ባህላዊ የሀብት ማብሰሪያ ሥርዓት በወላይታ

የሰው ልጅ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፍላጎቱን ለማሟላት በግልና በጋራ ከሚያከናውናቸው ድርጊቶች መካከል ባህላዊ ክንዋኔዎች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ክንዋኔዎች የማንነቱ መገለጫዎች፣ የፈጠራ ጥበቡና የክብሩ መታወቂያዎች ሆነውም ኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን የሚገልጹባቸው ባህላዊ ሥርዓቶች ባለቤቶች ናቸው፤ በዚህም ሲዳኙ፣ በጋራ ሲሠሩ፣ ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ፣ ማህበረሰቡን ሲያስተዳድሩ፣ ጠላቶቻቸውን ሲከላከሉ፣ ወዳጅነትና ዝምድናቸውን ፣ ወዘተ ኖረዋል፤ እየኖሩም ናቸው፡፡

ለዚህም በወላይታ ብሔር በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የሚከናወኑ የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከብሔረሰቡ ባህላዊ ስርአቶች መካከል ‹‹ዳላ፣ ሊቃ እና ግሟ›› Daala, liiqaanne gimuwaa/ የሚለው ባህላዊ የሀብት ማብሠሪያ ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡

1.ዳላ (Daalaa)

የዳላ (daala) ሥርዓት የሚፈጸመው አንድ አርሶ አደር ለፍቶ፣ ጥሮ ግሮ ያከማቸውን ሀብቱንና ንብረቱን በአግባቡ ጠብቆ እንደዛውም ከብቶቹን በየሰው ቤትና በራሱ ቤት በማስጠበቅ ቁጥራቸው አንድ መቶ ሲሞላ የሚፈፀም ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ በወላይታ ብሔረሰብ የቆየ ባህል መሰረት የከብት ርቢ ከሀብት መገለጫዎች ዋነኛው ሲሆን፣ በዚህ ሀብታም መሆኑን /ብልፅግናውን/ የሚያበስርበት ሥርዓት ዳላ (Daala) በመባል ይታወቃል።

በሀብት ማብሰር ሥርዓት ሂደቱ የባለሀብቱ ከብቶች ቆጠራ ይከናወናል፡፡ የሥርዓቱ ስያሜም ከከብቶቹ መካከል በተመረጠው በሬ ላይ ከሚታሰር ቃጭል (daala) ጋር ይያያዛል፡፡ የዳላ ሥርዓት መፈጸም የአርሶ አደሩ የከብቶች ቁጥር መቶ መድረሱን ማረጋገጫ ነው፡፡

የከብቶቹ ቁጥር አንድ መቶ መድረሱን ከተረጋገጠ በኋላ ለሥርዓቱ አፈጻጸም አስፈላጊው ዝግጅት ይደረጋል። የዝግጅቱ የመጀመሪያ ተግባር ለወዳጅ ዘመዶች፣ ለመንደርተኞች እና ለሥርዓቱ ታዳሚዎች ቀጠሮውን ማሳወቅ ሲሆን፣ የዳላ ሥርዓት የሚፈጸመው ቅዳሜ ዕለት ይሆናል፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዕለቱ ገዳም ቀን ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡

ለሥርዓቱ ክዋኔ አንድ ሳምንት ሲቀረው ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ ቆጠራ የሚካሄድበትን ሥፍራ ያዘጋጃል፤ ሥፍራው በግለሰቡ ቀዬ አካባቢ ሰፋ ተደርጎ ዙሪያ ክብ በጸዳቂ እንጨት ይታጠራል፡፡ በመሀሉ ምሶሶ አይነት ቋሚ ጫፉ ሳይቆረጥ እንዲቆም ይደረጋል፤ አዘገጃጀቱም ለቆጠራ የሚሰበሰቡት የከብቶችን ቁጥር ባገናዘበ መልኩ እንጨት የሚቆምበትን ሥፍራ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡

በግቢው መግቢያ ላይ ባሀብቱና ቆጣሪው ረዳት ቆጣሪዎች ይቆማሉ፡፡ ለድግሱ ዝግጅት በባህሉ መሰረት ከሚሰናዱ ምግቦችና መጠጦች መካከል ዋና ዋናዎቹ ሙቿ (muchchuwaa), ፖሻሙዋና (Pooshamu­waa)፣ ሎጎሙዋ(loggomuwaa) እና ቦርዴ (bordiyaa) መጠጦች ይጠቀሳሉ፡፡

ሥርዓቱ ከሚካሄድበት ዕለት አንድ ቀን ቀደም ተብሎ ለእንግዶች ማረፊያ ይዘጋጃል፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ዋዜማ ዳላውን (ቃጭሉን) ያዘጋጀው ባለሙያ ከነቃጭሉ እና ከብት ቆጣሪው ባለሀብት ቤቱ (Gabarachchaw) እየበሉና እየጠጡ ባለሀብቱን እያሞገሱ ያድራሉ፡፡

በዳላ ሥርዓት ጅማሮ የባለሀብቱ ባለቤት / ከእልፍኝ/ ከሳሎን ሚስትዬው ከጓዳ በእምብርክክ እንደ ከብት ወደ ቆጣሪው (Gabarachchaw) ዘንድ በመቅረብ የተዘጋጀላቸውን ትኩስ ወተት “yeesuwaa” አብረው ይጎነጫሉ (Daggoosona)::

በመቀጠል መሰል የዳላ ሥርዓት ለመፈፀም ዕቅድ ያለው ባለሀብት በዕለቱ ሥርአቱን ከሚፈፀመው ባለሀብት ጋር አብሮ የ“daggetta” ሥርዓት ያከናውናል፡፡ በመቀጠል በጋባራቻ “Gabarachchaw” ወይም ከቀንድ በተሠራ ማንኪያ (mooqiyaa) የቀረበላቸውን ምግብ በባለሀብቱና ባለቤቱ ጀምሮ ታዳሚዎችን ያጎርሳቸዋል፡፡

በመቀጠል ቆጣሪው “Gabarachchaw”፣ ባለሀብቱ እና ታዳሚዎች የተጋበዙ ዘመድ አዝማድን ወደ ተዘጋጀው የቆጠራ ቦታ ይመራሉ፡፡ የቆጠራውን ሂደት የሚከታተሉ ታዳሚዎች የአጥሩን ዙሪያ ከብበው የሚቆሙ ሲሆን፣ ቆጣሪው /Gabarachchaw/ እና ባለሀብቱ ቆጠራው በሚካሄድበት ስፍራ መግቢያ ላይ በተዘጋጀላቸው ስፍራ በመቆም ቆጠራውን ያከናውናሉ፡፡

በዳላ ሥርዓት ከብቶችን ለመቁጠር የሚጠራው ቆጣሪ “Gabarachcha” ለራሱ ከአራት ዓመት በፊት ይህንን ሥርዓት የፈጸመ መሆን እንዳለበት ባህሉ ያዝዛል። አለበለዚያ የተቆጠሩ የግለሰቡ ከብቶች አይበረክቱም ተብሎ ይታመናል፡፡

ዋናው ቆጣሪ እሱን በቆጠራ ከሚያግዙት ከሌሎች ስድስት ሰዎች ጋር በአጥሩ መግቢያ በር አጠገብ በመቆም ቆጠራውን የሚካሂድ ሲሆን፣ ቆጠራውን ሲጀምር በቅድሚያ ወደ አጥር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት በባለሀብቱ ቤት የሚገኙ ከብቶች ናቸው፤ ቀጥሎ ከውጭ የመጡት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ቆጠሪው /Gabarach­cha/ ከብቶቹ ወደ አጥሩ ውስጥ ሲገቡ በያዘው ለስለስ ባለ የቀርከሃ ቅርንጫፍ ጀርባቸውን እየነካ ይቆጥራቸዋል፤ በቆጠራው ከሚረዱት ቆጣሪዎች ጋር በመሆን ቆጠራውን ካጠናቀቀ በኋላ ባለሀብቱን ክፉ አይንካችሁ፣ በሽታ አይንካችሁ፣ ሞት አይግባባችሁ የሚል መልእክት በሚያስተላልፍ መልኩ ይመርቃል፡፡

ይህ የቆጠራ ሥርዓት ሲጠናቀቅ ባለሀብቱ ለቆጣሪው እና ቃጭሉን ላዘጋጀው የእጅ ባለሙያ የመደባቸውን ከብቶች በስጦታ መልክ ያበረክታል፡፡

በመቀጠል የሁሉቃ (hulluqaa) ሥርዓት ይከናወናል። በሥርዓቱ ከአጥሩ (ከበረቱ) አካባቢ በሁለት ሜትር ጥልቀት ተቆፍረው ውስጥ ለውስጥ በተገናኙ ጉድጓዶች ውስጥ ባለሀብቱ ለሥርዓቱ ማስፈፀሚያ የተዘጋጀውን አንድ ጋን ቦርዴ፣ ወተት፣ የተነጠረ ቅቤ፣ ማር አንድ ላይ በመጀመሪያው ጉድጓድ ውስጥ በመጨመር ወደ ሁለተኛው ጉድጓድ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም በጉድጓድ ውስጥ አንድ በሬ እና በግ ባለሀብቱ በጦር የሚባርክ ሲሆን፣ የእንስሳቱ ደም ቀድሞ ከነበረው ፈሳሽ ጋር እንዲቀላቀል ይደረጋል፡፡ በጉድጓድ ውስጥ የታረደውን ከብት ሥጋ የአካባቢው ወጣትና አርሶ አደሮች ወደሌላ ሥፍራ በመውሰድ እንደቅርጫ ይከፋፈሉታል፡፡

ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ባለሀብቱ በጉድጓዶቹ ውስጥ ሾልኮ የሚያልፍበት ሥርዓት (hulluqaa) ደግሞ ይፈፀማል፡፡ በሂደቱ መጀመሪያ በአንደኛው ጉድጓድ ውስጥ በመግባት ወደ ሁለተኛው በማስተላለፊያ ቱቦ በኩል ሾልኮ በማለፍ በሁለተኛው ጉዳጓድ ውስጥ ገብቶ ቀጥ ብሎ ይቆማል፡፡

ባለሀብቱ ያገባ ሴት ልጅ ካለችው ባሏ (አማቹ) የባለሀብቱን እጅ በመያዝ ከጉድጓድ ውስጥ ያወጣዋል። የhulluqaa ሥርዓት የሚፈጸመው በባህሉ ሀብቱ በትክክለኛ እና እውነተኛ መንገድ የተሰበሰበ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡

ባለሀብቱ ከጉድጓድ ውስጥ እንደወጣ ሽለላውን በዜማ ያሰማል፡፡ በዚህ አኳኋን የዳላ ሥርዓት እንደተፈጸመ እንግዶች ወደ ምሳ ግብዣው የሚያመሩ ሲሆን፣ በዚህ ወቅትም ቆጣሪው /ጋባራቻው/ ባለሀብቱን ያሞግሰዋል፡፡ ሥርዓቱ እንደተፈጸመ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

2.ሊቃ (Liiqa)

“ሊቃ” ማለትም ላቀ፣ ዘልቆ ሄደ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በብሔሩ ባህል መሠረት በቁጥር አንድ ሺህ እና ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው ከብቶች ያረባ አንድ ግለሰብ ድግስ አዘጋጅቶ እና ዘመድ አዝማዱን ጠርቶ ከብቶቹን እንደ ዳላው በማስቆጠር ሀብቱን የሚያበስርበት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ለሥርዓቱ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችም ሆነ አስፈላጊው ሁሉ ልክ እንደ ዳላው ተመሳሳይ ናቸው፤ የአጥሩ (በረቱ) አዘገጃጀትም ከፀዳቂ እንጨት ሆኖ የተቆጣሪ ከብቶችን ቁጥር በማገናዘብ የሚሰራ ይሆናል፡፡

የሊቃው ፈፃሚ ባለቤት በሊቃው (Liiqaa) ዋዜማ ወደ ባለሀብቱ ቤት ተጋብዘው መጥተው ባደሩ እንግዶችና በዕለቱ እድምተኞች ታጅቦ እየፎከረ እና እየሸለለ ወደ ቆጠራ ማማው እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ የከብት ቆጠራ በደማቅ ሥርዓት ከመጀመሩ ቀደም ተብሎ አንድ ሰንጋ በሬና አንድ በግ ታርዶ ደማቸው ከተቀላቀለ በኋላ “ሞላና (mollanaa)” የተባለው በባህሉ የሊቃ ከብቶችን እንዲቆጥር ሥልጣን የተሰጠው ግለሰብ ጣቱን በደም እየነከረ በተሰበሰቡ ከብቶች ላይ ይረጭባቸዋል፡፡ ሥርዓቱ የሚፈጸመው ከብቶቹን በሽታ እንዳይነካቸውና የአርቢያቸውም ዕድሜም እንዲረዝም ያደርጋል ተብሎ በባህሉ ስለሚታመን ነው፡፡

ባለሊቃው ማማው ላይ ከመውጣቱ አስቀድሞ ደምና ትኩስ ወተት በተቀላቀለበት ጉድጓድ ውስጥ ይገባና እንዲሻገር ይደረጋል፡፡ ይህ የሚከናወነው እንደ ዳላ ሥርዓት ሁሉ ከብቶቹ የራሱ እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለማረጋገጥ ሲባል ነው፤ የሰው ከብት ቀላቅሎ ሥርዓቱን ከፈፀመ ከብቶቹ በሙሉ ያልቃሉ የሚል የብሔሩ ባህላዊ እምነትም አለ፡፡

በመቀጠል ግለሰቡ ማማው ላይ ወጥቶ በመቀመጥ ሥነ-ሥርዓቱን ይከታተላል፡፡ በቅድሚያ በቤቱ ረዥም ዕድሜ የቆየች ላም ተመርጣ በቀዳሚነት ወደ በረቱ እንድትገባ ይደረጋል፡፡ በመቀጠል ቆጣሪው ሞላና (mol­lannaa) የተሰበሰቡ ወደ በረቱ የሚገቡትን ከብቶች አንድ በአንድ በእርጥብ ቀርከሃ ቅጠል እየነካ ይቆጥራቸዋል፡፡

ሞላና (mollanaa) ይህን ተግባር ለማከናወን የግድ የሊቃን ሥርዓት ከፈጸመ አንድ ዓመት ሞልቶ ያለፈው መሆን እንዳለበት ባህሉ ያዝዛል፤ ዓመት ሊሞላው አንድ ቀን ቢቀረው እንኳ “ሞላና (mollanaa)” ተብሎ ከብት እንዲቆጥር ሥልጣን አይሰጠውም፡፡ ይህም የሚደረግበት ዋናው ምክንያት ልክ እንደ ዳላው የባለሀብቱ ከብቶች አይበረክቱም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ከብቶቹ ተቆጥረው ሲያልቁ በመጨረሻ ወደ በረት በሚገባው በሬ አንገት ላይ “ዳላ” ቃጭል ይንጠለጠልበታል፡፡ በመቀጠልም በሬ ይታረድና የሥነ-ሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል፡፡

የቆጠራው ሥነ-ሥርዓት እንዳበቃ ባለ ሊቃው ግለሰብ ከሸማ ተሠርቶ በጥለት የተዠጎረጎረውን ሴሬ ሃዲያ የሚባለውን ባህላዊ ሱሪ በመታጠቅ ከላይ በለበሰው ላይ የነብር ወይም የአንበሳ ቆዳ ደርቦ በፀጉሩ ላይ የሰጎን ላባ ይሰካል፡፡ ባጌጠ ፈረስ ላይ ሆኖ በከብቱ ቁጥር በክር የተያያዘ የሾላ ወይም የእንቧይ ፍሬ አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ በማጌጥ በእጁ ቃጭል ይዞ በእድምተኞች ታጅቦ ከሚስቱ ጋር በመሆን በአቅራቢያው ወደሚገኘው ገበያ ያመራል፡፡

በገበያ ውስጥ ‹ኡልዱዱዋ›› (uldduduwaa) የተሰኘ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ እየተነፋ ወደ ገበያው ሲደርሱ ሚስቱ በተቀመጠችበት ፈረስ አስረግጣ አንድ ጋን ሙሉ ቦርዴ ከሰበረች በኋላ ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቦታ በመሄድ ባልና ሚስት ቦርዴውን ባንድ ቅል (dagget­ta) በጋራ ይጠጣሉ፡፡ በዚያም እየተጫወቱ ከቆዩ በኋላ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ የሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል፡፡

ግሟ (Gimuwaa)

በነባሩ የወላይታ ባህል በአብዛኛው ጊዜ የሊቃ እና የዳላን ሥርዓት ያከናወነ ግለሰብ ባለቤት የግሟ (የሴቶች ባህላዊ የሀብት ብስራት) ሥርዓት ትፈጽማለች፡፡ ወይንም አንዲት ሴት ጠንክራ ሰርታ በራሷ ያረባቻቸው ከብቶች መቶ እና ከዚያ በላይ ከሆኑ ደግሞ ይህንኑ ሥርዓት ትፈጽማለች ማለት ነው፡፡

በ Gimuwa ሥርዓት ከብት የምታስቆጥር ሴት የመውለድ ዕድሜን የዘለለች (ያረጠች) መሆን አለባት። ሥርዓቷን የፈጸመች ሴት ከፍተኛ ማህበራዊ ከበሬታ የሚሰጣት ሲሆን የማማከር ሚና የምትጫወት ሲሆን የማጀትም ሆነ የግብይት ሥራ አታከናውንም አገልጋዮቿ ያከናውኑላታልና፡፡ እንዲሁም ከብረት የተሠራውን ግሞ ብራታ “Gimo birataa” አምባር በእጇና በእግሯ አጥልቃ በአሽከሮቿ ታጅባ ወደ ሥፍራው ትሄዳለች፡፡

የግሟ ሥርዓት የምትፈጽመው ሴት ሀብቷን ለማብሰር ከባሏ ጋር ወደ ገበያ ስትገባ በተዘጋጀላቸው ስፍራ ሲቀመጡ ታዳሚዎችም በዙሪያቸው ይቀመጣሉ፤ በዚህም የሶስት ጋን ቦርዴ መስተንግዶ ይደረግላቸዋል። በሂደቱ ብልፅግናዋን ለመግለጽም የተወሰኑ ሳንቲሞች በመበተን ለገበያተኞች ትሸልማለች፡፡

በዚህ ሁኔታ ሥርዓቱ እየተፈጸመ እያለ ከሠራተኞቿ የተወሰኑት ወደ ገበያ ውስጥ በመግባት ለሽያጭ ከቀረቡት የዕቃ ዓይነቶች አንዳንድ በመግዛት ያመጡላታል፡፡ ይህንንም ሠራተኞቿንና አጃቢዎቿን አሸክማ በእነርሱ ታጅባ ወደቤቷ ትመለሳለች፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ ‹‹ኦናካ ጊማሱ›› (“onakka gimaasu) ተብላ ትከበራለች፡፡ ይህም የሥነ-ሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል፡፡

ይህ ማራኪው እና ተመልካችን የሚመስጠው የወላይታ ብሔር የሀብት ማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሲከበር እና በብሔሩ ተወላጆች ሲከናወን የኖረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የአከባበሩ ሥርዓት ጥንታዊ ባህላዊ ይዘቱን እየለቀቀ የመጣ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል ባለሀብቶችን የሚያወድሱ ነባር ሥነ-ቃላት በሌሎች ተተክተዋል፡፡ ይህ እና ሌሎችም የሥርዓቱ መልኮች እየተበረዙ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡

ይህ ሥርዓት ቁጠባንና ተግቶ መሥራት የሚያበረታታ በመሆኑ በሚገባ ቢያዝ ለልማታዊ ባለሀብቶች እውቅና ለመስጠትና ሌሎች የእነሱን እግር ተከትለው እንዲተጉ ለማድረግ እንደሚጠቅም ይታመናል፡፡

ደስታ ወጋሶ

አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You