ክረምቱን የገፋባትን ቡታጋዙንና ከሽቦ አልጋው ደረት ላይ የተጣበቀችውን ምላስ የምታህል ስስ የጥጥ ፍራሹን የተመለከተ ሁሉ “አረ እባክህን አግባ?” ሳይለው አይቀርም፤ ወላጆቹ እንኳን “ምነው አዱኛህን ብናይ?” ሲሉት “እየጸለይኩ ነው” ብሎ ይመልስላቸዋል። “እስከመቼ? የተዘጋ በር ላይ ቆመህ ታንቀላፋለህ እንዴ? አንኳኳ እንጂ” ይሉታል።
ኃይሉ ሁልጊዜ ስለትዳር ባሰበ ቁጥር የዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲው የመቶ አለቃ ግሩም ኃይሌ የእህል ውሃ አገጣጣሚ ትዝ ይለዋል። አርቲስት ግሩም ኃይሌ (መቶ አለቃ) ከቢሮ የመውጫ ሰአት የታክሲ ትርምሱ ወረፋ ማግኘት ቸግሮት በእግሩ ሲያዘግም ሆድ የባሰው የአዲስ አበባ ሰማይ በእንባ ተቀበለው። ከመንገዱ መሃል ወገብ ቆሞ ታክሲ ቢያንቃቃ በቆፈኑ ከመገረፍ በቀር ጠብ ያለለት ነገር የለም። ይህን ጊዜ በዓይኑ ዙሪያ ገባውን ሲቃኝ ከሱ ትንሽ ራቅ ብሎ ዣንጥላ ይዛ የቆመች ሴት ተመለከተና ወደርሷ አቀና።
ካጠገቧ እንደደረሰ “አርፋጅ ሳይቀጣጠር ይገናኛል” ሲል ቀለዳትና “ንግስት ሆይ! ከድንኳንዎ እንድገባ ይፍቀዱልኝ?” አለ ከፊቷ እንደማጎንበስ ብሎ። እሷም ቃል ሳይወጣት በሰውነት ቋንቋ መፍቀዷን ገልጻ አስጠለለችው። ከብዙ የታክሲ ጥበቃ በኋላ ተስፋ ቆርጠው እንዲሸኛት ፈቃዷን ጠይቆ የእግር ጉዞው ተጀመረ።
በደራው ጨዋታ ዝናቡን ረስተው ማንነታቸውን ሲገላለጡ ልብ ለልብ ለመገናኘት በቁ። አድራሻ ተለዋውጠው የጀመሩት ወዳጅነት አድጎ ጎጆ ከመቀለስ አደረሳቸው። ኃይሉም ትዳርን ሲያስብ ፈጣሪ ሲሰጥ እንጂ በፍለጋ አለመሆኑን ተገንዝቦ ያቺን አጋጣሚዋን ቀን መጠበቅ ይዟል፤ ጓደኞቹ ግን “እገሊትን ብታያት? እንትናን አልፈቀድካትም?” እያሉ ይወተውቱታል። ገና ለገና “ሰው አለኝ” ብሎ አጓጉል ቦታ ላለመውደቅ እየተጠነቀቀ ነው። እንዲህ አይነቱ ሃሳብ ሲያስጨንቀው አንድ ሽማግሌ ያጫወቱት ወግ ትዝ ይለውና ይጽናናል።
ፈጣሪ “እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደእኔ ኑ፤ ችግራችሁ ይቀልላችኋል” ይልና ሰው ሁሉ እንደየችግሩ መጠን በፌስታልም በጆንያም ተሸክሞ ይጓዛል፤ ከራሱ አልፎ ተርፎም ለሌላ ሰው አሸክሞ የሚሄድም አለ። ጨለማ ከወረሰው አዳራሽ ውስጥ እንዲያስቀምጡት ከተደረገ በኋላ መልሰው እንዲያነሱት ታዘዙ፤ ሰው ሁሉ ግን በስህተት የሌላ ሰው ችግር እንዳያነሳ ሰግቶ “የራሴው ይሻለኛል” ብሎ ማንሳቱን ተወው።
ኃይሉ በጥሞና ሲያሰላስል ቆይቶ ከልቦናው ጋር መከረ። “መጀመሪያ ባል መሆን እችላለሁ? ምራቄንስ የዋጥኩ ሰው ነኝ? ሚስት ዘውድ ነች፤ ዘውድ ለመድፋት ደግሞ በጊዜና በሁኔታዎች ተፈትኜ የነጠርኩ ጥበብ ፈትሎ እንዳስጌጠው ሸማ የጠራሁ መሆን ይጠበቅብኛል። ለዚህም አንድ ሰው በዓለም ሲኖር ባለሁለት ፎቅ ቤት ቢኖረው መልካም ነው። በምድር ቤቱ ውስጥ ከወላጆቹ የወረሰውን ሀብትና ንብረት ያስቀምጥበታል፤ ባንደኛው ፎቅ ላይ እሱ ራሱ ይኖርበታል፤ በሁለተኛው ፎቅ ላይ ደግሞ እንግዳ ያሳርፍበታል። ይህ ምሳሌ ነው። ምድር ቤቱ የትናንት ታሪክና ማንነት፣ አንደኛው ፎቅ የዛሬ ህይወት፣ ሁለተኛው ፎቅ የነገው ተተኪ ትውልድ ነው፤ አንድም ቤቱ ዘመናዊ ነው።
በዘመን ቤት አሰራር ውስጥ ምድር ቤቱ መሰረት፣ አንደኛው ፎቅ ግርግዳ፣ ሁለተኛው ፎቅ ጣሪያ ነው፤ እናም የነገው ተተኪ ትውልድ ልጄ እንዲሁም የቤቴና የኑሮዬ መሰረት፣ ግርግዳና ጣሪያ የሆነችው ሚስቴ ወርቅ ሆና ስትመጣ ወርቅ ሆኜ መጠበቅ አለብኝ። ደግሞኮ” አለና ከአስቴር አወቀ ሙዚቃ ስንኝ ተውሶ ራሱን ገሰጸ።
“ያገኙትን አፍሰው ቢበሉት፣
ያስቸግር የለም ወይ ሲውጡት።”
ከመገናኛ ወደሳሪስ በሚሄደው ታክሲ ወንበር ይጋሩ እንጂ በመሃላቸው ንግግር የለም። ታክሲው ከቦታው ደርሶ ተሳፋሪው ሲራገፍ የኃይሉ ስልክ ከኪሱ አፈትልኮ ወንበር የተጋራችው ሳሮን እጅ ገባ። “ለባለቤቱ እንዴት ነው መመለስ የምችለው?” እያለች በመጨነቅ ላይ ሳለች ከሰአታት በኋላ ያነሳችው ስልክ ደወለ። ህሊናዋ እረፍት እየተሰማው ከተቀጣጠሩበት ስፍራ ስትደርስ
“ተይ አላልኩሽም ወይ ኩል ተኩሎ ሜዳ፣
አይን ወረተኛ ነው ያመጣል እንግዳ።”
እንዲሉ ዓይኗ ቀላውጦ ታክሲው ውስጥ የተሰማት እንግዳ ስሜት ነፍስ ዘርቶ ልቧ ውስጥ ተገላበጠ። “ሻይ ቡና እንበል?” ስትለው ኃይሉ እየተግደረደረ ከቆመበት ባስ መጠበቂያ አቅራቢያ ወደሚገኘው ብሉ ጃይዝ ሪስቶራንት ዘለቁ። እንኳን በልቶት ሰምቶት የማያውቀው ባለፈረንጅ ስሙ ምግብ መጥቶ መአዱን መቁረስ ሲጀምሩ ሳሮን ጉልቻ የሚያክል ጉርሻ አስተካክላ ዘረጋችለት። እንደፈራ ሁኔታው ቢያሳብቅም ማፈሩን ላለማጋለጥ እየጣረ የግዱን ተቀበላት። ምላሱ ተሳስሮ ሰውነቱ በላብ ሲዘፈቅ አንደበቱ ተለጉሞ ጨዋታ ከዳው። በልተው እንደጨረሱ ማወራረጃ ይዘው ፉት ሲሉ ሳሮን ዝምታቸውን ለመስበር ወግ መዘዘች።
“የንግድ ቦታዎቻችን ስማቸው ፈረንጅኛ ነው፤ ታዲያ ይሄ ነገር ከባህል አንጻር ችግር ያለው አይመስልህም?” በማለት ለወሬ ጋበዘችው። “ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታቸውን አገናዝበው ለልጆቻቸው እንዲሁም ለንግድ ተቋሞቻቸው ስም የሚያወጡበትን የወላጆቻችንን ወግና ባህል ኋላ ቀር ነው ብለን ሁለመናችንን የፈረንጅ አፍ ወረሰው፤ እንዲህ አይነቱን አጓጉል ልማድ ለማረቅም እንደቻይናው ማኦዜዶንግ ያለ የባህል አብዮት አቀንቃኝ ያስፈልገናል” አለ ዓይኑን ፍለጋ የሚቃብዘው ዓይኗን ላለማየት እየሸሸ። ሂሳብ ከፍለው ወጡና ከታክሲ ተራ ሸኝቷት ሲመለስ እቃ የረሳች ይመስል ስሙን በመጥራት ካስቆመችው በኋላ ስትሮጥ መጥታ “አግብተሃል?” ብላ ስትጠይቀው ጥይት የሳተው አራስ ነብር ሆነ።
“ግራ እንደምትጋባ አውቃለሁ፤ ግን እመነኝ ጥሩ ሴት ነኝ። ጥሩ ወንድ ነውና የምሻው ካላገባህ እንጋባ፤ ደግሞም ልብ በል፤ በሁለት ቀን ውስጥ ካልደወልክልኝ አንተም እኔም የሌላ ሰው መሆናችን ነው” አለችና አድራሻዋን የጻፈችበትን ወረቀት አሳቅፋው ወደኋላ ዞራ ሳታይ ጉዞዋን ወደፊት ቀጠለች።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም