
- ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በቡታጅራ ተጀምሯል
ቡታጅራ፡– የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞችን ከመፋዘዝና ከእርጅና የሚታደጉ መሆናቸውን እና ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በቡታጅራ ከተማ መጀመሩን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አሕመድ አስታወቁ፡፡ በግማሽ ቀን ብቻ ከሕዝብ ጋር በተደረገ ውይይት 101 ሚሊዮን ብር ለኮሪደር ልማቱ ሥራ መሰብሰብ መቻሉን ገለጹ፡፡
አቶ አብዶ፣ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቡታጅራ ከተማ የሚሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ ጠቅላላ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ሥራ በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በከንቲባ ፕሮጀክት ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት ወደሁለተኛው ምዕራፍ የተሸጋገረ ሲሆን፣ እየተሠራ ያለውም በሦስት ምዕራፍ እንዲጠናቀቅ ታስቦ ነው፡፡ ይህ ከተሞችን ከመፋዘዝና ከእርጅና የሚታደገው የኮሪደር ልማት ሥራ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛው ምዕራፍ ተጀምሯል፡፡
በመጀመሪያው ዙር እየተሠራ ያለው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ነው ያሉት ከንቲባ አብዶ፣ ሁለተኛውም መጀመሩን ጠቁመው ይህ ገቢን አሟጥጦ በመሰብሰብ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚሠራ ልማት ነው ብለዋል፡፡ የሚሠራው ሥራ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ የሚያስወጣ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ከሌላ ከማንም የሚመጣ ሳይሆን ከውስጥ አቅም የሚመነጭ ነው፡፡ የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን እንዴት እንደቀየረና እንዳስዋበ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በዚህ አግባቡ እየተሠራ በመሆኑም በርካታ ከተሞችን ከመፋዘዝና ከእርጅና እየታደጋቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በቡታጅራ ከተማ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም ነው፤ የኢትዮጵያ ከተሞች ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የሚያሟሉ ባለመሆናቸው ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ከተማዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ነዋሪውም ሆነ ኢንቨስተሩ ለኑሮ፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ማዕከልነት፣ ለኮንፍረንስ ተመራጭ የሆኑ ከተማዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ቡታጅራ ከተማን የበለጠ ለማስዋብ እየተሠራ ነው፡፡
በእኛም ከተማ የሚለሙ የወንዝ ዳርቻዎች እና የሕዝብ አደባባዮችም አሉ ያሉት ከንቲባው፣ ሌሎች በርካታ ሥራዎችንም የኮሪደር ልማቱ የያዘ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እየተሠራ ያለው ሥራ ከተማዋን በአዲስ መልክ የመሥራት ያህል ነው፡፡ ይህን እየሠራን ያለነው ከማኅበረሰባችንና ከባለሀብቱ ጋር ተግባብተን ነው፡፡ የጋራ ጥረት፣ ቁርጠኝነትና ግብ ጥለን እንደ አንድ ትልቅ ፕሮጀክታችን አስበን እየሠራን እንገኛለን፡፡ እስከ አሁንም ያለው አፈፃፀም የተሻለ የሚባል ነው፡፡
እንደ ከንቲባ አብዶ ገለጻ፤ በኮሪደር ልማቱ የከተማው ሕዝብ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚያበረታታ ነው፡፡ በግማሽ ቀን ብቻ ከሕዝብ ጋር በተደረገ ውይይትም 101 ሚሊዮን ብር ከሕዝቡ ከራሱ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህ ቀላል የሚባል ተሞክሮ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማኅበረሰቡ የኮሪደር ልማቱ ደርሶበት ቦታውን እየለቀቀ እና ቤቱን እያፈረሰ እንኳ የራሱን ቤት እራሱ መልሶ እየገነባ ለኮሪደር ልማቱ ርዳታ ያደረገበት ሁኔታ በጣም የሚደገፍ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ሥራችንን በጥራት፣ በፍጥነትና በቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን፡፡
የተሻለ ከተማ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚል ግብ ይዘን በመሥራት ላይ ነን፡፡ በዚህም ሥራ የተሻለ ውጤት እየታየ ነው፡፡ የሕዝቡም ሆነ የተቋማት ግብረ መልስ እያመላከተን ያለው ይህንኑ ነው፡፡ ለዚህ ምስክር መሆን የሚችለው በኮሪደር ልማት ምክንያት ቤቱ እየፈረሰበት እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለኮሪደር ልማቱ ድጋፍ የሚያደርግ ማኅበረሰብ ማየት መቻላችን ነው ብለዋል፡፡ ነዋሪው ሕንጻ ፈርሶበት ሳያማርር ደስተኛ ሆኖ ‹‹እኔም ለከተማዬ ዐሻራዬን አሳርፋለሁ›› በሚል ሁለትና ሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ያልተጠበቀ በጎነት ነው፡፡ ይህን ሕዝብ ደግሞ በልማት መካስ ከእኛ የሚጠበቅ ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም