
ከሀገራችን የእሳተ ገሞራ ታሪክ ጋር አንድ አካል ሆኖ ይነሳል። የስምጥ ሸለቆ ከፈጠራቸው ታላላቅ ገጸ በረከቶች መሀልም ዋንኛው መሆኑ ይነገርለታል። ታላቁ የባቱ ደምበል ሀይቅ። ባቱና ዙሪያ ገባው ቆላማ በመሆኑ ሞቃታማ የአየር ንብረትን ተላብሷል። የሀይቁ ተፈጥሯዊ ስጦታ ግን ደረቃማውን አየር አዋዝቶ ለኑሮ ተስማሚና ለህይወት አመቺ ጸጋዎችን ሲለግስ መዋሉ የተለመደ ነው።
ከአዲስ አበባ 163 ካሬ ሜትር ርቀት ላይ እንገኛለን። ዘመናዊው የመንገድ ዝርጋታም እስከ ከተማዋ ጥግ በምቾት ለመድረስ አስችሎናል። የዓሳ ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የበርካታ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ባለቤት ወደ ሆነችው የባቱ ከተማ። ባቱ በ1953 ዓ.ም የተመሰረተች የሀይቅ ዳር ከተማ ናት።
ከተማዋ በአምስት ውብና ማራኪ ደሴቶች የተከበበች መሆኗ ተፈጥሮን አጣጥማ በወጉ ለመጠቀም አስችሏታል። የደሴቶቿ ውብ ተፈጥሮ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የጥምቀት በዓልና የጀልባ ላይ ትዕይንት በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏል። የስፍራው ላይ ተፈጥሯዊ ጸጋ በዚህ ብቻ አይቋጭም። አለፍ ሲል ደግሞ ለሀገር ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር ወደሆነው ታላቁ የኢንቨስትመንት መንደር አጓጉዞ ያደርሳል።
የከተማዋን እምብርት ይዞ ሰፊውን በረከት የሸፈነው ሰፊ የአበባ እርሻ ለአካባቢው ህብረተሰብ ፣ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆን ከጀመረ ድፍን ሀያ ዓመታትን ቆጥሯል። የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬዎች አምራችና ላኪዎች ማህበር 130 አባላት ያሉት ግዙፍ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው።
ይህ ማህበር በአበባና አትክልት፣በፍራፍሬና ቅንጥብ አበቦች እንዲሁም በእፀ ጣዕም ምርቶች ላይ ተሳትፎ ያላቸው ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን አቅፎ ይንቀሳቀሳል። በዚህ ሂደትም የኒዘርላንድ፣ህንድ፣እስራኤልና ኢኳዶር ባለሀብቶች ዋንኛ ተሳታፊዎች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ የዓለም ገበያውን በተቆጣጠረው የአበባ ምርት በአፍሪካ ሀገረ ኬንያ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች። ኬንያ በ3600 ሄክታር ላይ አበቦችን በማልማትና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ መሆን እንደቻለች ይነገርላታል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከኬንያ በመቀጠል የሁለተኛነት ደረጃን የምትይዘው ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 1440 ሄክታር መሬት በአበባ እርሻ ልማት ተሸፍኗል። ከዚህ የመሬት ይዞታ ውስጥ 500 ያህሉ ሄክታር የሚገኘው በባቱ መሬት ላይ ነው።
አሁን ላይ መገኛቸውን በከተማዋ አቅራቢያ ያደረጉ አምስት ግዙፍ የእርሻ ልማቶች በተለያዩ ስፍራዎች የሚያበቅሏቸውን የአበባ ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነትን አስፍተዋል። በየቀኑ፣ ዓመቱን ሙሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘው ለዓለም ገበያ የሚደርሱት የኢትዮጵያ አበቦች በየጊዜው ተፈላጊነታቸው በመጨመር ላይ ይገኛል። ለሀገር የውጭ ምንዛሪን በማስገባት ረገድ በሦስተኝነት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠር በኩልም ከ200 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ አስችሏታል።
ከአበባ ምርቶች መሀል ‹‹ሮዝ›› የተሰኘው የአበባ ዝርያ ተፈላጊና ተመራጭ መሆኑ በዓለማችን እጅግ ተወዳጅነትን አትርፏል። ‹‹የሮዝ መገኛ ምድር ›› በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያም በዚህ የአበባ ምርት በዓለም የሦስተኝነት ደረጃን ትይዛለች።
ሀገራችን ከኮሎምቢያና ኢኳዶር ቀጥሎ ሮዝን በበቂ ዝግጅት አምርታ ለዓለም ገበያ ማቅረቧ ታዋቂነትን አትርፎላታል። በዋንኛነት የሮዝ አበባ ምርት መገኛ የሆነችው ባቱም ለዚህ ውጤትና ታላቅ እውቅና የራሷን ድርሻ ማበርከቷ ተመዝግቦላታል።
በሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ የሮዝስ ፒለሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ሰለሞን እንደሚሉት፤ በሀገራችን የአበባ ምርት ኢንቨስትመንት ዕድሜ ከሁለት አስርት ዓመታት አይበልጥም። የዛሬ ሃያ ዓመት የምርት ሂደቱ ሲጀመር ማንም በዚህ ኢንቨስትመንት ዙሪያ በቂ ዕውቀት አልነበረውም። ዛሬ ላይ ግን በአምራች እጆች ብርታት የአውሮፓን ገበያ የሚቆጣጠር ታላቅ ለውጥን ማረጋገጥ ተችሏል።
የዝዋይ የአበባ እርሻ ልማት በሃያ ሺ ቋሚ ሠራተኞች የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ኩባንያ ነው። ከነዚህ ሠራተኞችም 80 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው። እንደ አቶ ኤርሚያስ ዕምነት ኢንቨስትመንቱ በሴቶች አብላጫነት መሸፈኑ ምርታማነቱ በጥራትና በብቃት ልቆ ፤ ተወዳዳሪነት እንዲፈጠር አግዟል። ሴቶች ኃላፊነትን በመወጣትና በልዩ አትኩሮት በመሥራት ጠንቃቆች መሆናቸውም በሥራው ተመራጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
እነሆ! በአበቦቹ እርሻ መሀል ተገኝተናል። የቡድን ስብሰባችን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር(ኢትመባሴማ) እና ከኢትዮጵያ ሆልቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ጋር ተቀናጅቷል። ዙሪያ ገባችን በደማቅና ውብ አበቦች ሽታ ታጅቧል። ሊነኳቸው ቀርቶ ሊመለከቷቸው የሚያጓጉ የተፈጥሮ አበቦች በጠንካራ እጆች መሀል እየተዋቡ ነው። በስፍራው ሰፊውን ቦታ የሚሸፍኑት ብርቱ ሴቶች የድርሻቸውን ለመወጣት ዕረፍት ይሉትን አያውቁም። የአበቦቹ መንደር በቀለማት ድምቀትና በልዩ መዓዛ ተገልጧል። ጉልበትን የሚያግዙ ማሽኖች ለአፍታ ሥራ አይፈቱም። ዘወትር በሥራ ከሰሉ እጆች ተዛምደው በፍጥነት ይቆርጣሉ፣ ያሽጋሉ። በዚህ ቦታ አንድ አይነት የሚባል አየር አይታሰብም። በየአፍታው ከፍተኛ ሙቀትና ከባድ ቅዝቃዜ ማስተናገድን ግድ ይላል። ይህ ሂደት ለአበቦቹ መኖር እስትንፋስ የሚሰጥ፣ ሕይወትን በወጉ የሚቀጥል ስጦታ ነው።
አሁን 42 ሄክታር በሚሸፍነው የሮዝስ አበባ እርሻ ልማት ውስጥ ነን። በዚህ ስፍራ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው 54 አይነት አበቦች ይገኛሉ። በቦታው ከአንድ ሺ አራት መቶ በላይ ሠራተኞች በየቀኑ የአበቦቹን ዕድገት ለማስቀጠል በጥንቃቄ እየሠሩ ነው። እያንዳንዳቸው በአካባቢው የአየር ንብረት ልክ ተስማሚነት እንዲኖራቸው በቴክኖሎጂ አቅም እንዲታገዙ ተደርጓል።
በስፍራው ያሉ አበቦች እድገታቸውን ጨርሰው ለሽያጭ ከመብቃታቸው በፊት ናሙናቸው ተቆርጦ ወደ አውሮፓ ገበያ ይላካል። ደንበኞች ይዘቱን አይተው ሲስማሙና ይሁንታቸውን ሲሰጡ ለንግድ ሂደቱ በሚያመች መልኩ ዝግጅቱ ይጠናቀቃል። እንደ አቶ ኤርሚያስ አገላለጽ አንድ አበባ በመደብ ከተተከለ በኋላ በቀን ለሦስት ጊዜ ይሰበሰባል።
በአንድ መደብ እስከ አምስት መቶ የሚደርሱ አበቦች ይተከላሉ። የመጀመሪያዋ አበባ ብቅ ስትልም አነስተኛ ችግኝ ሆና ትወጣለች። በግራና በቀኝ በጠብታ መስኖ በቂ ውሃ የሚያገኙት አበቦች ሁሌም ዕድገታቸው የተጠበቀ ነው። ከመሀል የሚደባለቅላቸው ለም ማዳበሪያ በኮምፒውተር እየታገዘ ለእያንዳንዳቸው ምግባቸውን በጠብታ ያደርሳል።
አበቦች ተተክለው በአርባ አምስተኛው ቀን ላይ በማሽን የታገዘ እንክብካቤን ያገኛሉ። ከሃምሳ ቀን በኋላም በሙሉነት የሚጠበቁት የመጀመሪያዎቹ አበቦች በውብ ገጽታ ለእይታ ይደርሳሉ። በዚህ ሥፍራ በየቀኑ ባለቀለማት አበቦች ይመረታሉ፣ በጥንቃቄ እየተቆረጡም ወደ ማቆያቸው ይገባሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የአበባ ባህርይ እንደ ሌሎች ምርት አይደለም። በየቀኑ ይመረታል፣በየቀኑ ወደገበያ ይላካል። የአበባ ምርት በማቀዝቀዣ ውስጥ ከአስራ አምስት ቀናት በላይ ሊቆይ አይገባውም። እንዲህ ከሆነ ተፈላጊነቱ ይቀንሳል። በተቃራኒውም ቀድሞ ከተላከ ለእይታ እንዳይሰለች ስለሚያሰጋ የቀናት ምጣኔው የተስተካከለ እንዲሆን ታስቦበታል።
የአበቦች የሽያጭ ሂደት በአብዛኛው በደንበኞች ፍላጎት ላይ የሚመዘን ነው። እንደወቅቱ መፈራረቅና እንደየፍላጎት መጠን አቅርቦቱ ይለያያል። ደንበኞች በሚፈልጉት ደረጃ ያሻቸውን የማቅረብ ኃላፊነት ደግሞ የገበያው ግዴታ ነው። በአንድ አጋጣሚ የተላከውን አበባ ለመቀበል ፍላጎት ባይኖራቸው በፍጥነት የመቀየር ኃላፊነትን መውሰድ ያስፈልጋል።
አንዳንዴ የአበባ ማሳን ሙሉ ለሙሉ በመንቀል በሌላ የመተካት አሠራር ሊኖር ይችላል። ይህ አይነቱ መንገድ ኪሳራ ማስከተሉ ባይቀርም ዋንኛ ዓላማው የደንበኞችን ፍላጎት በመሙላት የዓለምን ገበያ መቆጣጠር ነው። ይህ ሂደትም ከግብርናና የገቢዎች ሚኒስቴር እውቅና ውጪ እንደማይሆን ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ።
የአበቦችን የአቆራረጥ ዘዴ በመቀያየር የሽያጭ ገበያውን ማራኪ ማድረግ ይቻላል። እስካሁን ባለው ተሞክሮም የሮዝ አበባ ምርት በዓለም ገበያው ሂደት ነጥፎና ተቀዛቅዞ አያውቅም። ሁሌም ከወቅቶች መፈራረቅና ከግል እይታዎች ጋር ተዛምዶ ተፈላጊነቱን እንዳደመቀው ቀጥሏል። ለዚህ ስኬታማነትም የአበባውን እርሻ በስፋት የያዙት ብርቱ ሴቶች አስተዋጽኦ የላቀ ነው።
በእርሻው ላይ ሕይወታቸውን የሚቀጥሉት አበቦች ሁሌም ጤንነታቸው በባለሙያዎች ይረጋገጣል። ለዚህ ዕውንነትም በየጊዜው ደህንነታቸውን የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ክትትል ያደርጋሉ። በመስክ ጉብኝት ጊዜ በአበቦቹ ላይ ልዩ ምልክት ቢታይና በነፍሳት ቢጠቁ እያንዳንዱ ደረጃ በጥናት ተለይቶ ሪፖርት ይደረጋል። የአበቦቹን ይዞታ የሚገልጸው የምልክት መጠቆሚያም ወደ ቀጣዩ የመፍትሔ ርምጃ ፈጥኖ የሚያደርስ ይሆናል።
በመስክ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች የመጀመሪያው መፍትሔ ተፈጥሮን በተፈጥሮ ማከም ነው። በአብዛኛው ጎጂዎቹን ነፍሳቶች ሌሎች ነፍሳቶች እንዲመገቧቸው በማድረግ አበቦቹን መታደግ ተለምዷል። ከእርሻው ማሳ የሚወገዱና አረንጓዴ ይዘት ያላቸው የተፈጥሮ ውጤቶች ተመልሰው በማዳበሪያነት ጥቅም ላይ ይውላሉ። ወደ ባዮ ጋዝ ተቀይረውም ግልጋሎትን ይሰጣሉ። በሥራ ላይ የቆየው ውሃም ዳግም ተመልሶ መሬቱን የሚያርስበት ሂደት የተመቻቸ ነው።
ከዚህ አለፍ ሲል ግን የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው የደረጃ መስፈርት መሠረት አነስተኛ የሚባሉ ኬሚካሎችን ለአበቦቹ መጠቀም ግድ ይሆናል። ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት፤ የኬሚካል ርጭቱ ከሥራ ሰአት ውጪ፣ ከሰዎች ንክኪ በራቀ መልኩ የሚካሄድ ነው።
እንደ አቶ ኤርሚያስ አገላለጽ፤ በአበባ ምርት ሂደት ከኬሚካልና ማዳበሪያ አጠቃቀም ጋር በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱ ይደመጣል። መሬቱ ዳግም እንደማያበቅል በእርግጠኝነት የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ይህ እውነታ ግን ሁሌም ከአባባል የዘለለ አይሆንም። ኬሚካልና ማዳበሪያ ማለት እጅግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁና በቀላሉ የሚሞከሩ ግብአቶች አይደሉም።
ለምሳሌ ማዳበሪያን ለመጠቀም እያንዳንዷ አበባ በስሌት የተቀመጠላትን ግብአት ብቻ መውሰድ ይኖርባታል። የአፈሩ መብዛትና ማነስም በዓመት ሁለት ጊዜ ሊመረመር ግድ ይለዋል። ኬሚካልም ቢሆን መጠኑ በጥንቃቄ ተጠንቶ ለተገቢው ጥቅም የሚውል እንጂ ያለአግባብ እንደ ወንዝ የሚፈስ አይደለም።
ማንኛውም ባለሀብት ደግሞ ገንዘቡን በአግባቡ ሊጠቀምበት እንጂ ለተባለው አይነት ዓላማ ሊያውለው አይሻም። በአቶ ኤርሚያስ ዕምነት ከምንም በላይ በሀገርና ወገን ላይ ይህን ጥፋት ላለማድረግ ኢትዮጵያዊነት ይሉት እውነት ሰቅዞ የሚይዝ ሀቅ ይሆናል።
ከአበባ እርሻና ኬሚካል ጋር ተያይዞ በሰው ልጆች ጤና ጉዳት ያደርሳል የሚባለው አሉባልታም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላይ አጥልቶበት ቆይቷል። እስከ ዛሬም ይህ ሥራ ዘር እንዳይቀጥል፣ትውልድ እንዳይለመልም ያደርጋል በሚል የተጽዕኖ መስመር መቀጠሉን ያስታውሳሉ።
አቶ ኤርሚያስ ግን ለዚህ አባባል ትክክል ያለመሆን ዋቢ የሚያደርጉት በእርሻ ልማታቸው ላይ ያለውን የወሊድ መጠን በማሳየት ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ በነበረው ሪፖርት በግቢው 55 ያህል ሴቶች መውለዳቸውን ያረጋግጣሉ።
በብራም ፍላውርስ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊው አቶ ዱሬሳ ኤልያስ በሁለተኛው የጉብኝት መስክ ላይ ያገኘናቸው ባለሙያ ናቸው። አቶ ዱሬሳ በብራም ፍላወርስ ኩባንያም ተመሳሳይ ሂደት እንደሚከወን ይናገራሉ። በአበባ ምርት ሂደት ኩባንያው የአውሮፓን ገበያ ፍላጎት ለመሙላት የራሱን ዘዴ ይጠቀማል። አበቦች ተቆርጠው ከመጡ በኋላ በማራኪ ቁመና ተዘጋጅተው እንዲላኩ የስፍራው ላይ ሴቶች የእጅ ጥበባቸውን ይጠቀማሉ።
አበቦቹ በሚፈለገው ደረጃ የገበያውን ፍላጎት እንዲይዙ ለማድረግም በካምፓኒው አርማና ሥም በማስዋብ በተዘጋጁ መጠቅለያዎች አሳምረው ዝግጁ ያደርጓቸዋል። የዓለምን ገበያ ከመቀላቀላቸው አስቀድሞም አስፈላጊውን የጥራት ቁጥጥርና የኮድ መለያን ማሟላት ግድ ይሆናል።
እንደ አቶ ዱሬሳ ማብራሪያ፤ ከምርቶቹ መሀል አንዱ እንኳን የጥራት ችግር ቢኖርበት ደንበኞች ለማስረጃ ፎቶ አንስተው ሊልኩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። ይህ አጋጣሚ ቢከሰት ደግሞ ማን እንደሰራችው፣ የትኛዋ አረጋግጣ እንዳሳለፈችው የሚጠቁም የኋላ ማስረጃ መገኘቱ አይቀሬ ይሆናል።
ይህ መሆኑ ለሀገርና ለወገን ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ በአትኩሮትና በጥንቃቄ መሥራቱ የተለመደ ኃላፊነት ነው። በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የማይሸሽጉት ኃላፊዎች፤ እስካሁን ግን በጥራት ጉድለት ሳቢያ የተመለሰ ምርት ያለመኖሩን የሚናገሩት በእርግጠኝነት ነው። በተለይ ግን አሁን ላይ በአንዳች ስህተት ወደ አውሮፓ እንዳይገባ ጥንቃቄ የሚደረግበት አንድ አደገኛ የነፍሳት አይነት የተለየ ትኩረት ሆኗል።
ይህ አደገኛ ነፍሳት ለአበባ ገበያው ዕንቅፋት እንዳይሆን በየቀኑ የቁጥጥር ሥራው ይካሄዳል። በእርሻ ልማቱም በተለየ ዕውቀት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ነፍሳቱ አልፎ እንዳይወጣ በጥንቃቄ እየሠሩ ይገኛሉ።
መገኛቸውን ባቱ ላይ ያደረጉት አምስት የአበባ እርሻዎች ዛሬ ላይ የአውሮፓን ገበያ እያወዱት ነው። የሀገር ኢኮኖሚውን በመገንባትና የውጭ ምንዛሪን በማስፋትም ድርሻቸው ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ በአበባ ሽያጭ ከአውሮፓ አልፋ የዓለምን ገበያ እንድትቆጣጠር የየዕለቱ ብርታትና ጥንካሬ ለወደፊቱ ውጤት ጠንካራ ማሳያ በመሆን ሊመዘገብ ይገባል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም