
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የበርካታ የማዕድን ሀብቶች ባለቤት ነው፡፡ ከእነዚህ የማዕድን ሀብቶቹ መካከል ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉት ማዕድናት ይጠቀሳሉ፡፡ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉትን እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ሲልካሳንድ፣ ላይምስቶን፣ ካኦሊን የመሳሰሉትን ለማልማት የሚያስችል ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ክልሉ በአዲስ መልኩ ተዋቅሮ ከተመሠረተ ገና ሁለት ዓመታት ያልሞላው ቢሆንም፣ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሥራ በመግባት በክልሉ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች በቅድሚያ በመለየት ልማት ላይ እንዲውሉ የማድረጉን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይ የክልሉን የማዕድን ሀብቶች በመለየት ለኢንቨስትመንት ክፍት እንዲሆኑና በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ከክልሉ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን መኔዶ እንደሚሉት፤ ክልሉ ከተመሠረተ አንድ ዓመት ከስምንት ወራት አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜም አንስቶ የማዕድን ዘርፉን የሚመራ የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ በማቋቋም በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡
ክልሉ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ያለው በክልሉ ያሉ ማዕድናትን በማጥናት ልየታ ማድረግ ላይ ነው። የማዕድን ልየታው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በጥናት እየተካሄደ ሲሆን፣ አዋጭነቱም እየተረጋገጠ ይሠራል።
ሥራው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቹን ያካተተ ማሕቀፍ የያዘ መሆን ይኖርበታል፤ ከዚህ አኳያም ክልሉ ያለውን አቅም ለመለየት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው፡፡ ለዚህም ከማዕድን ሚኒስቴርና ዘርፉን ከሚመራው የክልሉ መዋቅር እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በክልሉ የሚገኙ ማዕድናት ልየታ ሥራው ይከናወናል፡፡
በቀድሞው ክልል ወቅት በክልል ደረጃ ብዙ ወጪ ወጥቶባቸው የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ አሁን ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥር በሚገኙ ማዕድናት ላይ ትኩረት በማድረግ የልየታ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቀድሞውን ጥናት እንደ ማስረጃ በመያዝ መኖራቸው በጥናት የተረጋገጠ ምን ዓይነት ማዕድናት አሉ በሚሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም የክልሉን ማዕድን ለማልማት በአዲሱ ክልል በጂኦሎጂስቶች የተደራጀ ከክልል ጀምሮ እስከታች ያሉ ባለሙያዎች በተሰባሰቡበት ቡድን አማካይነት በውስጥ አቅም መሥራት ያለበትን በመለየት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎ እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡
በዩኒቨርሲቲዎችና እንደ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በመሳሰሉት የጥናትና ምርምር ተቋማት ጥናቶች ተካሂደው እንደነበር አስታውሰው፤ ጥናቶቹንና መረጃዎቹን በማሰባሰብና በመናበብ የክልሉን የማዕድን ሀብቶች በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። አሁንም በዩኒቨርሲቲዎች ጥናቶች እየተደረጉ መሆናቸው ይገልጻሉ፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በክልሉ ስለመገኘታቸው በጥናት ከተረጋገጠው እንደ የድንጋይ ከሰል፣ ሲልካሳንድ፣ ላይም ስቶንና ካኦሊን የመሳሰሉት የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናት በተጨማሪም፣ ለግንባታ ግብዓትነት የሚውሉ የኮንስትራክሽን ማዕድናትም በስፋት እንደሚገኙ በጥናት ተረጋግጧል።
ክልሉ ለማዕከላዊ መንግሥት ያለው ቅርበት፣ ከመሬት አቀማመጥና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በብዙ መልኩ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉም ጠቅሰው፣ በመሆኑም ክልሉ እነዚህን ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶችን ለአዲስ አበባና ዙሪያ አካባቢዎች በዋነኛነት ይመግባል ብለዋል፡፡
ክልሉ ሰፊና እምቅ አቅሞች ያሉት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እነዚህን ሀብቶች በአንድ ጊዜ ለይቶ ለማወቅ አይቻልም ሲሉም ጠቅሰው፤ የልየታ ሥራው በየጊዜው እየተካሄደ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመትም የማዕድን ዘርፉን በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው ያስታወቁት፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በዘርፉ ለማከናወን ከታቀዱት ዘርፈ ብዙ ተግባሮች መካከል የመጀመሪያው ፍቃድ አሰጣጥን ይመለከታል፤ የማዕድን ዘርፉ የፍቃድ አሰጣጥ ሥራ ከሌሎች ዘርፎች የተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ ማድረግን ይፈልጋል፡፡
ማዕድን አላቂ ሀብት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ክልሉ ያለውን አቅምና ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በልዩ ሁኔታ መመራትንም እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ፡፡ የክልሉ የፍቃድ አስተዳደር ሥራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማዕድንን የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እና በማዕድን ሚኒስቴር ተገምግሞ እንደ ሀገር ለሌሎች ተሞክሮ ይሆናል ተብሎ የተወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በክልሉ የማዕድን ዘርፍ ልማት ለመሰማራት በርካታ ፍላጎት ስላለ ብቻ ፍቃድ አይሰጥም፡፡ ማዕድን የሕዝብና መንግሥት አላቂ ሀብት ስለሆነ ከተለመደው አሠራር በተለየ ሁኔታ መምራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት እስካልተዘረጋ ድረስ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ማዕድን ከጸጥታ እና ከኢኮኖሚ ጋር የሚያያዝ ከመሆኑ ባሻገር መልሶ የማይገኝና በአግባብ ሊመራ የሚገባውም ነው። ክልሉ በዚህ ላይ ጥሩ ሠርቷል፡፡
ለእዚህም ሲባል በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልግ ፍቃድ ጠያቂ አካል የሚለይበት ተቋማዊ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ በዘርፉ እንደ ሀገር የተቀመጡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግቦች አሉ፤ ለእዚህም ሲባል ሥራው በጥንቃቄ እንደሚከናወን ያስረዳሉ፡፡
ቀደም ሲል የተሰጡ ፍቃዶችም ኦዲት እንደሚደረጉ አቶ መኮንን ተናግረው፣ ፍቃዶች ኦዲት ይደረጋሉ ሲባል ፍቃድ ጠያቄው አካል ፍቃድ ስለወሰደ ብቻ ባለመብት ነው ማለት አይቻልም ይላሉ፡፡ ፍቃዱን የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት መሆኑን አመልክተው፣ በዚህ መሠረት እያከናወነ ያለው እንቅስቃሴና ኤጀንሲው እያደረገ ያለው ድጋፍ ምን ይመስላል የሚሉት ጉዳዮች ጭምር እንደሚገመገሙ አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ፍቃዶች በአረንጓዴ፣ በቢጫና በቀይ የሚገመግሙቡት አሰራር መቀመጡን ተናግረው፣ በቀይ የተገመገሙት ፍቃዶች በተቆጠሩ ነጥቦች በአግባቡ ተገምግመው የሚጠበቅባቸውን ካላሟሉ ፍቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል፡፡ በቢጫ የተቀመጡ ፍቃዶችን ደግሞ ከጉድለቶቻቸው በፍጥነት ታርመው ማስተካከል ያለባቸውን እንዲያስተካክሉ የማድረግ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚሠራም ያብራራሉ፡፡
ዘንድሮ በማዕድን ዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ፍቃድ መሰጠቱን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 14 የምርመራና የማምረት ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ 10 ፍቃዶችን መስጠት ተችሏል ብለዋል። በተመሳሳይ በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች ላይም 300 የማምረት ፍቃዶች ለመስጠት ታቅዶ፤ 356 ባለሀብቶች (ኢንቨስተሮች) ፍቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ማዕድን የማልማት ፍቃድ ወስደው ወደ ተግባር ባልገቡት ላይም ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ በተቋሙ ፍቃድ አስተዳደር አሠራር መሠረት ያልሠሩ አራት የምርመራና አንድ የማምረት ፍቃድ ውላቸው እንዲሰረዝና እንዲቆረጥ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ሁለት የማምረት ፍቃድ የወሰዱ አካላት በውሉ መሠረት ወደ ተግባር ባለመግባታቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፤ በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች በባሕላዊ መንገድ ማዕድን እንዲያለሙ ፍቃድ ከተሰጣቸው መካከል የፍቃድ ጊዜያቸውን የጨረሱ 117 ማህበራትም ውላቸው መቋረጡን አስታውቀዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ለኢንዱስትሪ እና ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት በማምረት በኩል ከፍተኛ ምርት እየተመረተ መሆኑንም አቶ መኮንን ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በዚህም በስድስት ወራት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ የኮንስትራክሽን ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ፤ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ ተመርቷል፡፡ 24ሺ167 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለማምረት ታቅዶ፤ ከእቅድ በላይ 30ሺ 813 ቶን ማምረት ተችሏል፡፡
በክልሉ በስድስት ወራት በማዕድን ዘርፉ ከተለያዩ ክፍያዎች (ከአዳዲስ ፍቃድና እድሳት፣ ከሮያሊቲ ክፍያ፣ ከመሬት ኪራይ፣ እና ሌሎች አገልግሎቶች) 41 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 60ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም አፈጻጸሙን ከእቅዱ በላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የማዕድን ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይታመናል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዘርፉ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለአራት ሺ 117 ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህም በአብዛኛው በባሕላዊና በአነስተኛ የማዕድን ፍቃድ ታቅፈው በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች የሚሠሩ መሆናቸው አመላክተዋል፡፡
ማዕድን በማምረት ሂደቱ መልሶ ማልማት የሚባል ፓኬጅ እንዳለም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ ይህ ፓኬጅ ማዕድን በማምረት ሂደት የተጎዱ ቦታዎችን መልሶ ማልማትና አካባቢው የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ላይም እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በስድስት ወራት ሦስት ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት መልሶ ለማልማት ታቅዶ፤ ሁለት ነጥብ ስድስት ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ መልሶ የማልማት ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በማዕድን ዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ጠቁመዋል፡፡ ከችግሮቹ መካከል ዋንኛው ስለዘርፉ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን አንዱ መሆኑን ተናግረው፣ በየደረጃው ያሉት የኅብረተሰብ ክፍሎችም፣ የመንግሥት አካላትም ሆኑ በዘርፉ የሚሠማሩ አካላት ለዚህ ዘርፍ ያላቸው ግንዛቤ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በዚህ የተነሳም ችግሮች በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያንቀሳቅሳሉ ተብለው ከተለዩ አምስት ዘርፎች አንዱ መሆኑን አስታውቀው፣ ከአሻጋሪነቱ አንጻር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን በዚህ ልክ ተረድቶና ተገንዝቦ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናብቦ መሥራት እንደ ቤት ሥራ ተወስዶ እየተሠራበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በዘርፉ ከተሰማሩ አምራቾች አንጻር እያጋጠመ ያለው ዋንኛው ተግዳሮት የገበያ እጥረት ነው፡፡ ለአብነትም በክልሉ ፊልድስፓር የተሰኘ ማዕድን የሚመረት ሲሆን፣ ከተረካቢዎች አንጻር የዋጋ መዋዠቅ እና ትክክለኛ ገበያ ማግኘት አለመቻል እንደሚስተዋል አምራቾቹ በተደጋጋሚ ያነሳሉ፡፡
ክልሉ ለእዚህም ገበያ የማፈላለግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡ ዘንድሮ በተዘጋጀው የማዕድን ኤክስፖ ላይ ማዕድናት የማስተዋወቅ፣ ገበያ የማፈላለገና የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራዎች መሥራታቸው አመልክተው፣ በክልሉ መንግሥት በኩልም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ክልሉ አዲስ ከመሆኑ፣ ማዕድናት የሚገኙባቸው ቦታዎች ካላቸው ርቀትና ለትራንስፖርት አመቺ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ቦታው ለመድረስ ያልተሟሉ ነገሮች እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ። ኤጀንሲው እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እንደ ሀገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተናበበ ለመሥራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘላቂነት ያለውና በቂ የአቅም ልየታ እንዲኖር የሚያደርጉ ተቋማት እንዲኖሩ የማድረጉ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ ይህም ባለፈው በተካሄደው ሀገራዊ መድረክ ላይ የጋራ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ትልቁ ትኩረታችን ያለንን የማዕድን ጸጋ አቅም መለየት ነው›› ብለዋል፡፡
የማዕድን አቅምን ለመለየት አስቻይ ሁኔታዎች የግድ ያስፈልጋሉ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአቅም ልየታ ላይ የሚሠሩ በቂ አጥኚ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ይጠቁማሉ፡፡ ግብዓቶችም ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በቀጣይም የክልሉን የማዕድን ሀብቶች (ጸጋዎችን) መለየት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ሲሉ አስታውቀው፣ ምክንያቱም በክልሉ የሚገኙ ማዕድናትን አቅም በአግባቡ ከተለየ ሌሎቹን ለመሥራት እምብዛም አያስቸግርም ይላሉ፡፡
በሀገር ደረጃውም እንዲሁ የማዕድን ጸጋን ከመለየት አኳያ ገና ብዙ ያልተነኩ ጉዳዮች እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ፡፡ ምን አለን የሚለውን በደንብ ማወቅና መለየት እንዲሁም በሰነድ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በክልላችን አለን የምንላቸውን የማዕድን ሀብቶች አስመልክቶ የተካሄዱ ጥናቶችን በተደራጀና በተሰነደ መልኩ እጃችን ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል ይላሉ፤ ‹‹በማዕድን ዘርፉ ሊሠሩና ሊያለሙ የሚችሉ የሀገር ውስጥና ውጭ ባለሀብቶችን መሳብ የምንችለው የማዕድን አቅማችንን ከፍ ስናደርግ እንዲሁም ጥናቱን ከመደርደሪያ አውርደን መጠቀም ስንጀምር ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የክልሉን የማዕድን አቅም በጥናት በማረጋገጥ እና በተዘረጋው የፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት ሀገራዊ አዋጭነታቸውና የተቀመጡ ሁኔታዎችን ሊያሳካ በሚችል መልኩ የማስተሳሰር ሥራዎች እንደሚሠሩም ይገልጻሉ፡፡ በዘርፉ ሊሠሩና ሊያለሙ የሚችሉ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ለመሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም