አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ 20 ዞኖች ውስጥና በ 32 የተመረጡ ከተሞች በአንድ ጀምበር ከ 200 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ መያዙ ተገለፀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በሰጡት መገለጫ በዘንድሮው ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም፤ በክልሉ ባሉ 20 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 290 የገጠር ወረዳዎች፤ በ 6ሺ747 ቀበሌዎችና በ 32 የተመረጡ ከተሞች በዕለቱ በ12 ሰዓታት ውስጥ ከ 200 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ መፈጠሩን አስረድተዋል ።
ይህን ዓላማ ለማሳካት በክልሉ ኮሚቴዎች ተዋቅረውና የዞንና ወረዳ አስፈፃሚና ቴክኒካል ኮሚቴዎች ተገቢና የተሰናሰለ የወረዳ፣ ዞን እና ክልል መረጃ ማዕከል በማደራጀት እስከ ፌዴራል የሚደርስ መረጃን የማድረስ ስልት በመዘርጋት፤ በቂ የችግኝ ዝግጅትና የጉድጓድ ቁፋሮም መከናወኑን አቶ ዳባ ገልፀዋል፡፡
የፈጻሚ አካላት ተሳትፎን በተመለከተም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ፍቃደኛ ችግኝ ተካዮች ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው ለ 26 የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ለ 54 የክልል መስሪያ ቤቶችም በሶስት በተመረጡ ከተሞች በሰበታ፣ በሆለታና የረር ከ36 ሺህ በላይ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ዳባ አክለውም እስካሁን ባለው ሁኔታ ክልሉ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደሚቻል ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
ወይንሸት ካሳ