የብዙ ታሪክ እና ታሪክ ሠሪ ሕዝብ ሀገር እንኳን በደህና መጣችሁ !

ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ፣ የሺ ዓመታት የሀገረ መንግሥት ምስረታ እና የተለያዩ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ባለቤት ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ቀድማ በመቀበል የምትታወቅ ፣ ነጻነቷን በተጋድሎ በማጽናት ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ፋና ወጊ የሆነች ፣ ዛሬም ለነጻነት እና ለፍትህ ድምጿን ከፍ አድርጋ በማሰማት ከፍ ያለ እውቅና ያተረፈች ሀገር ነች።

ሕዝቦቿን ለዘመናት አብሮ በሰላም ለመኖር ያስቻሉ የአብሮነት እሴቶች ያሏት ፣ በህብረ ብሄራዊነት የደመቀ የታሪክ ትርክት እና አብሮ የመኖር የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነች ፣ይህንን የሚሸከም በዘመናት ውስጥ የተገነባ ባህላዊ ፣ማህበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን የገነባች ሀገር ነች።

በአክሱም ዘመነ መንግሥት ወጥ ከሆነ አለት ለዓለም እስከዛሬ ምስጢር የሆኑ ሐውልቶችን ፣ በላሊበላ ዘመነ መንግሥት ከወጥ ድንጋይ የተፈለፈሉ ቤተ መቅደሶች ገንብተው ያለፉ የሥልጣን ፋና ወጊ የሆኑ ሕዝቦች መኖሪያ ፣ የአባ ጅፋር እና የጎንደር ቤተመንግሥታትን በመገንባት ለዘመናዊ የሕዝብ አስተዳደር ተጠቃሽ የሆኑ መሪዎችን ያፈራች ነች።

የሀገር ፍቅር እና ጀግንነትን ለትውልዶች ማውረስ የቻሉ ታላላቅ መሪዎች እና የጦር ጀነራሎችን ከቀደምት ዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ ማፍራት የቻሉ ፣ ለሀገራቸው መሞትን ክብር አድርገው የተቀበሉ፣ ለፍትሕ እና ለነጻነት ቀናኢ የሆኑ ፣ ከጎረቤቶች ሀገራት ጋር አብሮ በሰላም እና በፍቅር የሚኖሩ ፣ በታሪክ ዘመናቸው በሌሎች ላይ ጣት ያልሰበቁ ሕዝቦች መገኛ ነች ።

ለአስራ ሦስት ወራት ፀሐይ ደምቃ የምትታይበት ፣ወንዞች ዓመቱን ሙሉ እየፈሰሱ ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተፈጥሯዊ ትስስር የሚፈጥሩባት ፣ ከፍ ባሉ ተራሮች እና ኮረብቶች የተሞሸረች ፣ ለሕይወት ተስማሚ በሆኑ የተፈጥሮ አካባቢዎች የታደለች ፣ ለዘመናት ለመንፈሳዊ እሴቶች ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጡ ፣ የባለ ብዙ ተስፋ ወጣቶች ሀገር ነች።

በቅኝ ገዥነት መነቃቃት በብዙ አጀብ እና ወጀብ ባህር ተሻግሮ የመጣውን የፋሽስት ጣሊያን ጦር በተባበረ ክንድ፣ በላቀ የነጻነት እና የሀገር ፍቅር መንፈስ ፣ ብዙ መስዋእትነት በጠየቀ ጀግንነት አዋርዶ በመሸኘት ለጥቁር ሕዝቦች የይቻላል መንፈስን ማጋባት የቻሉ ፣ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል እርሾ የሆነ የዓድዋ ድል ባለቤት ነች።

ሕዝቦቿ ለነጻነት እና ፍትህ ካላቸው ቀናኢነት የተነሳም ፣ በአፍሪካ ተንሰራፍቶ የቆየውን የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በጽናት በመታገል እና በማታገል ፋና ወጊ ናቸው፤ አፍሪካዊ የሆነውን የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ፣አስተሳሰቡ አድጎ አፍሪካዊ መሠረት እንዲኖረው በብዙ የታገሉ ፣ በዚህም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት የላቀ አበርክቶ በማበርከት ተጠቃሽ ናቸው።

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የአፍሪካውያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አጀንዳዎች መስተናገጃ ማእከል ሆና የቆየች ፣ ለአፍሪካውያን ብሩህ ነገዎችን ለመፍጠር በሚደረገው አፍሪካዊ ጥረቶች ውስጥ ጎልታ የምትታይ ፣ ለአፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት አበክራ የምትሠራ በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸራት ነች።

ዛሬ ላይ ለአፍሪካውያን የኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ አቅም የሚሆን የለውጥ መንገድ ውስጥ የምትገኝ ፣በተለመደው የይቻላል መንፈስ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ታሪክ ለማድረግ በአዲስ መነቃቃት ውስጥ የምትገኝ ፣ በዚህም ተስፋ ሰጪ ተጨባጭ ስኬቶችን በማስመዝገብ ፣ ዓለምን በአዲስ የታሪክ ትርክት ለማስደመም መንገድ የጀመረች ሀገር ነች።

የዘመኑን የብልፅግና ውስብስብ ተግዳሮቶች በአዲስ ሀገራዊ የፖለቲካ – ኢኮኖሚ ዕይታ ለመሻገር በሚያስችል ሀገራዊ መነቃቃት ፣ ለአፍሪካ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንሳኤ የሚሆን የታሪክ እጥፋት ላይ የምትገኝ ፣ የፓን አፍሪካኒዝምን በወንድማማችነት ተደምሮ የመቆም አስተሳሰብ በላቀ መሠረት ላይ በማዋቅር ለአፍሪካውያን ተጨማሪ የይቻላል መንፈስን ማጋባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነች ።

በዚህ ታሪካዊ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባዎችን ለመታደም የመጣችሁ የአህጉሪቱ እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች እና ተወካዮች፣ጋዜጠኞች እና የክብር እንግዶች እንኳን የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት ወደሆነችው ጥንታዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ። የመለወጥ ታሪካችን ጀምሮ የዓይን ምስክሮች በመሆናችሁ ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው !

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You