ለአግሮ ኢንዱስትሪው ምርታማነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት

ከጥራት ሥራ አመራር ፋይዳዎች መካከል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል አግልግሎት ሰጪዎችና አምራች ደርጅቶች እንዲሁም የግብርና ምርት አቀነባባሪዎች በተሠማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል የሚለው ይጠቀሳልየሠራተኞቻቸውን የሥራ ብቃት ፣ የደንበኞቻቸውን ፍላጎት እና የሠሯቸውን የወደፊት መዳረሻ ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አቅም እንደሚፈጥሩላቸውም ይታመናል

የጥራት ሥራ አመራር በዓለም አቀፍ ደረጃም ወሳኝ ሚና ይጫወታል የጥራት ሥራ አመራር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥራ ላይ እንዲውል ያደረገው ጃፓናዊው ደብሊን ኤድዋርድ ዴሚንግ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ሰው በጃፓን የጥራት አባት በመባል ይታወቃል

ይህ ታዋቂ ሰው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጥራት ሥራ አመራርን በመተግበር ስሙን አስጠብቆ የኖረውንና በጥራቱ የሚታወቀውን ቶዮታ መኪናን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ማስቻሉን መረጃዎቹ ጠቅው፣ ኩባንያዎቹና ድርጅቶቹ የሰው፣ የገንዘብ እና የተፈጥሮ አቅማቸውን ተጠቅመው ወደ ተሻለ ለውጥ እንዲሸጋገሩ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ያመለክታሉ

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም በተለይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ጎን ለጎን ለአግሮ ኢንዱስትሪው ሽግግር መሳለጥ አስቻይ የተባሉ መርሃ-ግብሮችን ነድፋ በመተግበር እየሠራች ትገኛለችበተለይም የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን በጥራትም ሆነ በምርታማነት ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ ያስችላቸው ዘንድ የግሉን ዘርፍ አቅም የሚያጎለብቱ የድጋፍና የቁጥጥር ማሕቀፎችን በማዘጋጀት እንዲሁም መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት እያከናወነች ያለችው ሥራ አበረታች መሆኑ ይጠቀሳል

በእነዚህ ዓመታት የኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት ለማሳደግ በመንግሥት ከተሠሩ አንኳር የልማት ተግባራት መካከል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ የተመረቀው የጥራት መንደር ዋነኛው ነውየጥራት መንደሩ ለዘላቂ እድገት መሠረት የሚጥልና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ ያበሰረ ስለመሆኑም በወቅቱ ተጠቁሟል

የተቀናጀና ደረጃውን የጠበቀ የጥራት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን፤ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በብዛት የማይገኙ የሴራሚክ፣ የባትሪ እና የሶላር ሃይል ማመንጫ መፈተሻ መሣሪያዎችን ለመፈተሽ የሚያስችሉ ላብራቶሪዎችም ጭምር አሉት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የጥራት መሠረተ ልማት ለዘላቂ ዕድገት መሠረት መሆኑን ገልጸውም ነበርበተለይ ጥራት ያለው ምርት ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችል እንዲሁም ጥራት ከዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተሳሰረ መሆኑንም አመላክተዋልከዚህ አኳያ የጥራት መንደሩ ደረጃቸውን የጠበቁና ጤናማ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረው፣ እጅግ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና በኢትዮጵያ ምርቶች ወጪ ንግድ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደታመነበትም ገልጸዋል፡፡

ለረጅም ጊዜያት በወተት እና የወተት ተዋፅኦ ምርቶች ማቀነባበር የሚታወቀው ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ (ማማ ወተት) ለምርት ጥራትና ደህንነት መጠበቅ እያከናወነ ባለው ሥራ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተቀብሏል

ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ (ማማ ወተት) ዓለምአቀፍ ተዋዳዳሪነትን ለማጎልበትና የጥራት ደረጃቸውን ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ ካሉ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች መካከል አንዱ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተጠቅሷልድርጅቱ ላለፉት 30 ዓመታት በምርት፣ በተደራሽነትም ሆነ ጥራት አቅሙን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብን ሲያደርግ ቆይቷልለበርካቶች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ለግብዓትና ለምርት አቅርቦትም እንዲሁ ከበርካቶች ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሠራ ሲሆን፣ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ድርጅቱ የሌሎች ሀገራትን ልምድ እና ተሞክሮ በመቅሰም በ2017 ዓ.ም የምርት እና አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ የሚያስችል ዓለምአቀፍ የጥራት ሥራ አመራር እና የምግብ ደህንነት ሥርዓት /food sefe­ty and Quality Management system እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ሕጋዊ አሠራሮችን ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር /Enterprise Re­source Planning (ERP)/ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን (ሲስተሞችን) ተግባራዊ አድርጓል

የድርጅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳራ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ምርታማነትን በማሳደግና በጥራት በማምረት በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ለዓመታት ርብርብ አድርጓልበተለይም በ2017 ዓ.ም የአይ. ኤስኦ 9001፡ 2018 ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ሥራዎቹን እና አገልግሎቶቹን ከምንጊዜውም በላይ ዘመናዊ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

‹‹ድርጅታችን ለምግብ ደህንነት እና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለ30 ዓመታት ዘልቋል›› ያሉት ወይዘሮ ሳራ፤ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘቱ ለቀጣይ ስኬት ይበልጥ እንዲነሳሳ እንደሚያደርገው ይናገራሉ። ለሰርተፍኬቱ መገኘት ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከተው የሠራተኞችና የማህበረሰቡ የተቀናጀ ጥረት እንደሆነም ጠቅሰዋልበቀጣይም ዘርፉን በማስፋት የአግሮ ኢንዱስትሪውን ምርቶች በጥራት በማምረት ለሀገሪቱ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መጎልበት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት አጠናክሮ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል

የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ይመር በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢንዱስትሪው በ1986 ዓ.ም ሰበታ ፋርም ተብሎ የተመሠረተ ሲሆን፣ ከወተት ላሞች ርባታ ወደ ማቀነባበር ሲገባ በ1996 ዓ.ም ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ተብሎ የስያሜ ለውጥ አድርጓልበአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 150 ሺህ ሊትር ድረስ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ምርቶችን የማቀነባበር አቅም ያለው ሲሆን፣ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ አድል ፈጥሯል፤ ከ50 ሺህ በላይ ከሚሆኑ አርሶ/ አርብቶ አደሮች ጋር ደግሞ የገበያ ትስስር በመፍጠር እየሠራ ይገኛል

በቀጣይም ከአንድ ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል ለመፍጠር ማቀዱን ጠቁመው፣ ከ250 ሺ በላይ ከሚሆኑ አርሶ/ አርብቶ አደሮች እና ምርቱን በመላው ሀገሪቱ ለተጠቃሚ ከሚያደርሱ ከሁለት ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ወኪሎች በአጠቃላይ 300 ሺህ ከሚሆኑ ዜጎች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ማቀዱን አቶ ሙሉጌታ ያመለክታሉ

የኢንዱስትሪው ምርት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ምዘና አልፎ ጥራቱ መረጋገጡ በሸማቾች ዘንድ ያለውን እምነት እንደሚያጠናክርለት ጠቅሰው፣ በቀጣይም በተሻለ ጥራት እንዲያመርት እንደሚያነሳሳው ጠቁመዋል

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው ‹‹ለአንድ ኢንዱስትሪ እድገት የሠራተኞቹና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው የጥራት ጉዳይ ለአንድ ግለሰብ ብቻ ሊተው አይችልም፤ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ፣ ድካምና ልፋትን ይጠይቃል›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ከብዙ ድካምና ልፋት በኋላ የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ የአይ.ሶ 9001፡2018 የጥራት ሥራ አመራር እንዲሁም የምግብ ደህንነት ቁጥጥር አይሶ 22000 ሰርተፍኬት ያገኘው ለጥራት ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጡ እንደሆነ ያስረዳሉ

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳመለከቱት፤ አግሮ ኢንዱስትሪው ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማጎልበት በዋናነት ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮችን አሟልቶ ወደ ገበያ መግባት ይጠበቅበታል ለእዚህም አንደኛውና ወሳኙ ጉዳይ የተሻለ ጥራት ይዞ ወደ ገበያ መቅረብ ነው ሁለተኛው ሸማቹ ዋጋው የቀነሰ ምርት የሚፈልግ መሆኑን መረዳት፣ ሌላኛው በተባለው ጊዜ የተባለው ቦታ ማድረስ መቻል ነውእነዚህን ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች በተከታታይ ይዞ መገኘት ከዘርፉ ተዋናዮች በወሳኝነት ይጠበቃል

እንደ አቶ እንዳለው ገለፃ፤ ቀደም ሲል ጥራት ደንበኛው የሚፈልገውን ብቻ ማሟላት አይነት ተደርጎ ይወሰድ ነበርበአሁኑ ወቅት ግን ደንበኛው ከሚፈልገውም በላይ እርካታ ማምጣት መቻልም ይጠበቃልከዚህ አንፃር ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ላለፉት 30 ዓመታት የምርት ጥራቱንም ሆነ ተደራሽነቱን ማስፋት ችሏልበጥራትም ሆነ በማሸጊያ ደረጃ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የበቃው በባለቤቱ፣ በሠራተኞቹና በአመራሩ ቁርጠኝነት ነው

‹‹ጥራት ሲባል ዛሬ የሚሰጠው የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የጥራት ጉዳይ የአንድ ኢንዱስትሪ ባህል እንዲሆንም ይፈለጋል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የዛሬው ሰርተፍኬት ለነገ ትልቅ ሞራል ሆኖ ሁሉም ጥራትን ባህል አድርጎ እንዲሠራ የሚያነሳሳ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል

አግሮ ኢንዱስትሪው ጥራትን ባህል ለማድረግ በቅድሚያ የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር ለጥራት መሻሻል የሚሆን መሠረተ ልማት መዘርጋት እንደሚጠበቅ ያመለክታሉ፡፡

መንግሥት ለጥራት ትልቅ ቁርጠኝነት ወስዶ ፣ ከፍተኛ መዋለንዋይ አውጥቶ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጥራት መንደር መገንባቱን ጠቅሰው፣ በጥራት መንደሩ ያሉት ተቋማት ባይገነቡ ኖሮ ማማ ወተት ምርቱን በሶስተኛ ወገን ማስፈተሽ ይጠበቅበት እንደነበርም ገልጸዋልይህ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት በሌላ ሀገር ማስፈተሽን የግድ ይል እንደነበርም ያስረዳሉ

እሳቸው እንዳብራሩት፤ መንግሥት የጥራት መንደሩን ከ ስምንት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ነው የገነባውበመንደሩ ከሰባት ነጥብ ሁለት ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ወደ 20 ህንፃዎች ተገንብተዋልመንደሩ ከ150 በላይ ላብራቶሪዎችም አሉትበዚህም በምግብና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ብቻ ሳይሆን በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ ፣ በኮንስትራክሽን ግብዓት፣ በኤሌክትሪክ ላይ ፍተሻ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡

በተጨማሪም ጥራትን ለማረጋገጥ አቅሙ የጎለበተ፣ ቁርጠኛ የሆነ ሠራተኛ፤ አቅራቢና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊኖሩ እንደሚገባ አቶ እንዳለው አመልክተው፣ ‹‹ባለቤት አንድ ሰው ነው፤ ግን አጠቃላይ የኢንዱስትሪው ማህበረሰብ አጠቃላይ ሠራተኛ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል›› ይላሉለሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ አቅራቢ ወይም መጋቢ የሆናችሁ አካላትም በጥንቃቄና በጥራት ማምረት ወሳኝነት እንዳለው መገንዘብ አለባችሁ ሲሉም አስታውቀዋል

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን የፈረመች እንደመሆኗ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለመወዳደር አቅሟን ማጎልበት ይኖርባታልይህ ብቻ ሳይሆን የዓለም የንግድ ድርጅትንም ከአንድና ከሁለት ዓመት ባላነሰ ጊዜ ሙሉ በአባልነት እንደምትቀላቀልም ይጠበቃል‹‹ስለዚህ ገበያው ለእኛ ብቻ አይደለም ፤ ለበርካታ ኢንዱስትሪዎች ነው፤ ያኔ በጥራት ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤል አንበርብር በበኩላቸው፤ በጥራት ለሚያመርቱ አምራቾች እውቅና መስጠት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ተወዳዳሪነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

ማማ ወተት ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ሰርተፍኬት ማግኘቱ ምርቱን በመላው ዓለም ለማቅረብ እንደሚያግዘው ያመለክታሉ። ‹‹የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የጥራት ደረጃን በከፍተኛ ደረጃ ለመጠበቅና የሸማቹን እምነት ለማጎልበት የምግብ ሥራ አመራር ሥርዓትን ወደ መተግበር መግባቱም የድርጅቱን ቁርጠኝነት ያሳያል›› ይላሉ፡፡

በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች ከምግብ ደህንነት ጋር የሚነሱ የአደጋ ስጋቶችን ለማስወገድ የሚከና ውኗቸው ተግባሮች በምግብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሃላፊነትን በመውሰድ አስተማማኝ ተቋም እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸውም ያስገነዝባሉድርጅቱ የአይ.ሶ 9001፡2018 የጥራት ሥራ አመራር እንዲሁም የምግብ ደህንነት ቁጥጥር አይሶ 22000 ሰርተፍኬት ማግኘቱ የሥራ ውጤማነቱን ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚያግዘው ይናገራሉለህብረተሰቡም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል

እሳቸው እንዳሉት፤ የምስክር ወረቀቱ ከምግብ ደህንነት ጋር የሚነሱ አደጋዎች እንዲቀንሱ ያደርጋል፤ የድርጅቱን የገበያ ተወዳዳሪነት ያጠናክራል፤ ወጪ ይቀንስለታል፤ ተጨማሪ የሥራ እድልም መፍጠርም ያስችለዋልበተለይ ጥራት ላይ አተኩሮ እንዲሠራ በማድረግ ከፍተኛ ምርታማነት እንዲኖረው ያደርጋል፤ የአሠራር ቅልጥፍናውንም ይበልጥ ያሳልጥለታል

መንግሥት የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እያደረገ ላለው ጥረት ወሳኝ ሚና እንደ ሚጫወትም ጠቁመው፤ ሌሎች መሰል ኢንዱስት ሪዎችም ይህን ተሞክሮ በመውሰድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል ፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You