* ለመኸር እርሻ 70 ሺህ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል
ኢ.ዜ.አ፡- የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ስራ በጀመረበት የመጀመሪያ አንድ ዓመት ለ150 ሺህ መንገደኞች አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።
የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ የተቀላጠፈ የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ነው። የጂቡቲ ተጓዦች አገልግሎት የሚያገኙትም ዓለም አቀፍ መስፈርቱን አሟልተው ነው።
በቀን እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ መንገደኞች በባቡር ትራንስፖርት እንደሚገለገሉ የጠቆሙት ኢንጂነር ጥላሁን፣ የባቡር መስመር ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደስራ መግባቱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የመንገደኞችንም ሆነ የጭነት የጉዞ ጊዜ በመቀነስ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልቅ ስኬት ነው›› ብለዋል።
በሌላ በኩል ድርጅቱ ለመኸር የግብርና ስራ የሚውል 70 ሺህ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቱንም አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ የእቅድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሜኑ ጁሃር ማዳበሪያው በ26 የባቡር ጉዞዎች አዳማና ሞጆ ደርሶ ለግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ማስረከብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ የሚያጓጉዘው በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አሜኑ፣ በገባው ውል መሰረት በፍጥነት አጓጉዞ ለተፈለገለት ዓላማ እንደሚያቀርብም ተናግረዋል፡፡ በበርካታ መኪናዎች ተጓጉዞ በሦስት ቀናት ውስጥ ይገባ የነበረውን ሸቀጥ ከ10 እስከ 11 ሰዓታት በሚፈጅ ጊዜ ብቻ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ ማድረስ እየተቻለ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱም በጫኝነትና አውራጅነት ለተደራጁ 300 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም አቶ አሜኑ ተናግረዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ ድርጅቱ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት ጋር የትራንስፖርት ውል በመፈፀም በአስቸኳይ ወደ አገር ውስጥ መግባት ያለባቸውን ሸቀጦች እያጓጓዘ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህልም ከኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እና ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር ውል በመግባት ከፍተኛ ጭነት ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል፡፡
የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ12 ዓይነት ካርጎዎች የተለያዩ የጭነት አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011