አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከነበረበት የስጋት ደረጃ በመውጣት ውጤታማ አፈፃፀም ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ተቋሙ በ2011 የበጀት ዓመት ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከነበረበት የስጋት ደረጃ በመውጣት ውጤታማ የሥራ አፈፃፀም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ተቋሙ በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ነበሩበት፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የደንበኞቹን ቁጥር 43 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በማድረስ የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካትና ካለፈው የበጀት ዓመት የ15 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በገቢ አሰባሰብ ረገድም፣ 36 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 85 በመቶ አሳክቷል፡፡ በዚህም 24 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አግኝቷል፤16 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ግብር ከፍሏል፡፡ በአጠቃላይ ገቢም ሆነ በትርፍ ካለፈው ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
አዳዲስና የተሻሻሉ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ ደንበኞችን ከማርካት፣ ተደራሽነትን ከማሳደግና የገቢ ምንጮችን ከማስፋት አንፃር አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ተቋሙ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶችም 98 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሰብስቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ሳይከፈሉ የቆዩ ብድሮችና የአገልግሎት ክፍያዎች መከፈላቸው ከበጀት ዓመቱ ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ተቋሙ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል እንደረዳው ተናግረዋል፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃርም ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በገንዘብና በዓይነት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ተቋሙን ካጋጠሙትና የአገልግሎት ጥራት መጓደል እንዲከሰት ካደረጉ ችግሮች መካከል የፋይበር መስመሮች መቆረጥና ስርቆት፣ የቴሌኮም ማጭበርበርና የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ዋነኛ ተጠቃሾች እንደነበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት ተፈጥሮ የነበረውን የኢንተርኔት መቋረጥ በተመለከተም ‹‹ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ኢንተርኔት የመዝጋት ፍላጎት የለንም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ አገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ኢንተርኔት ለማቋረጥ ተገደናል፡፡ እንደመንግሥትም እንደተቋምም ኢንተርኔት መዝጋት ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል ብለን ባናምንም ሁሉም ነገር መከናወን የሚችለው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር በመሆኑ ችግሮች ሲፈጠሩ መንግሥት መሰል እርምጃዎችን ለመውሰድ ሊገደድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢንተርኔት የተዘጋው ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት ነው፡፡
ከተቋሙ ባልተወሰደ መረጃ ‹በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ኢትዮ ቴሌኮም በቀን አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር እያጣ ነው› ተብሎ በአንዳንድ አካላትና መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨው ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው ፡፡ኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርኔት በተቋረጠባቸው ቀናት ያጣው አጠቃላይ ገንዘብ 204 ሚሊዮን ብር ነው›› ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
አንተነህ ቸሬ