
“መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ዜጋ ፓስፖርት ሊያገኝ ይገባል”– ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፦ መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ዜጋ ፓስፖርት በቀላሉ ሊያገኝ እንደሚገባ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዲስ በሀገር ውስጥ የተመረተ ኢ-ፓስፖርት ይፋ አድርጓል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ዜጋ ፓስፖርት በቀላሉ ማግኘት አለበት።
የኢ-ፓስፖርት ጥቅም ላይ መዋል መጀመሩ ሀገራችንን ከፍ የሚያደርግና ደኅንነታችንን የሚያልቅ መሆኑን ተናግረው፤ ኢ-ፓስፖርት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን በማዘመን ተጠያቂነትን እና ግልፅነትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ አንድምታ ይኖረዋል ብለዋል።
በዘመናዊ እና ዲጂታላይዝድ ዓለም ውስጥ በቴክኖሎጂ ራስን በመቻል የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከዚህ በኋላ መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውንም ዜጋ አገልግሎት በተቀላጠፈ መንገድ ማግኘት እንዳለበት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች እና የጉዞ ሰነዶች ዘመኑን የዋጁ እና የተራቀቁ የደኅንነት ባሕሪያት እንዲኖራቸው መደረጉ ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልፀው፤ የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ተግባራዊ መደረጉ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር ለዜጎች የተሰጠውን ክብር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት የአገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ አዲሱ ኢ-ፓስፖርት እስከአሁን ኢትዮጵያ ካላት ፓስፖርት በዓይነቱና በደረጃው እጅግ ከፍ ባለ ጥራት የተዘጋጀ የጉዞ ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል።
የአንድን ግለሰብ ባዮሜትሪክ መረጃ ጨምሮ የጣት ዐሻራዎችን፣ የፊት ለይቶ ማወቂያ እና የኤሌክትሮኒክስ ቺፕስ እንዲያካትት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ሪፎርም ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የጉዞ ሰነዶችን ዘመናዊ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል፤ ይፋ የተደረገው ኢ-ፓስፖርት ሀገሪቱ ዲጂታል ኢትዮጵያን ከመፍጠር አኳያ እየሠራች ያለችውን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህንን ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መምራት መቻል ትልቅ ድል እንደሆነ ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ለፓስፖርት ኅትመት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የፓስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ የቆየው 20 ዓመት ባለፈው ቴክኖሎጂ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በዚህ አሠራር የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም፤ አዲሱ ቴክኖሎጂ ግን ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ፓስፖርታቸውን በፍጥነት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል።
በቅርቡ በመላው ሀገሪቱ 14 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዝግጅት ተደርጓል፤ በዚህም ሰዎች ከአካባቢያቸው ሳይርቁ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አብራርተዋል።
አዲሱ ኢ-ፓስፖርትም ከዚህ በፊት የሚያጋጥሙ የደኅንነት ችግሮችን ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ መሆኑን አስረድተዋል።
ነባሩ ፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜው እስኪያበቃ ጥቅም ላይ መዋሉን እንደሚቀጥል አንስተው፤ የዕድሳት ጊዜው ሲደርስ በኢ-ፓስፖርት እንደሚተካ ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም