አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተፈጠሩ ላሉት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ዋነኛ ምክንያት በህብረተሰቡ ዘንድ በንባብ የተደገፈ እውቀት ያለመኖሩና የስነ ምግባር ጉድለት መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት የትውልዱ አንባቢ አለመሆንና በመፅሀፍት የታገዘ ዕውቀትና ስነምግባር የተላበሰ አስተዳደግ አለመኖር አሁን ላለው ችግር ዋንኛ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀላፊው ገለጻ በአንድ ሀገር ውስጥ ሰዎች በሰላም፣ በፍቅር ፣በመተሳሰብና በአንድነት የሚኖሩት ከልጅነታቸው ጀምሮ ባዳበሩት የስነምግባር ደረጃ ነው ፤ ትምህርት ቤቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እንዲሁም የፍልስፍናና ኪነጥበብ ማዕከላት የሰዎች ስነልቦና የሚገነባባቸው በመሆናቸው የህብረተሰቡንም የአስተሳሰብ ልህቀት ደረጃ ለማሳደግ ትልቁ ስራ በነዚህ ማእከላት ሊሆን ይገባል፡፡
ኢንጅነሮች ህንፃና መንገድ እንደሚሰሩትና ሀኪሞች ህመምተኛን አክመው ጤና እንደሚሰጡት ሁሉ በማህበረሰቡ ላይ መንፈሳዊ ስራዎች ካልተሰሩ አሁን እንደሚታየው አንዱ ባንዱ ላይ ለጥፋት እንደሚነሳ መገንዘብ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
ትውልድን በንባብ በማነፅ ዘርፍም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊገነባ ያቀደው አዲሱ የመፅሀፍት ቤት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ያሉት ሀላፊው፤ በአንድ ጊዜ 30 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችልና በቁጥርም ብዙ መፅሀፍት ያሉበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሀላፊው የከተማ አስተዳደሩ ለመፅ ሀፍት ቤቱ ትልቅ በጀት በመመደብና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማንበቢያ ስፍራን በመገንባት ትውልዱን የመታደግ ስራን ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ብዙ ችግሮቻችንም የሚፈቱበት ቦታ ይሆናል የሚል ተስፋን መሰነቁን ጠቁመዋል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ደመላሽ ከበደ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው መፅሀፍት ቤቱን ለመገንባት በ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ የተበጀተለት ሲሆን አንድ አመት ከ ስድስት ወር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል ፤ በስራው ላይም ከ ሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ይሰማራሉ ፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
ዳግማዊት ግርማ