
በአንዱ ቀን በማለዳው ከእንቅልፉ ሲነቃ አዕምሮው ‹‹ለወደፊትህ ሕይወትህ ምንም ዋስትና የለህም፤ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚያጋጥሙህ ጉዳዮች ጭንቀት ውስጥ ነህ፤ ብቻህን የቤተሰብህን ኃላፊነት እንደተሸከምክ ነው›› በሚል አሉታዊ ሃሳብ ደጋግሞ የሚመጣበትን አንድ ግለሰብ በአዕምሮህ ተመልከት። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሌም ቀኑን በብሩህ ተስፋ የሚጀምር፣ በቆራጥነት እና ፈተናዎችን ለማሸነፍ ባለው እምነት ጠንካራ የሆነ ሌላ ግለሰብ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።
ሁለቱም ሰዎች አንድ ዓይነት ምግብ የሚመገቡ፣ አንድ ዓይነት የኑሮ ደረጃና ችግር ያጋጠማቸው ቢሆንም ለችግሮቻቸው ያላቸው እይታ አዎንታዊና አሉታዊ በመሆኑ ብቻ የአዕምሮም ይሁን አካላዊ ጤንነታቸው ፍፁም የተለያየ ነው። ለመሆኑ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ዛሬ በ”መጋቢ አዕምሮ” አምድ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሰዎች ችግሮችን ለመጋፈጥ ያላቸው እሳቤና አዕምሯዊ ምላሽ ስላለው ልዩነት በዝርዝር እንመለከታለን። አዎንታዊ አስተሳሰብ አካላዊ ጤናን እንዴት እንደሚጠብቅና አሉታዊ ሲሆን ደግሞ በምን መልክ እንደሚጎዳ እንመለከታለን።
በመግቢያችን ላይ ያነሳናቸው ሁለቱ ግለሰቦች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሲኖሩ ተመሳሳይ ምግቦችን ሊመገቡ እና ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥማቸው ቢቆይም አካላዊ ጤንነታቸው በጣም የተለየ ነው። ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ ስናነሳ ምክንያቱን እንደሚከተለው እናገኘዋለን። ነገሩ እንዲህ ነው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የጤና ሳይንስ ጥናቶች እንደሚጠቁሙን አዕምሮ እና አካል በጣም የተሳሰሩ ናቸው። የምናስበው እና የሚሰማን ነገር “በጭንቅላታችን” ውስጥ ብቻ አይቆምም። አስተሳሰባቸውን ሰውነታችን እንዴት እንደሚሠራ እንደሚፈውስ እና እንደሚያድግ ይወስናል።
አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ እሳቤያችን በአካላችን ጤንነት ላይ ስላለው ተፅዕኖና ትስስር ማወቅ በተለይ በእለት ተእለት ኑሯቸው ላይ ለየት ያለ ፈተና ለሚገጥማቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች ወሳኝ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ባሕል በእጅጉ አነስተኛ በሆነበት፣ ባሕላዊ ልማዶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን በሚቀርጹበት ከባቢ ላይ በሆንበት እና የጤና መስጫ ተቋማትና መሠረተ ልማት ተደራሽነት ውስን በሆነበት ሀገር ለረዥም ጊዜ በጤንነት እና በደህንነትን ለመቆየት ዋስትና እንዲኖረን አዎንታዊ አስተሳሰብ መገንባት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የዛሬው ዋና ትኩረታችን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም በእነዚህ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ላይ በማተኮር አስተሳሰቦች፣ አመለካከቶች እና እምነቶች በአካላዊ ጤናቸው ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለማየት እንሞክራለን። የወጣቶችን እሳቤ ማስተካከልና ጤናቸውን መገንባት የነገዋን ኢትዮጵያ ከመገንባት የማይተናነስ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም እናመላክታለን።
የጤና ሳይንስ ምርምሮችና ግኝቶች እንደሚያመለክቱት የአእምሮ እና የሰውነት ግንኙነት ጤናማ አለመሆን አካላዊ ጤንነትን ይጎዳል። ዘመናዊ ሳይንስ ውጥረት፣ ጭንቀት እና አሉታዊ አስተሳሰብ በሽታ የመከላከል ሥርዓትን ያዳክማል ይላል። ውፍረትን በመጨመር፣ እንደ ስኳር በሽታ እና የልብ ህመም ያሉ ሥር ለሰደዱ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
በተቃራኒው ደግሞ አእምሮ በአዎንታዊ (ተስፋ፣ ጽናት፣ እና የዓላማ) ስሜቶች የተሞላ ከሆነ በሽታ የመከላከል አቅማችንን እንደሚያሳድግ እነዚህ ሳይንሳዊ ጥናቶች ይነግሩናል። አዎንታዊ አስተሳሰብ ከበሽታ በቶሎ የማገገምን አቅም ይፈጥርልናል፤ አልፎ ተርፎም እድሜያችንን ያራዝመዋል።
ለምሳሌ በጥናቶቹ እንደተመላከተው በሕይወታቸው ምስጋናን ወይም በጎ አስተሳሰብን የሚይዙ ሰዎች ዝቅተኛ የኮሌስትሮል መጠን “የጭንቀት ሆርሞን” እና የተሻለ የልብ እና የደም ቧንቧ ጤንነት አላቸው። በተመሳሳይ የወደፊት ተስፋቸው ብሩህ መሆኑን የሚያስቡ፤ እውቀታቸው በጥረት ሊሻሻሉ እንደሚችሉ የሚያምኑ ግለሰቦች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ሚዛናዊ አመጋገብ እንዲሁም ጤናማ ልማዶችን የመከተል እድላቸው ሰፊ ነው። እነዚህ ልማዶች ደግሞ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ድብርት እና ሌሎች ሁኔታዎችን ይከላከላሉ። በመሆኑም አስተሳሰባችን በቀጥታ ከአካላዊ ጤንነታችን ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያመላክታል።
ተላላፊ በሽታዎች እና ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች (እንደ ኤች አይ ቪ፣ ስኳር በሽታ ያሉ) ሁለቱም አሳሳቢ ጉዳዮች በሆኑባት ኢትዮጵያ አዎንታዊ አስተሳሰብ መያዝ አካላዊ ጤናችንን ለመጠበቅና ከሚያጋጥመን ህመም አስቀድመን የመከላከያ መሳሪያ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ባሕላዊ እና ማህበረሰባዊ ሁኔታዎች ወጣቶች ለጤንነታቸው ያላቸውን አመለካከት ይቀርጻሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች ናቸው። የእነዚህ ወጣቶች ጤንነት የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ይወስናል። ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አሳሳቢ የጤና ችግር በስፋት መኖሩን ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በየቀኑ የሚሰጠውን የ60 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያሟሉ ሕፃናትና ወጣቶች 28 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው፤ በከተሞች ደግሞ ከገጠር የባሰ ነው። ረጅም ሰዓት በሞባይል ስክሪኖች ላይ ማሳለፍን የመሰሉ አሉታዊ ባህሪያት እየጨመሩ ነው።
እነዚህ አሀዛዊ መረጃዎች የሚናገሩት ውስኑን የኢትዮጵያውያን የጤና አጠባበቅ ባህሪ ብቻ ነው። ከቁጥሩ በስተጀርባ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን የሚያደናቅፉ አመለካከቶች እና እምነቶች አሉ። ይህንን በገሃዱ ዓለም ምሳሌዎች ለመመልከት እንሞክር።
የመጀመሪያው ማስረጃ በአዲስ አበባ እ.ኤ.አ በ2023 የተደረገ ጥናት ነው። ጥናቱ እንደሚያመለክተው ራሳቸውን “በአካል ብቃት እንቅስቃሴ” የሚያነቃቁ ታዳጊ ወጣቶች በስፖርት የመሳተፍ፣ ከቤት ውጭ የመጫወት ወይም ወደ ትምህርት ቤት በእግር ጉዞ የመሄድ እድላቸው አናሳ ነው። ይህ አጋጣሚ ወጣቶቸ በራሳቸው እንዳይተማመኑ፣ ለችግሮቻቸው ቁልፍ ማግኘት እንዳይችሉ እና በአሉታዊ አስተሳሰብ የተሞሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል ራሳቸውን እንደ “ሰነፍ” አድርገው የሚቆጥሩ ታዳጊዎች እንቅስቃሴን ከማድረግ ተቆጥበዋል፣ ይህም ወደ እንቅስቃሴ አልባነት ዑደት እና የጤና እክል እየዳረጋቸው ነው።
ከአዲስ አበባ የተገኙትን እነዚህ ጥናታዊ ውጤቶች የሚያንፀባርቁት በተለይ ልጃገረዶች ብዙውን ጊዜ የኅብረተሰቡን የፆታ ሚናዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ብዙዎቹ ስፖርቶች “ለወንድ ልጆች” እንደሆኑ በማመን ከጨዋታ ይልቅ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ያስቀድማሉ። በጊዜ ሂደት ይህ አስተሳሰብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እድላቸውን እየገደበው ነው።
ከዚህ ምሳሌ መገንዘብ የምንችላው ባሕላዊ እሳቤዎች ሰዎች ጤናቸውን መጠበቅ የሚያስችሉ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እንደሚገድብ ነው። ይህ አሉታዊ አስተሳሰብ ወጣቶች ራሳቸውን በበጎ እንዳይመለከቱና በራስ መተማመናቸው እንዳያድግ ያደርጋል። ቀስ በቀስ አስተሳሰብን ጤናማ ከማድረግ ጀምሮ አካላዊ ቅልጥፍናን ለመጨመር እንዳንችል ያደርገናል።
አመለካከት ማረቅ እና የማህበረሰብ ድጋፍ ማሳደግ
በጅማ፣ ኢትዮጵያ በተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ብዙውን ጊዜ ልጃገረዶች ከቤት ውጭ እንዳይጫወቱ የሚከለክሉት በደህንነት ጉዳዮች ወይም በባህላዊ ደንቦች ነው። በጥናቱ ተሳታፊ የሆነች አንዲት እናት እንዲህ ስትል ትገልጻለች “ልጄ ወደ ጨዋታ ሜዳ ከሄደች ትንኮሳ ስለሚደርስባት እጨነቃለሁ። ቤቷ ብትቆይ ይሻላል››። በውጤቱም ልጃገረዶች በቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ ወንዶች ደግሞ በእግር ኳስ እና በሌሎች የቡድን ስፖርቶች ይደሰታሉ።
እነዚህ አመለካከቶች ከባድ መለያየትን ይፈጥራሉ። እንደ ጥናታዊ ጽሑፉ ማስረጃ የጅማ ወንዶች ልጆች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ደረጃ ከፍ ያለ መሆኑን ሲገልፅ፤ ልጃገረዶች ግን እንደ ደህንነታቸው የተጠበቀበት ቦታ እጦት እና የቤተሰብ አለመስማማት ያሉ መሰናክሎች ይገጥሟቸዋል። ይህ እሳቤ አሉታዊ የሆነ አስተሳሰብን ከማበረታታት አልፎ የጤና እክል እያመጣ ይገኛል።
ሌላኛው ምሳሌ፤ ችግርን የመቋቋም ችሎታ የተመለከተ ነው። ወጣቶች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግርና የትምህርት ጫና እያጋጠማቸው ለወደፊት ሕይወታቸው ብሩህ አስተሳሰብና ተስፋ የሚያደርጉ ከሆነ በተመሳሳይ ለጤንነታቸው ቅድሚያ የመስጠት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል። ለዚህ ምሳሌ በአርባ ምንጭ ከተማ የተደረገ አንድ ጥናት እንመልከት። በከተማዋ “አዎንታዊ አመለካከት” ያላቸው ታዳጊዎች ከትምህርት ሰዓት በኋላ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይታያሉ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት ይመገባሉ፤ በአስቸጋሪ ጊዜያት ወቅት ማህበራዊ ድጋፍ የማግኘት እድላቸውም ሰፊ ነው።
በተቃራኒው ተስፋ የቆረጡ ወይም የተጨናነቁ ታዳጊዎች ብዙ ጊዜ ተቀምጠው ይታያሉ። በተደጋጋሚ በአንድ ቦታ ላይ የመቀመጥ ልማዶችን የመከተል፣ ምግብን የመዝለል ወይም ራስን የመንከባከብ ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል። ጥናቱ በጊዜ ሂደት ይህ ልማዳቸው በሽታ የመከላከል አቅማቸውን እንደሚያዳክምና ለህመም ተጋላጭነታቸውን እንደሚጨምር ያመላክታል። ስሜታዊ ደህንነት እና አካላዊ ጤንነት እርስ በርስ የተቆራኙ ናቸው። ህመምን የመቋቋም ችሎታን ማዳበር የጭንቀት እና የጤና መጓደል ዑደትን ይሰብራል።
የኢትዮጵያ የ2018 ሪፖርት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ክፍተቶችን አጉልቶ ያሳያል። 32 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ብቻ የስፖርት መገልገያዎች አሏቸው። ስምንት በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መኖሪያዎች ለእንቅስቃሴ እና ለጨዋታ ምቹ ናቸው። ፓርኮች፣ የእግረኛ መንገዶች ወይም የትምህርት ቤት ፕሮግራሞች፣ ወጣቶች ንቁ ሆነው ለመቆየት እንዳይችሉ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
በርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርኮች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ የሳይክል መንገድና፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በስፋት እየተገነቡ ይገኛሉ፤ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። መንግሥት በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ መዋዕለ ንዋይ ሲያፈስ የመጫወቻ ሜዳዎችን መገንባት ወይም ተወዳጅ ነፋሻማ መጓጓዣን ማስተዋወቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ የስፖርት ሜዳዎች ያላቸው ትምህርት ቤቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቦታን ብቻ ሳይሆን የቡድን ሥራ እና የሥነ ምግባር ባሕልን ያዳብራሉ።
የመፍትሔ ሃሳቦች
ጤናማ አስተሳሰብ መገንባት ከምንም በላይ አካላዊ ጤንነትን ለመጠበቅ ይረዳል። በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ለወጣቶች ትምህርት እና ግንዛቤ መስጠት አስፈላጊ ነው። ትምህርት ቤቶች “አዎንታዊ አስተሳሰብ መገንባትን” በተመለከተ ከሥርዓተ ትምህርት ጋር በማዋሃድ የተማሪዎችን አስተሳሰቦች ጤናን እንዴት እንደሚጠብቁ ማስተማር ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ወጣቶች በትምህርትና በሌሎች ማህበራዊ ጫናዎች ውስጥ ሲቆዩ ያንን መቋቋም የሚያስችል የአመለካከት ለውጥ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
ማጠቃለያ
በአስተሳሰብ እና በአካላዊ ጤንነት መካከል ያለው ጥብቅ ትስስር የማይካድ ነው። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጎጂ ልማዳዊ ደንቦችን፣ ውስን ሀብቶች እና ውጥረት የተሞላበት የኑሮ ዘይቤን እና ልዩ ልዩ መሰናክሎችን ለማሸነፍ የግለሰብም ሆነ የጋራ ርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል። ቀዳሚው ርምጃ ግን አዎንታዊ አስተሳሰብን መገንባት ነው። አዎንታዊ በሆኑ እሳቤዎች የተሞላ አዕምሮ በራስ መተማመንን በመገንባት፣ ስለ ራስ በጎ ግንዛቤን በማጎልበት፣ ገዳቢ እምነቶችን በመገዳደር ቁልፍ ድርሻ ይጫወታል። አካላዊ ጤንነትንም ያረጋግጣል። በመሆኑም ይህንን መርህ በመከተል በአዎንታዊ እሳቤ የተሞላና አካላዊ ቅልጥፍና ያለው ትውልድ መፍጠር ይቻላል። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም