
በትናንትናው እለት በመኖሪያ ቤታቸው ሞተው የተገኙት የሆሊውድ ተዋናይ እና የባለቤታቸውን አሟሟት እስከ አሁን ማወቅ እንዳልተቻለ የኒው ሜክሲኮ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ፖሊስ ይህንን ያለው ጥንዶቹ ከሞቱ የቆዩ መሆናቸውን የሚገልጹ አንዳንድ ምልክቶች በአስከሬናቸው ላይ መታየቱን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የኦስካር ሽልማቶች አሸናፊው እና የዘጠና አምስት ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ ሄክማን አስከሬን የተገኘው ከማዕድ ቤቱ አጠገብ በምትገኝ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ሲሆን የስልሳ አምስት ዓመቷ ባለቤቱ ቤትሲ አራካዋ ደግሞ በመታጠቢያ ቤታቸው ውስጥ አስክሬኗ መገኘቱ ታውቋል፡፡ የፖሊስ ባለስልጣናቱ በአስከሬናቸው ላይ ምንም አይነት የጉዳት ምልክት እንዳልተገኘ የገለጹ ሲሆን፤ አሟሟታቸው አጠራጣሪ በመሆኑ ምርመራ ከፍቻለው ማለቱ ታውቋል፡፡
ባለስልጣናቱ አክለውም ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ መንገድ ህይወታቸው አልፎ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ውስጥ እንደገቡ ገልጸው፤ እስከ አሁን የሞታቸው መንስኤ ምን እንደሆነ አልታወቀም ብለዋል፡፡ ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በትወና ህይወት ውስጥ የቆየው ዝነኛው ሀክማን ‹‹ዘ ፍሬንች ኮኔክሽን እና አንፎርጊቭን›› በተሰኙ ፊልሞች ላይ በይበልጥ ዝናው እንደገነነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሙያውም በፊልሙ ዘርፍ ብዙዎች የሚጓጉለትን እና ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የኦስካር ሽልማት ሁለት ጊዜ እንዳሸነፈ ተገልጿል፡፡
ሀክማን በሙያው ውስጥ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ ከመቶ በላይ ገጸ-ባህሪያትን ተላብሶ እንደተጫወተ ሲታወቅ በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ማንኛውንም ገጸ-ባህሪ መጫወት የሚችል በሚል የአድናቆት ስምም የተቸረው ተዋናይ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ተዋናይ ሀክማን በአውሮፓውያኑ 1930 በካሊፎርኒያ የተወለደ መሆኑን የህይወት ታሪኩ ያትታል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የሳንታፌ ግዛት ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሠረት፤ ኦልድ ሰንሴት በተሰኘው ሰፈር ወደሚገኘው የጂን ሀክማን መኖሪያ ቤት ፖሊሶችን ያሰማራ ሲሆን፤ ስፍራው ሲደርሱ ጥንዶቹን ጨምሮ ውሻቸውም አብሮ እንደሞተ ለማረጋገጥ ችለዋል። የፖሊስ ኃላፊው አዳን ማንዶዛ ሃሙስ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹ከሞቱ የቆዩ ይመስላሉ፣ ለምን ያህል ጊዜ የሚለው ግን አይታወቅም› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
አክለውም ‹ግድያ ነው በሚለው ላይ ምንም አይነት መተማመኛ ምልክት አላየንም፡፡ ሆኖም ግን ይሄንን ዝም ብለን አናልፈውም፡፡ ሁሉንም አቅጣጫዎችን እናጤናለን› በማለት ተናግረዋል፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው የተገኙት መርማሪ ፖሊስ ጥንዶቹ ከሞቱ እንደቆዩ ገልጸው፤ ለዚህም እንደምክንያት ያነሱት የሟች ቤትሲ አራካዋ እጅና እግር የመበስበስ እንዲሁም ከተለመደው ለየት ብሎ መታየቱን አንስተዋል፡፡
በመኖሪያ ቤታቸው ለሞት የሚዳርግ የጋዝ መፍሰስ ምልክት እንዳልታየ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ያሳወቀ ሲሆን፤ የእሳት አደጋ መስሪያ ቤት በበኩሉ የካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ጋዝ ወይም መመረዝ እንዳላጋጠመ ተናግሯል። በቤትሲ ጭንቅላት አጠገብ ተንቀሳቃሽ ማሞቂያ የተገኘ ሲሆን፤ ይህም ድንገት መሬት ላይ ወድቃ ከሆነ ይዛው ሊሆን እንደሚችል መርማሪዎች ጥቆማ ሰጥተዋል። ለጥንዶቹ የካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ እንዲሁም የመርዛማ ንጥረ ነገሮች ቅድመ ምርመራ እንዲደረግ መርማሪዎች ማስታወቃቸው ተሰምቷል፡፡
ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት መርማሪዎች የሞታቸው ምክንያት እስከ አሁን እንዳልታወቀ ገልጸው፤ በመታጠቢያ ቤቱ ጠረጴዛ ከቤትሲ አስከሬን አጠገብ በሀኪም የታዘዘ የመድኃኒት ጠርሙስ፣ የተበታተኑ ክኒኖች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ የጀርመን ሴፐርድ ዝርያ ያለው ውሻ ከወይዘሮዋ አስከሬን አጠገብ በቁም ሳጥን ውስጥ መገኘቱ ተያይዞ ተገልጿል፡፡ መርማሪ ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ በመኖሪያ ቤታቸው ጥገና የሚያከናውኑ ሁለት ሠራተኞችን ማነጋገሩን ያስታወቀ ሲሆን፤ ሠራተኞቹ ጥንዶቹን በአካል አይተዋቸው እንደማያውቁ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡ ለመረጃው የቢቢሲ የዜና ምንጭን ተጠቅመናል፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም