
ኢትዮጵያ 38ኛውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለማዘጋጀት ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፤ ስብሰባው በሰላም ተጀምሮ እንዲያልቅ ከማድረግ ጀምሮ፤ የጉባዔው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ደማቅ ትዝታዎች እንዲኖሯቸው፤ ከሁሉም በላይ “ይቻላል” በሚል ሀገራዊ መነቃቃት ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ለውጥ እና ለውጡ በተጨባጭ እያስገኘላቸው ያለውን ስኬት በማየት፤ በተመሳሳይ መንገድ ለመሰለፍ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው።
ኢትዮጵያውያን በቀደመው ዘመን በዓድዋ የቅኝ ገዥዎችን አንገት ያስደፋ አንጸባራቂ ድል በመቀዳጀት፤ አፍሪካውያንን እና በመላው ዓለም በከፋ የግፍ አገዛዝ ውስጥ ለነበሩ ትውልደ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ችቦ ማቀጣጠል ችለዋል። በዘመኑ “ይቻላል” ተብሎ የማይገመተውን የቅኝ ገዥ ኃይል ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር እና የነፃነት ቀናዒነት በአደባባይ አዋርደው መመለስ ችለዋል።
ይህ ትናንት ኢትዮጵያውያን ለነፃነት እና ለፍትሕ ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የጻፉት የደመቀ ታሪክ፤ ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን እና ትውልደ አፍሪካውያን ነፃነትን መስዋዕትነት በሚጠይቅ ትግል የመጎናጸፍ መነቃቃት ፈጥሯል። ይህም በጊዜ ሂደት አፍሪካዊ መሠረት ላለው የፓን አፍሪካኒዝም መወለድ የዘር ፍሬ ሆኗል።
የቀደሙት የአፍሪካ አባቶች ይህንን አፍሪካዊ እሳቤ /ፓን አፍሪካኒዝምን/ መሠረት በማድረግ፤ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ውስጥ የነበሩ አፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችንን ነፃ ማውጣት የሚያስችል እልህ አስጨራሽ ትግሎችን አድርገዋል። በዚህም መላው አፍሪካዊ አሁን ያገኘውን ነፃነት ተቀዳጅቷል።
የነፃነት ትግሉ ከሁሉም በላይ የአፍሪካውያንን አንድነት የጠየቀ፤ አፍሪካውያን በአንድነት መቆም እንዳለባቸው ያመላከተ ነው። አፍሪካውያን በነፃነት ትግሉ ወቅት የፈጠሩት አንድነት ከነፃነት ማግስት ጀምሮ፤ የቅኝ ግዛት በፈጠራቸው የማንነት ግራ መጋባቶች እና የልዩነት ትርክቶች በብዙ ተፈትኗል፤ አሁንም እየተፈተነ ነው።
ይህም አፍሪካውያን ብዙ መስዋዕትነት በእጃቸው ያስገቡትን ነፃነት፤ ሙሉ ማድረግ በሚያስችል የኢኮኖሚ ነፃነት ተጨባጭ ማድረግ ሳይቻላቸው ቀርቷል። ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ የሰው ኃይል አቀናጅተው የበለፀገች አፍሪካን እውን ማድረግ እስከ ዛሬ ፈተና ሆኖባቸዋል።
ከዚህ ይልቅ አፍሪካውያን የግጭቶች እና የጦርነቶች ማዕከል፤ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱበትን ዓለም አቀፍ ገጽታ ተላብሰዋል። ለዘመናዊ የስደት ባርነት፤ ላልተገባ የተጎሳቆለ ሕይወት እና ተስፋ መቁረጥ ተዳርገዋል። ችግሮቹ በፈጠሯቸው ድባቴዎችም በነፃነቱ ትግል ዘመን የተፈጠረው የይቻላል መነቃቃት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ተዳፍኖ ቆይቷል።
አፍሪካውያንን ከዚህ ድባቴ ለማውጣት ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን ድህነትን እና ኋላቀርነትን በይቻላል መንፈስ ታሪክ ለማድረግ የጀመሩት መነቃቃት እና መነቃቃቱ በተጨባጭ እያስገኘ ያለው ውጤት ትልቅ የመንፈስ መነቃቃት እና የትግል ቁርጠኝነት ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል ።
በቀደመው ዘመን የዓድዋ ድል መላውን አፍሪካዊ ለነፃነቱ እንዲነቃቃ የመንፈስ አቅም፤ የማንቂያ ደውል እንደሆነው ሁሉ፤ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ የጀመሩት ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጅማሮ እና የጅማሮው ስኬቶች፤ አፍሪካውያን የኢኮኖሚ ነፃነታቸውን ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል መነቃቃት እንዲፈጥሩ የማንቂያ ደውል ነው።
ኢትዮጵያውያን በቀደመው ዘመን በይቻላል መንፈስ፤ አይቻልም የተባለውን ችለው ለዓለም እንዳሳዩ፤ ዛሬ ድህነትን እና ኋላቀርነትን በተባበረ አንድነት፤ በመደመር እሳቤ ታሪክ ለማድረግ የጀመሩት አዲስ የታሪክ ጉዞ በብዙ ስኬታማ ክንዋኔዎች ታጅቦ ዓለም አቀፍ እውቅና እየተቸረው ነው።
ኢትዮጵያውያን ዛሬ፤ በየዓመቱ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ከውጪ ያስገቡት የነበረውን ስንዴ በማስቀረት፤ በስንዴ ምርት እራሳቸውን ችለው ለሌሎች መትረፍ የሚያስችል ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም መፈጸም የሚያስችል አቅም አዳብረዋል፤ ከአንድ ምዕተ-ዓመት በላይ የቆዩ ከተሞችን ዘመኑን በሚመጥን መንገድ በማደስ እና በመገንባት እየሄዱበት ያለው ርቀት አፍሪካውያንን በብዙ መልኩ የሚያነቃቃ ሆኗል።
የትናንቶቹ የነፃነት አባቶቻችን ስለነፃነት የፈጠሩት አፍሪካዊ አንድነት የነፃነት ትግሉን ለውጤት እንዳበቃው፤ አሁን ያለው አፍሪካዊ ትውልድ ቅኝ አገዛዝ ከፈጠራቸው የማንነት ግራ መጋባቶች እና የልዩነት ትርክቶች ወጥቶ በአንድነት መንቀሳቀስ ቢችል የአፍሪካ የኢኮኖሚ ነፃነት እውን የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ በመደመር እሳቤ፤ በይቻላል መንፈስ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ለመውጣት፤ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን እየተጓዙበት ያለው የለውጥ መንገድ እና መንገዱ እያስገኘ ያለው ስኬት ተጨባጭ ማሳያ ነው። አፍሪካውያንም እንደ ዓድዋው ድል ከዚህ ብዙ ሊማሩ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም