅ ተግባራዊ ምርምር ላይ መሆን አለበት:: በሴት ተመራማሪዎች መሪነት የሚደረጉት ምርምሮች ዩኒቨርሲቲው በልዩ ሁኔታ የሚከውናቸው ናቸው። በሴቶች የሚካሄዱ የተለያዩ የምርምር ሃሳቦች ተገምግመው በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዲጠናቀቁ ይደረጋል። በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ በምርምር ዙሪያና በሌሎችም ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው:: በተለይ በምርምር ረገድ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሴቶች በዋና መሪነት የሚሠሩባቸው ምርምሮች እንዲስፋፉ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ሴት ተመራማሪዎች በማገዝ መሪ ተመራማሪ ሆነው የሚሠሩት ምርምር ውጤት ወደማኅበረሰቡ ሄዶ ችግር ፈቺ እንዲሆን ሁሉም የዩኒቨርሲቲያችን ማኅበረሰብ ድጋፍ ያደርጋል። ሴቶች በየቀኑ ከሚያጋጥሙን ችግሮች ተነስተን መፍትሔ የሚያፈልቁ ሊተገበሩ የሚችሉ የምርምር ሃሳቦችን ይዘን እንመጣለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደምም ሴቶች የሚሠሯቸው ምርምሮች ተግባራዊ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። በወንዶች ከሚሠሩ ምርምሮች ይልቅ የሴቶቹ ሰፊ ተግባራዊ የመሆን ዕድል የሚኖረው ለምንድን ነው ?
ኡባ (ዶ/ር)፡- ሴቶች ለብዙ ነገር ቅርብ ነን። አንድን የምርምር ሥራ ለመሥራት ሲነሱ ሁልጊዜም በራሳቸውም ሕይወት ሆነ ማኅበረሰቡ ውስጥ ነገሩ በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚያልፍ ይረዳሉ። ጤናን በምሳሌነት ብናነሳ በእናቶች፣ በሕጻናት እና በአጠቃላይ በማኅበረሰብ ጤና ላይ ምርምሮችን ሲያደርጉ ለጉዳዩ እጅግ ቅርበት ስላላቸው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያቀርቡትን ምክረ ሀሳብ በቀላሉ መተግበር ይቻላል ብዬ አምናለሁ። አንድ ወንድ የጤና ባለሙያ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እንደ ሴት የጤና ባለሙያ ስለእናቶች ጤና ስሜታዊ መረዳት ሊኖረው አይችልም። በኢኮኖሚውም ብንመለከተው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ሰፊ ሕዝብ እንዳላት ሀገር በትንሽ ገበያ ላይ ነግደው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ብዙ ሴቶች አሉ። የተማረች ሴት የሴቶችን ችግር በቀላሉ አይተው ችግሮችን ለይተው ተንትነው የመፍትሔ ሃሳቦችን ሊያስቀምጡ ይችላሉ። ዞሮ
ዞሮ ምርምር የሚሠራው ችግርን ለመፍታት ነው። ችግሩ ግን በትክክል ያለ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ እኮ መላምቶች ይሆናሉ። ሴቶች በዚህ ረገድ በትክክል ያለ ችግርን የመለየት ዕድላቸው ሰፊ ነው የሚል እይታ ነው ያለኝ። በጥናት ማረጋገጥ የሚቻል ነገር በመሆኑ ትክክልም ነው። ምናልባት በወንዶች የሚሠሩ ምርምሮችን ወስዶ ከሴቶች ጋር ማነጻጸር ከተቻለ ራሱን ችሎ አንድ የምርምር ርዕሰ ጉዳይ ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ በስፋት እንዲታዩ ለማድረግ በተለየ ሁኔታ የምታደርጉት ጥረት አለ?
ኡባ (ዶ/ር)፡- በዩኒቨርሲቲያችን በመጀመሪያ ደረጃ አመራር ቦታ ላይ ለሚወዳደሩ ሴቶች በአዎንታዊ ድጋፍ (አፈርማቲቭ አክሽን) 10 በመቶ ነጥብ እንጨምርላቸዋለን። ስለዚህ አንድ ሴት ከተወዳደረች እዛ ቦታ ላይ የመምጣት ዕድሏ በጣም ሰፊ ይሆናል ማለት ነው። መካከለኛ አመራር ለመሆን ለሚወዳደሩ ሴቶች ሰባት ነጥብ አምስት በመቶ አዎንታዊ ድጋፍ ይጨመርላቸዋል። የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ ላይ የተቀመጠው አዎንታዊ ድጋፍ ሦስት በመቶ ነው። እኛ ሴቶች በየደረጃው በአመራር ደረጃ እንዲሳተፉ ስለምንፈልግ የበለጠ ድጋፍ ማድረግን መርጠናል። በዩኒቨርሲቲያችን በአመራር ደረጃ ያለው የሴቶች ተሳትፎ 23 በመቶ ደርሷል። ከተቻለ ይህን ቁጥር ወደ ሃምሳ በመቶ ለማሳደግ ነው ጥረት የምናደርገው።
ከሴቶች ምርምር ጋር በተያያዘ የሚደረገው ድጋፍ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም አለ። የእኛ ዩኒቨርሲቲ በሴት የሚመራ ተቋም ስለሆነ ትንሽ ለየት ባለ ሁኔታ ሴቶችን ማብቃት ላይ አተኩረናል። በነገራችን ላይ አዎንታዊ ድጋፍ የሚባለው ነገር አንዳንድ ጊዜ ይረሳል። ሁላችንም ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። በእኛ ዩኒቨርሲቲ ግን በየትኛውም ቦታ ላይ ጨርሶ የማናልፈው ትልቁ አጀንዳችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች እርስዎ ትልቅ አርዓያ ነዎት። የሕይወት ተሞክሮዎን የሚያጋሩበት ከእነርሱ ጋር የሚገናኙበት የግንኙነት መድረክ አለ ? በግቢ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ከሴት ተማሪዎች ምን አይነት አስተያየት ያገኛሉ?
ኡባ (ዶ/ር)፡– ሴት ተማሪዎች ወደግቢያችን ሲቀላቀሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እናዘጋጅላቸዋለን። በዚያ ላይ የራሴን የሕይወት ተሞክሮ አካፍላቸዋለሁ። ይህን አንዳንድ ጊዜ ለኃይስኩል ተማሪዎችም አደርጋለሁ። እኛን እያዩ እንዲነሳሱ ስለሚያደርግ ትርጉም ያለው ነገር ነው። የእኛ እዚህ መኖር ከታች ያሉ ሴት ልጆች ይቻላል ለካ ብለው እንዲያስቡ እና እንዲጥሩ ያደርጋቸዋል። ሴት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ብዙም ስላልተለመደ እንደሚቻል እንዲያስቡ ይጋብዛቸዋል። የእኔን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሴቶችንም ተሞክሮ እንዲጋሩ እናደርጋለን። ሴቶችን ለማብቃት ከሚሠሩ ሥራዎች አንዱ ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን እያመጡ ከእነርሱ እንዲማሩ የማድረግ ሥራ ነው።
የተለያዩ ችግሮች በሚጋጥሟቸው ጊዜም በቅርበት ችግሮቻቸውን ያዋዩናል። ዩኒቨርሲቲያችን በየዓመቱ ከሚቀበላቸው ተማሪዎች 30 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ ሴት ተማሪዎች ሁሉ እኛ ጋር ያሉትም የሚደርሱባቸው የተለያዩ ጥቃቶች አሉ። ወደ ግቢችን የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እስኪመለሱ ድረስ ከተለያዩ ጥቃቶች እንዲጠበቁ ዩኒቨርሲቲያችን በትኩረት ይሠራል። በተለይ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ላይ ሰፊ ጊዜ ወስደን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን በመስጠትና በማንቃት ራሳቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎችን እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች የሥራ መስኮች በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር ከፍ እንዲል ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ኡባ (ዶ/ር)፡– በነገራችን ላይ አሁን ብዙ ለውጦች አሉ። ከፓርላማ ጀምሮ በካቢኔ ደረጃ በርካታ ለውጦች ተደርገዋል። እነዚህን ማጠናከር አለብን። በሁሉም ነገር ብንመለከታቸው ሴቶች ነገሮችን በጥንቃቄ ከመሥራት አንጻር የተሻለ ቁርጠኝነት አላቸው። የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል ስለሆኑ ያለሴቶች ተሳትፎ የምንፈልገውን ነገር ማሳካት አንችልም። በየትኛውም ቦታ ላይ አሁን ካለው በተሻለ መንገድ መደገፍ አለባቸው። ወደ ኃላፊነት ቦታ ላይ መምጣት ያለባቸው እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም። በቂ የሆነ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷቸው፤ አብቅተናቸው መሆን አለበት። ሴቶችን ካበቃናቸው ተፈጥሮ ከለገሳቸው ጥንካሬ ጋር ተዳምሮ ምንም ነገር ያስቸግራቸዋል ብዬ አላስብም።
አዲስ ዘመን፡- በቅርስ ጥበቃ ረገድ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ ?
ኡባ (ዶ/ር)፡– የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰቡ ባሕል፣ ታሪክ እና ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ አበክሮ ይሠራል። ቅርሶችን በመጠበቅ፣ ምርምር በመሥራት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመናል። ዩኒቨርሲቲያችን አቅዶ ከሚሠራቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የማኅበረሰቡ ባሕል እና ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይ እና ለሚቀጥለው ትውልድ በተገቢው መንገድ እንዲተላለፉ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡
ኡባ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም